ሰላምን ያበሰረ ውልደት

ታኅሣሥ የመኸር መካተቻ የበጋ መባቻ ወር ናት። ያለነው ደግሞ የታኅሣሥ ወር በሚወጣበት የጥር ወር በሚገባበት ዋዜማ ነው። ከታኅሳስ 25 ጀምሮ እስከ መጋቢት ያሉት ወቅቶች በጋ ይባላሉ። በመፀው ወይም መኸር መካተቻ እና በበጋ መባቻ ላይ እንገኛለን። ስለወቅቶቹ ያነሳነው ነገርን ነገር ያነሳዋል በሚል ነው፡፡

ወርሃ ታኅሳስ የጥጋብ ጊዜ በመሆኑ ሰውና እንስሳት እንደልባቸው በልተው ጠጥተው የሚዝናኑበት ወቅት ነው። አዝርዕት ተዘርተው እሸት የሚበላበት፤ ሰብሉም የሚታጨድበት ነው። በአጨዳ ጊዜያት ከአጨዳ አምልጦ ከእጅ ሾልኮ መሬት የሚቀረው እህል ቃርሚያ ይባላል። ለዝንጀሮና ለወፎች ይተዋል እንጂ አይለቀምም ። ጉንዳኖች እንኳ ለክረምትና ለዓመት ቀለብ የሚሆናቸውን ስንቅ የሚሰበስቡበት በዚሁ ወር ነው፡፡

የገና በዓልም የሚከበረው በዚሁ ወር መጨረሻ ነው። ገና (ቃሉ ይጠብቃል) በየዓመቱ በኢትዮጵያ ታኅሳስ መጨረሻ እና በፈረንጆቹ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሁለት ሳምንት ቀድመው የሚያከብሩት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ነው። ፈረንጆች ”ክሪስማስ” የሚሉት ማለት ነው። እንደጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር አሮጌው ዓመት ሲወጣ አዲሱ ዓመት ሊመጣ ባለበት ዋዜማ ሳምንት የሚከበር ነው።

ፈረንጆቹ ገናቸውን አክብረው ሲያበቁ አሮጌ ዓመታቸውን ይሰናበታሉ። ለምዕራባውያን ይህ ወቅት ትልቅ የፍስሃና የደስታ ሳምንታት ተደርጎ ይታሰባል። ብዙዎቹ ዓመቱን ሠርተው እረፍት የሚወስዱት መዝናኛ ቦታዎች የሚሄዱበት እና የሚዝናኑበት ነው። ገሚሶቹ ደግሞ ወደ ተለያዩ ሀገሮች ሄደው የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በመጎብኘት ራሳቸውን ዘና ፈታ የሚያደርጉበት ወቅት ነው።

ምዕራባውያን አዲሱ ዓመት በዓላቸውን ባከበሩ በሳምንቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ገና በሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊት ይከበራል። ከላይ እንደጠቀስነው ገና በክርስትና እምነት ተከታዮች ታኅሣሥ መጨረሻ ይከበራል። እንደላሊበላ በመሳሰሉ የቱሪስት መዳረሻዎች የልደት በዓል ብዙ የሀገር ውስጥ ሰዎች እና የውጭ ቱሪስቶች በታደሙበት በትልቅ ሥነሥርዓት ይከበራል።

በልደት በዓል ዋዜማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ትውፊት በአብያተ ክርስቲያናቱ ሁሉ ሌሊት እስከ ዘጠኝ ሰዓት በጸሎትና በያሬዳዊ ዝማሬ ይከበራል። በተለይ በላሊበላ ቤተ ጊዮርጊስ በእረኞችና መላዕክት ተምሳሌት ቀሳውስቱ የልደት በዓል ወረብና ዝማሬ ያቀርባሉ፡፡

ከቤተክርስቲያኑ አናት ዙሪያ ያሉት ካህናት የመላዕክት፣ ከታች በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ በምድር ያሉት ቀሳውስት የእረኞች ምሳሌ ሆነው ማለት ነው። ይህም ጌታ በቤተልሄም በከብቶች በረት በተወለደ ጊዜ እረኞችና መላዕክት እንደተገኙና እንዳመሰገኑ ለማጠየቅ ነው። በቦታው ያለ ምዕመኑ ሁሉ ጧፍ እያበራ በዓሉን ያከብራል።

የአከባበር ሥርዓቱ በቦታው ለየት ያለ ስለሆነ ወደፊት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት ሊመዘገብ እንደሚችል ተስፋ አለኝ። ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት መበርታት አለባቸው። ይህም የበለጠ ቱሪስት እንድንሰበስብ እና ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ የሚረዳ ነው።

በዘመናችን እየጠፋ ያለውና በከተሞች ስሙ ብቻ የቀረው የገና ጨዋታ በገና በዓል ወቅት በገጠር አካባቢዎች ይካሄዳል። አንዳንዶች ገና የሚለው ቃሉ የመጣው የገና ሩር ወይም ጥንግ መምቻ ዘንግ ከሚጠቀሙበት ነው ይላሉ። የገና ዘንጉን ወደ ቀኝ ሲያዞሩት ገ ይሆናል በተቃራኒው አቅጣጫ ሲያዞሩት ና ይመስላል የሚሉ አሉ።

ለዚህም ገና እንደተባለ ይነገራል። በብዛት በገና ጨዋታ የሚጫወቱት ወንዶች በሁለት ምድብ ተከፍለው ነው። የገና ጨዋታው ሲጠናቀቅ አሸናፊው ወገን በሆታና በግጥም ተሸናፊውን ወገን ይሰድባል። ይህም የገና ተሳዳቢ ይባላል።

በነገሥታቱ ዘመን ገና ይጫወቱ ስለነበር ፤የነገሥታቱ ወገን ቢሸነፍ የገና ጨዋታ አሸናፊው ወገን በግጥም በዜማ በጭፈራ እንዳሻው የሚሳደብበት ነፃነት ነበረው። ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የተባለው ከዚህ የተነሳ ነው።

ያሬድ ማህሌታይ በመጽሀፈ ድጓ አራቱን የታኅሣሥ ሳምንታት ስያሜ ሰጥቶ እንዲዘመር አድርጎታል፤ በዚህም መሠረት ሳምንታቱ ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ ልደት በሚባል ይጠራሉ። ስብከት የተባለው ሙሴ በኦሪት ነቢያት በትንቢት እንደተናገሩለት ለማመላከት ነው።

ብርሃን የተባለው ‹‹ እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው›› የሚለውን የዳዊት ትንቢትና ጌታም በወንጌል‹‹ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ›› ያለውን አስመልክቶ ነው። አንድም የብርሃናት ጌታ ስለሆነ የምሥራቅ ነገሥታት በኮከብ ተመርተው ቤተልሄም የጌታን ልደት ተገኝተው ታድመው አክብረዋል፡፡

ሦስተኛው ሳምንት ኖላዊ ይባላል። እረኛ ማለት ነው። ‹‹ እግዚአብሔር እረኛዬ ነው›› መዝ 22 ፡1 እንዲሁም ጌታ‹‹ መልካም እረኛ እኔ ነኝ ያለው›› ይሰበክበታል። እናም ወቅቱ እረኞች የታደሙበት የእረኛ ልደት ነው፡፡

በዘመኑ አሥራ ሁለት ነገሥታት ከነሠራዊታቸው ጉዞ ቢጀምሩም ዘጠኙ የሠራዊታቸው ስንቅ በማለቁ ሲመለሱ፤ ሦስቱ ነገሥታት ማለትም የፋርስ የባቢሎንና የኢትዮጵያ ነገሥታት ግን በኮከብ ተመርተው ቤተልሄም እንደደረሱ ስንክሳር ያስረዳል።

በልደቱ ተገኝተው ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡ። በመዝሙርም

‹‹ የጥበብ ሰዎች መጡ ሰምተውት በዜና

እያበራላቸው ኮከብ እንደ ፋና

… ሰብዓ ሰገል መጡ ሊሰግዱ በሙሉ

የእስራኤል ንጉሥ ወዴት ነው እያሉ

እጅ መንሻውን ሰጡት እንደ የሥርዓቱ

እጣኑን ለክህነት ወርቁን ለመንግሥቱ …›› እየተባለ በዚሁ በልደት ወቅት ይዘመራል፡፡

በጌታ ልደት መላዕክት፣ እረኞች ነገሥታት ተገኝተዋል። በወንጌልም እንደተጠቀሰው እረኞችና መላዕክት

‹‹ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት

ወሰላም በምድር ስምረቱ ሃሌ ሉያ

ሃሌ ሃሌ ሃሌ ሉያ ›› እያሉ ዘምረዋል። ትርጉሙም ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ ሉቃ 2፡ 14 ማለት ነው። በቤተክርስቲያንም በልደት ወቅት ይህን መሰል የልደት መዝሙሮች ይዘመራሉ።

በልደቱ ዕለት የታደሙት ነገሥታት ወርቅ ያቀረቡለት የነገሥታት ንጉሥ ነህ ሲሉ ነው። ወርቅ ወርቅነቱ የሚረጋገጠው በእሳት ተፈትኖ ነው። አንተም በሰውነትህ መከራ ያጋጥምሃል ሲሉ ነው። ዕጣን ምዕዝ ነው ፤ከሩቅ የሚሸት ነው። የተስፋም ምሳሌ ነው፤ተስፋ ያልያዙትን እንደያዙት ያላዩት እንዲያዩት ያደርጋል፤ ካህናት ዕጣን ያጥናሉ አንተ ግን ሊቀ ካህናት ነህ ሲሉ ነው። ቀድሞ ዕጣን የምንገብርላቸው ጣዖታት ኃላፊያን ናቸው። አንተ ግን ኅልፈት የለብህም ሲሉ ነው።

ከርቤ መገበራቸውም ከርቤ መራራ በመሆኑ በስቅለት መራራ ጽዋን እንደሚጎነጭ ሲናገሩ ነው። አንድም ከርቤ የተሰበረውን አጥንት ይጠግናል አንድ ያደርጋል፤ ጌታም በሰውና መላዕክት መካከል የነበረውን መለያየት አንድ ያደርጋል፣ ይጠግናል ሲሉ ከርቤ እንደሰጡት የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ያስረዳል። እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ፤ መልካም በዓል፡፡

ይቤ ከደጃች.ውቤ

 አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You