በኢትዮጵያ የኀብረት ሥራ ማህበራት ከተቋቋሙ ረጅም ታሪክ አስቆጥረዋል:: በዚህም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ትጠቀሳለች። በሀገሪቱ ዘመናዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በቅድመ አብዮት ጊዜ በ1953 ዓ.ም የገበሬዎች እርሻ ድንጋጌ በማውጣት የተጀመረ ሲሆን፤ በደርግ ዘመንም ሆነ ከደርግ ሥርዓት በኋላ ዓለም አቀፍ መርሆችን በማካተትና ማሻሻያ በማድረግ የኅብረት ሥራ ማህበራት ድንጋጌዎችና አዋጆች ወጥተው ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ህብረት ሥራ ማህበራት በእድሜ ደረጃ ከ60 ዓመት በላይ ቢያስቆጥሩም፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያ ያላቸው አስተዋጽኦ ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ለዚህ ደግሞ በየሥርዓቱ የነበረው የኅብረት ሥራ ማህበራት እንቅስቃሴ የተለያየ መልክ እየያዘ እና መንግሥታትም የፖለቲካ መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙባቸው ስለነበር ሲሆን፤ ይሄም ህብረት ሥራ ማህበራቱ መድረስ በነበረባቸው የእድገት ደረጃ ላይ መድረስ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል:: በዚህም በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ከኢትዮጵያ ልምድ የወሰደችው ጎረቤት ሀገር ኬንያን ያህል እንኳን ልትጠቀምባቸው አልቻለችም::
ለምሳሌ፣ ከኢትዮጵያ ልምድ የወሰደችው ኬንያ፣ አሁን ላይ 45 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ጥቅል ምርት የሚሸፈነው በህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ነው :: የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ማህበራት ግን ከዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም:: እናም የህብረት ሥራ ማህበራት እስካሁን በሀገረቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚጫወቱት ሚናቸው ስለምን አላደገም? ካለፈው ስህተታቸው ተምረው ውጤታማ እንዲሆኑስ አሁን ላይ ምን እየተሰራ ነው? በሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በማተኮር፣ ከፌዴራል ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ ጋር ቆይታ አድርገናል:: መልካም ምንባብ::
አዲስ ዘመን፡- የተቋሙ ስያሜ ከኤጀንሲ ወደ ኮሚሽን መቀየሩ በሚያከናውነው ተግባር ላይ የሚኖረው ፋይዳ ምንድን ነው?
ዶክተር ጌታቸው፡- የአሁኑ የህብረት ሥራ ኮሚሸን እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ይባል ነበር:: ይሄም ኢህአዴግ ከገባ በኋላ በአዲስ መልክ በመደራጀቱ ነው:: ሆኖም ከዛ በፊት በ1994 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 274/ 94 መሰረት ሲደራጅ ስያሜው ኮሚሽን ነበር:: ይሁን እንጂ በሂደት የተለያዩ ለውጦች ሲመጡና የተለያዩ አደረጃጀቶች ሲፈጠሩ ኤጀንሲ የመሆን ዕድል አጋጥሞት ነበር:: በ2014 ዓ.ም ግን በድጋሜ የአስፈጻሚ አካሉን ተግባርና ኃላፊነት ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሰረት የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ወደ ኮሚሽን እንዲያድግ ተደጓል::
ወደ ጥያቄው ስመለስ እያንዳንዱን መዋቅራዊ አደረጃጀት (ለምሳሌ፣ ኤጀንሲ፤ ኮሚሽንና ሚኒስቴር) ደግሞ የየራሳቸው ደረጃ አላቸው:: የእኛም ተቋም ከኤጀንሲ ወደ ኮሚሸን ከፍ ሲል በሰው ኃይል አደረጃጀት ያድጋል:: በዚህ አግባብም አስፈላጊው ሥራ ተከናውኖ ተግባርና ኃላፊነቱ የተሻለ እንዲያድግ ተደርጓል::
ከዚህ በተጓዳኝ ኮሚሸን መሆኑ፣ ፖሊሲን በራሱ አርቀቆ ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት የማቅረብ ስልጣን ይኖረዋል:: በዚህ መሰረት የራሱን ፖሊሲ ለማርቀቅ የፖሊሲ ጥናቶን ማካሄድ ተችሏል:: በዚህ በጀት ዓመት የመደበኛው ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ በዋናነት በኮሚሽኑ ትልቅ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ታስቦ በእቅድ እየተሰራ ነው::
በተለይ በሀራችን የህብረት ሥራ ማህበራት ከተቋቋሙ ወደ 63 ዓመታትን አስቆጥረዋል:: ለምሳሌ፣ በ1953 ዓ.ም የመሬት አዋጅ ድንጋጌ በሚል እንዲቋቋሙ ተደርገዋል:: ይህም ትልቅ ዕድሜ ሲሆን፤ አንዳንድ ተቋማት ከዚህ በኋላ ተቋቁመው ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል:: ነገር ግን የህብረት ሥራ ማህበራት ትልቅ ዕድሜ ቢያስቆጥሩም ዕድሜያቸውን ያህል መስራት አልቻሉም:: በመሆኑም የተፈጠረውን እድል ተጠቅሞ ይሄን ለመቀየር እየተሰራ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፡- ህብረት ሥራ ማህበራቱ የዕድሜያቸውን ያህል እንዳይሰሩ፣ እንዳያድጉና እንዳይዘምኑ የሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር ጌታቸው፡- የህብረት ስራ ማህበራት ስርዓቶች በተቀያየሩ ቁጥር የስርዓቱ ፖለቲካ ማስፈጸሚያ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር:: ለምሳሌ፣ በንጉሱ ጊዜ ከማህበራት ጋር ተያይዞ ራሱን የቻለ አመለካከት ነበር:: ደርግ ሲመጣ ደግሞ የራሱን የሶሻሊስት አስተሳሰብን እንዲያራምዱለት የገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበር በሚል በመቋቋሙ የስርዓት አራማጅ አደረጋቸው:: በዚህም ህብረተሰቡ ስለህብረት ስራ ማህበራት የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው አድርጎታል::
በኢህአዴግ ጊዜ ለውጥ ሲደረግ ማህበራቱ የመጥፋት ሁኔታዎች አጋጥሟቸው ነበር:: በአጠቃላይ መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር ከተቋቋሙለት ዓላማቸው በማፈንገጥ የየሥርዓቱ ማስፈጸሚያ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር:: በዚህም የሀገራችን የህብረት ሥራ ማህበራት ካስቆጠሩት እድሜ አንጻር የሚጠበቅባቸውን ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም::
አዲስ ዘመን፡- የህብረት ሥራ ማህበራት በዕድሜያቸው ልክ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው የሥርዓት ማስፈጸሚያ መሆናቸው ብቻ ነው? ወይስ ሌሎች ምክንያቶች አሉ?
ዶክተር ጌታቸው፡- ቁልፉ ችግር የነበረው የአስተሳሰብ ነው:: ይህ ሲባል ከሥርዓት ለውጥ ጋር የሚመጣ የተለያየ አስተሳሰብ ስላለ ማህበራቱን ወደ ኋላና ወደፊት ሲጎትታቸው ይስተዋላል:: የመንግሥት ሥርዓት በተቀያየረ ቁጥር አብሮ የሥርዓቱን አስተሳሰብ የማራመድ ነገር ነበር::
ይህ እንዳለ ሆኖ በራሳቸው የውስጥ አሰራርም ደካማ ናቸው:: ብዙ ቁጥር የሚሸፍኑት በግብርናው ዘርፍ የተቋቋሙ ማህበራት ናቸው:: እነዚህ ማህበራት የሚመሩት ባልተማረ የሰው ኃይል እና አርሶ አደሮች ነው:: እስካሁን ድረስም በግብርናው ዙሪያ የሚገኙ ማህበራት የሚመሩት በአርሶ አደር ነው:: ሆኖም የግብርና ስራውን በሚፈለገው ልክ ለማንቀሳቀስ ማህበራቱን በተማረ የሰው ኃይል መምራት ያስፈልጋል:: ነገር ግን በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነው::
ነገር ግን የህብረት ሥራ ማህበራት ማለት የቢዝነስ ማንቀሳቀሻ አካልና የኢኮኖሚ ተቋም ናቸው:: የኢኮኖሚ ተቋምን ደግሞ በደንብ አስቦና አቅዶ መምራት ይጠይቃል:: ነገር ግን በእኛ ሀገር ማህበራት በደንብ አስቦና አቅዶ የመምራት ችግሮች ይስተዋላሉ::
በተጨማሪም በእኛ ሀገር ማህበራት እንደ አንድ ትልቅ ክፍተት የሚታየው በስራቸው የሚቀጠሩ ሥራ አስኪያጆች ከማህበሩ ውጪ ያሉ መሆናቸው ነው:: ይህ ተናቦ በመስራት ሂደት ላይ ችግር ፈጥሯል:: በማህበራቱ ላይ የሚካሄድን ምዝበራ በአግባቡ ከመቆጣጠር አንጻር ክፍተቶች መኖሩ ሌላው በሀገራችን የሚገኙ ማህበራት ከእድሜአቸው አንጻር በስራቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል:: ከሰራተኛው እስከ የቦርድ አመራሩ በገባው ቃል መሰረት ውጤት በማምጣት ረገድ የሚጎድል ነገር አለ::
ማህበራቱ በቢዝነስ ውስጥ ያላቸው ፍላጎት አነሳ በመሆኑ፣ የአባላቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ባለመቻላቸው፤ አባሉም የእኔ ነው ብሎ አምኖ ተቀብሎ በመደገፍና በመስራት በኩል ችግሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል:: በተለይም የፍላጎት ወይም መተማመን አለመኖር በመፈጠሩ ሁሉም በገባው ቃል መሰረት እንዳይሰራ አድርጓል:: በቢዝነስ ውስጥ ደግሞ መተማመንና ለስራው ፍላጎት ከሌለ፤ በአባላት ውስጥ ተጠቃሚነት ካልተረጋገጠ ውጤት ሊገኝ አይችልም::
ከዚህም ባሻገር የመንግሥት መዋቅር ከላይ እስከ ታች ድረስ ወጥ ያለመሆን ችግር ማህበራት በእድሜቸው ልክ መስራት እና ማድግ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል:: ምክንያቱም፣ ከኮሚሽን ጀምሮ እስከ ህብረት ስራ ማህበራት ድረስ ማህበራትን የሚደግፋበት ወጥ የሆነ አሰራር የለም:: ስለዚህ መዋቅራዊ ችግር ሌላኛው በሀገራችን ለሚገኙ ማህበራት ፈታኝ ሁኔታ ነው::
ከአደረጃጀቱ አኳያ ብንመለከት የማህበራቱ በየአቅጣጫው የተበተነ ነበር:: አዋጅ በቁጥር 274/94 ከወጣ በኋላ ግን በተሻለ መልኩ አደረጃጀታቸው እንዲሰበሰብ ተደርጓል:: ይሁን እንጂ አሁን ላይ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በሪፎርም መመለስ አለበት ተብሎ እየተሰራ ነው::
አዲስ ዘመን ፡- ማህበራቱ በለውጥ ጎዳና ተጉዘው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ ኮሚሽኑ ምን እየሰራ ነው?
ዶክተር ጌታቸው፡- ማህበራቱ በለውጥ ጎዳና ተጉዘው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን ሚና ማሳደግ እንዲችሉ ለማድረግ በአሁኑ ሰዓት ኮሚሽኑ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተሰራ ነው:: ለዚህ ሥራችን ከኢትዮጵያ ልምድ ወስዳ ውጤታማ የሆነችውን ኬንያን መመልከት በቂ ቁጭትና መነሳሳትን የሚሰጠን ነው:: ምክንያቱም፣ ኬንያ የህብረት ሥራ ልምድን የወሰደችው ከኢትዮጵያ ነው:: በደርግ ጊዜ ከተቋቋሙት እንደ አጋርፋና አርዳይታን የመሳሰሉ የማሰልጠኛ ተቋማት ሙያተኞች ወደ ኬንያ እየተላኩ ስልጠና እንዲሰጡ ተደርጓል::
በእነዚህ ባለሙያዎች ለኬንያውየን የተሰጠው ስልጠናም በኬንያ የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራትን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏቸዋል:: በዚህም አሁን ላይ ለኬንያ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገት 45 በመቶ አስተዋጽኦ አላቸው:: ምክንያቱም፣ 76 በመቶ የሚሆነው የወተት ምርት፤ 90 በመቶ የሚሆነው የጥጥ ምርት በህብረት ስራ ማህበር የሚቀርብ ነው:: የቤት ልማት ሲታይ አብዛኛው በሚባል ደረጃ የህብረት ስራ ማህበራት የሚገነቡት ነው:: ከዚህ በተጨማሪ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡት የህብረት ስራ ማህበራት ናቸው:: የራሳቸውም ባንክ አላቸው:: በአጠቃላይ ሲታይ በኬንያ የህብረት ስራ ማህበራት በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው::
ከዚህ አንጻር ከኢትዮጵያ ህብረት ሥራ መፈጠር በኋላ የተመሰረቱት የኬንያ የህብረት ሥራ ማህበራት የደረሱበት ደረጃ ስንመለከት እኛ የት ነን? ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው:: ለምሳሌ፣ በኢትዮጰያ 110 ሺ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት፤ 403 ዩኔኖች፤ አምስት ፌዴሬሽኖች አሉ:: የሁሉም ህብረት ስራ ማህበራት ካፒታል ሲሰላ 59 ቢሊዮን ብር ነው:: አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደማለት ነው:: በኬንያ ግን አምስት ሺ ኅብረት ስራ ማኅበራት ስምንት መቶ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካፒታል አላቸው:: ይህ ምን ያህል ካፒታላቸው እንዳደገ የሚያሳይ ነው:: የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ማህበራት ግን ከስምና ቁጥር ውጭ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት የላቸውም::
አዲስ ዘመን፡- የህብረት ሥራ ማህበራት በየጊዜው ከሚፈጠርባቸው መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆኑ፣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ምን ታስቧል?
ዶክተር ጌታቸው፡– የህብረት ሥራ ማህበራት አጠቃላይ ከመንግሥት ተፅዕኖ ነጻ ይወጣሉ ማለት ትክክል አይደለም:: ምክንያቱም የሚያገናኛቸው አሰራር ይኖራል:: በተቃራኒው ደግሞ የማያገናኛቸው ይኖራል:: ዋናው ነገር ሚናቸውን በውል በመለየት መደጋገፍ ነው:: እስካሁን ባለው ሂደት መንግስት የኦዲት፤ የኢንስፔክሽን፤ የፋይናንስ መሰል ሙያዊ ድጋፍ እየሰጠ ነው::
ጣልቃ መግባት ሲባል ግን በህብረት ስራ ማህበራት የዕለት ተዕለት ስራቸው ላይ እየገባ መወሰን የለበትም ነው:: ወይም ማህበራቱ ያመረቱት ምርት “በዚህን ያህል ዋጋ ሽጡ” ብሎ ዋጋ መቁረጥ እና በቦርድ ውሳኔ ላይ ጣልቃ ገብቶ መወሰን የለበትም ለማለት ነው:: በአጠቃላይ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ መሳሪያ መሆን የለባቸውም:: ነገር ግን ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል::
አሁን ላይ እየተሰራ ያለው ሪፎርም ማህበራትን ነጻ ከማድረጉም ባለፈ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመሩ መደገፍ ባለባቸው ደረጃ ልክ እንዲደገፉ አሰራር ለማበጀት የሚረዳ ነው:: ለዚህም መንግስት ፖለተካዊ ቁርጠኝነት ጭምር ኖሮት እየተሰራ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ሪፎርሙን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ ስራው እንዴትና በማን እየተመራ ነው?
ዶክተር ጌታቸው፡- የሪፎርም ስራው በግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ የሚሰበስቡት አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ሲሆን፤ የቴክኒክ ኮሚቴው ደግሞ በህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሽሰማ ገብረ ስላሴ የሚመራ ነው:: ይህም እስከ ታችኛው የመዋቅርና የአደረጃጀት እርከን የሚወርድ ነው::
በዚህም እስካሁን የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር የህብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርሙ የሚሰጠው ጥቅም፤ የነበሩ ችግሮች ምን ምን እንደሆኑ፤ እንዴት መቀረፍ እንዳለባቸው የማስገንዘብ ስራ ሲሰራ ቆይቷል:: እንደ ሀገርም የህብረት ሥራ የሪፈርም ንቅናቄ ተጀምሮ የተለያሰዩ ስራዎችን እየሰራን ነው::
አዲስ ዘመን፡- የሪፎርም ስራው መቼ ይጠናቀቃል? ምን ምን ጉዳዮችንስ ይመልሳል?
ዶክተር ጌታቸው፡– የሪፎርም ስራው ሁለት መልክ አለው:: በዚህ አመት የታቀዱ አዋጅና ደንብ የማያስፈልጋቸው እስካሁን መስራት ሲገባን ያልሰራናቸውን ተግባራትን መስራት ቅድሚያ የተሰጠው ነው:: ከዚህ ባሻገር ግን የሪፎርም ስራው ከዓመት በላይ ጊዜ ሊወስድ ይችላል:: ምክንያቱም በግብርና መር ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ድጋፍ አማካኝነት የዓለም ባንክ ድጋፍ የሚያደርገው አማካሪ ተቀጥሮ በጥልቀት የፖሊሲ ስራዎችን የሚመለከት ጥናት እየተሰራ ነው::
ኮሚሽኑም በዓመት ውስጥ የሚሰራቸው በዋናነት አምስት ተግባራቶች አሉት:: የመጀመሪያው ማህበራቱ ቁጥራቸው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ሀብታቸውና ጉልበታው/አቅማቸው ተበታትኗል:: ከዚህ አንጻር በአንድ ሥራ ክልል ውስጥ አንድ ተመሳሳይ የህብረት ሥራ ማህበራት ካለ ሌላ ተመሳሳይ የህብረት ሥራ ማህበራት መፈጠር እንደሌለበት በአዋጁ ተቀምጧል:: ነገር ግን የኢትዮጵያ የቀበሌዎች ብዛት 17 ሺ ሆኖ እያለ 110 ሺ የሚደርሱ የህብረት ሥራ ማህበራት ተፈጥረዋል::
የግብርና ማህበራት ብቻ ሲታዩ ወደ 28 ሺ ይደርሳሉ:: ስለዚህ አንዱ ስራ አዋጁን በትክል ተግባራዊ ማድረግ ነው:: ይህ ሲደረግ የተበታተኑትን ማህበራት ሰብሰብ በማድረግ ጉልበታቸውና ካፒታላቸው እንዲጠነክር ማድርግ ነው :: ይህም የፋይናንስ ችግራቸውን ሌላ ሳይጠብቁ ሊቀርፉ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ስለዚህ ማህበራትን የማዋሃድ ስራ ለመስራት በዕቅድ ተይዟል::
ሁለተኛው፣ የህብረት ሥራ ማህበራት በአርሶ አደርና ባልተማረ የሰው ኃይል ስለሚመሩ ቦርዱ በባሙያ መደገፍ አለበት ተብሎ የባለሙያዎች አማካሪ ቦርድ (professional advisory board) የሚል እየተተገበረ ነው:: ይህ ሲሆን ቴክኒካል ክፍተቶች ይቀረፋሉ:: ሶስተኛው፣ የህብረት ሥራ ማህበራት ችግር ፋናንስ ነው:: ይን ችግራቸውን ለመፍታት እየተሰራ ነው:: በሀገራችን የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራት ከፍተኛ የፋናንስ ችግር ስላለባቸው ብዙ ጊዜ በተለይም ምርት በሚሰበሰብብት ወቅት በቀጥታ ምርት ከአርሶ አደሩ በመግዛት በተፈለገው ልክ ገበያውን ሲያረጋጉት አይታዩም :: ስለሆነም ይህን ችግር ለመቅረፍ የራሳቸውን ባንክ ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው::
ሌላው ችግር፣ የህብረት ሥራ ማህበራቱን ሊደግፍ እና ሊወክል የሚል ራሱን የቻለ ተቋም አለመኖሩ ነው:: በሀገራችን ህብረት ስራ ማህበራት፤ ዩኔኖችና የፌዴሬሽን አደረጃጀቶች አሉ:: ነገር ግን እነዚህን ሰብሰብ አድርጎ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወክል ተቋም የለም:: በምርምር፤ በስልጠና፤ በበጀት፤ በኦዲትና በሌሎች ስራዎቸ ሊደግፋቸው የሚችል ብሔራዊ ተቋም የለም::
ይህ ተቋም ልክ እንደመንግሥት “አክት” የሚያደርግ ነው:: ለምሳሌ፣ የወጣቶች ሊግ የሚባል አለ:: ይህ ወጣቶች ሊግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶችን ይወክላል:: ህብረት ሥራ ማሀበራት ላይ ስንመጣ ግን የህብረት ሥራ ማህበራትን የሚወክል የልም:: አርሶ አደሩንም እንዲሁ የሚወክል ተቋም የለም:: በዚህ ሰዓት አርሶ አደርን ሊወክሉ የሚችሉ ህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው :: እነሱን የሚወክል በፌዴራል ደረጃ ሊግ መኖር ነበረበት :: አሁን ላይ ኮሚሽኑ ብቻ ነው እኔ ነኝ የማቀውቅላችሁ እያለ እየሰራ ነው :: በሌሎች ሀገራት ላይ ግን ማህበራትን እና አርሶአደሮችን ሊወክል የሚችል ተቋም በስፋት አለ:: በመሆኑም ይህን አይነት ወካይ ተቋም ለመገንባት እየሰራን ነው ::
ሌላኛው፣ ኦዲቲንግ ነው:: 106 ሺህ ማህበራትን በአንድ ዓመት ኦዲት ማድረግ አንችልም :: በኦዲት አሰራር መሰረት በዓመት አንድ ድርጅት በየአመቱ ኦዲት መደረግ አለበት :: ኦዲት ካልተደረገ ያ ማህበር ጤናማ ሊሆን አይችልም:: አርሶ አደሩ ደግሞ ወደ ህብረርት ስራ ማህበሩ ያለችውን ገንዘብ ይዞ የሚመጣው መንግሥትን አምኖ ነው :: በየአመቱ ኦዲት መደረግ ካልተቻለ እንዴት ነው የአርሶአደሩን ሀብት መጠበቅ የሚቻለው? ምክንያቱም ከላይ እስከታች ድረስ ኦዲት የማድረግ የአቅም ውስንነት አለ:: ስለዚህ እኛ የምንወክለው ማህበር ኦዲት መደረግ አለበት ብልን መመሪያ አዘጋጅተናል:: ይህ መመሪያ የሪፎርሙ አካል ነበር :: አሁን ላይ በፍትህ ሚኒስቴር ጸድቆ መጥቶልናል::
አዲስ ዘመን ፡- የኦዲት ችግር ከነበረ 106 ሺህ ማህብራት ባሉበት ሀገር ከዚህ በፊት የነበሩ የኢዲት ሥራ አፈጻጸማችሁ ምን ይመስል ነበር?
ዶክትር ጌታቸው፡- አንዱ የእኛ አፈጻጸም ችግራችን የኦዲት ሸፋን ነው :: ካሉን አጠቃላይ ማህበራት አንጻር ሲታ የኦዲት ሽፋናችን ከ25 እስከ 30 በመቶ በልጦ አያውቅም:: በዓመት ውስጥ ኦዲት እናደርጋለን ብልን ከያዝነው እቅድ አንጻር ግን እስከ 85 በመቶ እንደርሳለን:: ነገር ግን በየዓመቱ ሁሉም መደረግ ነበረበት:: ከዚህ አንጻር ሲታይ የኦዲት ሽፋናችን ዝቅተኛ ነው:: ይህ ደግሞ የሀብት ብክነት እያመጣ ነው:: ማህበራትም ምዝበራ ውስጥ እየገቡ ነው::
አዲስ ዘመን ፡- አምራቾቹን ከዩኒየኖች ጋር ከማገናኘት አንጻር ያሉ ጥንካሬዎች እና ውስንነቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ጌታቸው፡– እነኚህ ማህበራት የተወሰነም ቢሆን ካፒታል አላቸው:: በዚች ካፒታላቸው ለገጠሩ ማህበረሰብ የፋይናንስ ምንጭ ሆነው እያገለገሉ ያሉት የህብረት ሥራ ማህበራት አሉ:: በተለይ ባንክ ባልደረሰበት አካባቢ የህብረት ስራ ማህበራት የህዝባችንን ችግር እየቀረፉ ናቸው:: በስራ አድል ፈጠራም ቢሆን የህብረት ስራ ማህበራት የጎላ ድርሻ አላቸው ::
ለምሳሌ፣ የዘመናዊ ታክሲ አግልግሎት በአዲስ አባባ ብንመለከት በስፋት ገንዘብ እየተሰጠ ያለው አዋጭ የገንዘብ ቁጠባ ማህበር ነው:: አሁን በቅርብ አሚጎስ ላዳ ታክሲዎችን ወደ ዘመናዊ ታክሲ እየቀየረ ነው::
በከፍተኛ ደረጃ ወደ አግሮ ፕሮስሲንግ ስራሳ የገቡም አሉ:: 36 የሚሆኑ የህብረት ስራ ማህበራት እሴት በመጨመር ወደ ከፍተኛ አግሮ ፕሮሰሲንግ ስራዎች ገብተዋል:: ከዚህ በተጨማሪ 98 በመቶ የሚሆነው የግብርና ግብዓት የሚሰራጨው በህብረት ስራ ማህበራት ነው::
የሁላችንም ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩ የህብረት ስራ ማህበራት አሉ:: የሪፎርሙ ዋና አላማም በሀገራችን የሚገኙ ሁሉም ማህበራት በእነዚህ ማህበራት ልክ እንዲደሰሩ ማድረግ ነው ::
አሁን ላይ የህብረት ስራ ማህበራት የሀር ውስጥ ግብይት ከ9 እስከ 18 በመቶ ነው:: ይህ ማለት ከ80 በመቶ በላይ የሀገሪቱ ግብይት ከህብረት ሥራ ማህበራት ውጭ ይካሄዳል ማለት ነው:: የህብረት ሥራ ማህበራትን የገበያ ድርሻ ማሳደግ ካልተቻለ በሚፈለገው ልክ ገበያውን ማረጋጋት አይቻልም:: የሪፎርሙ አንዱ ዓላማም የማህበራቱን የገበያ ድርሻ ማሳድግ ነው:: ምክንያቱም የገበያ ድርሻቸው ካላደገ ገበያውን ማረጋጋት አይችሉም ::
በሌሎች ሀገራት ላይ ዋጋን የሚተምኑት የህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው :: በዚህም ሌላው የነጋዴ ክፍል ዋጋ ተቀባይ ነው:: በእኛ ሀገር ግን ዋጋ ሰጪ ሳይሆኑ ከነጋዴው ዋጋ ተቀባይ ናቸው:: ይህ ደግሞ በታሰበው ልክ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ማረጋጋት አያስችላቸውም::
አዲስ ዘመን ፡- ዩኒየኖችን እና አርሶ አደሮችን በቀጥታ እንዲገናኙ በማድረግ በሀገራችን የሚስተዋለውን ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በሪፎርሙ ምን ታስቧል?
ዶክትር ጌታቸው፡- ይህ የንግድ ሥርዓት ነው :: አንዳንዴ በንግድ ሥራ ሥርዓቱ ማህበራት በራሳቸው የሚሰሯቸው ስራዎች አሉ:: የህብረት ሥራ ማህበራት የራሳቸውን አቅም ከገነቡ፣ የፋይናስ ችግር ከተቀረፈላቸው ደላላ የሚባለው ነገር ላይመጣ ይችላል:: የህብረት ስራ ማህበራቶች በተፈለገው በወቅቱ ገንዘብ በመያዝ የአርሶ አደሮችን ምርት መግዛት በማይችሉበት ጊዜ ደላሎች በቀላሉ ወደ ገበያው ይገባሉ:: ይህ ደግሞ ላልተገባ የዋጋ ንረት ይዳርጋል::
ብዙ ጊዜ መንግሥት ለህብረት ሥራ ማህበራት የሚሰጣቸው የተዘዋዋሪ ፈንድ ድጋፍ ዘግይቶ ነው የሚደርሰው:: ገንዘቡ ከዘገየ ደግሞ ምርቱ በደላላ ስለሚወሰድ ምርት የለም ማለት ነው:: ስለሆነም በሪፎርሙ የአርሶ አደሮችን እና ዬኔኖችን በቀጥታ በማገናኝት ደላሎችን እና ያልተገባ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ለመከላካል የህብረት ስራ ማህበራትን የፋይናንስ አቅም የማጎልበት ሥራ እየሰራን ነው::
አዲስ ዘመን ፡- ተቋሙ የራሱን ተቋም ለመገንባት እና ራሱን ለማስተዋወቅ ምን እየሰራ ነው?
ዶክትር ጌታቸው ፡– ተቋም ማለት ህንጻው ከሆነ ህንጻ የለንም :: ግን መዋቅር ያለው ተቋም አለን :: ራስን ከማስተዋወቅ አንጻር ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ:: ስለሆነም በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ተጠቅመን የህብረት ስራ ኮሚሽን ምን የሚሰራ ነው የሚለውን ለማስተዋወቅ ከፍተኛን ስራዎች እየተሰሩ ነው ::
አሁን ላይ ኮሚሽኑ “ብራንዲግ” ላይ እየሰራ ነው:: የተቋሙ ሎጎ ኮፕ ( coop ) ነው:: ነገር ግን ቀለሙ ኢንተርናሽናል ኮፕረቲቭ አልያንስ ነው:: እሱን ወደ ፊት የራሳችን ሎጎ ምን መሆን አለበት የሚለውን አብረን ከሪፎርሙ ጋር እየሰራን ነው::
አዲስ ዘመን ፡- የተክኖሎጂ ሽግግር ጋር በተያያዘ በሪፎርሙ ምን ታቅዷል?
ዶክትር ጌታቸው፡- አንዱ የህብረት ሥራ ማህበራት ችግር ቴክኖሎጂን አለመጠቀም ነው:: በሪፎርሙ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ለማድርግ ካቷል:: የህብረት ሥራ ማህበራት ፋይናሽያል ተቋም እንደመሆናቸው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው:: የፋይናሽያል አሰራራቸው በቴክኖሎጂ መደገፍ አለበት:: አሁን ላይ አንዳንድ የብድር ተቋማት የራሳቸውን ሰርቨር ኖሯቸው የባንክ አሰራር እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው ::
አዲስ ዘመን ፡- ለቃለ መጠየቅ ፈቃደኛ ሆነው ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን::
ዶክተር ጌታቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ሞገስ ተስፋ እና ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥር 1/2016