በሀገራችን በዓል ደምቅ፣ ሽብርቅ እንዲል ከሚያደርጉት መካከል የባህል አልባሳት ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁባቸው እና ራሳቸውን ከሚገልጹባቸው መንገዶች መካከልም እንዲሁ የባህል አልባሳት ይገኙበታል።
በሀገሪቱ በርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች እንደመኖራቸው የባህል አልባሳቱም አይነት በዚያው ልክ እጅግ በርካታ ናቸው። የባህል አልባሳቱ ከብሄረሰብ ብሄረሰብ ከክልል ክልል፣ ከዞን ዞን የተለያዩ መሆናቸውም ይታወቃል። እነዚህ አልባሳት በሙሉ በበዓላትና በሌሎች የተለያዩ ዝግጅቶች ወቅት ሲለበሱ የአልባሳቱን ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆን ዝግጅቶቹን ውብና ደማቅ ያደርጓቸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእነዚህ የሀገር ባህል አልባሳት ተፈላጊነት እየጨመረ መጥቷል። ለእዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከልም አልባሳቱ የሚመረቱበት ዲዛይን እና አልባሳቱ በብዛት እየተመረቱ ለገበያ እየቀረቡ ያለበት ሁኔታ እንደሆነም ይገለጻል። በባህል አልባሳት ማምረቱም ሆነ ዲዛይን በማድረጉ ላይ በርካታ ዜጎች ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ።
ባህላዊ አልባሳቱ በዲዛይናቸው እየተሻሻሉ እየዘመኑ የኢትዮጵያውያንን ቱባ ባህል ሳይለቁ ለተጠቃሚው ይደርሳሉ። ተጠቃሚዎችም እንደየምርጫቸው እነዚህን ልብሶች ለራሳቸው ፣ ለቤተሰብ እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው አሰርተው በአላትን አብረው ደምቀው ይውላሉ። ለእዚህም በአል በደረሰ ቁጥር የባህል አልባሳት ገበያው ይደራል።
ለዘንድሮው የገና በዓል የአልባሳት ገበያው ምን እንደሚመስል ለመቃኘት በአዲስ አበባ ከተማ በባህል አልባሳት ማምረትና ሽያጭ በእጅጉ ከሚታወቀው ሹሮ ሜዳ ጎራ ብለናል። የአልባሳት መደብሮቹ ቁጥር ስፍር የላቸውም። ከየት ለመጀመር ይከብዳል፤ የአይን አዋጅ ነው የሚባለው፤ በሁሉም መደብሮች የእናቶች፣ የወጣቶች፣ የህጻናት የባህል አልባሳት በጉልህ ስፍራ ተሰቅለው ይታያሉ።
በገበያው አካባቢም ሆነ ወደ መደብሮቹ ሲገባም ሸማቾች በብዛት ይታያሉ። ሸማቾች ብቻቸው፣ ሁለት ሶስት ሆነው፣ ልጆች ይዘው፣ ወዘተ ገበያውን ይቃኛሉ። ለናሙና የተሰቀሉትን እየተመለከቱ ፣ አመራረቱን፣ ዋጋውን ይጠይቃሉ፤ ከአንዱ መደብር ይወጣሉ ፤ ሌላው ጋ ይገባሉ።
የአልባሳት ሻጮቹም ገበያተኛውን ማስተናገዳቸውን ተያይዘውታል፤ አልባሳቱን እያወረዱ፤ እየሳቡ ያሳያሉ፤ ያብራራሉ፤ ዋጋ ይጠራሉ። አልባሳቱን ሲያሳዩ አይደክማቸውም።
ለበዓሉ የተዘጋጁ አልባሳቱን የምንችለውን ያህል ከቃኘን በኋላ ገበያው ምን ይመስላል ስንል ነጋዴዎችንና ሸማቾችን ጠየቅን። በሽሮ ሜዳ የባህል አልባሳትን ከሚያቀርቡ ሱቆች ውስጥ ከአራት አመት በላይ የሰራችው ዘውድነሽ አበበ ማህበረሰቡ አሁን አሁን ከበዓላት ወቅት በተጨማሪ ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሀገር ባህል አልባሳትን ምርጫው እያደረገ መጥቷል ትላለች።
በግላቸው ከሚያሰሩ ሰዎች በተጨማሪ በቡድን በመሆን ፣ቤተሰብ ፣ ጓደኛሞች ፣ የተለያየ ማህበር ያላቸው ማህበርተኞች ለተለያዩ ፕሮግራሞች በህብረት አንድ አይነት የሀገር ባህል ልብስን እንደሚያሰሩም ገለጸችልን። ይህ ወቅት ምንም እንኳን የበዓል ወቅት ቢሆንም ገበያ ቀዝቀዝ ማለቱን ዘውድነሽ ትናገራለች። በገበያው ላይ ያሉት አልባሳት የሚሰሩቡት ግብዓት ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት የአልባሳቱን ዋጋ መጨመሩን ጠቅሳ፣ የበዓል ገበያው ከአምናው ይልቅ ዘንድሮ ቀዝቀዝ ማለቱን ገልጻለች።
ዘውድነሽ እንደምትለው፤ የባህል አልባሳቱ የተለያየ አይነት ናቸው፤ መነን እና ሙሉ ለሙሉ በሸማኔ እጅ የሚሰሩ አይነት አልባሳት አሉ። አብዛኛውን ሰዎች በሸማኔ እጅ የተጠለፈውን ይበልጥ ይመርጣሉ።
አንድ የባህል ልብስ በሸማኔ እጅ ሲሰራ ከሳምንት ያለፈ ቀናትን ይወስዳል የምትለው ዘውድነሽ፣ በዚህ አይነት መንገድ የሚዘጋጁ የባህል አልባሳት ለሸማኔዎች የሚከፈለውን ዋጋና የመሸጫ ዋጋው እንዲጨምር እንደሚያደርጉ ትገልጻለች። ልብሱ በጥንቃቄ የሚሰራ በመሆኑና የሚሸጥበት ዋጋም ከፍ ያለ በመሆኑ የሸማቾች ምርጫ እንደማይሆን ትናገራለች፤ ይህ አይነቱ ልብስ ሸማቾቹ ፊታቸውን ወደሌሎቹ አልባሳት እንዲያዞሩ ያደርጋል ብላለች።
ሌላኛው የበዓል አልባሳትን በመስራት ለገበያ በማቅረብ ከአምስት አመት በላይ ያስቆጠረው ‹‹ ሸራተን ስታይል የሀገር ባህል ›› የሚባለው ድርጅት ነው። አቶ ጠሀ አህመድ/ ስማቸው የተቀየረ/ የድርጅቱ ሰራተኛ ናቸው። ቀደም ሲል በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ለሀያ አመታት በተለያዩ የጥልፍ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ሰርተዋል። በዚህ ድርጅት ውስጥም በሲንጀር የሚሰሩ የጥልፍ ስራዎች ይሰራሉ፤ የሀገር ባህል ልብስ ስራ የራሱ ጊዜ እንደሚወስድ አቶ ጠሀ ጠቅሰው፣ ይህን ልብስ የሚፈልጉ ሰዎች አስቀድመው ማዘዝ እንዳለባቸው ይናገራሉ።
አቶ ጠሀ በስራው ረጅም ዓመት ከመቆየታቸው እንደተገነዘቡት በእጅ የተጠለፉ አልባሳት ይበልጥ ተፈላጊ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት፤ ሸማኔዎች በየጊዜው የተለያዩ ዲዛይኖችን እንደሚያዘጋጁ ይናገራሉ። በዘመናዊ ማሽን ( በሲንጀር ) የሚሰሩ ፣ በልብስ ላይ ውበትን የሚሰጡ ፣ ለየት እንዲሉ የሚያደርጉ ተዘጋጅተው የተቀመጡና በአልባሳቱ ላይ የሚለጠፉ ጥለቶች እንዳሉም ይገልጻሉ። የድሮ የሚባሉ ቱባ የባህል አልባሳትም አሁንም ድረስ ተፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አዳዲስ ዲዛይኖች እንዲሁ በየጊዜው ይተዋወቃሉ ሲሉ ያብራራሉ።
የባህል አልባሳት በአሁኑ ሰዓት በሁሉም የማህበረሰብ ክፍል እየተወደዱ መጥተዋል፤ እንደ ፊቱ ጊዜ አይደለም ሲሉ ይገልጻሉ። መነን ፣ የእጅ ጥልፍ ፣ ንግሰተ ሳባ፣ የአክሱም ፈትል የሚባሉ ባህልን የጠበቁ ልብሶች እንዳሉም ተናግረዋል ።
እነዚህ የባህል አልባሳት እንደሚዘጋጁበት የግብአትና የዲዛይን አይነት ዋጋቸውም ከ3ሺ500 እስከ 15 ሺህ ብር ከፍ ሲልም ደግሞ 30 ሺህ ብር ድረስ እንደሚያወጡም ገልጸዋል። በእጅ የተጠለፉ ልብሶችም ለገበያ እንደሚቀርቡም ጠቁመዋል።
የባህል አልባሳት ገበያው በብዙ አይነት ቀለማት ዲዛይን ልብሶች የተሞላ በመሆኑ ለሸማቹም ቢሆን ለመምረጥ አስቸጋሪ እና የአይን አዋጅ መሆኑ የማይካድ ነው። ሰዎች በሚወዱት ቀለም ላይ ተመርኩዘው ቢመርጡ አሰራሩ ላይማርካቸው ይችል ይሆናል፤ ከአሰራሩ ደግሞ ዲዛይኑና አሁናዊ የሆነው ፋሽን ሊሰባቸው ይችላል።
በዲዛይኑ ተስበው፣ አይናቸው የገባውን ልብስ ሲመርጡ ደግሞ ለልብሱ የተሰጠው ዋጋ ቆም ብለው እንዲያስቡ ሲያደርጋቸው፣ መልሰው በምርጫቸው ላይ ከነጋዴዎቹ ጋር ሲነጋገሩ በግብይቱ ወቅት ታዝበናል። ወይዘሮ ለምለም ወዳጆ በአልባሳት ገበያው ከባለቤታቸውና ሴት ልጃቸው ጋር ነው የተገኙት። የአልባሳት ገበያውን ሲቃኙ ቆይተው ለልጃቸውና ለራሳቸው ቀሚሶችን መግዛታቸውን ይገልጻሉ። የአልባሳቱ ዋጋ ከበፊቱ ብዙም ጭማሪ እንደሌለው የተናገሩት ወይዘሮ ለምለም፣ በአልባሳት ዘርፉ ላይ እየታየ ያለውን የዲዛይንና ጥራት መሻሻል አድንቀዋል።
ሰሚራ በርሄ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም