በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ እና ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መነኻሪያ (Manufacturing Hub) እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍም ትልቅ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ::
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹንና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን (Dire Dawa Free Trade Zone) በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን (Industrial Parks Development Corporation – IPDC) ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ስራዎች ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ቁጥር ለመጨመርና ከኢንቨስተሮች ጋር ያለውን ትስስር ለማሻሻል አዳዲስ የሪፎርም ተግባራትን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል:: እነዚህ ተግባራትም ብዙ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹና ነፃ የንግድ ቀጣናው እንዲገቡ ማድረግ ችለዋል:: በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ 177 ሼዶች መካከል አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን እየጠበቁ ያሉት 20ዎቹ ብቻ ናቸው፤ 157 ሼዶች በባለሃብቶች ተይዘዋል:: አምስት ፓርኮች (አዳማ፣ ቦሌ ለሚ፣ አዲስ፣ ሰመራ እና ድሬዳዋ (የማኑፋክቸሪንግ ክፍሉ)) በመሙላታቸው አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ማስተናገድ አይችሉም::
ኮርፖሬሽኑ ይህን ባለሃብቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የማስገባት ጥረቱን ቀጥሎበት፣ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ለማምረት ፍላጎት ካላቸው 11 ኩባንያዎች ጋር የስራ ስምምነቶችን ተፈራርሟል:: ከኩባንያዎቹ መካከል አብዛኞቹ ሀገር በቀል አምራቾች ሲሆኑ፣ ሦስቱ ድርጅቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ከስራ ውጭ ሆኖ ወደቆየው መቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገቡ ናቸው::
ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገቡት እነዚህ ኩባንያዎች፤ ወደ መቐለ፣ ጅማ፣ ቦሌ ለሚ፣ ባህር ዳር እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ተግባራት ላይ ይሰማራሉ:: 31ሺ ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ እና አራት ነጥብ አምስት ሄክታር የለማ መሬት ይረከባሉ:: በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ዘርፎች የሚሰማሩት ኩባንያዎች ከ50ሺ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ:: ኩባንያዎቹ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ከአምስት ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ::
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ ኩባንያዎቹ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ፣ በፋርማሲቲካልና በሌሎች የአምራች ዘርፎች እንደሚሰማሩ ጠቁመው፣ የስራ እድል ለመፍጠር፣ የወጪ ምርት ለመጨመር፣ ገቢ ምርት ለመተካት፣ ጥቅል ሀገራዊ ምርትን ለማሳደግ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖራቸው ይገልፃሉ:: ኩባንያዎቹ ለስራ እድል ፈጠራ ከሚያበረክቱት አስተዋፅዖ በተጨማሪ፣ የምርት ተግባራት በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ በማድረግ ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግርን ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱና ይህም የምርት ስራዎች ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ እንደሚያደርግ ይናገራሉ::
አቶ አክሊሉ ‹‹ከአስራ አንዱ ኩባንያዎች መካከል አብዛኞቹ ሀገር በቀል ኩባንያዎች ናቸው:: ባለፈው አንድ ዓመት በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን የማነቃቃት፣ የማበረታታትና ወደ አምራች ዘርፉ ገብቶ ውጤታማ ስራዎችን እንዲሰራ የማድረግ ስራ ነው:: በዚህ ሂደት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ አምራች ዘርፉ እንዳይገቡ መሰናክል የነበሩ ችግሮችን ለይተን መፍትሄ እየሰጠን እንገኛለን:: በ2016 ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከገቡ አምራቾች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው›› በማለት የሀገር ውስጥ አምራቾች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ትኩረት ስለመሰጠቱ ያስረዳሉ::
እሳቸው እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚሰጠው ቦታ አነስተኛ ነበር:: በ2015 እና 2016 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲነቃቁ፣ ባለሃብቶቹ ያሉባቸውን የፋይናንስና ሌሎች ክፍተቶችን የሚሞሉ ተግባራት ተከናውነዋል:: በመሆኑም በ2015 እና ዘንድሮ ከተመዘገቡት ባለሃብቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው::
አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ ጓዙን ጠቅልሎ የሚሄድ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ጥገኛ ሆኖ መቀጠል ተገቢ ስላልሆነና ተወዳዳሪ የሆነ የሀገር ውስጥ ባለሃብት ማሳተፍና መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተጀመረው ስራ ውጤት እያመጣ ይገኛል:: ሀገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ስራ ላይ ለመሰማራት የሚያሳዩት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ፣ የኩባንያዎቹ የማምረት አቅም አድጎ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተወዳዳሪ የመሆን አቅማቸውም ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ያመላክታል::
ስምምነት ከተፈራረሙት ኩባንያዎች መካከል ሦስቱ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከስራ ውጭ ሆኖ ወደቆየው መቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገቡ እንደሆኑ የሚናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ ስምምነቶቹ ፓርኩን ወደ ስራ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዙ ያስረዳሉ:: ‹‹የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ፓርኩ ወደ ስራ እንዲመለስ ኮርፖሬሽኑ ኮሚቴ አዋቅሮ ሲሰራ ነበር:: በጦርነቱ ምክንያት ከስራ ውጭ የነበሩ የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ወደ ስራ እንዲመለሱ፣ በሞራልም በፋይናንስም እንዲጠገኑና አገግመው ወደ ስራ መንፈስ እንዲመለሱ ጥረት ተደርጓል፤ ያልተከፈላቸው ውዝፍ ደመወዛቸውም እንዲከፈላቸው አድርገናል›› ብለዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በፓርኩ ውስጥ በምርት ስራዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ባለሃብቶች ስራ አቋርጠው ወጥተው ስለነበር ወደ ስራ እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገዋል:: ፓርኩ በጦርነቱ ጉዳት ባይደርስበትም ውስን ጥገናዎች ተደርገውለት በሙሉ ቁመና ለስራ ዝግጁ እንዲሆን ተደርጓል:: በዚህ ውጤታማ ጥረት ነባር ኢንቨስተሮችን ወደ ስራ መመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ከሦስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ መቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመግባት የሚያስችላቸውን የስራ ስምምነት እንዲፈርሙ ማድረግ ተችሏል::
የኢንቨስትመንት ዘርፍን ለማሳደግ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ጥራቱን የጠበቀና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ የሚናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ አክሊሉ፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲያመርቱ ኮርፖሬሽኑ በልዩ ትኩረት ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ:: ኮርፖሬሽኑ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ተግባራዊ ባደረጋቸው የሪፎርም ተግባራት አማካኝነት ለዘመኑ የሚመጥን እና ለኢንቨስተሮች ምቹ የሆነ የኢንቨስትመንት አመራርና አስተዳደር ለማስፈን ጥረት እያደረገ ይገኛል ይላሉ::
‹‹ግልፅ የሆነ የኢንቨስተሮች መመልመያ መስፈርት፣ ቀጥተኛ የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን/ ማስተዋወቂያ/ ዘዴዎች እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን የማበረታቻ ማዕቀፎች ዝግጅት፤ አዲስ የመዋቅር ጥናትና ትግበራ፤ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ትብብር መፍጠሪያ እና የዲጂታል አሰራር ስርዓት ተግባራት ኮርፖሬሽኑ እየተገበራቸው ከሚገኙት የሪፎርም ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው:: በእነዚህ ተግባራት አማካኝነት የባለሃብቶችን ቁጥርና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል›› ሲሉም አስታውቀዋል::
‹‹ጵንኤል ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት ከተፈራረሙ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው:: ከ16 ሚሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገበው ይህ ሀገር በቀል ኩባንያ፣ ቆርኪ በማምረት ላይ ተሰማርቶ ይገኛል:: ኩባንያው የምርት ስራውን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በተረከበው 10 ሺ ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ ላይ የሚያከናውን ይሆናል:: ምርቶቹን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ገበያዎች የማቅረብ እቅድ ያለው ይህ ድርጅት፣ ለ115 ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ይጠበቃል::
የኩባንያው መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ብርቱካን አበበ ድርጅታቸው ቆርኪ በማምረት ከ12 ዓመታት በላይ ልምድ እንዳለው ጠቁመው፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የተፈራረሙት ስምምነት የምርት ስራቸውን ለማስፋትና አቅርቦታቸውን ለመጨመር ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ይገልፃሉ::
በተሻለ አቅም ለማምረት የማምረቻ ቦታ እጥረት እንደነበረባቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ብርቱካን፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ያደረጉት ስምምነት ይህን ችግር እንደሚፈታላቸው ይገልፃሉ:: ‹‹ኩባንያችን የውጭ ምንዛሪ በማዳን ረገድ ትልቅ ሚና ባለው ተኪ ምርት የማምረት ተግባር ላይ የተሰማራ ቢሆንም የቦታ ችግር ነበረበት:: ከኮርፖሬሽኑ ጋር ያደረግነው ስምምነት ለዚህ ችግር መፍትሄ ይሆናል:: የማሽን ተከላ ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ስራ ለመጀመር እየተዘጋጀን እንገኛለን:: የመጠጥ ምርቶች ዘርፍ ትልቅ የገበያ ፍላጎት ያለው በመሆኑ ዘርፉ በሚፈልገው ጥራትና ብዛት ልክ ግብዓት ማቅረብ ብዙ ጥቅሞች አሉት:: ይህን ምርት ሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ከኤክስፖርት ያላነሰ ፋይዳ አለው›› ይላሉ::
የ‹‹ዶክተር ማርቆስ ኩባንያ›› ባለቤት ዶክተር ማርቆስ ገሰሰ በበኩላቸው፣ የሰላም ስምምነቱ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ መቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመግባት የህክምና ቁሳቁስን በማምረት ስራ ላይ ለመሰማራት ማቀዳቸውን ይገልፃሉ:: እሳቸው እንደሚሉት፣ የህክምና ቁሳቁስ በከፍተኛ መጠን ተፈላጊ በመሆናቸውና ኢትዮጵያ እነዚህን ቁሳቁስ በብዛት ከውጭ የምታስገባ በመሆኑ በዘርፉ መሰማራት ለሀገርና ለህዝብ እጅግ አስፈላጊ፣ ለባለሃብቶችም አዋጭና አትራፊ ነው::
ቀደም ሲል በመቐለ ከተማ በህክምና ኢንቨስትመንት ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ማርቆስ፣ ወደ መቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው የሚሰማሩበት ስራ ለ127 ዜጎች የስራ እድሎችን እንደሚፈጥር ይገልፃሉ:: በአምስት ሺ 500 ካሬ ሜትር ላይ ባረፈ አንድ ሼድ ውስጥ የሚከናወነው የዶክተር ማርቆስ ኩባንያ የምርት ስራ፣ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ማምረት እንደሚጀምር ዶክተር ማርቆስ ገሰሰ ተናግረዋል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2016