ኢትዮጵያ የበርካታ የቱሪዝም መስህቦች መገኛ ነች። እነዚህን መስህቦች ወደ መዳረሻነት ቀይሮ የቱሪስት ፍሰቱን መጨመር ደግሞ ከዘርፉ ተዋንያን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። ባለፉት ዘመናት የሀገሪቱን ሀብቶች በሚፈለገው ልክ የማስተዋወቅና ከዚያም ተጠቃሚ የመሆን ሂደቱ አዝጋሚ የሚባል እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። የቱሪዝም ልማቱ፣ ጥበቃው እንዲሁም የቱሪስቶች ትኩረት በውስን የኢትዮጵያ መዳረሻዎች ላይ ብቻ የተገደበ ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቱሪዝሙን ዘርፍ መነቃቃትና እድገት አቅጣጫ የሚቀይሩ እርምጃዎች በመንግሥት እየተወሰደ ይገኛል። ዘርፉን ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ተርታ መድቦ ልዩ ትኩረት ከመስጠት ጀምሮ አገሪቱ የቱሪዝም እምቅ አቅሞቿን አውቃ ለእድገቷ መሰላል እንዲሆኑ ለማስቻል ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እየሠራች ትገኛለች።
መንግሥት በዘርፉ ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችንና አስቻይ ማዕቀፎችን ከመንደፍ እና በሥራ ላይ ከማዋል ባሻገር መዳረሻዎችን በማልማት፣ በማስተዋወቅና የግሉ ዘርፍን ተሳትፎ በማበረታታት ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። በዚህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ፈጣን እድገት እያስመዘገበችና የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቱም ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።
ዘርፉ በኮቪድ ወረርሽኝ ስርጭትና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች ፈተና ውስጥ ወድቆ እንደነበር ባይታበይም በተለይ በሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ በመሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ ጉልህ እድገቶችን አሳይቷል። እነዚህ ፕሮጀክቶች የፈጠሩት መነቃቃት ያጋጠሙ ችግሮችን ተቋቁሞ የቱሪስት ፍሰቱ እንዳይቋረጥና ችግሮቹ የፈጠሩትን መቀዛቀዝ መቋቋም እንዲቻል በር ከፋች ሆኗል።
ከአዳዲስ የመዳረሻ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ባሻገር የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቱን የጉብኝት ፍላጎት የማነቃቃት፣ የማስተዋወቅ እንዲሁም ሀገር አቀፍ ጥሪዎችን የማድረግ ተግባሮች ባለፉት ዓመታት ተፈጽመዋል። ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መጥተው ከባሕልና ከማንነታቸው ጋር እንዲተዋወቁ፣ የውጪ ቱሪስቶች ከዚህ ቀደም ባልተለመዱ የኢትዮጵያ ክፍሎችና መስሕቦችን እንዲተዋወቁ እና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቱር ኦፕሬተሮችና የዘርፉ ተዋንያን የነበራቸው ድርሻ ቀላል የሚባል አይደለም። ይህ ጥረት አሁንም እንደቀጠለ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከሳምንታት በፊት ከዳውሮ ዞን እስከ ኮንታ በሚዘረጋው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ተገኝተው ‹‹የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ›› መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ አባላት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከባሕላቸው፣ ከማኅበረሰቡ፣ ከታሪክና ከተፈጥሮው ጋር እንዲተዋወቁና ለኢትዮጵያም አምባሳደር ሆነው እንዲያስተዋውቁ ጥሪ አድርገው ነበር።
ጥሪው በኢትዮጵያ በቱሪዝም ላይ እየተወሰዱ ካሉ የማነቃቃት እርምጃዎች ውስጥ የሚካተት ነው። የቱሪዝም ሚኒስቴር በተመሳሳይ ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮችን በመቅረፅ እስከ 2017 ዓ.ም የሚዘልቅ የሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ አባላት ጥሪን ይፋ አድርጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል። ካሳለፍነው የገና በዓል አንስቶ ጥሪውን የተቀበሉ የሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ይገኛሉ። ሚኒስቴሩና የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴም በሰጠው መግለጫ እየተደረገ ያለው አቀባበል በቀጣይ ምዕራፍ ወደ አገራቸው ለሚመጡ ተነሳሽነትን እየፈጠረ መሆኑን አስታውቋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በተለይ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጥሪውን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ ለሁለተኛው ትውልድ የተደረገው ጥሪ ዋና የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዓመታት በውጭ ሀገራት ኖረዋል፡፡ ልጆች አፍርተዋል፡፡ ልጆቻቸው የማንነት ጥያቄ አለባቸው። የመጡበትን የእናት የአባቶቻቸውን አያቶቻቸውን ሀገር ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ለማሳካት ጥሪው አስፈልጓል።
ሚኒስትሯ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የሚያኮራ ታሪክና ባሕል አላት፡፡ እነርሱም ውብ የሆነ ተፈጥሮ ያላት ሀገር አለቻቸው። ይህ እንደመሆኑ መሰል ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ የሁለተኛው ትውልድ አባላትም መነሻቸውን ያውቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም መነሻ ነች፡፡ የሰው ልጅ መገኛ ነች። ‹‹የእናት የአባቶቼ የአያቶቼ ሀገር›› የሚለው ስሜት በውስጣቸው አለ። እንደ ሰው ልጅ ሁሉም መነሻችንን ማወቅ ይፈልጋል፡፡
‹‹ጥሪው ሁለተኛ መጥተው ባሕልና ታሪካቸውን እንዲያውቁ እንዲሁም ለወገኖቻቸው መስጠትና መቀራረብ እንዲችሉ መንገድ ለመፍጠር ነው›› የሚሉት ሚኒስትሯ፤ የያዝነው የጥር ወር ብዙ ፌስቲቫሎች ያሉበት በመሆኑ በተለያየ መልኩ ሀገራቸውን ባሕላቸውን ለማወቅ የተመቸ አጋጣሚ የሚፈጠርበት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም የተለያዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ያስረዳሉ። ባሕላቸውን እንዲያውቁ፣ እንዲማሩና ወደተለያዩ የሀገራችን ክፍል ሄደውም ራሳቸው በራሳቸው እንዲያገኙ ምቹ አጋጣሚ መፈጠሩን ያስረዳሉ፡፡ ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገራቸው የገቡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በርካቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።
አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ዩኒት አስተባባሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህቦች ለማስተዋወቅ ጥሪው ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው። የሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራዎች ወደ እናት አገራቸው ሲመጡ ከፍተኛ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይጠበቃል፤ ዘርፉንም በተለየ የማነቃቃት አቅም ይፈጥራል።
‹‹ጥሪውን አስመልክተን የተለያዩ ዝግጅቶችን በማሰናዳት ላይ እንገኛለን›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ በቱሪዝም ሚኒስቴር ሰብሳቢነት በሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ በቅርብ ግዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ሳምንት የሚል ደማቅ ሥነ ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ይገልፃሉ። በመሰናዶው ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች እንዳሉ በመግለፅም ከዚህ ወስጥ ባሕልን ማስተዋወቅ የሚረዱ ጭፈራዎች፣ ሙዚቃዎች፣ ባሕላዊ አልባሳት የሚተዋወቁበት ይሆናል። በዝግጅቱ የዕደ ጥበባት ውጤቶች፣ የኢትዮጵያ ድምፆች (ሙዚቃ መሣሪያዎች)፣ ባሕላዊ ምግቦችና የአዘገጃጀት ሥነ ሥርዓቶች ለሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ እንግዶች የሚተዋወቅበት ዝግጅት የሚያካትት ነው።
‹‹ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በሩቅ ከሚሰሙት በዘለለ በቀጥታ ቀርበው በማየት እና በመሳተፍ ባሕላቸውን እና ማንነታቸውን የሚተዋወቁበት ነው›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ በኢትዮጵያ ሳምንት ዝግጅት ላይ ከባሕላዊ ሁነቶቹ በተጨማሪ ጉባኤዎች እንደሚኖሩ ይናገራሉ። በሚኒስቴሩ በኩልም የቱሪዝም መስህብ ማስተዋወቅ ሥራ እንደሚከናወን ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ ሳምንት ላይ ከሚከናወኑ ሁነቶች ባሻገር ልዩ ልዩ የጉዞና ጉብኝት ዝግጅቶች ተዘጋጅተዋል።
አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ (ኢቲ ሆሊደይስ) በቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሁለተኛ ትውልድ የዲያስፖራ ክፍል ፍላጎትና ባሕሪ መሠረት ያደረጉ የጉዞና ጉብኝት ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ ሆቴሎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ከፍተኛ ቅናሽ አድርገው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ አገራቸው ያላትን የቱሪዝም ፀጋዎች እንዲያውቁ፣ ባህላቸውን እንዲረዱና እንደ ሀገር መሠረታቸውን ዳግም እንዲገናኙ በማሰብ የተዘጋጁ ናቸው። ክልሎችም ከዋናው ዝግጅት ጋር በተናበበ መልኩ የተለያዩ ሁነቶችን እንደሚያሰናዱ ይጠበቃል።
ሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ሲደረግ በርካታ ሁነቶችን ታሳቢ በማድረግ ነው። ከዚህ ውስጥ ጥሪው በተደረገ ሰሞን የገና በዓል በመሆኑ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ባሕል፣ በዓላትና ፌስቲቫሎች ጋር እንዲገናኙ እድሉን እንደሚፈጥር ሲገለፅ ቆይቷል። የያዝነው የጥር ወርም በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ወቅት ነው። ይህ አጋጣሚም ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃይማኖታዊ ፌስቲቫሉ ላይ ተገኝተው ሥነሥርዓቱን ለመታደም እድሉን ይፈጥርላቸዋል።
አቶ ቴዎድሮስ ደርበው እንደሚሉት፣ የጥምቀት በዓል በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ይከበራል። በተለይ በጎንደር፣ በባቱ (ዝዋይ)፣ በኢራንቡቲ ባማረና በልዩ ሁኔታ እንደሚከበር አንስተው ጥሪ የተደረገላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንም እንደየፍላጎታቸው እና የግል መርሐ ግብራቸው ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚኖር ይገልፃሉ። በልዩ ሁኔታ በቱሪዝም ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሁነት እንደማይኖርና በኢትዮጵያ ሳምንት የሚጠቃለል መሆኑንም ያነሳሉ።
ይሁን እንጂ ጥምቀት ከማይዳሰስ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ መካከል በዩኔስኮ የተመዘገበ ታላቅ የኢትዮጵያውያን ባሕል መሆኑን ያነሱት አቶ ቴዎድሮስ፣ ማንም ሰው በሀገር ውስጥ ተገኝቶ በዚህ ታላቅ ሀይማኖታዊ በዓል ላይ ሳይታደም አይቀርም ይላሉ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህንን ሀይማኖታዊ በዓል አንደ አንድ የቱሪዝም መስህብ እንደሚያስተዋውቅ ያነሳሉ። ወደ አገራቸው የገቡ የሃይማኖቱ ተከታዮች ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በበዓሉ ላይ ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ይገልፃሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን አውቀው ለቀሪው ዓለም እንዲያስተዋውቁ፣ ከባሕልና ማንነታቸው ጋር እንዲገናኙ እና ከታሪካዊ መሠረታቸው ጋር ጥብቅ ትስስር እንዲፈጥሩ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በቱሪዝሙ ዘርፍ ላይ ትልቅ ለውጥ ያስገኙ ጥረት በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ አባላት የተደረገው ጥሪም የዚሁ ጥረት አካል ነው፡፡
ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከተደረጉ ጥሪዎች ውስጥ አንዱና የመጀመሪያው በ2014 የተካሄደው ተጠቃሽ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው። በወቅቱ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ በመንግሥት ይፋዊ ጥሪ ተካሂዶ፣ ጥሪው ስኬታማ እንደነበር መረጃዎች ጠቁመዋል። በጊዜው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገናን በላሊበላ፤ ጥምቀትን በጎንደር እንዲሁም የሙስሊሙ ማኅበረሰብም ረመዳንን በኢትዮጵያ እንዲያከብሩና ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ የቱሪዝም መስህቦችን እንዲጎበኙ ተደርጎ ነበር።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም