እጅግ በርካታ ዓመታትን ከትያትር ቤት ሳይርቅ በኪነ-ጥበብ ሙያ ውስጥ ቆይቷል:: ትያትር አንዴ ከገቡበት ለመተው የሚቻል ሙያ ስላለመሆኑም ያነሳል:: ለዚህም ይመስላል በተለያዩ የቴሌቪዥን ድራማዎች፣ ፊልሞች እና ፕሮግራሞችን በማቅረብ በቴሌቪዥን መስኮት ብንመለከተውም እሱ ግን በተለያዩ ትያትሮች ላይ በመጫወት አሁንም ድረስ በመድረክ ላይ አለ:: በዛሬው ዝነኞች ገጻችን ስለ ሥራና ሕይወቱ ስንል እንግዳችን አድርገነዋል::
ውልድት እና እድገቱን ያሳለፈው በደጃች ውቤ ሰፈር ነው:: በሰሜን ማዘጋጃም ይኖር ነበር:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በራስ አበበ አረጋይ ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን ተፈሪ መኮንን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ደግሞ ኪነ-ጥበብን ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረበት ነው:: ለኪነ-ጥበብ መነሻ በሆነው የተፈሪ መኮንን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ቆይታው በአሁን ሰዓት አንጋፋ ከሆኑ ተዋንያን አርቲስት ሽዋፈራው ደሳለኝ እና ሌሎች ባለሙያዎች ጋር ከጅምሩ አብረው ስለመሆናቸው ያነሳል:: የዛሬው የዝነኞች ገጽ እንግዳችን ተዋናይ ሄኖክ ብርሃኑ::
ከትያትር ውጪ የሙዚቃ መሳሪያዎች ክራር፣ ኪቦርድ ፣ ድራም የሙዚቃ መሳሪያዎች ይጫወታል:: ምክንያቱም የልጅነት ፍላጎቱ ሙዚቀኛ መሆን ነበር:: ይህ ፍላጎት ያለ ምክንያት የመጣ አልነበረም። ሄኖክ አሁን ያለበትን ሙያ ከወላጆቹ የወረሰ ይመስላል:: አባቱ ብርሃኑ ዮሴፍ ሙዚቀኛ የነበሩ ሲሆን በሀገራችን በቀዳሚነት ከሚጠሩ ባንዶች ውስጥ በሮሀ ባንድ ውስጥ ድራመር፣ በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት፣ በኢትዮ ስታር ባንድ፣ በዳዲሞስ ባንድ የሙዚቃ ሥራቸውን ያቀርቡ የነበሩ አንጋፋ የሙዚቃ ሰው ናቸው:: እናቱም ወይዘሮ አስቴር ማሞ ተወዛዋዥ እና ተዋንያን ነበሩ:: ከመላኩ አሻግሬ ጋር በመሆን “አንድ ጡት” የሚል ትያትር ሰርተዋል:: ‹‹ማጣትና ማግኘት›› የሚል ትያትር ላይ ተውነዋል::
ሄኖክ የአባቱን ፈለግ በመከተል የመሰናዶ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ህልሙን ለማሳካት በሀገራችን የሙዚቃ ትምህርት ቤት ታሪክ ውስጥ በቅድሚያ በሚነሳው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመማር ከአንድ ሺህ በላይ ከሆኑ ተማሪዎች በማወዳደር፤ ከዚያም ከተቀሩት 80 ተማሪዎች ውስጥ አልፎ፣ ቀሪ 30ዎቹ ውስጥ ገብቶ ይወደው የነበረውን የሙዚቃ ትምህርት ለመማር ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ጉዞውን ጀመረ:: ሄኖክ ኪነ-ጥበብ ከልጅነቱ የተሳበበት ነውና በያሬድ የሙዚቃ ትምህርቱን ከመቀላቀሉ በፊት ‹‹ፋቡላ የትያትር ቡድን›› በጊዜው አማተር፣ የአሁን አንጋፋ የትያትር ባለሙያዎች ጋር የተለያዩ የትያትር ሥራዎችን ያቀርቡ ነበር:: ይህን ቡድን ያቋቋመው ተፈራ ወርቁ ሲሆን ቡድኑ ብዙ የትያትር ባለሙያዎችን ያፈራ ነው:: ቡድኑ የተለያዩ ትያትሮችን እየሰራ ለእይታ ያቀርብ ነበር:: ‹‹ድርብ ሀዘን›› በዚህ ቡድን የጊዜው አማተር ተዋንያን የአሁን አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተጫወተው የሙሉ ሰዓት ትያትር ነበር:: ከዚያም ሄኖክ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን ‹‹ገድሉ አሰግደው›› የሚባል የትያትር ቡድን አቋቁመው ‹‹የአባቷ ልጅ›› የተሰኘ፣ በጊዜውም ተወዳጅ የነበረ ትያትርን ለእይታ አቅርበዋል::
ሄኖክ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው ትምህርቱ ጊዜና ልቦናን መስጠት የሚፈልግ ሲሆን እርሱ ደግሞ በትያትሩ ላይ ይበልጥ እየተሳበ በመምጣቱ ከሙዚቃ ትምህርት ቤት ጥሪው ወደ ሆነው ትያትር ሸፈተ:: ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራው፣ ለእርሱ ፕሮፌሽናል የሚለው የትያትር መድረክ “ሮሚዮና ጁሊዬት”፣ “ጁሊዬስ ቄሳር” የተሰኙ ትያትሮች ላይ “ካስት” የተደረገበት ገጠመኝ ነበር:: ትያትሩ የሚታይበት ቦታ በማዘጋጃ ቤት ነበር:: ከዚያም በተለያዩ ጊዜያት ልምድና ፍላጎትን ተሰጥኦን ባጣመረ መልኩ የትያትር ሕይወቱን ቀጠለ:: አሁንም ድረስ የተለያዩ ትያትሮችን በተለያዩ ገጸ- ባህሪያትን ወክሎ እየተጫወተ ይገኛል::
ሄኖክ ከሰራባቸው ትያትሮች ‹‹ሩብ ጉዳይ›› በጣም ተወዳጅ የነበረ ትያትር ነበር:: “ትናንሽ ፀሐዮች” እንዲሁ በርካቶች የሚወዱት የማይረሳ የሬዲዮ ድራማ ነበር:: ‹‹ማበዴ ነው››፣ ‹‹ሸብ ረብ›› (በፋና ቴሌቪዥን) ሰዎች ልብ ላይ የቀሩ ሥራዎቹ ናቸው::
ሄኖክ ብርሃኑ በኪነ-ጥበብ ውስጥ በርካታ ዓመትን አስቆጥሮ ከሚወደው ትያትርም ሳይጠፋ፣ በፊልሙ ዓለምም እንዲሁ የተለያዩ ፊልሞችን እየሰራ፤ አቅሙንም በማጎልበት የተለያዩ የቴሌቪዥን ድራማዎችና ሌሎች ፕሮግራሞችን እየሰራ ይገኛል:: በርካታ ገጸ-ባህሪያትን ወክሎ ለረጅም ዓመታት እየተጫወተ ሲቆይ ግን ለመጫወት የሚመርጠው፤ አልያም በፍጹም መሥራት የማይፈልገው፣ ገጸ-ባህሪ ብሎ የሚለየው እንደሌለ ይናገራል:: ‹‹እንደ አንድ ባለሙያ የተሰጠንን ገጸ-ባህሪ መምረጥ ባለሙያ አያስብልም ብዬ አምናለሁ:: ትያትር የገሀዱ ዓለም ነጸብራቅ በመሆኑ አንድ ተዋናይ ሆኖ መገኘት አለበት›› በማለት ለሙያው ያለውን ታማኝነትና አመለካከት ይገልጻል::
ሄኖክ በአሁን ሰዓት ‹‹የሌሊት ሙሽሮች›› የተሰኘ ትያትር በየሳምንቱ ሐሙስ፣ “የሚስቶቼ ባሎች” ትያትር እንዲሁ በዓለም ሲኒማ የሚሰራባቸው ትያትሮች ናቸው :: በየሳምንቱ በተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት በቦታው ተገኝተው ተመልካች ፊት የትወና ብቃታቸውን ይዘው ይቀርባሉ:: ይህ ትልቅ የሥራ ሥነ-ምግባርን የሚጠይቅ ነው:: ‹‹የትያትር ሙያን ከሌሎች ሙያዎች ለየት የሚያደርገው ይህ ነው:: ሐሙስ ቀን ትያትር የሚያሳይበት ሰዓት በመሆኑ ሐሙስ ሐሙስ ምንም ዓይነት ፕሮግራም አልይዝም:: ትያትሩ ሁለት ዓመትም ሊታይ ይችላል:: ነገር ግን የእይታ ጊዜው እስኪያበቃ ድረስ እዚሁ እገኛለሁ::›› የሚለው ሄኖክ ከዚህም በተጨማሪ ረቡዕ ረቡዕ የሚታይ “የሚስቶቼ ባሎች” የተሰኘ ትያትር እንዲሁ አለው ይህንንም ቀን አክብሮ በቦታው እየተገኘ ለተመልካቾቹ ያቀርባል::
ትያትር ሁልጊዜም ከተመልካች ፊት የሚቀርብ በመሆኑ ለተመልካች የተለየ ስሜት የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ለተዋንያንም ሁልጊዜም አዲስ ይሆናል:: ‹‹የትያትርን ሙያ ለየት የሚያደርገው ነገር ሁሌም ለምንሰራው ትያትር መድረክ ላይ ወጥቼ ትያትሩን እስክጀምረው ድረስ ልዩ የሆነ ፍርሃትን ይፈጥርብኛል:: 40 ትያትሮችን ብሰራም 41ኛው ላይ ሊያስፈራን ይችላል:: ይህ ስሜት ግን ወደ መድረክ ወጥቼ ማውራትና ከተመልካች ጋር መዋሀድ ስጀምር የሚጠፋ ስሜት ነው::›› በማለት ይህ ስሜት በእርሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተዋንያን ላይም የሚከሰት ነገር እንደሆነ ያነሳል::
ትያትሩ ላይ ቆየት ያለ ጊዜን ካሳለፈ በኋላም ወደ ፊልም ሙያ መግባቱ አልቀረም:: አንድ ከሀገረ አሜሪካ የመጣ ሰው ፊልም መሥራት ይፈልግ ነበርና ሄኖክም በዚህ ፊልም ላይ ለመሳተፍ ኦዲሽን ፈተናውን ወሰደ:: የፊልሙ ርዕስ ‹‹ላቭ ዶት ኮም›› የሚል የመጀመሪያ ፊልሙን ለመሥራት ቻለ:: ጊዜው ትንሽ ቆየት ስለማለቱም ይገልጻል :: ከዚያ በኋላ ‹‹ ውርስ ›› የተሰኘ ድራማ ሰራ። ትያትር መስራቱንም ቀጠለ:: ሄኖክ ከፊልምና ከሥራዎቹ ባሻገርም በቴሌቪዥን ድራማዎቹ እንዲሁ ወደ ተመልካች መቅረቡን ቀጠለ:: በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ የነበረውን “ገመና” የቴሌቪዥን ድራማ አንድ እና ሁለት፣ የ“መለከት” ድራማ፣ “ያልተሄደበት መንገድ” የተወነባቸው የቴሌቪዥን ድራማዎች ናቸው:: አሁን በቅርቡ ፋና ቴሌቪዥን ላይ “የሚጀመር “ማረፊያ” የሚል ድራማ ላይም በተዋናይነት ተሳትፏል::
ትያትር አስቀድሞ የተሳበበት እና ሥራውን የጀመረበት ሙያ ይሁን እንጂ፣ ኪነጥበብ ቦታው ሰፊ በመሆኑ ፊልም እና የተለያዩ ሥራዎችንም ይሰራል:: ነገር ግን፣ ሄኖክ ትያትር ከእነ አስጨናቂነቱ እና ኃላፊነቱ ጭምር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው:: ‹‹ለፊልም ሥራም ቢሆን ክብር አለኝ:: እውነት ለመናገር ግን ትያትር ይበልጥ ያዘነብልብኛል:: ፊት ለፊት ቁጭ ብሎ የሚያየኝ ሰው ላይ የያዝኩትን ስሜት ማስተጋባት አለብኝ። ምክንያቱም ፊት ለፊት፤ ግንባር ለግንባር ገጥመን ነው የምንተያየው። እያንዳንዱ እቅስቃሴያችንን ይመለከቱታል::›› ይላል ለዛም ይመስላል ረጅም ዓመታትን በትያትር ቤት ውስጥ ለመቆየት የቻለው:: ፊልም፣ ትያትር፣ የቴሌቪዥን ድራማ፣ የተለያዩ ፕሮግራሞችን መምራት በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ሄኖክ አለበት::
ኪነጥበብ የአንድ ሀገር ገጽታዋን የሚያሳይ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ግን በውስጧ ያሉ ባለሙያዎች የሚገባቸው ቦታ ያገኙ አይመስልም:: በሙያው ውስጥ ፍቁሩ ኖሯቸው ለሚቆዩ ባለሙያዎች የልፋታቸውን ዋጋ አያገኙበትም ሲል ይገልጸዋል:: ‹‹በዚህ ሰዓት ከአንድ ትያትር መግቢያ ዋጋ ይልቅ የአንድ ማኪያቶ ዋጋ ይበልጣል›› ሲል ሁኔታውን ያስረዳል:: “ሁኔታዎች ከሙያው መውጣትን ቢያስመኙም ፍቅሩ ግን ይህን ተቋቁሞ የማቆየት አቅም አለው” በማለት ይገልጻል:: እርሱም ይህን መርጧል::
በትያትር ሙያ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ያን ያህል ተከፋይ አይደሉም የሚለው ሄኖክ የኮቪድ ወቅት ለነዚህ ባለሙያዎች በጣም ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳል:: ምክንያቱም በጊዜው ትያትር መታየት ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ ባለሙያዎችም ሌላ የገቢ ምንጭ አልነበራቸውም:: ‹‹ትያትር ለብቻ የሚሰራ ነገር አይደለም፤ በቡድን የሚሰራ ነው:: ጊዜው ደግሞ ያንን የሚፈቅድ ባለመሆኑ ብዙ ባለሙያዎች፣ እኔንም ጨምሮ ተፈትነዋል:: ነገር ግን የትያትር ሙያው ተትቶ የሚተው አይደለም›› ሲል ያስታውሳል::
ሄኖክ በትያትር ሙያ ውስጥም እያለ በተለያዩ ፊልሞች ላይ፣ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ይሰራል:: ከዚህም በተጨማሪ ሄኖክ የተለያዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እና ቶክሾዎችን ይመራል:: ከዚህ ቀደም በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረ መዝናኛ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ‹‹የአፍታ ጨዋታ›› ፕሮግራምን፤ በአሁን ሰዓት ደግሞ በፋና ቴሌቪዥን የሚተላለፍ ‹‹ጥበብ በፋና›› የተሰኘ ፕሮግራም ይመራል:: እነዚህ ሥራዎችም ሌላ የገቢ ምንጭ እንደሆኑለት ይናገራል::
ሄኖክ የተለያዩ ድራማዎች፣ ፊልም፣ ትያትር ላይ የተለያዩ ገጸ-ባህሪዎችን ወክሎ ተጫውቷል:: የግጥምጥሞሽ ጉዳይ ነው ብሎ የሚገልጸው ግን በተደጋጋሚ ዳያስፖራ ሆኖ የተጫወተውን ነው:: ‹‹ዋትስ አፕ እና ቤተሰቡ›› የደራሲና ዳይሬክተር ኃይሉ ፀጋዬ ሥራ የሆነው ትያትር ላይ ዳያስፖራ ሆኖ ተጫውቷል:: ይህም በዚህ ትያትር ብቻ ሳያበቃ በሌሎች ፊልሞች ላይም እንዲሁ ዳያስፖራ ሆኖ ተውኗል:: ሄኖክ ሙያው በየእለቱ፣ በየሥራዎቹ የተለያዩ አዳዲስ ልምዶች የሚቃኙበት በመሆኑ ሙያው በራሱ በብዙ ገጠመኞች የተሞላ መሆኑን ያነሳል::
ሄኖክ በአንድ ወቅትም በሠራውና ‹‹ቤተሰቡ›› በተሰኘ ትያትሩ ተወዳድሮ አንደኛ ደረጃን ይዞ የወርቅ ሜዳልያ እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል:: በ1995 ዓ.ም እንዲሁ ተስፋ ኢንተርፕራይዝ ባዘጋጀው የትያትር ፌስቲቫል ላይ በነበረው የትያትር ውድድር አሸናፊ ነበር::
ሄኖክ በዚህ የኪነጥበብ ሙያ ውስጥ ከተማሪነት ጊዜው አንስቶ ከ30 ዓመት በላይ ቆይቷል:: በቅርቡ የሚወጣ ‹‹ትዝታና ፍቅር›› የተሰኘ አዲስ ፊልም ይዞ እንደሚመጣ ተናግሯል:: ወደፊትም የራሱን ትያትር ፕሮዲውስ የማድረግ (የማዘጋጀት) እቅድ እንዳለው ይናገራል:: ሄኖክ በአሁን ሰዓት በዓለም ሲኒማ እየታየ የሚገኘው ‹‹የሚስቶቹ ባሎች›› ትያትር ላይ እየሰራ ይገኛል። ትያትሩ በፕሮዲውሰርነት የተሳተፈበት ሥራ መሆኑንም አንስቷል:: በቅርቡ ደግሞ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን አንድን ትያትር ለእይታ ለማቅረብ በሂደት ላይ ይገኛል:: ከትወና ባሻገር በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በማቅረብ የተለያዩ መድረኮችን የሚመራ ሲሆን፣ የራሱ መዝናኛ ላይ ያተኮረ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማዘጋጀት እንዲሁ በእቅዱ ውስጥ ያለ ሙያዊ ሥራ ነው::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም