የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ ትምህርት ቤቶች ላይ እየተሠራ ነው

 ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ብትሆንም፤ አሁን ላይ ግን እነዚህ ባህላዊ የማንነት መገለጫዎች በአግባቡ ተጠብቀው ባለመቀጠላቸው በመጤዎቹ እየተበረዙ ይገኛሉ። ባህላዊ እሴቶች ስፖርትና ባህላዊ ጨዋታዎችንም የሚያካትት ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ዘመናዊ ስፖርቶች በመስፋፋታቸው በሚፈለገው ልክ ትውልዱ ሊያውቃቸው አልቻለም።

በእርግጥ የባህል ስፖርቶቹ በፌዴሬሽን እንዲመሩና ህግና ደንብ ተዘጋጅቶላቸው በተደራጀ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ተሰርቷል። ይሁንና የሚመለከታቸው አካላት የዘመናዊ ስፖርት መሰረት የሆኑትን የባህላዊ ውድድሮችና ጨዋታዎች ከማስፋፋትና በወጣቱም ዘንድ ተዝውታሪ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር የተሰራው ስራ በቂ የሚባል አይደለም። በገጠራማ አካባቢዎች ባህላዊ የስፖርት ጨዋታዎች አሁንም ተዘውታሪ ይሁኑ እንጂ፣ በከተሞች አካባቢ ስለስፖርቱ በታዳጊዎች ዘንድ ያለው ዕውቅና እጅግ አናሳ ነው። ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ የሚያስችሉ ውድድሮችና ፌስቲቫሎች መካሄዳቸው አስፈላጊነታቸው ባያጠያይቅም በዓላትን ብቻ ጠብቀው እንዲካሄዱ ከማድረግ ባሻገር ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው።

የባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ባህላዊ ማንነታቸውን ሳይለቁ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ በሀገር አቀፍ፣ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው። የገና በዓል መከበርን እንዲሁም ወቅቱ የባህል ስፖርቶችን በስፋት ለማካሄድ አመቺ መሆኑን ተከትሎ የሚደረገው ይህ ዓመታዊ ውድድርና የባህል ፌስቲቫል ለ14ኛ ጊዜ በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተናጋጅነት በጉቶ ሜዳ በድምቀት በመካሄድ ላይ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መሪነት የተጀመረው ይህ ውድድር ‹‹የባህል ስፖርት ለአብሮነትና ለሃገር ግንባታ›› የሚል መሪ ሃሳብ አንግቧል።

ውድድሩን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፤ የባህል ስፖርቶች እንዲያድጉ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ታሪካዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲተላለፋ ቢሮው ያከነወናቸውን ተግባራት አውስተዋል። የባህል ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርት መነሻ መሆናቸውን በመረዳት እንዲያድጉና ዓለም አቀፍ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል። የአፍሪካ መዲና እና የብሄር ብሄረሰቦች መኖርያ የሆነችው አዲስ አበባ 21ኛውን የኢትዮጵያ የባህል ስፓርቶች ውድድርና እና 17ኛውን የባህል ፌስቲቫል ታዘጋጃለች። በመሆኑም ከተማ አቀፍ ውድድሩ ለሃገር አቀፍ ውድድር አስተዳደሩን የሚወክሉ ምርጥ ስፓርተኞች ለማፍራት የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በሚገኘው ዘመናዊነት ምክንያት ተዘውታሪነቱ በመመናመን ላይ የሚገኘው የባህል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግም፤ እንደሌሎች ስፖርቶች ሁሉ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶችን በመክፈት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በውድድሩ ወቅት አስታውቋል። በይበልጥም ስፓርቱን ለማሳደግ እና ለማስፋፋት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስፋት እንዲሳተፉበት ጥሪ ቀርቧል። እየተካሄደ በሚገኘው ውድድር ላይም ከ8ሺህ በላይ ስፓርተኞች እንደሚሳተፉም ተመላክቷል።

በጉቶ ሜዳ በተካሄደው የመክፈቻ መርሃ ግብር በስፖርት ጋዜጠኞችና በአርቲስቶች መካከል በተካሄደው የገና ጨዋታ ውድድር የስፖርት ጋዜጠኞች 1 ለምንም በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። 14ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በ9 የባህል ስፖርት ዓይነቶች የሚደረግ ሲሆን፤ ውድድርና ፌስቲቫሉ እስከ ጥር 9 ቀን 2015 ዓም የሚቀጥል ይሆናል።

 አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You