የዋልያዎቹ ወርቃማ ኮከብ ስንብት

መነሻው ኮረም ሜዳ ነው። ውቢቷ ሀዋሳ በኮረም ሜዳ አቧራዎች ካፈራቻቸው የእግር ኳስ ፈርጦችም አንዱ ነው። በተስጥኦ የዳበረ አጥቂዎችን ከግብ እንደ ልብ የሚያገናኘው ምርጡ የጨዋታ አቀጣጣይ ሽመልስ በቀለ ጌዶ። ኳስን ሜዳ ላይ በጥበብ ሲያንከባልል ያምርበታል። ፈጣን፣ ብልጥ እና አመለ ሸጋም ነው።

ለዓመታት በወጥ አቋም በኢትዮጵያ እግር ኳስ የደመቀው ሽመልስ በቀለ ከኮረም ሜዳ እስከ ፈረሰኞቹ ቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚያም ከወርቃማው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትውልድ የአፍሪካ ዋንጫ ዐሻራ ጋር በከፍታው የደመቀው ኮከብ ለ15 ዓመታት ከተጫወተለት የብሔራዊ ቡድን ቆይታው ከቀናት በፊት ራሱን አግልሏል።

ከግብጽ የተለያዩ ክለቦች ውጤታማ የዓመታት ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ሕይወቱ ማግስት በአንጋፋው መቻል በኳስ ሕይወቱ አመሻሽ ከላቀ ተጽእኖው ጋር ዛሬም የቀጠለው ኮከብ ባለፈው ሐሙስ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አዳማ ላይ ታላቅ ግልጋሎት ከሰጠበት የእናት ሀገሩ እግር ኳስ ስፖርት ድንቅ ማስታወሻውን እንደተወ በክብር መለየቱንም ይፋ አድርጓል። ከደቡብ አፍሪካ እስከ ካሜሩን በሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ከአይረሴ ትውስታዎቹ ጋር ያንጸባረቀው ኮኮብ ሳይተካም ከዋልያው ተለይቷል።

ዋልያዎቹ ጥቅምት 4/2005 ዓ.ም ሱዳንን ድል አድርገው ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለሱና ደቡብ አፍሪካ ላይ የማይረሳውን ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያሳዩ ሽመልስ በወርቅ ቀለም የተጻፈ የታሪክ ዐሻራ ነበረው። ከካይሮ የክለብ እግር ኳስ ሕይወት የተሳካ ቆይታ እስከ ካላባር ናይጄሪያ የዓለም ዋንጫ ፍጥጫም ይህ የመሃል ሜዳ ኮከብ ነበረ። ከስምንት ዓመታት በኋላም የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ድረስ የኮረም ሜዳው ኮከብ ቁልፍ የዋልያዎቹ ኮከብ መሆኑን አስመስክሯል።

 ከአስደናቂው የዋልያዎቹ አጥቂ ሳላዲን ሰይድ እስከ አዳነ ግርማ፣ ጌታነህ ከበደ ከዚያም በአቡበከር ናስር የትውልድ ቅብብል ከድንቅ አጥቂዎች የማይረሱ ግቦች ጀርባ ሚስጥር የነበረው ይሄው ኮከብ ነው።

 ከሀዋሳ የጀመረው የሽመልስ በቀለ የእግር ኳስ ጉዞ ማረፊያውን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት አድርጎ ነበር። ወደ ሊቢያ ትሪፖሊ ተጉዞ፣ ሊቢያ ጦርነት ውስጥ በገባችበት ወቅት አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፏል። ከዛም በሱዳን እና በግብጽ የተለያዩ ክለቦች ውስጥ ከተጫወተ በኋላ ዘንድሮ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ለመቻል እግር ኳስ ክለብ ፊርማውን አኑሯል።

በ15 ዓመታት የብሔራዊ ቡድን ቆይታው ለዋልያዎቹ በ83 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 16 ግቦዎችን ማስቆጥር የቻለ ሲሆን፤ 13 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበልም ችሏል። አመለ ሸጋው አማካኝ አንዴ ቢጫ ካርድ የተመለከተ ቢሆንም ቀይ ካርድ ግን ተመዞበት አያውቅም ።

ዋልያዎቹን አምበልነት መምራት የቻለው ሽመልስ ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሉን ‹‹ጊዜው አሁን እንደሆነ ይሰማኛል፤ ብሔራዊ ቡድኑን የምሰናበትበት ወቅት የምወደውን እና የምጓጓለትን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ወክዬ የምጫወትበት ጊዜ እንዳበቃ ይሰማኛል›› ሲልም ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያን ለሁለት አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በማብቃት ደማቅ ታሪክ እና ትልቅ ዐሻራን ማሳረፍ የቻለው ሽመልስ ‹‹በቀጣይም ከሀገሬ እና ብሔራዊ ቡድኑ ጎን በመሆን በስሜት እና በኩራት ዋልያዎቹን የማበረታታ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ›› በማለትም ተናግሯል። አክሎም ‹‹ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻዋ ቀን በእኔ እምነቱ ኖሯችሁ ከጎኔ ለነበራችሁ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ›› ሲልም የስንብት መልዕክቱን አጋርቷል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክብርን ያሳካው ሽመልስ፣ ከሀገር ውጭም በሊቢያ ለአሊተሃድ እና ለሱዳኑ ኤልሜሪክ መጫወቱ የሚታወስ ነው፡፡ በቀጣይም ወደ ግብጽ በማቅናት ፔትሮጀክት፣ ኤልጉና፣ ማስሪ ኤልመካሳ እና ኤን ፒፒ አይ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ ከአስር ዓመታት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላም ወደ ሀገሩ በመመለስ መቻልን የተቀላቀለው ዘንድሮ ነው።

 ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን እሁድ ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You