አቶ ተፈራ ሻውል ኪዳነቃል – ባለደማቅ አሻራ ዲፕሎማት

ዲፕሎማሲ በሀገራትና መንግሥታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የሚካሄድ ዘርፈ ብዙ የውጭ ግንኙነቶች የሚከወኑበት ሁነኛ ጥበብ ነው። የዲፕሎማሲ ዋና ተግባር በአገራት መካከል ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ማስተዳደር እና ሰላማዊ ግንኙነትን ማረጋገጥ ሲሆን የንግድ ስምምነት ድርድሮችን፣ በጋራ ችግሮች ዙሪያ ውይይትን፣ አዳዲስ ፖሊሲዎች መተግበርን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ያካትታል:: ኢትዮጵያም የሺ ዓመታት ዲፕሎማሲ ልምድ እንዳላት ሀገር ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ስትጠቀምበት ቆይታለች::

ዲፕሎማሲ ወይንም የኹለትዮሽ ግንኙነት ማለት ሀገራት በሰላማዊ መንገድ እርስ በእርሳቸው ሀገራዊ ጉዳዮቻቸውን የሚፈጽሙበት እና ሰጥተው በመቀበል መርህ የየሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩበት መንገድ እንደሆነ እሙን ነው።

በዚህ ፅሁፍ የሀገር ባለውለታ ብለን ታሪካቸውን የምናስነብባችሁ ሰው በአንድ በኩል በጋዜጠኝነት ያገለገሉ ሲሆን ረጅም ዘመናቸውን ደግሞ በዲፕሎማሲ የሰሩ ሰው ናቸው:: ብስራተ ወንጌል ከዛሬ 59 አመት በፊት ሲጀመር ይህ ብስራተ ወንጌል ነው የሚለውን መክፈቻ ያሰሙ ናቸው:: በጀርመን ፤ በካርቱም ፤ እንዲሁም በቼክ ሪፖብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል:: በተባበሩት መንግሥታት ለረጅም አመታት የሰሩ ናቸው:: የቀድሞ ዲፕሎማት አምባሳደር ተፈራ ሻውል፤ ራሳቸው በአምባሳደርነት ከማገልገላቸው በላይ ልጃቸውም ወደዚህ ክቡር ሙያ እንዲሳብ በር የከፈቱ ሰው ናቸው።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ታሪክ ከማሟሻዎቹ አንዱ የሆነው የብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ተመርቆ ስራውን ሲጀምር የተሰማው የመጀመሪያ ድምፅ የአምባሳደር ተፈራ ሻውል ነው። “ይህ የብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ነው” ከግማሽ ከፍለ ዘመን በላይ ወደ ኋላ መለስ ብለው ወቅቱን ሲያስታውሱ ‘ንጉሰ ነገስቱ ብስራተ ወንጌልን ሲመርቁ “ይህ የብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ነው” ብዬ መጀመሪያ ቁልፉን ሲጫኑ ያበሰርኩት እኔ ነኝ’ ይላሉ። በዚህ ቀደምትነታቸውም ኩራት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።

አምባሳደር ዲፕሎማትና የሚድያ ባለሙያ አቶ ተፈራ ሻውል ኪዳነቃል በጥቅምት 6 1936 ዓ.ም በሸዋ ዞን በሆለታ ነበር የተወለዱት:: አለቃ ሻውል ኪዳነቃል ወላጅ አባታቸው ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ ሳሳሁልሽ ኪዳኔ ይባላሉ:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሆለታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በደብረብርሀን ተከታትለዋል:: በመጨረሻም ወደ ደብረዘይት ተዘዋውረው ደብረዘይት ወንጌላዊት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ:: በሆለታ የንጉሱ የጦር ትምህርት ቤትን የተጎራበተ ልጅነታቸው ብዙ አሳይቷቸዋል… ‘ጥይት ከመተኮስ በስተቀር ወታደሮቹ የሚያደርጉትን በሙሉ እናደርግ ነበር’ ይላሉ ልጅነታቸውን እያሰቡ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሆለታ አጠናቀው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረ ብርሃን እንዳጋመሱ… እርሳቸው እንደሚሉት “በወቅቱ በነበረ ሽግሽግ…” በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት እየተከፈለላቸው ደብረ ዘይት በሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ኮሌጅ በአዳሪነት እየተማሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በደብረ ዘይት የነበራቸውን ቆይታ እንደሚወዱት ይናገራሉ። ለዚህም በሃገር ውስጥና በውጭ ሀገር መምህራን መማራቸው፣ ከመደበኛው የትምህርት ስርዓቱ ጎን ለጎን ተጨማሪ ክህሎቶችን መቅሰማቸው፣ በእረፍት ጊዜአቸው በይርጋዓለም ሆስፒታል የሚሰጡት የበጎ ፈቃድ ግልጋሎትና ሌሎችንም ቀበምክንያትነት ያነሳሉ።

የዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪ በነበሩበት በአንድኛው ቀን፤ አዲስ ለሚቋቋም አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ለድምፅ ፈተና የሚሄዱ ጓደኞቻቸውን ያገኟቸውና ‘አብሬአችሁ ሄጄ ተፈትናችሁ እስክትወጡ ውጭ እጠብቃችኋለሁ’ ብለው በአንድነት ወደ መፈተኛ ቦታው ያቀናሉ። ጓደኞቻቸውን የፈተነው ፈታኝ አይቷቸው ኖሮ አስገብቶ ፈተናቸውና ከተዘጋጁት ይልቅ ያልተዘጋጁት ተፈራ ሻውልን በአንደኝነት አሳልፎ በትርፍ ሰዓታቸው እንዲሰሩ ቀጠራቸው። አንዲት አንቀፅ ካነበቡ በኋላ የመጀመሪያ ክፍያቸው 25 ብር እንደነበረ ያስታውሳሉ።

ዜና አንባቢም ዜና ተርጓሚም ሆነው በብስራተ ወንጌል ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ለከፍተኛ ትምርህት ወደ ጀርመን ሲያቀኑ፤ የሬዲዮ ጣቢያን በጋዜጠኝነት ስልጣን ባርኮ የመክፈት ታሪካቸው በዚያም ተደገመ። የጀርመን ድምፅ ዶቼበሌ የአማርኛው ክፍል ሲመሰረት አሻራቸው አለበት።

የጀርመን ቆይታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ የብስራተ ወንጌል ስራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ‘ለሃይማኖታዊ ስብከት ቢቋቋምም ሚዛናዊ ሚዲያ ነበር’ ሲሉ በሚገልጡት እናት ቤታቸው በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በድጋሜ ወደ ጀርመን የሚሄዱበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ጀርመን ፍራንክፈርት ላይ በወንበዴዎች ቦንብ የተወረወረበት የኢትዮጵያ አውሮፕላን መጠነኛ እክል ገጥሞት ወደ ሃገሩ ከተመለሰ በኋላ የጀርመን ፕሬስ ስለኢትዮጵያ የሚፅፈው ጥሩ ያልሆነ ጽሑፍ ያሳሰባቸው የወቅቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ከተማ ይፍሩ፤ ችግሩን ለመፍታት በስልክ አስጠርተው ‘እዚያው ስለተማርክ የግርማዊ ንጉሰ ነገስት ልዩ ጸሐፊ ሁነህ ቦን ከተማ ብትሄድ’ እንዳሏቸው ያስታውሳሉ።

በወቅቱ ሀገር ውስጥ የነበራቸውን ኑሮ ‘በጣም የተንደላቀቀ’ ብለው የሚገልፁት ተፈራ ሻውል ይከፈላቸው ከነበረ ደመወዝ ከግማሽ በላይ ለሚቀንስ፣ ከጋዜጠኝነት ወደ አምባሳደርነት ለሚያሻግራቸውና ከእናት ሀገራቸው በአካልም ቢሆን ለሚያርቃቸው ሀገራዊ ተልእኮ ‘ከሀገር በላይ ምንም የለምና’ በማለት ይሁንታን ሰጡ። በጀርመን የተጣለባቸውን ተቀዳሚ ሀገራዊ ኃላፊነት ሲወጡ ቆይተው የ66ቱ ድርቅ ሲከሰት ለተጎጅዎች እርዳታ እንዲደረግ የበኩላቸውን እንደተወጡ ያስታውሳሉ።

በመቀጠልም ወደ ሱዳን ካርቱም ተዛውረው ሲሰሩ በሀገር ውስጥ የመንግስት ለውጥ ሁኖ የወቅቱ አለቃቸው ዳዊት አብዲ በደርግ ሲጠሩ አምባሳደር ተፈራ ጉዳይ ፈፃሚ ሆነው በዚያው ቆዩ። አስቀድሞ አለቃቸውን የጠራ ደርግ ድጋሜ እርሳቸውንም ጠርቶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስ ጉዳይ ሃላፊ አድርጎ ሾማቸው፤ ቀጥሎ ደግሞ አሰራቸው።

3 ዓመታት ታስረው በተፈቱ በ3ኛው ቀን ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም አስጠርተው በስህተት ስለመታሰራቸው ይቅርታ ጠይቀው “በምን እንካስህ” ብለው እንደጠየቋቸው ያስታውሳሉ። ‘አንድ መሪ ስህተቱን አምኖ ለሀገሬ እንድሰራ እድል ከሰጠኝ ከዚህ በላይ ካሳ አልፈልግም’ ብለው መመለሳቸውን አሁንም ድረስ አይረሱትም። የሰርቶ አደር ጋዜጣ አዘጋጅ እንዲሆኑ እድል ቢሰጣቸውም ባለመፈለጋቸው የቱሪዝም ኮሚሽን አማካሪ ሆኑ፤ ቀጥሎም የቀይ መስቀል ዋና ፀሐፊ ሆኑና በ77 ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አሰባሰቡ።

በድርቁ ወቅት የነበራቸው አስተዋፅኦ ተቆጥሮ፣ ምስራቅ ጀርመን የነበሩት አምባሳደር የልብ ህክምና ሊያደርጉ መሆኑ ታስቦ ለ3ኛ ጊዜ ወደ ጀርመን ተላኩና መሉ አምባሳደር ሆኑ። በዚያ ለስሚንቶ፣ የጨርቃ ጨርቅና ሴራሚክ ፋብሪካዎች መቋቋምና ለበርካታ ተማሪዎች ስኮላርሽፕ መሳካት አብዝተው ጣሩ።ወደ ችኮዝላቫኪያ ተዛውረው እየሰሩ እያለ ሌላኛው የመንግስት ለውጥ ሆነና ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ተጠሩ።

በርካታ ወዳጆቻቸው እንዲቀሩ ቢመክሯቸውም ያለምንም ፍርሃት ጓዛቸውን ጠቅለው ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የወቅቱ ባለስልጣናት ‘ከዚህ የበለጠ አርበኝነት የለም’ እንዳሏቸው ያስታውሳሉ። ለ3 ዓመታት በኢህአዴግ መንግሥት ስር ሰርተዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአማካሪዎች መማክርት ጉባኤ አባል ሆነው የሚወዷት ሀገራቸውን ያገለገሉት አምባሳደር ተፈራ 3 ወንድ ልጆችን ስላፈሩበት ትዳር ሲጠየቁ ‘ያኔ ደፋር ነበርኩ’ ብለው ወደ ሚያስታውሱት የወጣትነት ዘመናቸው በትዝታ ይሄዳሉ።

በአቶ ከተማ ይፍሩ አማካኝነት ወደ ጀርመን ከማቅናታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሽምግልና የላኩት የወቅቱ አለቃቸው የነበሩ ሻለቃ አሰፋ ለማን ጨምሮ ቢትወደድ አስፍሃ ወልደ ሚካኤል፣ ጀነራል ደረሴ ዱባለና ጀነራል ደበበ ኃይለ ሚካኤልን ነበር። የክብር ዘበኛ ምክትል የነበሩት ጀነራል ከበደ ዋጋዬ ሽምግልናውን ተቀብለው ያኔ አዲስ በነበረው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል የተወሰኑ ሰዎችን ያሳተፈ ኮክቴል አድርገው ልጃቸው ወይዘሮ ወይንሸትን ለአምባሳደር ተፈራ ይሰጣሉ። ይህ በሆነ በማግስቱ ‘አውሮፕላን ተሳፈርን’ ይላሉ አምባሳደር ተፈራ ሻውል።

በሰርጋቸው ማግስት የተንደላቀቀ ያሉትን ኑሮ አስትቶ ባህር ያሻገራቸው፤ በስህተት 3 አመት አስሮ በፈታቸው መንግስት ስር ከ10 አመታት በላይ እንዲያገለግሉ ያደረጋቸው፤ ጡረታቸውን ሲቀሙ ‘ይሁን ሀገሬን አልከስም’ ያስባላቸው፤ የአማካሪዎች መማክርት ጉባኤ አባል እንዲሆኑ ሲጠየቁ በከፍተኛ ደስታና ኩራት እንዲቀበሉት ያስቻላቸው የፀና የሀገር ፍቅራቸው መሆኑን ይናገራሉ። ‘እስር ቤቱ ይረሳል፤ የተደረገብህ ግፍ ይረሳል፤ ከሀገር የሚበልጥ ግን የለም’ ይላሉ።

አቶ ተፈራ በ1950ዎቹ መጨረሻ ጋብቻ የመሰረቱ ሲሆን ሁለተኛው ልጃቸው አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በአሁኑ ሰአት የቦይንግ አፍሪካ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ናቸው። ወደዚህ ሥራ ከመምጣታቸው በፊት በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነበሩ:: ዲፕሎማትነትን ከወላጅ አባቴ ከአቶ ተፈራ እያየሁ አደግኩ የሚሉት የዚህኛው ዘመን ዲፕሎማት ሄኖክ በፈረንሳይ ሀገር የህግ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው::

‹‹አባቴ ከሰው ጋር የመግባባት ልዩ ክህሎቱ ይደንቀኛል:: ይህም ለአንድ ዲፕሎማት የግድ የሚያስፈልገው ነው:: ሌላው አባቴ ሀገሩን ለማገልገል ያለው ፍቅር ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ነው:: ሁለገብ እውቀቱም ለብዙዎች የሚገርም ነው:: ስለ ሀገሩ ብሎም ስለ አካባቢ ሁኔታ ጠንቅቆ አውቆ ነው የሚመራው :: በመሆኑም ብዙ ነገሮች ይሳኩለታል:: በዚያ ላይ ከጋዜጠኝነት ወደ ዲፕሎማትነት የተሸጋገረ በመሆኑ የተግባቦት ክህሎቱ ልቆ የተገኘ ነው:: በመሆኑም ዛሬ ላለሁበት ደረጃ አባቴ ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚነገር አይደለም:: ›› ሲሉ ልጃቸው አምባሳደር ሄኖክ ስለ አቶ ተፈራ ማለትም ስለአባታቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል:: አምባሳደር ተፈራ በአሁኑ ወቅት የ78 አመት ሰው ሲሆኑ በብዙዎች የሚከበሩ ላገራቸው ጥልቅ ፍቅር ያሳደሩ በወርቃማው ዘመን ሀገራችን ያፈራቻቸው ታላቅ ሰው ናቸው::

የቀድሞ ዲፕሎማት አቶ ተፈራ ሻውል ብዙ ያልተነገረለቸው ቢሆንም እርሳቸው ስራዬ ይናገር በማለት ብዙም ለመታየት የሚጓጉ አይደሉም:: ነገር ግን በዘመናቸው የሰሩት ድንቅ ስራ ዛሬ በአዲሱ ትውልድ በበጎ ይወሳል:: ዲፕሎማሲ በሀገራችን እንደ ዋና ህልውና በሚታይበት በአሁኑ ወቅት የእነ ዲፕሎማት ተፈራ ሻውል ግለ-ታሪክ ብዙ ትምህርት የሚቀሰምበት ነው:: በተለይ ሚድያ እና ዲፕሎማሲን አንድ ላይ አጣምረው እውቀት ያከማቹ ታላቅ ሰው እንደመሆናቸው ኢትዮጵያ ብዙ ልትጠቀምባቸው የሚገቡ ሰው ናቸው::

የቀድሞ ዲፕሎማት አቶ ተፈራ ራሳቸውን ብቁ ዲፕሎማት ከማድረጋቸው ባሻገር ልጃቸውም የእርሳቸውን አርአያ ተከትሎ እንዲያድግ አድርገዋል:: በዚህ ውጤታማ አባት ሊባሉ እንደሚገባም እሙን ነው:: ኢትዮጵያ በወርቃማው ዘመን የኖሩ ብርቱዎቿን በወጉ መንከባከብ ፤ ታሪካቸውን በወጉ መዘከር አለባት:: እንደ ዲፕሎማት አቶ ተፈራ ያሉ ሰዎች ተንቀሳቃሽ ቤተ መጽሀፍት እንደማለት ናቸው::

እኛም ለሀገራቸው በቅንነት እና በታማኝነት ያገለገሉ የሀገር ባለውለታዎች በሚዘከሩበት አምዳችን በዚህ ሳምንት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ቀን ምክንያት በማድረግ በዘርፉ ሀገራቸውን ባለመታከት ያገለገሉትን አምባሰደር ተፈራ ሻውልን አመሰገንን፤ ረዥም ዕድሜና ጤናም ለእሳቸው ተመኘን።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ጥር 1/2016

Recommended For You