
አዲስ አበባ፡- የ2016 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን በደመቀ ሁኔታ በጎንደር ከተማ እንዲከበር የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ::
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው ለኢትዮጵያ ድርጅት እንደገለጹት፤ የጥምቀት በዓልን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በከተማ ደረጃ በከንቲባ የሚመራ አንድ ዐብይ ኮሚቴ እና ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተደራጅተው ወደ ሥራ በመግባት የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ናቸው::
በተለይም በጎንደር ፋሲለደስ ባህረ ጥምቀት በሚከናወንበት ሥፍራ የሚያስፈልጉ የግንባታ፣ የጽዳት እና ሌሎች ጊዜያዊ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል ብለዋል:: አቶ አበበ፤ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር አስፈላጊው ውይይት መደረጉን አስታውቀው፤ በዚህም እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ከባለፉት ዓመታት በተለየ መንገድ ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል::
አገልግሎት ሰጪዎች ለበዓሉ ተሳታፊዎች የተሟላና ቀልጣፋ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል:: ኃላፊው በተጨማሪም ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ በተሠራ ሥራም ክብረበዓሉን በከተማው ለመታደም ለሚመጡ ጎብኚዎች ከላሊበላ በቀጥታ ጎንደር የአየር ትራንስፖርት የተጀመረ መሆኑንም አስታውቀዋል::
እንዲሁም በከተማው የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ ሲሆን ከአየር ማረፊያ ሆቴል የሚያደርስና ከተማ ውስጥ ለውስጥ የሚያስጎበኙ በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል:: አቶ አበበ እንደገለጹት፤ በዓሉ የከተማውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ አለው:: ይህንንም ለመጠቀም ሰላም ዋና መሠረት ሲሆን ለዚህም ሕዝቡ የጸጥታው ባለቤት እንደሆነ በተደጋጋሚ በተዘጋጀ መድረክ ተረጋግጧል::
እንግዶች የጥምቀት በዓልን በከተማው ከማክበር ባለፈ ቆይታቸውን የሚያራዝምባቸው፣ የአካባቢውን ጸጋ የሚመለከቱበት ብሎም በዘርፉ ላይ ኢንቨስት የሚደርጉበትን ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ነው የገለጹት:: ከበዓሉ በፊት የባህል ሳምንት መድረክ የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቁመው፤ ሰፊ ማህበረሰብ የሚሳተፍበት በመሆኑ የዝግጅት ሥራዎች እንደተሠሩ አቶ አበበ አስታውቀዋል::
እንዲሁም በዓሉን ምክንያት በማድረግ በበዓሉ ማግስት በከተማ ደረጃ የኢንቨስትመንት ፎረም ይካሄዳል:: በዚህ መድረክም እንግዶችን በኢንቨስትመንት ለማሳተፍ በግልጽ ጨረታ ከ 12 ነጥብ 7 ሄክታር በላይ መሬት በሊዝ ለባለሀብቶች ለማስተላለፍ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል::
በአሁኑ ጊዜ ጎንደርና አካባቢው በመደበኛና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ ሲሆን በከተማው የተሟላ አገልግሎት እየተሰጠ ነው:: በመሆኑም እንግዶች ያለምንም ስጋት በዓሉን ማክበርና በአካባቢው የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን መጎብኝት የሚችሉ መሆኑን በመገንዘብ እንዲጎበኙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2016