የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ በኮትዲቯር ይጀመራል

ኮትዲቯር ከ40 ዓመታት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የምታሰናዳው የአፍሪካ ታላቁ የእግር ኳስ ውድድር 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ይጀመራል። በደቡባዊቷ የሀገሪቷ ክፍል በሚገኘው አቢጃን ከተማ ላይ የተገነባው አዲሱ አላሳኔ ኦታራስታ ስታዲየም ደግሞ በመርሃ ግብሩ መሠረት የመክፈቻውን ጨዋታ በአዘጋጇ ኮትዲቯር እና ጊኒ ቢሳው መካከል ያስተናግዳል። ከሰሞኑ በባህላዊ አልባሳት ደምቀው ወደ ሀገሪቷ ሲያቀኑ የቆዩት የተለያዩ ሀገራት ብሄራዊ ቡድኖች ተጠቃለው የገቡ ሲሆን፤ የዋንጫ ፍልሚያቸውንም ከዛሬ አንስቶ ያከናውናሉ። በአምስቱ ከተሞቿ የሚገኙት ስድስት ስታዲየሞቿም 24ቱ ቡድኖች የሚያደርጓቸውን 52 ጨዋታዎች እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን ዓይን ከዛሬ አንስቶ ወደ አፍሪካ የሚያማትር ሲሆን፤ ለወትሮ ሞቅ ደመቅ ብለው ይካሄዱ የነበሩት የአውሮፓ ሊጎችም ተቀዛቅዘው የአሠልጣኞቻቸውና አስተዳደሮቻቸው ትኩረት በአፍሪካውያን ወጣቶች ላይ ሊሆን ይገደዳል። የቀድሞ ቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲ ተጫዋች የነበሩትን ዲድየር ድሮግባ እና ቱሬን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ከዋክብትን ያፈለቀችው ምዕራባዊቷ ሀገር በዚህ የውድድር መድረክ ተሳትፎዋ ሁለት ዋንጫዎችን ስታነሳ፤ ሁለት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሳ ተሸንፋለች። ለአራት ጊዜያት ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ፈጽማለች። በአህጉረ አፍሪካ ጠንካራ ከሚባሉ ብሄራዊ ቡድኖች የሚመደበው ኮትዲቯር ባለፈው ወር የፊፋ ሀገራት ደረጃ መሠረት ከአፍሪካ 7ኛ ደረጃን ሲይዝ ከዓለም ደግሞ 49ኛ ላይ ነው የተቀመጠው።

በሀገሪቷ በነበረው ዝናባማ የአየር ሁኔታ ወራትን በማራዘም አሁን ላይ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይም ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ የስፖርቱ ቤተሰቦች ይታደማሉ በሚል ይጠበቃል። ለዚህ ውድድር ሲባል አራቱ ስታዲየሞች አዲስ የተገነቡ ሲሆን፣ ሁለቱ ደግሞ እድሳት የተደረገላቸው ናቸው። ለዚህ ዝግጅት ሀገሪቷ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ከስታዲየም ግንባታ ባለፈ ለመንገዶች፣ ሆስፒታሎች፣ ለአየር ማረፊያዎች እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታ እና እድሳት ማዋሏንም የኮትቯር እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እድሪስ ዲያሎ ይገልጻሉ። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ለዘለቀችው ሀገሪቷ የአፍሪካ ዋንጫውና እሱን ተከትሎ በተደረገው የመሠረተ ልማት ግንባታም አዲስ ምዕራፍን ይከፍታል በሚል ተስፋ የሰነቁም በርካቶች ናቸው።

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ሀገራትን ወደ ማሳተፍ የተሸጋገረው የአፍሪካ ዋንጫ፤ ቡድኖቹን በ6 ምድብ ከፍሎ ያፎካክራል። በዚህም በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ያልተጠበቀ አቋም በማሳየት የእግር ኳስ ቤተሰቡን ያስደመመችው ሞሮኮ፤ በተመሳሳይ የዚህ ውድድር ክስተት በመሆን ዋንጫውን ልታነሳ እንደምትችል የበርካቶች ግምት ሆኗል። የአፍሪካ ዋንጫን ሰባት ጊዜ የግሏ በማድረግ ቀዳሚ የሆነችው የፈርኦኖቹ ሀገር ግብጽም ለዋንጫ ቅድመ ግምት ያገኘች ሀገር ስትሆን፤ እአአ የ2021ዱን የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ናይጄሪያ፣ ጋና እና ኮትዲቯርም ለዋንጫው ተጠባቂ ቡድኖች ናቸው። ይህንን የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሽልማት ገንዘቡ መጠን ማደጉ ሲሆን፤ አሸናፊ በመሆን ዋንጫውን የሚያነሳው ቡድን 7 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ይሆናል። ይኸውም ከቀድሞው በ40 ከመቶ ብልጫ ያለው ነው።

በምድብ ድልድሉ መሠረት የመጀመሪያው ምድብ የውድድሩን አዘጋጅ ሀገር ኮትዲቯርን ጨምሮ ናይጄሪያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጊኒ ቢሳው ተካተውበታል። ምድብ ሁለት ግብጽ፣ ጋና፣ ኬፕቨርዴ እና ሞዛምቢክን ያቀፈ ሲሆን፤ በምድብ ሶስት ስር ደግሞ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ጊኒ እና ጋምቢያ ይገኛሉ። ቀጣዩ ምድብ አልጄሪያን ከቡርኪና ፋሶ፣ ሞሪታኒያ እና አንጎላ ጋር ያገናኛል። ቱኒዚያ በምትገኝበት ምድብ ደግሞ ማሊ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናሚኒያ ተደልድለዋል። በመጨረሻው ምድብ ደግሞ ሞሮኮ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ዛምቢያ እና ታንዛኒያ ይገኛሉ። በየምድቡ በሚኖራቸው ነጥብ መሠረት ሁለቱ ምርጥ ቡድኖች በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፉ ሲሆን፤ አራቱ ምርጥ ሶስተኛ ቡድኖችም 16ቱን የሚቀላቀሉ ይሆናል።

ከዛሬ አንስቶ እስከ የካቲት 3/2016ዓም የሚቆየው ውድድሩ ከ32ቱ ሀገራት ተውጣጥተው ጨዋታዎቹን የሚመሩ 68 ዳኞች ተዘጋጅተዋል። በውድድሩ ተሳታፊ የማትሆነው ኢትዮጵያ ደግሞ በኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በብቸኝነት ትወከላለች።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You