አትሌቲክስ በውድድር ዓመቱ

ከአቴንስ ቀጥላ ሁለተኛውን ኦሊምፒክ ያስተናገደችውና የዘመናዊው ኦሊምፒክ መስራች ፔሪ ደ ኩበርቲን ሃገር የሆነችው ፈረንሳይ ግዙፉን የስፖርታዊ ውድድሮች መድረክ በታሪኳ ለሦስተኛ ጊዜ ታዘጋጃለች:: ይህ ኦሊምፒክ ከዛሬ አንስቶ 198 ቀናት የሚቀሩት ሲሆን፤ ውቢቷ ፓሪስም ከ100 ዓመታት በኋላ ዳግም ለምታስተናግደው ኦሊምፒክ ዝግጅቷን በማገባደድ ላይ ትገኛለች:: የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑ ሀገራትም በስፖርት ትልቁን ክብር ለሚያቀዳቸው ለዚህ ውድድር ወራት እየቀሩት አስቀድመው ስፖርተኞቻቸውን በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ::

ከቀናት በፊት በተያዘው አዲሱ የውድድር ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የአትሌቲክስ ስፖርታዊ ውድድሮች የሚከናወኑ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል እጅግ ተጠባቂው ኦሊምፒክ ነው:: የስፖርተኞች የብቃት ጥግ መለኪያና የውድድሮች ሁሉ ቁልፍ በሆነው ኦሊምፒክ፤ በአስደናቂ አትሌቶች፣ በአስደማሚ ብቃት፣ ድራማዊ ክስተቶችና ባልተጠበቁ ሁኔታዎች የታጀበ በመሆኑ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ እጅግ አጓጊ ነው:: በዚህ ዓመትም ኢትዮጵያን ጨምሮ 200 ከሚሆኑ ሀገራት 2ሺህ አትሌቶች እርስ በእርሳቸው የሚፎካከሩ ይሆናል:: ዛሬ ላይ የታወቀችበትን የአትሌቲክስ ስፖርት በኦሊምፒክ አሐዱ ያለችው ኢትዮጵያም ዝግጅቷን አስቀድማ የጀመረች ሲሆን፤ የዝግጅት ምዕራፎቿንም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ በሚል ከፋፍላ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች:: ይህንን የሚመራው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ካለፉት ኦሊምፒኮች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁለገብ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስታውቋል::

የተጠናቀቀው የአትሌቲክስ ውድድር ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የተከናወኑበት ነበር:: በዓመቱም በስፖርቱ “ስኬታማ” በሚል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ሃገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ውጤታማ ሊባል የሚችል ጊዜን አሳልፋለች:: በተያዘው የውድድር ዓመትም የፓሪሱን ኦሊምፒክ ጨምሮ በሚከናወኑት አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ በውጤታማነት ስሟ የሚጠራበት እንደሚሆን ይጠበቃል:: ይህም ስኬት አስደናቂ አቋም ላይ በሚገኙ ዝነኛ እንዲሁም ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ባስመዘገቡ ተተኪ አትሌቶች ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ተጨማሪ የዓለም ክብረወሰኖችና የዓለም አትሌቲክስ ምርጥ አትሌቶች ሽልማትም በዓመቱ ይጠበቃል::

በዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ መርሐ ግብር መሠረት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ውድድር ከወር በኋላ ይካሄዳል:: ይህም ውድድር የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ሲሆን የስኮትላንዷ ግላስኮ ደግሞ አዘጋጅ ከተማ ናት:: በመጪው የካቲት ወር ከ22-24/2016 ዓ∙ም በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ በመም ውድድሮች አስደማሚ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ አትሌቶች ዓመቱን በድል ለመጀመር የሚፋለሙበትም ይሆናል:: ከሁለት ዓመት በፊት ቤልግሬድ ላይ 9 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ሃገራት አንደኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር እጅግ ተጠባቂ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ናት::

ከሳምንታት በኋላ ደግሞ የዓለም አቀፉ ሀገር አቋራጭ ውድድር ይደረጋል:: ከሁለት ዓመት በኋላ በድጋሚ ይህንን ውድድር የምታስተናግደው የሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ ከመላው ዓለም የሚሰባሰቡትን ምርጥ አትሌቶች ለመቀበል ዝግጅቷን አጠናቃለች:: በውድድሩ ተፎካካሪ አትሌቶችን አሰልፈው በርካታ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ከሚታወቁት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንዱ ሲሆን፤ ለዚህ ውድድር የሚሆኑ አትሌቶች የሚመረጡበት ውድድርም ከቀናት በኋላ ይከናወናል:: የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 41ኛውን የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር ጥር 5/2016 ዓ∙ም ካከናወነ በኋላም ቡድኑን መርጦ ውጤታማ ወደሚያደርገው ዝግጅት ይገባል::

እአአ በ2017 ዓለም አቀፉ የሪሌ ሻምፒዮና ሲጀመር አስተናጋጅ የነበረችው በሃማስ የዘንድሮውን ውድድር በድጋሚ ታሰናዳለች:: ይህ ውድድር በሚያዚያ ወር መጨረሻ በተለያዩ ርቀቶች በሁለቱም ፆታ፣ እንዲሁም በድብልቅ የሚከናወን የዱላ ቅብብል ሩጫ ነው:: በነሐሴ ወር መጨረሻ ደግሞ ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያዎችን የምታስቆጥርበትና ምርጥ ወጣት አትሌቶች የሚታዩበት የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ይደረጋል:: ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት የሚል ዓላማ የሰነቀው ይህ ውድድር በደቡብ አሜሪካዋ ሊማ ሲደረግ ቀጣዮቹ የአትሌቲክስ ስፖርት ከዋክብት የሚታዩበት መድረክም ነው::

ዓመቱን ሙሉ የሚከናወኑት የቱር ውድድሮችም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የሚጠበቁ የአትሌቲክስ ውድድሮች ናቸው:: ዳይመንድ ሊግን ጨምሮ፣ የዓለም የቤት ውስጥ የቱር ውድድር፣ የሀገር አቋራጭ ቱር፣ የእርምጃ ቱር፣… የተባሉ የአንድ ቀንን ጨምሮ በርካታ የመም እና የሜዳ ተግባር ውድድሮች በየሳምንቱ ይደረጋሉ:: በእነዚህ ውድድሮች ላይም ኢትዮጵያውያኑ ከዋክብት ከውጤት ባለፈ ክብረወሰኖችን በመሰባበር ፈጣን ሰዓቶችን እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር 1/2016

Recommended For You