
አዲስ አበባ፡- በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ከሚያጡ ዜጎች መካከል 86 በመቶ እግረኞች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን አስታወቀ::
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ሰሞኑን 400 ረዳት ተማሪ ትራፊክ አስተናባሪዎችን ለአንድ ወር አሠልጥኖ አስመርቋል::
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚዴቅሳ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ በዓመት ከአራት ሺህ በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጣሉ:: በአዲስ አበባ ደግሞ በቀን አንድ ሰው ሕይወቱን ያጣል::
ዳይሬክተሩ በ2015 ዓ.ም የትራፊክ አደጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሞት አደጋን መቀነሱን ገልጸው፤ በ2015 ዓ.ም 408 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው አጥተዋል:: ይህ ከ2014 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸርም ስምንት በመቶ በትራፊክ የሚደርስ የሞት አደጋ ቀንሷል ብለዋል::
የትራፊክ ግጭት ዋና ዋና መንስኤዎች መካከል በፍጥነት ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ እና የልጆች የደህንነት መቀመጫ አጠቃቀም እንዲሁም ሞተር አሽከርካሪዎች የጭንቅላት መከላከያ ቆብ አለማድረግ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል:: የሞት አደጋ ከደረሰባቸው የመንገድ ተጠቃሚዎች ውስጥ እግረኞች 86 በመቶ እንደሚይዙ ገልጸው፤ እግረኞችን ከአደጋው ለመታደግ የተጠናከሩ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል::
በዚህም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የትራፊክ አደጋ ለመከላከል ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝና በተለያዩ ጊዜያቶች ተማሪዎችን በትራፊክ አገልግሎት ላይ እያሠለጠነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል::
ከ11ዱም ክፍለ ከተማ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 400 ተማሪዎች የተግባር ሥልጠና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በኩልና የንድፈ ሃሳብ ሥልጠና ደግሞ በትራፊክ ማኔጅመንት ባለሙያዎች በኩል አሠልጥኖ በትናንትናው እለት ማስመረቁን ገልጸዋል::
ተማሪዎቹ በትምህርት መግቢያና መውጫ ሰአት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ይሠራሉ ያሉ ሲሆን ባለሥልጣን መሥሪያቤቱም ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል::
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ዓመታት ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑ 200 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከአምስት ሺህ በላይ ረዳት ተማሪ የትራፊክ አስተናባሪዎችን አሠልጥኖ ወደ ሥራ አሰማርቶ ይገኛል::
ዳይሬክተሩ ተማሪዎቹ የመንገድ ትራፊክ ፍሰትን በማስተናበር መደበኛ የትራፊክ ፖሊሶችን በማገዝ እግረኛውን በተለይም ተማሪዎችን መደበኛ የእግረኛ መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያግዙ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተሠራ ሥራም በትምህርት ቤት አካባቢ የሚደርስ አደጋን መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል::
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2016