የቱሪዝም ሚኒስቴር ከወራት በፊት የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ሀገር አቀፍ አውደ ርእይ ማካሄዱ ይታወሳል። በመድረኩም ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የባህል፣ የቱሪዝም ሀብቶቻቸውን ያስተዋወቁ በርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። ከእነዚህ ውስጥ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አንዱ ነው። ክልሉ በውስጡ የሚኖሩ ብሔረሰቦችን ቱባ ባህል፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ ቅርስ እና ልዩ ልዩ መስህቦችን በአውደ ርእይው ለውጪና ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ማስተዋወቅም ችሏል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚኖሩ ነባር አምስት ብሔረሰቦች መካከል የጉሙዝ ብሔረሰብ አንደኛው ነው። በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው አውደ ርእይ ላይ የብሔረሰቡ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና የቱሪዝም መስህብ ሀብቶችን የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት ተካሂዷል። የዝግጅት ክፍላችን ዘጋቢ በስፍራው በተገኘበት ወቅት ስለ ብሔረሰቡ ባህልና የኑሮ ዘይቤም መረጃዎችን አግኝቷል።
ከዚህ ውስጥ የጉሙዝ ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አንዱ ሲሆን፣ በዛሬው አገርኛ አምድም ስለዚሁ ጉዳይ በጥቂቱ ዳሰሳ እናደርጋለን። በመድረኩ የተገኙት የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አድሬ ‹‹የጉሙዝ ብሄረሰብ ባህላዊ እሴቶች›› በሚል የተደረገን ጥናት መሰረት በማድረግ መረጃውን ሰጥተውናል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ጉሙዝ የሚለው የአማርኛ መጠሪያ በብሄረሰቡ ቋንቋ “ጉንዛ” ከሚለው ቃል የተወሰደ ሲሆን፣ ፍችውም ጀግና ፣ ጎበዝ ፣ ወንድ እንደ ማለት ነው። ከናይሎቲክ የዘር ግንድ የሚመደበውን የጉሙዝ ብሄረሰብ ጥንተ መኖሪያ አስመልክቶ በርካታ መላምቶች ቢኖሩም ‹‹በምዕራቡ የሀ ገራችን ክፍል ይኖሩ ነበር›› የሚለው ግን ባብዛኛው የብሔረሰቡ አባላት ዘንድ ተቀባይነት አለው። ብሔረሰቡ በጋራ የመኖር፣ በጋራ የመስራት ፣ በጋራ የመብላትና በጋራ የመጠጣት አኩሪና አስደሳች ማኅበራዊ ህይወትን ታድሏል።
‹‹ብሔረሰቡ እጅጉን አስደማሚ ባህል ፣ በእጅጉ ማራኪ ታሪክና በጣሙንም መሳጭ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶች አሉት›› የሚሉት አቶ ሽመልስ፤ ከእነዚህ መካከል ዴሞክራሲያዊ የምርጫና አስተዳደር ሥርዓት፣ ‹‹ቆሚያ›› ተበሎ የሚጠራ ባህላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያን ይጠቅሳሉ። በተለይ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያው ከተመረጡ የዛፍ አይነቶች ውጤቶች እንደሚሰራ ይገልጻሉ። የሙዚቃ መሳሪያው ሁነቶችን ወይም ከስተቶችን ምክንያት በማድረግ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ይገልፃሉ።
በምሳሌነት ሲጠቅሱም የብሔረሰቡ ታላቅ ሰው ወይም የሃይማኖት መሪ ሲሞት፣ የሰብል አዝመራ ደርሶ ወደ ጎተራ ሲገባ፣ በዘመን መለወጫና በክብረ በዓላት ወቅት ይሄ የሙዚቃ መሳሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውል ይጠቅሳሉ። በተጨማሪ በርካታ ባህላዊ ሀብቶች እንዳሉ ተናግረው፣ ከእነዚያ ውስጥ ‹‹ኤፂፃ›› በመባል የሚጠራውን በሴቶች እግር ላይ የሚታሰርና ለዘፈን ማድመቂያነት የሚያገለግል ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያን ይጠቅሳሉ። ሴቶቹ እግራቸውን ከፍ እያደረጉ በለመዱት ስልት ደጋግመው መሬቱን ሲመቱ እርስ በእርሱ እየተጋጨ “ክሽ ክሽ ክሽ፣ ክሽ” የሚል ማራኪ ድምጽ እንደሚያሰማ ይናገራሉ::
አቶ ሽመልስ የጉሙዝ ብሔረሰብ በርካታ ባህላዊ እሴቶች እንዳሉትና እነዚህ ሀብቶች በባህልና ቱሪዝም ቢሮው አማካኝነት ተጠንተው እንደተቀመጡም ይገልፃሉ። ሀብቶቹን ለማልማት ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑንም ይጠቁማሉ። በጥናት ተለይተው ከተሰነዱ የብሔረሰቡ ባህላዊ እሴቶች መካከል ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አንዱ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ይህ ባህላዊ የጋብቻ ሥነሥርዓት ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ፋይዳ አብራርተው፣ በምን መልኩ ተፈፃሚ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
በጉሙዝ ብሔረሰብ የጥሎሽ፣ የለውጥ፣ የቤተሰብ እና ሌሎች በርካታ ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ቢኖሩም፣ ለዛሬው እኛ በስምምነት የሚደረግ የብሔረሰቡን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት መርጠናል።
ጉሙዝ- ባህላዊ ጋብቻ ሥነ ሥርዓት
አቶ ሽመልስ በብሔረሰቡ ባህላዊ እሴቶች ላይ የተደረገውን ጥናት ዋቢ እድርገው እንዳብራሩት፤ የጉሙዝ ብሔረሰብ ከሁለት መቶ በላይ ጎሳዎች አሉት፤ በጥናቱ ወቅት ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው የሀገር ሽማግሌች ይህንኑ መስክረዋል። በብሔረሰቡ ዘንድ ጋብቻ የሚፈጸመውም በተለያዩ ጎሳ ባላቸው ጉሙዞች መካከል ብቻ ነው። በአንድ ጎሳ ወይም በተመሳሳይ ጎሳ መካከል ጋብቻ መፈጸም በጥብቅ የተከለከለና አስነዋሪ ተግባር ተደርጎ ይወሰዳል።
አንድ ሰው የአባቱንና የእናቱን ጎሳ /ዘር/ ማግባት አይችልም። በተመሳሳይ ጎሳ ጉሙዞች መካከል ጋብቻ ቢፈጸም በመካከላቸው የሚወለዱ ልጆች መጥፎ እድል ይገጥማቸዋል ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ በጉሙዝ ብሔረሰብ ከአንድ ጎሳና ዝምድና ባላቸው የብሔረሰቡ አባላት መካከል ጋብቻ መፈጸም በጥብቅ የተከለከለና የተወገዘ ነው። በስህተት እንኳን ጋብቻ ተፈጽሞ ቢገኝ እንዲፈርስ ይደረጋል።
‹‹ማንኛውም ህብረተሰብ የሚጀምረው ከቤተሰብ ሲሆን፣ የቤተሰብ መሰረቱ በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ጥንዶች እርስ በርስ ተፋቅረውና ተስማምተው የሚመሰርቱት የጋራ ህይወት ነው›› የሚሉት አቶ ሽመልስ አድሬ፤ ጋብቻ በህብረተሰብ ደረጃም ይሁን በጋብቻ ፈጻሚዎቹ ዘንድ መሰረታዊ ትርጉም ያለው፣ሰዎች ከአንድ የዕድሜ ክልል ወደ ሌላ የዕድሜ ክልል መሸጋገራቸውን የሚያረጋግጡበት፣ በማህበረሰብ ውስጥ የሚኖራቸው ተግባርና ኃላፊነት፣ ከበሬታና ተቀባይነት ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚቀየርበት፣ በግላዊ ሕይወታቸው ውስጥ ከራሳቸው አልፈው የሌላን ሰው ህይወት የሚጋሩበትና የራሳቸውን የሚያጋሩበት ልዩ ምዕራፍ ነው ሲሉም ያብራራሉ።
በብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘንድ በወጥነት የሚከወን ማህበራዊ ሥርዓት መሆኑንም ይገልፃሉ። የጋብቻ አፈፃፀሙና ባህላዊ ክዋኔው ግን ከቦታ ቦታ፣ ከባህል ባህል፣ ከሀገር ሀገር እንደሚለያይ ያስረዳሉ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ያሉ አምስት ነባር ብሔረሰቦችም የራሳቸው የሆኑ ልዩ ልዩ የጋብቻ ሥርዓት አፈፃፀምሞች እንዳሏቸው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያደረገውን ጥናት በማጣቀስ የሚገልፁት የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህ መካከልም የጉሙዝ ብሔረሰብ አንዱ እንደሆነ ያስረዳሉ። በብሔረሰቡ ዘንድ በባህላዊ መንገድ የሚከወኑ ሥነ ሥርዓቶች መኖራቸውን የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፣ እነዚህም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎችን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
‹‹በጉሙዝ ብሔረሰብ ባህላዊ ጋብቻ ማህበራዊ ፋይዳ አለው›› የሚሉት አቶ ሽመልስ አድሬ፤ በብሔረስቡ ዘንድ ባህላዊ ጋብቻ አንድ ጎሳ ከሌላ ጐሳ ጋር በመጋባት በሚያደርገው የጋብቻ ሥርዓት ተጋቢዎች ዘር በመተካት ትውልድ ያስቀጥላሉ እንዲሁም ከሁለት የተለያዩ ጎሳዎች በመፈላለግ ሲጋቡ ዘር ከመተካት በተጨማሪ የተጠናከረ ማህበራዊ ዝምድና፣ትስስርና ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ይላሉ። እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ግጭቶች እንዳይካረሩ ለማድረግና ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን ደግሞ ለመከላከል እንደሚረዳ ያስረዳሉ።
‹‹ከማህበራዊ ፋይዳው በዘለለ በጉሙዝ ብሔረሰብ የባህላዊ ጋብቻ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው›› የሚሉት የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ፤ በባህላዊ ጋብቻ አማካኝነት አንድ ጎሳ ከሌላ ጎሳ ጋር ተባብሮ በመስራት በሚያደርገው መስተጋብር ሌላ የጉልበት ኃይል ገዝቶ እንዳይጠቀም በማስቻል ወጪንም መቀነስ ያስችላል። ቤተሰብን በመመስረት ሥራን በጋራ በመስራት ገቢን ለማግኘት ይጠቅማል። በጋብቻ በመተሳሰር ያላቸውን ገቢ በቁጠባ እንዲጠቀሙ ያግዛል ይላሉ።
የስምምነት ጋብቻ
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ በጉሙዝ ብሔረሰብ ዘንድ ልዩ ልዩ ባህላዊ ከንዋኔዎችን መሰረት አድርገው የሚካሄዱ የጋብቻ አይነቶች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። ከእነዚያ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ‹‹የስምምነት ጋብቻ›› መሆኑን ይናገራሉ። የዚህን የጋብቻ ሥነሥርዓት ይዘትም ‹‹የጉሙዝ ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች›› በሚል በተሰራ ጥናት ላይ ተመስርተው ሥነሥርዓቱና አፈፃፀሙን እንደሚከተለው በምሳሌ አስደግፈው ይገልፃሉ።
‹‹የስምምነት›› ጋብቻ ሁለቱ ተጋቢዎች ከቤተሰብ ፍቃድ ውጪ ወንዱ ሴቷን በፍቅር አማሎ ይዞ የሚሄድበት የጋብቻ ዓይነት ነው። የጋብቻው ሂደትም መጀመሪያ ወንዱ ልጃገረዷን በተስካር፣ በገበያ እና በልዩ ልዩ ቦታዎች አይቶ ለጋብቻ ይፈልጋታል (ይከጅላታል)። ልጅቷን ባያት ጊዜም ይዘፍንና የፍቅር ጥያቄ ያቀርብላታል። ከዛም ከወደደችው የእጇን አንባር ትሰጠዋለች። እሱም ልጅቷ ወደ ምትኖርበት አካባቢ በመሄድ ውሃ ልትቀዳ ወንዝ ስትወርድ እየጠበቀ ‹‹ይዤሽ ልሂድ›› እያለ ያባብላታል።
እሷም ‹‹በአንድ ጊዜ ጠፍቼ አልሄድም፤ በሌላ ጊዜ ተመለስ›› ትለዋለች። በሌላ ጊዜ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ጠብቆ ይዟት እንዲሄድ ይለምናታል። አሁንም ‹‹በሌላ ጊዜ ተመለሱ›› ትላለች። በሶስተኛ ጊዜ ሲመለሱ ይዘዋት ይሄዳሉ። የልጁ ቤተሰቦችም በመገረም ‹‹እንዴት አመጣሀት›› ይላሉ። እሱም ተዋደን ነው፤ የእጅ አምባርም ሰጥታኛለች ብሎ ያሳያቸዋል። ቤተሰቦቹም የማን ልጅ እንደሆነች ይጠይቃሉ። የጥሩ ቤተሰብ ልጅ ከሆነች ደስ ብሏቸው ወዲያውኑ ‹‹ልጅቱ ያለችው ከእኛ ጋር ነው። ሌላ ቦታ እንዳትፈልጉ›› ብለው የተወሰነ ብር ጨምረው ሽማግሌ ይልካሉ።
የልጅቱ ቤተሰቦችም የልጁ ቤተሰቦች በስነ ምግባራቸው መልካም መሆናቸውን ሲሰሙ እንዲሁም ልጅቱ በፍላጐቷ መሄዷን ሲያረጋግጡ ምንም ቅሬታ ሳይሰማቸው የሽማግሌውን መልዕክት ከመስተንግዶ ጋር ይቀበሉታል።
ይህ አይነቱ ጋብቻ ምትክ ይጠይቅበትና የለውጥ ጋብቻ ይፈጸምበት ነበር፡ በአሁኑ ወቅት የለውጥ ጋብቻው እንዲቀር ተደርጓል። በብሔረሰቡ ዘንድ የለውጥ ጋብቻ መፈፀም የቀረ ቢሆንም፣ መልኩን ቀይሮ እንደሚስተዋል የሚናገሩ የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉም አቶ ሽመልስ አድሬ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት የጉሙዝ ብሔረሰብ በአብዛኛው እየፈፀመ ያለው የጋብቻ ዓይነት የስምምነት ጋብቻ እንደሆነ መረጃ ሰጪዎቹ ይናገራሉ። ሂደቱም መጀመሪያ አግቢው በገበያ ወይም በተስካር ቦታ አይቶ የወደዳትን ልጃገረድ በፍቅር አማሎ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ይዞ ይሄዳል። ከዛም ወደ ልጅቷ ቤተሰብ ሽማግሌ ይልካል። ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ለልጅቷ ቤተሰቦች እንደ ጥሎሽ አንድ በሬ፣ አስር ሺህ ብር የምሶሶ 3 ሺ ብር፣ አንድ ሰሀን ቆጭቆጫ፣ የተለያዩ መጠጦችንና የመሳሰሉትን ይዘው በመሄድ ከቤተሰብ ጋር ስምምነት ይፈጥራሉ። ከዚያ በኋላ የተወሰደውን መጠጥም ሆነ የሚበላ ነገር በመብላትና በመጠጣት ይደሰታሉ፤ ይጨፍራሉ። ከልጅቷም ጋር አብረው በሰላም ይኖራሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 3/2016