ለዘመናት የዘለቀው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቻችሎ የመኖር ባህል እንደገና ሊያብብ እንደሚገባው ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል የዘርፍ መስሪያ ቤት ሰራተኞች፣ ከፍተኛ ኃላፊዎችና አባ ገዳዎች የተገኙበት ሲፖዚየም በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የተካሄደ ሲሆን፥ የዜጎች ዘመን ተሻጋሪ የሆነው ተቻችሎ የመኖር ባህል እንደገና ሊያብብ እንደሚገባው ተነግሯል።
በዚህ ሲፖዚየም ላይ የመነሻ ሃሳብ ጽሁፍ ያቀረቡት የጨፌ ኦሮሚያ የህዝብ ግንኙነት አቶ ሀብታሙ ደምሴ ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ተቻችለው በአንድነት የኖሩባትና ለሌሎች ሀገራትም በምሳሌነት የምትጠቀስ ነች ብለዋል።
ዜጎች የአንዱን ተቋም አንዱ በመገንባት በመደጋገፍና በመተሳሰብ ለዘመናት በአነድነት የኖሩባት ሀገር ከመሆኗም ባሻገር በጋብቻና በደም የተሳሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋ።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ይህንን እሴት የሚሸረሽሩ ግጭቶች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
የሲፖዚየሙ ታሳታፊዎች በበኩላቸው የተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስት፣ የሃይማኖት ተቋማት አሁን ላይ በሀገሪቱ እየታየ ላለው ለውጥ ቀጣይነት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
በዚሁ ሲፖዚየም ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባም የተመላከተ ሲሆን፥ የዜጎች የአብሮ የመኖር እሴቶችን ለመሸርሸር ጥረት የሚያደረጉ አካላት ለህግ በማቅረብ ግጭቶችና መፈናቀሎች መቆም እንዳለባቸው ነው ተሳታፊዎቹ የተናገሩት።
የ13ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል አካል የሆኑ የተለያዩ ፕሮግራሞች በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ሲሆን፥ ከነዚህም መካከል ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት አዳራሽ የተካሄደው ሲንፖዚየም አንዱ ነው ተብሏል።ዘገባው የኤፍቢሲ ነው፡፡