የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በግብርና፣ በማእድን፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪና በመሳሰሉት ዘርፎች ለሚካሄዱ የኢንቨስትመንት ስራዎች ሊውሉ የሚችሉ እምቅ ሀብቶች ያሉት ክልል ነው፡፡ ክልሉ አስደናቂ የሆነ መልከዓምድራዊ አቀማመጥ፣ ልምላሜና የተፈጥሮ ሀብት ያለው በመሆኑም የባለሀብቶችን ትኩረት የሚስብ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ለኢንቨስትመንት ሊውሉ የሚችሉ የክልሉን ሀብቶች ለመለየት የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱትም፤ ክልሉ ለዓመታዊ ሰብሎች፣ ለቡናና ቅመማ ቅመም እና ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚውል ሰፊና ምቹ መሬት አለው፡፡ ክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ በማቅረብም ይታወቃል፡፡
በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎችም እንዲሁ ክልሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻና አማራጭ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የድንጋይ ከሰል በክልሉ በዳውሮ እና በኮንታ አካባቢዎች በስፋት ይገኛል። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በባለህብቶች እየተገነቡ ከሚገኙ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎች አንዱ እየተገነባ የሚገኘውም በእዚሁ ክልል ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በእዚህም ክልሉ የሀገሪቱን የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ለማሟላት እየሰሩ ከሚገኙ ክልሎች አንዴ መሆን ችሏል፡፡
ክልሉ በወርቅ ማእድን ሀብቱና ምርቱም ይታወቃል፡ ፡ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ማዕድን ምርት ለማዕከላዊ የገበያ ከሚያቀርቡ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ ኦፓልና ሌሎች ማዕድናትም በክልሉ ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል። በክልሉ ገና በጥናት ያልተለዩ ብዙ ሀብቶች ስለመኖራቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ በርካታ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሰራዎች ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ። የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡ አሁንም በርካታ ባለሀብቶች በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ነው ከክልሉ የተገኘ መረጃ ያመለከተው፡፡
የክልሉ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያከናወናቸውና እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባሮችም እንዲሁ ክልሉን ሌላው የኢንቨስትመንት መደረሻ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ሊጠቀስ ይችላል፡፡ እንደ ክልል ከተዋቀረ አጭር እድሜ ያለው ቢሆንም፣ በክልሉ ኢንቨስትመንቱ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ ሰፊ ጥናትና ውይይት ተደርጓል፡፡
ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ለማበረታታት የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና የካቢኔ አባላትን ጭምር ያሳተፈ የንቅናቄና የፕሮሞሽን ስራ በስፋት ተሰርቷል፡፡ ክልሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የተሰሩት የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስራዎች በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2015 የበጀት ዓመት አበረታች የኢንቨስትመንት አፈፃፀም ማስመዝገቡንና በ2016 የበጀት ዓመትም ይህን አፈፃፀሙን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ በ2015 የበጀት ዓመት ያስመዘገባቸውን ስኬቶች በ2016 የበጀት ዓመትም አጠናክሮ ለማስቀጠል እቅድ አዘጋጅቶ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ ያስረዳሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ በበጀት ዓመቱ በግብርና 84፣ በአገልግሎት 64 እንዲሁም በኢንዱስትሪ 58፣ በአጠቃላይ ለ206 ፕሮጀክቶች ፈቃድ በመስጠት ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዷል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ11 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንደሚያስመዘግቡና ከ109ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች (ሦስት ሺ 181 ቋሚ እና 105ሺ 951) የስራ እድሎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል፡ ፡ በክልሉ በርካታ ባለሃብቶች የተሰማሩት በግብርና ዘርፍ ነው፡፡ በርካታ ባለሀብቶች ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲሰማሩ ማድረግ ከ2016 የበጀት ዓመት እቅዶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ክልሉ ከግብርናው ዘርፍ ባሻገር ባለሀብቶች በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች በስፋት እንዲሰማሩ የሚያስችል የመሬት ዝግጅት ተግባር አከናውኗል፡፡
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ከአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 38 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል። በግብርና ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ለሚያስመዘግቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፣ አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ 427 ሚሊዮን ብር ለሚያስመዘግቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፣ 340 ሚሊዮን ብር ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡
የኢንቨስትመንት አቅም (Potential) በመለየት ረገድ፣ በስድስት ወራት ውስጥ 4ሺ744 ሄክታር ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ለማጥናትና ለመለየት ታቅዶ፣ 17ሺ 137 ሄክታር መሬት ተለይቷል፡፡ ከዚህ መሬት ውስጥ 6ሺ323 ሄክታር መሬት ለባለሃብቶች ለማስተላለፍ ታቅዶ፣ 8ሺ296 ሄክታር መሬት ማስተላለፍ ተችሏል፤በመሆኑም በአቅም ልየታና መሬት ማስተላለፍ ዘርፎች ከእቅዱ በእጅጉ የበለጠ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ለኢንቨስትመንት የሚሆን አቅም ያለውን መሬት በማጥናት ረገድ የበጀት ዓመቱ ጠቅላላ እቅድ 12ሺ650 ሄክታር መሬት ነው ለማጥናት ታቅዶ የነበረው፡፡ መሬት የተላለፈላቸው ባለሀብቶች ለአንድ ሺ 591 ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን፣ ለ621 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡
አቶ ከበደ እንደሚያስረዱት፣ ቀደም ሲል መሬት ወስደው ያላለሙ ባለሀብቶችን በተመለከተ፣ የመሬት ኦዲቲንግ ተግባር በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ነው፡ በስድስት ወራት 28 ፕሮጀክቶችን ኦዲት ለማድረግ ታቅዶ፣ 16 ፕሮጀክቶች ኦዲት ተደርገዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ 14 ፕሮጀከቶች መሬት እንዲቀነስባቸውና ስምንት ፕሮጀክቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ መሬት እንዲነጠቁ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ለ387 ፕሮጀክቶች ድጋፍና ክትትል ማድረግ ተችሏል፡፡
‹‹እንዲህ ዓይነት እርምጃዎች ካልተወሰዱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በታለመላቸው የጊዜ ገደብ ላይጠናቀቁ ይችላሉ፡፡ ይህ የኦዲቲንግ ሥራ መሬት ተረክበው የማያለሙ ባለሃብቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ወይም መሬቱን ለሌሎች አልሚዎች ለማስተላለፍ ያግዛል፡፡ የኢንቨስትመንት አዋጁ (1180/2010) ለባለሃብቶች የተሰጡ መሬቶች ሊነጠቁ የሚችሉባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በግልፅ አስቀምጧል፡ ፡ የባለሃብቶች የስራ እንቅስቃሴዎች በእነዚህ መስፈርቶች መሰረት ተገምግመው ቅድመ ሁኔታዎቹ ካልተሟሉ መሬት እንዲነጠቁ ይደረጋል›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ተቋማት ለባለሀብቶች መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማስፈን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ፕሮፖዛሎች በጥልቀት እንዲታዩ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፈቃድና መሬት በፍጥነት እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ ነባሮቹን የማጠናከር እና የተጀመሩትን የመጨረስ እንጂ አዳዲስ፣ በተለይ መንገዶችን፣ ለመገንባት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንደሌሉ አቶ ከበደ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፤ የበጀት እጥረት በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል ሊፈጥር የሚችለው ዋናው ችግር ነው። የክልሉ ዞኖች የሚመደብላቸው በጀት ቀደም ሲል በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር በነበሩበት ጊዜ የነበራቸው በጀት ነው፡ አገሪቱ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታም ተጨማሪ በጀት ለማግኘት የሚያስችል አይደለም፡፡
አቶ ከበደ እንደሚናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ባለሃብቶችን የማነቃቃት ስራዎች ተከናውነዋል፡ በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩና በስድስቱም ዞኖች የሚገኙ ባለሀብቶች በፌዴራል ደረጃ በተቋቋመው የግብርና አልሚ ባለሀብቶች ማኅበር ውስጥ አባል ሆነው በንቃት እንዲሳተፉ ተደርጓል፡ ፡ ከዚህ በተጨማሪም በሁሉም ዞኖች ላይ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችን በማስተባበር የሰብል አምራቾች ማኅበራት እየተቋቋሙ ይገኛሉ፡ ለአብነት ያህል በከፋ፣ ቤንች ሸኮ እና ሸካ ዞኖች ማኅበራቱ ተቋቁመዋል፤ በቀሪዎቹ ዞኖችም ማኅበራቱን ለማቋቋም እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
ባለፈው የበጀት ዓመት በተዘጋጀው የመሬት መጠቀሚያ ደንብ መሰረት የመሬት ክፍያ ያልከፈሉ ባለሃብቶች ክፍያ መክፈል መጀመራቸውም ትልቅ ስኬት እንደሆነ አቶ ከበደ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በመሬት ክፍያ ረገድ በተለይ ነባሮቹ ባለሃብቶች ክፍያ መክፈል እንዳለባቸው ታምኖበት፣ ለዞን ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ክፍያውን እንዲያስፈፅሙ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከተከናወኑ በጎ አፈፃፀሞች መካከል አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል›› ይላሉ፡፡
የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው፡፡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ ሲያስገባ ባለሀብቶች በተለያዩ መንገዶች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው፡፡
ማኅበረሰቡ ከኢንቨስትመንት ስራዎች በስራ እድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን ይጠበቃል፡ በዚህ ረገድ በክልሉ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለክልሉ ህብረተሰብ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንዳሏቸው ይገልፃሉ፡፡ ‹‹በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ‹አንድ ባለሃብት ወደ አንድ አካባቢ ሲመጣ ለማኅበረሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ምንድን ነው?› የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚሻ ዐቢይ ጉዳይ ነው›› የሚሉት አቶ ከበደ፣ ይኸው ጉዳይ የክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግባር አካል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
እሳቸው እንደሚያብራሩት፣ በክልሉ የሚገኙ ባለሀብቶች በሚያከናውኗቸው የኢንቨስትመንት ተግባራት አማካኝነት የስራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ፣ ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ስራዎቻቸውን በሚሰሩባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራትን ስለሚያከናውኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ በዚህ ተግባር በኩል ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህ የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ማኅበረሰቡ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል፡፡
ባለሀብቶችን በማስተባበር ባለፉት ስድስት ወራት 39 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመስራት ታቅዶ፣ 54 ኪሎ ሜትር መንገድ መስራት ተችሏል፡፡ ለሁለት አረጋውያን ቤተሰቦችም የመኖሪያ ቤቶች እንዲገነቡ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም የክልሉ የኢንቨስትመንት ቢሮ ባለሀብቶችን በማስተባበር ለሦስት ተማሪዎች ቋሚ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡
በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ፣ ባለሀብቶች ለአርሶ አደሩ 300 ኪሎ ግራም የቡና ምርጥ ዘር አቅርበዋል፤አጠቃላይ የምርት ስልጠናዎችን ሰጥተዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ጊዜም 425 አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም