ሚያዝያ 10 ቀን 1992 በሴኔጋል ሴዲዮ የተባለ ስፍራ ነው የተወለደው። ያደገው ግን በሴኔጋል ደቡባዊ እምብርት ውስጥ በምትገኘው ባምባሊ የተባለች ትንሽ መንደር ውስጥ ከሚኖር ማኅበረሰብ ጋር ነው። ይህ ሕጻን ወላጆቹ ከሚንከባከቡት በላይ ብዙ ልጆች ይዘው ስለተቸገሩ ነበር ከአጎቱ ጋር ለመኖር እትብቱ የተቀበረበትን ስፍራ ትቶ ወደ ባምባሊ መንደር የተጓዘው።
ከሁለት ሺህ የማይበልጥ ሕዝብ በሚኖርባት ትንሽ መንደር የጨርቅ ኳስ በየሜዳው እያንከባለለ የልጅነት ሕይወቱን መግፋት የተያያዘው ታዳጊ እድሜው ለትምህርት ቢደርስም ቤተሰቦቹ እሱን ለማስተማር በቂ ጥሪት አልነበራቸውም። ስለዚህ በየማለዳው ከእንቅልፉ ነቅቶ ምሽት ላይ ፀሐይ እስክትጠልቅ በትንሿ መንደር አቧራማ በሆነው ጎዳና ላይ ኳስ ሲያንከባልል መዋል ዕጣ ፋንታው ነበር። ይህን ሲያደርግ ግን በታዳጊ እድሜው ታላቅ ተጫዋች ሆኖ በእግር ኳስ ያልፍልኛል ብሎ በማሰብ አልነበረም።
ይህ ታዳጊ በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች አስደናቂ ብቃት በማሳየት አፍሪካ ካፈራቻቸው ድንቅ ተጫዋቾች አንዱ መሆን የቻለው ሴኔጋላዊ ሳዲዮ ማኔ ነው። ከፈረንሳይ ሊግ ሜትዝ ክለብ ተነስቶ በኦስትሪያው ሬድቡል ሳልዝበርግ አድርጎ ወደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሳውዝሃምፕተን የተሻገረው ማኔ በሜርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል የማይረሳ ታሪክ ሠርቶ በጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየር ሙኒክ አንድ ዓመት በማሳለፍ አሁን ላይ ታላላቅ ከዋክብት በተሰበሰቡበት የሳዑዲ ዓረቢያው ክለብ አል ናስር ከትሟል።
ድህነት ባጎሳቆለው መንደር የልጅነት ሕይወቱን ያሳለፈው ማኔ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት ያደረበት አገሩ ሴኔጋል እአአ በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜን ስትቀላቀል ከተመለከተ በኋላ ነበር። ታዳጊው ማኔ ትኩረቱን ወደእግር ኳስ ሲያዞር ግን ቤተሰቦቹ መቃወማቸው አልቀረም። ነገር ግን ብዙም አልተጫኑትም፣ እንደሃሳቡ ይጓዝ ዘንድም ከግብርና የሚያገኟቸውን ምርቶች እየሸጡ በአቅማቸው ይደግፉት ያዙ። የመንደሩ ሰዎችም ለታዳጊው ገንዘብ አሰባስበው ወደ ሴኔጋል መዲና አቅንቶ በተሻለ የእግር ኳስ አካዳሚ ውስጥ ብቃቱ እንዲጎለብት ረዱት።
ማኔ ከወገኖቹ የተደረገለትን ድጋፍ ይዞ ወደ ዳካር ያቀናበት ረጅም መንገድና ውጣ ውረድ ወደ ፈረንሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጉዞ ፕሮፌሽናል ተጫዋች እስከሆነበት እለት ያለው ታሪክ በራሱ አንድ ትልቅ መጽሐፍ ይወጣዋልና እሱን በሌላ ጊዜ መመልከት የተሻለ ነው።
አስደናቂ ችሎታውን ያስመሰከረው የክንፍ ተጫዋች በትንሿ መንደር በባዶ እግሩ የጨርቅ ኳስ ከማንከባለል ተነስቶ ከዓለማችን ኮከቦች አንዱ በመሆን የሀብትና የዝና ማማ ላይ ከወጣ በኋላ መነሻውን አልዘነጋም። መጀመሪያ ያደረገው ነገር ያገኘውን ቋጥሮ ቤተሰቦቹን በአንድ ትልቅ መኖሪያ ሕንጻ ውስጥ እንዲኖሩ ማድረግ ነበር። በዚያም የአካባቢው ማኅበረሰብ እሱ በትልቅ ደረጃ ሲጫወት ተሰብስበው እንዲመለከቱት ትልቅ ስክሪን ዘርግቶላቸዋል። የተለያዩ ድጋፎችንም በዓይነትና በገንዘብ እያደረገ ከትንሿ መንደር ነዋሪዎች ጎን ከመቆም ቦዝኖ አያውቅም።
ዓመለ ሸጋው ኮከብ አገሩ ሴኔጋልን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ያደረገው ባለፈው የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ነው። ከዚያ በፊትም ይሁን በኋላ እንደበርካቶቹ የዓለም ከዋክብት የእረፍት ጊዜውን በተንደላቀቁ ስፍራዎች ማሳለፍ ፍላጎቱ አይደለም። የዕረፍት ጊዜውን በተነሳባት ኮሳሳ መንደር ከድሃው ማኅበረሰብ ጋር ማሳለፍ ምርጫው ነው።
ትንሹ የባምባሊ ሕዝብ ካደገበት ማኅበረሰብ ተሻግሮ የመላው ሴኔጋላውያን ኩራት የሆነውን ልዑላቸውን ከአፍሪካ ዋንጫው ድል በኋላ በአንዱ ቀን እንዲጎበኛቸው ጋበዙት። የክብር እንግዳ ሆኖ በሄደበት ጊዜም በመንደሩ ከሌሎች ሴኔጋላውያን ጋር አንድ ጨዋታ አድርጓል። የመንደሩ የመጫወቻ ሜዳ ጭቃ ነበር፤ እሱ ግን ተጸይፎ አልተዋቸውም። ይልቁንም ጭቃው ላይ በሚገባ ተጫውቶ ነው የተሸኘው። ሲሸኝ ግን በልቡ አንድ ነገር ይዟል። ያደገበትና የታወቀበትን መንደር ሜዳ በሚመጥን መንገድ መሥራት።
ማኔ ይህንን በአዕምሮው ይዞ ወደ አውሮፓ ተመለሰ። ብዙም ሳይቆይ ሥራውን ጀመረ። ለመንደሩ ባምባሊ የሚመጥን ያለውን ሜዳም በአጭር ጊዜ ውስጥ አሠራ። ይህንን ሜዳ የፊፋን መስፈርት ባሟላ መልኩ አሰርቶ ካጠናቀቀ በኋላም ሥራ እንዲያስጀምር ሰሞኑን ነበር ተጋብዞ ወዳደገባት መንደር የተመለሰው። እሱም የሠራውን ነገር ተመልክቶ ‹‹አሁን የልቤ ሞልቷል›› ሲልም በሐሴት ተናግሯል።
‹‹ዛሬ ከእናንተ ጋር በመሆኔ እጅግ ተደስቻለሁ፣ ሁሉም ነገር ወደጀመረባት መንደሬ ባምባሊ እንኳን ደህና መጣችሁ፣ ለእኔ ትልቅ ትርጉም ባለው በዚህ የፊፋ ደረጃን ያሟላ የእግር ኳስ ሜዳ ፊት ስቆም በኩራት እና በደስታ በተሞላ ልብ ነው። ይህ ለምወደው መንደሬ የተሰጠኝ ስጦታ ብቻ አይደለም። ከሁሉም በላይ የአንድነታችን፣ የጥንካሬያችን እና ለእግር ኳስ ያለን ፍቅር ምልክት ነው›› በማለትም ማኔ ደስታውን አንጸባርቋል።
ማኔ ድክ ድክ ብሎ ላደገባት መንደር ያለውን ከመስጠት ሰስቶ አያውቅም። አሁን ካስመረቀው ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ ባሻገር ለመንደሩ ያላደረገው ነገር የለም። ከ750 ሺ ፓውንድ በላይ አውጥቶ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታል፣ ፖስታ ቤትና ነዳጅ ማደያ ከፍቷል።
በቅርቡ የእግር ኳስ ሜዳውን ባስመረቀበት ወቅትም ታሪካዊዎቹን የሴኔጋል አንጋፋ ኮከቦች ፓፒስ ሲሴ እና አል ሃጂ ዲዩፍን አስከትሎ እአአ 2021 ላይ በ455 ሺ ፓውንድ ያስገነባውን ሆስፒታል ሲጎበኝ ታይቷል። ይህ ሆስፒታል ከመንደሩ ባምባሊ ባሻገር በአቅራቢያ የሚገኙ ከ34 በላይ መንደር ነዋሪዎችንም የሚያገለግል ነው።
ማኔ በባምባሊ መንደር በ250ሺህ ፓውንድ ዘመናዊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም አስገንብቷል። ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆነው የመንደሩ ነዋሪ በወር 57 ፓውንድ ድጋፍ የሚያደርገው ማኔ ባስገነባው ትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች 326 ፓውንድ የማበረታቻ ሽልማት ይሰጣል። ትምህርት ቤቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በማደራጀትም ለእያንዳንዱ ተማሪ የላፕቶፕ ኮምፒዩተር በማደል በትምህርት ቤትም ይሁን በቤታቸው የ4G ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ አድርጓል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 5/2016