ኮሎምቢያ አስተናጋጅ የሆነችበት 11ኛው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ከወራት በኋላ ይጀመራል፡፡ ለዚህ ውድድር አፍሪካን የሚወክሉ አራቱ ቡድኖች ሊለዩ ከጫፍ የደረሱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም የዓለም ዋንጫ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ 180 ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡ ቡድኑ ላለበት ለዚህ ወሳኝ ጨዋታም ወደ ካዛብላንካ ያቀና ሲሆን፤ ከነገ በስቲያ ከሞሮኮ አቻው ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡
አራት ዙሮች ያሉትን የማጣሪያ ጨዋታ አልፎ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሰባስቦ ለዚህ ጨዋታ የሚሆነውን ዝግጅት ከታህሳስ 7/2016 ዓ∙ም አንስቶ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በ35 ሜዳ እና በእድሳት ላይ በሚገኘው አንጋፋው አዲስ አበባ ስታዲየም ሲያደርግ የቆየውን ዝግጅት አጠናቆም ከትናንት በስቲያ ምሽት ወደ ስፍራው አቅንቷል። ለቡድኑም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ፤ እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበትም ሽኝት ተደርጎለታል፡፡ ከሽኝቱ አስቀድሞም የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ዝግጅቱን በሚመለከት መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ ቡድናቸው በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ እንድትሆን የሚያስችላትን ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ቡድኑ ከሳምንታት በፊት ጥሪ የተደረገለት ከፕሪምየር ሊጉ ለተውጣጡ 31 ተጫዋቾች መሆኑን ያወሱት አሠልጣኙ፤ በሂደት ወደ 23 ዝቅ ቢደረግም የአንዲት ተጫዋች ፓስፖርት በመበላሸቱ 22 ተጫዋቾችን ይዘው ለመጉዋዝ መገደዳቸውን ጠቁሟል፡፡ ሞሮኮን ለመግጠም ዝግጅት ሲደረግ ቢቆይም በሚፈለገው ልክ ግን ሊሆን አልቻለም፤ ይኸውም የዝግጅቱ አንድ አካል እንዲሆን የጠየቁት የወዳጅነት ጨዋታ ባለመሳካቱ ነው፡፡ አሠልጣኙ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ዕድሎች እንዲመቻችላቸው ፌዴሬሽኑን ቢጠይቁም ምላሽ አለመሰጠቱ ጫና ይኖረዋል፡፡ በአንጻሩ ተጋጣሚያቸው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ከአልጄሪያ እና ቦትስዋና ቡድኖች ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን፤ ከዚህም የጥቂት ደቂቃ ተንቀሳቃሽ ምስል በመመልከት አጨዋወታቸውን ለመገንዘብ ተሞክሯል፡፡
በዚህም፣ በርካታ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ያሏት ሞሮኮ ፈጣን አጨዋወት ያለው ቡድን ያላት ሲሆን፤ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ጥረት እንደሚደረግም አሠልጣኙ አብራርተዋል። ከዚህ ባለፈ በሞሮኮ ያለው የአየር ሁኔታ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ ከጨዋታው 7 ቀናትን አስቀድሞ በመጓዝ የአየር ሁኔታውን ለመላመድ እንዲቻል ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም ይሁንታን አላገኘም፡፡ ሆኖም ባሉት ቀናት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ፣ እንዲሁም ከ17 ዓመት በታች እና ከ20 ዓመት በታች ከነበሩት ብሄራዊ ቡድኖች የተሰባጠረው ቡድናቸው ካለፉት ጨዋታዎች ልምድ እያገኘ መምጣቱን ተከትሎ ዓላማውን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት የሚደረግም ይሆናል። በተጨማሪም የቀድሞ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የነበሩ የአሠልጣኞች ቡድን አባላትን ጨምሮ በባለሙያዎች የሥነልቦና ጫና ውስጥ እንዳይገቡ የተሰራው የማነቃቂያ ሥራ ተጫዋቾቻቸውን እንደሚያግዝም አሠልጣኙ አንስተዋል፡፡
በየሁለት ዓመቱ የሚደረገው ይህ ውድድር ቀድሞ 16 ቡድኖችን የሚያሳትፍ ቢሆንም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን ቁጥሩን ወደ 24 በማሳደግ ይካሄዳል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአራት ቡድኖች የሚወከል ሲሆን፤ በማጣሪያውም 35 ቡድኖችን ሲያጫውት ቆይቷል፡፡ እስከ አራተኛው ዙር የደረሱ ስምንት ቡድኖች (እነዚህም ኢትዮጵያ እና ሞሮኮን ጨምሮ፤ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ግብጽ እና ካሜሮን ናቸው) ከነገ ጀምሮ ጨዋታቸውን በማከናወን በደርሶ መልስ አሸናፊ የሚሆኑት ወደ ኮሎምቢያ የሚጓዙ ይሆናል። ኢኳቶሪያል ጊኒን እና ማሊን በመርታት ለመጨረሻው ዙር የደረሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም በመጪው ቅዳሜ ከሜዳው ውጪ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ እጣ ፋንታውን የሚወስንበትን የመጨረሻ 90 ደቂቃ ከቀናት በኋላ በሜዳው (አበበ ቢቂላ ስታዲየም) ያካሂዳል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም