የ2016 የሠራተኞች የበጋ ወራት ስፖርታዊ ውድድሮች ከነገ በስቲያ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በሚከናወኑ የተለያዩ መርሀ-ግብሮች ይጀመራሉ። ለረጅም ወራት በሚካሄደው የበጋ ወራት ውድድሮች ወደ ሰላሳ የሚጠጉ የሠራተኛ ስፖርት ማህበራት እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።በየዓመቱ ጠንካራ ፉክክር የሚያስተናግደው የእግር ኳስ ውድድር በዘንድሮው የበጋ ወራት በርካታ ማህበራት ተፋላሚ ይሆናሉ።
በዚህ በእግር ኳስ ውድድር ሃያ አንድ ማህበራት ተሳታፊ ሲሆኑ ፉክክሩ በሁለት ዲቪዚዮን ተከፍሎ ይካሄዳል። በአንደኛ ዲቪዚዮን ዘጠኝ ማህበራት ተፎካካሪ ለመሆን ተዘጋጅተዋል፣ በሁለተኛው ዲቪዚዮንም አስራ ሁለት ማህበራት ናቸው ተፎካካሪ የሚሆኑት። የቤት ውስጥ የስፖርት ውድድሮችን ጨምሮ በአስር የስፖርት አይነቶች ፉክክር በሚደረግበት የበጋ ወራት ውድድር በሁለቱም ፆታ በአትሌቲክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቮሊቦል፣ ዳማ፣ ቼስ፣ ገበጣ፣ ገመድ ጉተታና ሌሎችም የስፖርት አይነቶች ከአንድ ሺ አምስት መቶ በላይ ሠራተኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ተናግረዋል።
ውድድሩ ከነገ በስቲያ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መክፈቻውን ቢያደርግም በቀጣይ ቀናት በተለይም የእግር ኳስ ውድድሮች በጎፋ ካምፕ ሜዳ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት፣ ስብስቴ ነጋሲ ትምህርት ቤት እንደሚካሄዱ አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል። የቤት ውስጥ ውድድሮችም ሜክሲኮ በሚገኘው የመብራት ኃይል ክበብ የሚካሄዱ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) በየዓመቱ ሶስት የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ያከናውናል። ለረጅም ጊዜ የሚካሄደውና በርካታ ሠራተኞችን የሚያሳትፈው የበጋ ወራት ውድድር አንዱና ዋነኛው ሲሆን፣ ዓለም አቀፉን የሠራተኛ ቀን (ሜይ ዴይ) አስመልክቶ የሚካሄደው ውድድር ሁለተኛው ነው። ሌላው በክረምት ወራት በተለይም በወንጂ ስቴድየም የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውና ሠራተኛውም በጉጉት የሚጠብቀው መድረክ ነው።
እነዚህ ውድድሮች ሠራተኞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋን ለማፍራት ፣ የሠራተኞችን አንድነት ለማጠናከር፣ የልማት ተቋሞቻቸውን ማስተዋወቅና የባለቤትነት ስሜታቸው እንዲጠናከር ዓላማ በማድረግ የሚከናወኑ ናቸው።
በኢትዮጵያ ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ አንጋፋ የስፖርት መድረኮች አንዱ የሆነው ይህ የሠራተኞች ውድድር በዚህ ዘመን ሠራተኛው በስፖርት የሚያደርገው ተሳትፎ ለሚሠራበት ድርጅት ውጤታማነት የሚኖረውን አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ አሠሪዎች እንደሚረዱት ይታመናል። በመሆኑም ስፖርቱ የሠራተኛውን አንድነትና ለጋራ ጉዳይ አብሮ የመቆም ባህሉን እንደሚያጠናክር ይነገራል። በሀገሪቱ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ እየተሳተፉ ጤናማ፣ ንቁና አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ውድድሮችን ማሰናዳት ውጤታማ ሠራተኛ ማፍራት እንደሚያስችል ይታመናል።
በአሠሪና ሠራተኛው መካከልም ጥሩ ግንኙነት እንዲዳብር በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ለኢንዱስትሪ ሰላም መስፈን የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ይታመናል። የሠራተኛ ማህበር ዓመታዊ ውድድሮችን ማዘጋጀት ሠራተኛውን እርስ በርስ ከማቀራረብ አንፃር የጎላ ሚና እንዳለውም ባለፉት በርካታ ዓመታት በተካሄዱ ውድድሮች ለመታዘብ ተችሏል።
በኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌዴሬሽን በሚሰናዱ ውድድሮች ላይ ተቋሞቻቸውን ወክለው በሚካፈሉ ተወዳዳሪዎች መካከል ከተቋም ጋር ያለውን መቀራረብ፣ ልምድ ማካፈል እንዲሁም ለተለያዩ ክለቦች ግብዓት የሚሆኑ ስፖርተኞች ማፍራት የቻለ ውድድርም ነው። በውድድሩ በሚካፈሉ ተቋማት መካከል በሚፈጠረው ፉክክር ምክንያትም ሠራተኛው የተሻለ ውጤት ይዞ ለመምጣት ሲሽቀዳደምና ለዓመታዊ ውድድሩ ዝግጅት ሲያደርግ መመልከት የተለመደ ነው።
የሠራተኛው የስፖርት መድረክ እንደ ሀገር በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ቢሆንም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እየተካሄደ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከነዚህ ፈተናዎች አንዱ የተሳታፊ ማህበራት ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉ ነው። የተሳታፊ ማህበራትን ቁጥር ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጥረት ማድረጉን እንደቀጠለ የሚናገሩት አቶ ዮሴፍ፣ “እኛ በርካታ ማህበራት እንዲሳተፉ ጥያቄ እናቀርባለን የሚመጡት ግን በሚፈለገው ልክ አይደለም፣ ይህ ከበጀትና አሰሪዎች ለስፖርት ካላቸው አመለካከት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፣ ለስፖርቱ ግንዛቤና ጥሩ አመለካከት ያላቸው አሰሪዎች ሠራተኞችን የማሳተፋቸውን ያህል የሌላቸውም አሉ።” በማለት ምክንያቱን ያስረዳሉ።
አዳዲስ ማህበራት ወደ ስፖርቱ የመምጣታቸውን ያህል በተለያዩ ምክንያቶች ነባር የነበሩ የሚቀሩበትም ሁኔታ አለ። የነዚህ አብዛኛው ችግር የበጀት ነው። ይሄ ሲስተካከል ግን ወደ ስፖርቱ ለመመለስ ፍላጎት አላቸው።
እንደ አቶ ዮሴፍ ገለፃ፣ የሠራተኛው ስፖርት በኮቪድ ምክንያት ለሶስት ዓመት ተቋርጦ ባለፈው ዓመት ለመመለስ ትልቅ ትግል ተደርጓል። ተሳክቶም ዘንድሮ ከኮቪድ በኋላ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የበጋ ወራት ውድድሮች ይካሄዳሉ። ያም ሆኖ የሠራተኛውን ስፖርት የሚያካሂድበት የራሱ የማዘውተሪያ ስፍራ አለመኖር ሁሌም የስፖርቱ ትልቅ ችግር ነው። ኢሰማኮ ሠራተኛው ስፖርታዊ ውድድሮቹን የሚያደርግበት የራሱ ማዘውተሪያ ስፍራ ባለቤት እንዲሆን ባለፉት ዓመታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 3/2016