“ከብልህ ደጃፍ ደረሰኝ ይቆረጣል”

ግዢ ስንፈጽምና አገልግሎት ስናገኝ ደረሰኝ የመቀበል ልምድ ያለን ምን ያህሎቻችን ነን ? በሀገራችን ደረሰኝ ባለመቁረጥ፣ ሐሰተኛ ግብይት በመፈጸምና ከዋጋ በታች ተምኖ ደረሰኝ በመቁረጥ መንግሥት ከታክስ ማግኘት ያለበትን ገቢ የሚያሳጡ በርካታ ከደረሰኝ ጋር የተያያዙ የማጭበርበር ተግባራት ይፈጸማሉ::

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ ለሕግ ተገዥ ባለመሆን ምክንያት ለጂዲፒዋ ከታክስ ማግኘት የሚገባትን 4 ነጥብ 5 በመቶ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ገቢ በየዓመቱ ታጣለች::

የአንደኛው ዓለም ዜጎች “ሞትና ግብር የማይቀር ነው” የሚል ብሂል አላቸው:: በሦስተኛው ዓለም ግን ግብር ከመክፈል ይልቅ ሞቱን የሚመርጠው ብዙ ነው:: እኛ ሀገር ደግሞ ነገሩ ይብሳል:: “ከሞኝ ደጃፍ ደረሰኝ ይቆረጣል” ብለው ደረሰኝ ደንበኞች እጅ እንዳይደርስ የሚያደርጉ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም:: እርግጥ ነው “ከብልህ ደጃፍ ደረሰኝ ይቆረጣል” ብለው ህግን አክብረው ደረሰኝ የሚቆርጡ ብዙ ሀገር ወዳዶች መኖራቸውም አይካድም::

ወዲህ ደግሞ ሸማቹ ማህበረሰብ ለፈጸመው ግዢና ላገኘው አገልግሎት የተጠየቀውን ከፍሎ ከመሄድ ባለፈ ደረሰኝ የመጠየቅ ልምዱ እምብዛም ነው::

ወጣት ሳምራዊት ነጋ በአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ናት:: በተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስትገለገል አብዛኞቹ ሳትጠይቅ ደረሰኝ እንደሚሰጧትና ዋጋውን ተመልክታ ክፍያ እንደምትፈጽም ትናገራለች:: በአንጻሩ በሸመታ ወቅት ከሱፐርማርኬቶች በቀር ደረሰኝ የሚሰጡ የንግድ ተቋማት እንደማያጋጥሟትና እርሷም ዋጋው እንዲቀንስላት ትኩረቷን ክርክር ላይ ስለምታደርግ ደረሰኝ መጠየቅን እንደማታስበው ትገልጻለች::

የ52 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ኃይሌ ታደሰ በበኩሉ፤ ግዢ ሲፈጽምም ሆነ አገልግሎት ሲያገኝ ደረሰኝ ሳይቀበል ፈጽሞ ክፍያ እንደማይፈጽምና በዚህም ምክንያት ከአንዳንድ ነጋዴዎች ጋር ግጭት ውስጥ እስከመግባት እንደደረሰ ይናገራል::

በሀገራችን ደረሰኝ ከመስጠትና ከመቀበል ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው ችግር ለህግ ተገዢ ካለመሆን ጋር የሚገናኝ ነው:: በዘርፉ በተለያየ ጊዜ የወጡና የተሻሻሉ የህግ ማዕፎች በመኖራቸው የህግ ክፍተት አለ ለማለት ይቸግራል::

የተጨማሪ እሴት ታክስን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር – 609/2001 አንቀፅ 2 (10) መሰረት ማንኛውም ታክስ ከፋይ ላከናወነው ሽያጭ ወይም ለሰጠው አገልግሎት ለደንበኛው ወድያውኑ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አለበት:: በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 47ሀ (9) (ሐ) ስር ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ግብር ከፋይ “ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ አይክፈሉ” የሚል የፅሁፍ ማስታወቂያ በሚታይ ቦታ በግልፅ ለጥፎ ካልተገኘ አንድ ሺህ ብር እንደሚቀጣ ይደነግጋል።

በተሻሻለው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 17 (1) ማንኛውም ነጋዴ ለሸጠው እቃ ወይም አገልግሎት ለሸማቹ ወድያውኑ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ተገልጿል::

የፌዴራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 120 (1) እና 131 (1) (ለ) ላይ ማንኛውም ደረሰኝ የመቁረጥ ግዴታ ያለበት ታክስ ከፋይ ያለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ ወይም አገልግሎት ከሰጠ ከ2 እስከ 5 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ በግልፅ ደንግጓል።

በተጨማሪ ግብይት ሳይፈፅም ደረሰኝ የሚቆርጥ ግብር ከፋይም ሆነ የሚቀበል ሰው ከ7 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ ተጠቅሷል። ታክስ ከፋዩን ያለደረሰኝ ሽያጭ ወይም አገልግሎት እንዲሰጥ የረዳ፣ ያበረታታ፣ የገዘ እና ያነሳሳ ወይም የተመሳጠረ ማንኛውም ግለሰብም ዋና ወንጀል አድራጊው (ግብር ከፋዩ) በሚቀጣበት ቅጣት ልክ እንደሚቀጣ ይደነግጋል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ መረጃና ሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ራቢያ ይማም ደረሰኝ ከመስጠትና ከመቀበል ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው ሰፋ ያለ ችግር ምክንያቶች ሁለት መሆናቸውን ይናገራሉ::

የመጀመሪያው ህብረተሰቡ መብቱን አውቆ አለማስከበሩ ነው የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ሁለተኛው የደረሰኞችን ትርጉም አለማወቅ መሆኑን አመላክተው፤ “ደረሰኞች የዕቃውን ዋጋ ገልጸውልን ብቻ የሚያልፉ ሳይሆኑ የከፈልነው ገንዘብ መንግሥት ጋር መድረሱን የምናረጋግጥባቸው ናቸው” ይላሉ::

አክለውም፣ አንዳንድ ህገወጥ ነጋዴዎች ሸማቹ ደረሰኝ በሚጠይቃቸው ጊዜ አልሸጥም ወይም አገልግሎት አልሰጥም በማለት ለማሸማቀቅ እንደሚሞክሩ ጠቁመው፤ ሸማቾች በአዋጅ የተሰጣቸውን ስልጣን በደንብ ተገንዝበው ወደ ውስጣቸው ስላላሰረጹ ‘እቃውን ወይም አገልግሎቱን አግኝቻለሁ ለምን እጨቃጨቃለሁ’ ብለው ትተው እንደሚሄዱ ይገልጻሉ::

ሳያውቁ ወንጀል በሆነው ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙና ካሳወቅናቸው በኋላ ወደ ሥርዓቱ የሚመጡ ብዙ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች አሉ ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በአንጻሩ ደግሞ አሻፈረኝ ብለው ከታክስ ራሳቸውን ለመሰወር፤ በገበያ የበላይነትን ለማግኘት እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ደረሰኝ መቁረጥ የማይፈልጉ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዳሉ ይናገራሉ::

በታክስ አስተዳደር አዋጁ አንቀጽ 120 መሰረት ደረሰኝ ሳይቆርጥ ግብይት ያከናወነ ሰው ግብይቱ ከ100 ሺ ብር በታች ከሆነ ከ25 ሺ ብር እስከ 50 ሺ ብር የሚደርስ አስተዳደራዊ ቅጣትና ከሦስት እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ ያመላከቱት ራቢያ፤ “ከ100 ሺ ብር በላይ የሆነ ግብይት ደረሰኝ ሳይቆርጥ የሚፈጽም ደግሞ ያከናወነውን ሽያጭ ትልቅ ዋጋ እንዲከፍልና ከሰባት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጣ ይደረጋል” ይላሉ::

አያይዘውም፤ “ሕገወጦችን የማንቀጣ ከሆነ አስተምረንና ገስጸን ግንዛቤ አስጨብጠን ወደሥቀራ የምናስገባቸው ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ይቀጭጫሉ፤ ከገበያም ይወጣሉ” በማለት ለሕጋዊ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ጥበቃ ማድረግ ስለሚያስፈልግና ሀገርም ታክስ ማግኘት ስላለባት በአዋጅ የተቀመጡት እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ይገልጻሉ::

ሸማቹ ማህበረሰብ ደረሰኝ መጠየቅን ባህል እንዲያደርግ ገቢዎች ሚኒስቴር በቀጣይ አዲስ አሰራር እንደሚከተል በአመላከቱበት ንግግራቸው፤ “ሸማቾች ለከፈሉት ተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሲጠይቁ በደረሰኝ ቁጥሩ የሎተሪ እጣ ውስጥ ገብተው ለሽልማት የሚታጩበትንና የታክስ ተመላሽ የሚያገኙበትን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ለመተግበር እየሰራን ነው” ሲሉ ሚኒስቴር መስሪያቤታቸው የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ለማሳለጥ ወጥኖ እየሰራ ስለመሆኑን ጠቁመዋል::

የገቢዎች ሚኒስቴር ውጥን ከተሳካ ደረሰኝ ከእጁ የማያደርሱት ነጋዴዎች ደጅ ድርሽ የሚል ሸማች አይኖርም:: “ከብልህ ደጃፍ ደረሰኝ ይቆረጣል” ባይ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎችም ይበዙልናል::

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You