ከ13 ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ አክርዲቴሽን አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን የሚያከናወን ነው፤ በዋናነት ብቃትና ተቀባይነት ያለው አገልግሎት የመስጠት ዓላማ ያነገበ ነው፡፡ በተለይም በውጭ እና ገቢ ምርቶች ላይ የሚሰራቸው ሥራዎች ከሀገሪቱ አጠቃይ ገፅታ ጋርም የሚያያዝ ነው፡፡
ተቋሙ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ዕድገት በሚያፋጥኑ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ነው፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም በዛሬው ዕትሙ የተቋሙን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴዎች፣ ቀጣይ እቅዶች እና አሁናዊ ክንውኖች በተመለከተ ከተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት አሁናዊ ቁመና ምን ይመስላል?
አቶ ወንድወሰን፡- የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ በ2003 ዓ.ም በኋላም ተጨማሪ ኃላፊነት እና ተልዕኮ ተሰጥቶት 2010 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ ሲቋቋም በዋናነት ብቃትና ተቀባይነት ያለው አገልግሎት መስጠትን ዓላማ አድርጎ ነው፡፡
ተቋሙ አሁን ያለውን ቁመና ከመያዙ በፊት እንደ ሀገር የግብርና እና የኢንዱስትሪ፣ ምርቶችና አገልግሎቶች አክርዴትድ የሚሰጠው በውጭ ሀገራት ነበር፡፡ ይህ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ አገልግሎቱ በዋነኛነት የተቋቋመውም ከሀገር ውስጥ የሚወጡትንም ሆነ የሚገቡትን ምርትና አገልግሎት በዋናነትም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ፣ በዚህም ሕዝብና ሀገር ማግኘት ያለባቸው ጥቅም እንዲያገኙ ለማስቻል ነው፡፡
አገልግሎት የተቋቋመው በሀገር አቀፍ ደረጃ እጅግ አንገብጋቢ የሆኑ ጥያቄዎች በመኖራቸው ነበር። ተቋማችንም አሁን ላይ እየተንቀሳቀሰ ያለው በዚህ ደረጃ ሁኔታዎችን ተገንዝቦ ነው፡፡ አክሪዲቴሽን ስንል አንድ ተቋም ሥራው እና አገልግሎቱን በአግባቡ ስለመወጣቱ የሚሰጥ ምስክርነት ነው፡፡ ይህ ምስክርነት ካልተሰጠ በስተቀር ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ከሀገር ሊወጡ አይችሉም። በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እና ተፈላጊ የመሆን ዕድላቸውም ዝቅተኝ ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ተቋሙ እንደሀገር ተመስርቶ ወደ ሥራ ገብቷል። በዚህም ቀደም ሲል ይወጣ የነበረን የውጪ ምንዛሪ ማዳን፤ ውጤታማ መሆንም ተችሏል፡፡
ተቋሙ 2004 ዓ.ም በሙሉ አቅሙ ሥራ በመጀመር ፈጣን እምርታ በማሳየት ዓለም አቀፍ የላብራቶሪዎች ትብብር ዕጩ አባል ሆኗል፡፡ ይህ በመሆኑም የኢትዮጵያ አክርዲቴሽን አገልግሎት ጋር በቅርበትና በጋራ ተደጋግፎ የመስራት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ በመቀጠልም ለክልል መንግስታት፣ ለከተማ አስተዳደሮች፣ ለሕግ ተርጓሚዎች እና አስፈፃሚዎች እና የተለያዩ አካላት ሥራውን ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በ2009 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የላብራቶሪዎች ትብብር አባል ሆኗል፡፡ ይህ ስኬት የመጣው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ማረጋገጫዎች ከተሰሩ በኋላ ነው፡፡ ለዚህም በተቋሙ ውስጥ የነበሩ አመራሮች እና ባለሙያዎች በርካታ ስኬታማ ሥራዎች አከናውነዋል፤ ሊመሰገኑም ይገባል፡፡
ቀደም ሲል የአክሪዲቴሽን ሥራ ይሰራ የነበረው በሕክምና ላብራቶሪ እና በፍተሻ ላብራቶሪ ላይ ብቻ ነበር፡፡ በሂደት ፈጣን እምርታ በማሳየት በኢንስፔክሽን አክርዲቴሽን ተጨማሪ ዓለም አቀፍ እውቅና ተገኝቷል። ለዚህም በ2014 ዓ.ም በጥራት ሥራ አመራር ሰርተፊኬሽን እና በ2015 ዓ.ም ደግሞ በሥነ-ልክ ካሊብሬሽን ላብራቶሪ ወሰኖች ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝተናል፡፡
በእርግጥ እንደ ሀገር አንዴ የተሰጠ ዓለም አቀፍ ዕውቅና በዓለም ገበያ ውስጥ ዘላለማዊ አይደለም። በየጊዜው ዓለም አቀፍ የላብራቶሪዎች ትብብር ባለሙያዎች እየተላኩ ምልከታ ያደርጋሉ፤ ይገመግማሉ። በቂ ሆኖ ካልተገኘ አንዳንዱን እውቅና ሊሰርዙ ይችላሉ፡፡ እኛ እስካሁን የተሰረዘብን እውቅና የለም። ካለን በተጨማሪ ሌሎች ዓለም አቀፍ እውቅናዎችን አግኝተናል፡፡ በዚህም ደንበኞቻችን ሳይጉላሉ እየተስተናገዱ ነው፤ ሀገርንም ከወጪ መታደግ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- ሀገሪቱ ካላት የምጣኔ ሃብት ዕድገት፣ የደንበኞች ፍላጎት እና ሌሎች ሁኔታዎች አኳያ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በቂ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ወንድወሰን፡- በተለያዩ ምክንያቶች በቂ ነው ማለት አንችልም፡፡ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘንባቸው ወሰኖች ውስን ናቸው፡፡ ሌላው አገልግሎቱ አስገዳጅ ባለመሆኑ ነው፡፡ የእኛ ደንበኛ በእኛ አክርዲት ለመደረግ አይገደድም፡፡ በማንኛውም ተቋም አክርዲትድ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ አካሄዶች አስቸጋሪ ቢሆኑም፤ በዚያው በተለመደው አካሄድ መሄድን የመምረጥ አዝማሚያ አለ፡፡ በኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት የግድ እውቅና ወይንም ምስክርነት ሊሠጥ ይገባል የሚል መመሪያ ወይንም አዋጅ ባለመኖሩ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች አሉ።
በአክሪዲቴሽን ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት አለ። የጥራት ጉዳይ ሲነሳ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈርቶቹ፣ ሳይንሱ እና ሌሎች መለኪያዎቹ ውስብስብ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ በቂ የተማረ የሰው ኃይል በሀገር ውስጥ አለመኖር ለስራው ተግዳሮት እየሆኑ ነው።
ለምሳሌ የውጭ እና ውስጥ አሰሰርስ (external and internal assessors) የምንላቸው አሉ፡፡ አሰሰርስ የምንላቸው ምስክርነት የሚፈልገው ተቋም ወይንም ከእኛ ምስክርነት የፈለገው ተቋም በተለያዩ መመዘኛዎችና ልኬቶች መዝኖና ተንትኖ ለተቋማችን ማናጅመንት አቅርበው እውቅና እንዲያገኝ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ሌላው ውስጣዊ አሰሰርስ (Assessors) ናቸው ፤ለነዚህ በቂ ደሞዝ መክፈል፤ ባለመቻላችን ለተሻለ ደመወዝ ወደሌላ አካባቢ ይፈልሳሉ፡፡ የውጭዎቹም በትክክል የሚመጣጠን ክፍያ ስለማያገኙ በሚጠበቅብን ልክና መጠን እያገለገልን ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህም ቢሆን ግን የመጣንበት የስኬት መንገድ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ ግን በአክሪዲቴሽን ከመጣነው መንገድ ይልቅ የምንሄድበት መንገድ ይርቃል፡፡ ካስመዘገብነው ድል ይልቅ ወደፊት የምናስመዘገብው ድል እንደሚበልጥ እናምናለን፡፡ በቂ የሰው ኃይል እንዳንቀጥር ከሚፈትኑን ችግሮች መካከል በቂ የሕንፃ መሰረት ልማት አለመኖር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየገነባነው ያለው ሕንፃ አሁን ካለን የሠው ኃይል በአራት እጥፍ ለመቅጠር ያስችለናል፤ መዋቅሩም ይፈቅድልናል።
አዲስ ዘመን፡- ደንበኞች በእናንተ አክርዲት ለመደረግ አለመገዳዳቸው እንደ ተቋም የሚፈጥረው ችግር እና እንደ ሀገር የሚያሳጣው ጥቅም አለ?
አቶ ወንድወሰን፡- አዎ! አለ፡፡ ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ እንረዳለን፡፡ ትኩረታችን በብዛት ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶች ላይ ነው፡፡ የሀገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶችም አክርዲት መደረግ አለባቸው። ለምሳሌ የተሽከርካሪዎች ‹‹ቦሎ›› የሚያድሱ ተቋማት መኪናው ብቃት አለው፣ አገልግሎት መስጠት ይችላል ብለው ለሚመለከተው አካል ይፅፋሉ፡፡ በመቀጠል ኢንሹራንስ እና የመሳሰሉት ይታደሳሉ፤ ፈቃድም ይሰጣል፡፡
ነገር ግን ተሽከርካሪው ብቃት አለው የሚሉት አካላት በራሳቸው ብቃታቸው ምን ያህል ነው ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ የባለሙያዎቻቸው ብቃት እና የማሽኖቻቸው ትክክለኛነት እስከምን ድረስ ነው ለሚለው ሕግ አክርዲትድ እንዲሆኑ አያስገድዳቸውም። ሌሎችም ላይ በተመሣሣይ ነው፡፡ አክሪዲትድ ስሆን እጠቀማለሁ ብሎ ካልመጣ በስተቀር ሥራውን መሥራት ይችላል፡፡ አሁንም ከተሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘ በየጊዜው የምንሰማውና የምንመለከተው የትራፊክ አደጋ የሚነግረን ነገር አለ። ተሽከርካሪዎቹ ብቃት አላቸው ብለው የሚመሰክሩ አካላትም ብቃት መፈተሽ አለበት። በመሆኑም በአገር ውስጥ ባሉ ምርትና አገልግሎቶች ላይ አክርዲቴሽን አስገዳጅ ባለመሆኑ ችግሮችን ለማየት እየተገደድን ነው፡፡
የተወሰነ ግንዛቤ ያላቸው ተወዳዳሪ ለመሆንና ብቃታቸው እንዲመሰከርላቸው ወደ ኢትዮጵያ አክርዲቴሽን አገልግሎት ይመጣሉ፡፡ ወደ ውጭ የሚወጡ ምርትና አገልግሎትም ላይ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት እውቅና ይፈልጋሉ፤ ዓለም አቀፍ ገበያውም ያስገድዳቸዋል፡፡ ካልሆነ ገበያውን ሰብረው መግባት አይችሉም ወይንም ተወዳዳሪ አይሆኑም፡፡ በሕንፃ ግንባታም ሲነሳ ከሦስት ወለል በላይ ሊፍት የሚጠቀሙ ኮንስትክራሽን ሥራዎች አክርዲትድ በተደረገ ተቋም እንዲገነቡ ይፈለጋል፤ ግን ይህም አስገዳጅ አይደለም፡፡ ይሁንና በየዓመቱ በዚህ ዘርፍ የምንከፍለው ዋጋ ይታወቃል፡፡ በተሽከርካሪ አደጋ የሚጠፋው የሰው ሕይወት እና ንብረት ውድመት ይታወቃል፡፡ ቢያንስ መንግስት ጨረታዎችን ሲያወጣ አክርዲት የተደረጉ ተቋማት ግድ ነው የሚለው ባይገባበትም እንኳን፤ አክሪዲት የሆነ ተቋም ቅድሚያ ይሰጠዋል የሚለው ሐሳብ ቢያካትት የተሻለ ነው፡፡ አሁን ላይ ችግሮቹን ለመፍታት ከኮንስትራክሽን እና ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር ሥራዎችን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡-በውጫዊ አሰሰሮች አክሪዲትድ የማድረግ ሂደቱ ለሙስና የመጋለጥ ዕድል የለውም?
አቶ ወንድወሰን፡- አለው፤ ግን ጠባብ ነው። ለብልሹ አሰራርና ሙስና የመጋለጥ ዕድሉ በሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ላይ ሊኖር ይችላል፡፡ መነጋገር ካለብን ለሙስና የመጋለጥ ደረጃው ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የመጋለጥ ዕድል አለው፡፡ ግን በላብራቶሪ ስለሚረጋገጥ በጥቂቶች ይሁንታ ብቻ የሚሆን አይደለም፡፡
ከላብራቶሪ ሥራ በተጨማሪም በቡድን የሚሠራ በመሆኑ ለሙስና የመጋለጥ ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ ሙስና የሚስፋፋው ውሳኔ ሰጪነት በአንድ ወይንም ሁለት ግለሰብ እጅ ብቻ ሲሆን ነው፡፡ ነገር ግን ውሳኔ በቡድን ሲሆን ሙስና በጣም ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም ከደንበኛ ጋር በመሆን ወይንም በመመሳጠር የሚፈፀም ሙስና አይኖርም ወይንም ለሙስና ተጋላጭነት ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ በርካታ አገልግሎት ፈላጊዎች እንደሚጉላሉ በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ ይህ ከሙስና ጋር አይያያዝም?
አቶ ወንድወሰን፡- ይህ በዚህ ደረጃ አሳሳቢ አይመስለኝም፡፡ እንደ ሀገር ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ‹‹National quality infrastructure›› አለ። የጥራት ተቋም የምንላቸው አሉ፡፡ እነዚህ የጥራት ተቋማት የእኛ ብቻ አይደሉም፡፡ ለአብነት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ምደባ ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት አሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የእኛ ደንበኞች ናቸው። የአንድ ነገር ትክክለኛነት ወይንም ልክነት በራሱ መስፈሪያ ወይንም አሰራር የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ሥነ-ልክ የአንድን ነገር ልክ ልኩን የመለካት አቅምና ብቃት አለው ወይ የሚለውን ደግሞ እኛ አክሪዲት እናደርጋለን፡፡
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በተመሳሳይ ብቃቱንና አቅሙን መልኩ እኛ አክሪዲት እናደርጋለን። ሆኖም ሀገር ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች አክርዲት ለመደረግ አስገዳጅ ባለመሆኑ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደ ሀገር ግን የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት አስፈላጊነት አስገዳጅ ባለመሆኑ በዚህ ግንዛቤ የመፍጠርና ማስፋት ላይ እየሰራን ነው፡፡ እኔ እስከማውቃው ድረስ ለሙስና የተጋለጠ ወይንም ይህን በተመለከተ የቀረበ አቤቱታ የለም ፡፡ ነገር ግን የደንበኞችን ጥያቄ በፍጥነት ያለመመለስ ወይንም መዘግየት ሊኖር ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ሌብነት ሙሉ ለሙሉ ዝግ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ እንደ ሀገር ሙስና ተብትቦ ሊጥለን ስለመሆኑ በተደጋጋሚ የተነገረ በመሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎችን መደበቅ አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የባህር በር ወይንም የወደብ ባለቤት ለመሆን የሚያስችላት የመግባቢያ ውል አስራለች፡፡ ይህ ደግሞ በገቢ እና ወጪ ምርቶች ላይ ከተለመደው አሰራር የተለየ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በዚህ ደረጃ ምን ያህል ዝግጁ ነው?
አቶ ወንድወሰን፡- ልክ ነው፡፡ የባህር በር ወይንም የወደብ አገልግሎት በአጠቃላይ ንግድ ነው። እኛ በዚህ ሴክተር ውስጥ ነን፡፡ ይህ ወደብ የመጣው ለእኛ ነው፡፡ ስለዚህ ከየትኛውም ሴክተር በላይ ሥራ ይበዛብናል፤ ጥርጥር የለውም፡፡ ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን የወደብ መገኘት ብቻ ሳይሆን ሰዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየሰራን ነው። አሁን ባለው ዓለምአቀፋዊነት እሳቤ ውስጥ መሪ ተዋናይ ለመሆን እየሰራን ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ምስክርነት የሚፈልግ ማህበረሰብ እየተበራከተ ይሄዳል፤ በዚህም ሥራ እየበዛ ይሄዳል፡፡
ቀደም ሲል በሰው ወደብ እና በአንድ መንገድ ስንሯሯጥ እና ምርቶችን ወደ ውጭ ስንልክ ነበር፡፡ ነገር ግን በራሳችን ወደብ ምርትና አገልግሎቶችን መላክ ስንጀምር ፍሰቱ አሁን ካለው መጠን ይጨምራል፡፡ ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትም ይበራከታሉ፡፡
የውጭ ባለሃብቶችም ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት መዳረሻነት እንደሚመርጧት ይታወቃል፡፡ አሁን ያለን ሠራተኛ መኖር ከሚገባው አንድ አራተኛው ነው፡፡ ካለን ሰራተኞች በእጥፍ የሚበልጠው ‹‹የፓር ታይም›› ሠራተኞች ናቸው፡፡ በመሆኑም አሁን ካለው ሰራተኛ በአራት እጥፍ መቅጠር ይጠበቅብናል፡፡
ስለዚህ ከወደቡ ባለቤትነት ጋር ተያይዞ አሁን ባለን አቅም ብቻ ብዙ መራመድ እንደማንችል እናውቃለን። ሕንፃ ግንባታችን በፍጥነት አጠናቀን በበቂ የሰው ኃይል ወደ ሥራ ለመግባት ጥድፊያ ላይ ነን፡፡ በወደቡ ዓማካይነት ወደ ውጭ ለምንልካቸውና ወደ ሀገር ውስጥ ለምናስገባቸው የግብርና፣ ኢንዱስትሪ ምርቶች እና አገልግሎቶች በፍጥነትና በጥራት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር እንፈጥራለን፡፡
ከዚህ በሻገር የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ላለፉት 13 ዓመታት በርካታ ልምዶችን አካብቷል። ከአፍሪካ የላብራቶሪ ትብብር እና ዓለም አቀፍ የላብራቶሪዎች ትብብር ጋርም ያለው ወዳጅነት በጣም ጤናማ ነው፡፡ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትም በመምጣት ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ልምድ እና ተሞክሮ የሚቀስሙ አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የሕንድ ትልልቅ ድርጅቶች የአክርዲቴሽን አገልግሎት እንድንሰጣቸው ሥምምነት ፈጽመናል፡፡
የሶማሌላንድ ጋርም በተመሳሳይ የአክሪዲቴሽን ሥምምነት ለመስጠት እየሰራን ነው፡፡ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ደግሞ የአክርዲቴሽን የሥራ ግንኙነት አለን፡፡ አቅማችንም እያደገ ነው፡፡ አንዳንዶች ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ ለአብነትም ኬኒያ በተለያዩ ወሰኖች አግኝታ ከነበረው እውቅና የተወሰዱባት ወሰኖች አሉ፡፡
ኢትዮጵያ ግን መሰል ችግሮች አላጋጠሟትም። ይልቁንም በየዓመቱ አዳዲስ የዕውቅና ወሰኖችን እየጨመርን ነው፡፡ ባለሙያዎቻችንም በአክሪዲቴሽን አገልግሎት ዙሪያ መለስ ማዕቀፍ ውስጥ በደንብ እየሄዱ ነው፤ ልምድም በሰፊው በማካበት ላይ ናቸው። ይሁንና አክሪዲቴሽን አገልግሎት እንደ ሀገር በሕዝቡ እና በመንግስት ሥራ ኃላፊዎች በሚገባው ልክ አልተሰራበትም፡፡ የመገናኛ ብዙሃን በዚህ ላይ ትልቅ ሚና እንዳላቸው እናምናለን፡፡
አክሪዲቴሽን አገልግሎት የትውልዱ የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከመኖር የሚቀድም ዓላማ የለውም፡፡ አክርዲቴሽን አገልግሎት ደግሞ ከሕይወታችን ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ የጥራት ጉዳይ በጣም አንገብጋቢ አጀንዳችን ነው፡፡ ሕብረተሰባችን አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ በተቃራኒ ለጥራት የተሻለ ማሕበረሰባዊ ዕይታ አለው፡፡ እኛም ከብዛት ጥራት የሚል ብሂል በተግባር እስከምናረጋግጥ ድረስ እንሰራለን፡፡ በብዙ የማሕበረሰባችን ክፍልም ጥራት ይወደዳል፤ ይፈለጋል፤ ይፈቀዳልም፡፡
ነገር ግን ወደ ንግድ በምንገባበት ጊዜ ጥራት የሌለው ነገር አግበስብሶ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የመክበር ዝንባሌ ያላቸው አንዳንድ ነጋዴዎች አሉ። እነዚህ ነጋዴዎች ለጥራት የሚሰጡት ትኩረት እምብዛም አይደለም። ሆኖም የማሕበረሰቡን አመለካከትና ግንዛቤ መቀየር ከተቻለ፤ አዋጅና መመሪያዎች ባያስገድዱም ሕብረተሰቡ ማስገደድ ይጀምራል የሚል እምነት አለን።
በመሰረቱ የትኛውም ዓለም ላይ አክርዲቴሽን አገልግሎት አስገዳጅ አይደለም፡፡ ማስገደድ የሚቻለው ግንዛቤ በመፍጠር ነው፡፡ በመሆኑም በሀገራችን በተለያዩ ዘርፎች ላይ ብቃት አለን ብለው እውቅና የሚሰጡ አካላት ወይንም ድርጅቶች ብቁ ናቸው ብለው እውቅና ከመስጠታቸው በፊት በራሳቸውም ብቃት እንዲኖራቸው ጭምር መሥራት ይገባል፡፡ እንደ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሳይንሱን ስንመለከተው እኛ ከነካናቸው ዓለም አቀፍ ወሰኖች ይልቅ ያልነካናቸው በጣም ብዙ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ክንደ ብርቱ ነው ለማለት ከ10 ስትራቴጂክ እቅዱ በመነሳት የት እንጠብቀው?
አቶ ወንድወሰን፡– 2022 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በአፍሪካ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ ግንባር ቀደም ለመሆን አቅደን እየሰራን ነው፡፡ አሁን ካሉን በላቀ ሁኔታ በሁሉም ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ወሰኖች ግንባር ቀደም ለመሆን እየተጋን ነው፡፡ ስለዚህ በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ዕውቅና ቀዳሚ እንሆናለን። በተመሳሳይ የማሕበረሰባችን፣ ምርት ላኪዎችና አስመጪዎች እና ሌሎች አገልግሎት ፈላጊዎች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የላቀ ምዕራፍ ላይ እንዲገኙ እንተጋለን፤ ግባችንን ለማሳካትም ያለመታከት እንሰራለን፡፡
አዲስ ዘመን:- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታ አመሰግናለሁ::
አቶ ወንድወሰን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም