የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የከተማዋን ነዋሪ ከሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭነትና ስጋት ለመከላከል ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ፈጥኖ በመድረስ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ የሚሰራ ተቋም ነው::
በሌላ በኩልም ኮሚሽኑ በከተማዋ የአደጋ ስጋት ናቸው የሚላቸውን አካባቢዎች በጥናት በመለየት ነዋሪው ራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም በማከናወን በኩል ላቅ ያለ ሚናም ያለው ሲሆን፤ በተለይም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች በውሃ የሚወሰዱ ሰዎችን የማዳን ሥራው እንደ ሀገር ከባድ ከመሆኑም በላይ የባለሙያዎቹ ቁጥር በጣት የሚቆጠር ስለመሆኑ ይነገራል::
እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ባለሙያዎችም የወንዞቻችንን ብክለት ችለው ሰው የማዳን ሥራቸውን በአግባቡ የሚሰሩ ቢሆንም፤ እነሱ በተለያየ ምክንያት ሥራውን ቢያቆሙ ግን ተተኪ እንደማይኖራቸው ደግሞ ይነገራል:: ምክንያቱም ዘርፉ እውቀት ያለው ስልጠና እንዲሁም የበቁ የሥራ መሳሪያዎችን ስለሚፈልግ ነው:: ዛሬ ላይ አራት ያህል የዘርፉ ባለሙያዎች ቢኖሩም ነገ እነዚህ ሰዎች በቦታው ላይ ባይኖሩ ተተኪ የማግኘቱ ነገር ችግር ውስጥ ነው::
ዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን ያደረግናቸው ባለሙያ ሥራቸው ሕይወትን ከማዳን በተለይም የራስን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ ለሌሎች በመኖር ውስጥ ያሉ ከጥቂቶቹ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑትን አቶ ሙሉጌታ ውዱ ናቸው:: አቶ ሙሉጌታ ውዱ በእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በማዕከል ፈልጎ ማዳን ድንገተኛ አደጋዎች ቡድን መሪና ባህር ጠለቅ ዋናተኛ ናቸው::
ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ ወረዳ ካላኮርማ በምትባል አካባቢ ነው:: እንደ አካባቢው ልጆች ከብት ጠብቀዋል፤ ተጫውተዋል፤ ቤተሰቦቻቸውንም አገልግለዋል:: ከዛም እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢው ወዳለው ሮቢት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመሄድ የመጀመሪያውን የትምህርት እርከን ማለትም ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ያለውን አጠናቀዋል:: አቶ ሙሉጌታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በቆቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለማጠናቀቃቸው ይናገራሉ::
«……..ውልደቴና እድገቴ ሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ ወረዳ ካላኮርማ በምትባል የገጠር ቀበሌ ነው:: አካባቢው ላይ እኔ ብቻም ሳልሆን በርካታ ሕፃናት ማደግ ባለብን የገጠር አስተዳደግ አድገን ሥራ ለምደን ቤተሰቦቻችንን አግዘን ኋላም እድሜያችን ለትምህርት ሲደርስ አቅራቢያችን ባለው ሮቢት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከዛም በቆቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታችንን ለማጠናቀቅ ችለናል» ይላሉ::
አቶ ሙሉጌታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አፋር ክልል በመሄድ በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የውሃ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ውስጥ በመግባት «በወተር ሰፕላይ እና ሳኒቴሽን» የትምህርት መስክ በዲፕሎማ ለመመረቅ በቅተዋል::
ከዚህ የትምህርት ቆይታ በኋላ አቶ ሙሉጌታ ሥራ መቀጠረን አላሰቡም ይልቁንም ሕዝቤን ማገልገል አለብኝ በሚል ወደ ፖሊስነት ሙያ ገቡ:: «….ፖሊስነት ለሀገርና ለሕዝብ መወገን ነውና እኔም የዲፕሎማ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ በፖሊስነት የሙያ መሰክ ተሰማርቼ ሀገሬንና ሕዝቤን አገለግል ዘንድ ከአካበቢዬ ተመልምዬ ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ሄድኩ::» ይላሉ::
በማሰልጠኛ ተቋሙም ከመሰሎቻቸው ጋር በመሆን ተገቢውን ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ በፖሊስነት ተቀጥረው ሥራቸውን ጀምረዋል:: አቶ ሙሉጌታ ከእግረኛ ፖሊስነት ጀምሮ በወንጀል መከላከል፣ በአድማ ብተና ፣ በቡድን መሪነትና በሌሎችም ኃላፊነቶች ለአምስት ዓመት ከስድስት ወራት አካባቢ ካገለገሉ በኋላ በራሳቸው ፍቃድ ሠራዊቱን ተሰናብተው ስለመውጣታቸው ያብራራሉ::
«አንዳንድ ሥራዎች ለእንጀራ ብለው ብቻ አይሰሩም ይባላል አዎ አንዳንድ ሥራዎች እንጀራ ከማብላት ባለፈ የሌሎችን ሕይወት መታደግ ብሎም ሰብዓዊነት ጭምር ይሆኑና ሰዎች ይሳቡባበቸዋል:: » የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ቀድሞም ቢሆን ወደ ፖሊስ ሠራዊትነት የገቡት «ሀገሬንና ሕዝቤን በምችለው አቅም ማገልገል አለብኝ» ብለው ነበርና ሠራዊቱን በፍቃዳቸው ከተሰናበቱ በኋላ ወደሌላ የማኅበረሰብ አገልግሎት ለገንዘብ ተብሎ ሳይሆን ለመንፈስ እርካታ ጭምር ወደሚሰራበት ተቋም ለመቀላቀል ወሰኑ::
አቶ ሙሉጌታ ወስነውም አልቀሩ በእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ውስጥ በእሳት ማጥፋት የሥራ ዘርፍ ለመቀላቀል ቻሉ:: «…እኔ የመረጥኩት ሥራ ምናልባትም ብዙ ሰዎች ተቸግረው ካልሆነ አልያም እንደእኔ የመንፈሳቸው ጥሪ አስቸግሯቸው ካልሆነ በቀር የማይመርጡት የሙያ ዘርፍ ነው» የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ሥራቸው ሰዎች ከአደጋ ሲሸሹ እነርሱ ደግሞ ወደ አደጋው ሰውንና ንብረትን ለማትረፍ ዘለው የሚገቡበት መሆኑን በመጠቆም የሥራውን አስከፊነት ያስረዳሉ::
« …እሳት ጠዋት የታየን ንብረትና ሰው ለማታ እንዳልነበር የሚያደርግ በጣም ዘግናኝ አደጋ ነው:: እንደ ከተማም ብዙ አስከፊ የእሳት አደጋዎችን እናያለን፤ በተቻለ መጠን አደጋው ስር ሰዶ የተባባሰ እንዳይሆን እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ጥሪው ከደረሰን ሰከንድ ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን:: በዚህም እስከ አሁን ብዙ ሰዎችንና ንብረትን ከውድመትና ከሞት ለማትረፍ ችለናል» በማለት ሁኔታውን ይገልፃሉ::
አቶ ሙሉጌታ በፖሊስነት የጀመሩት የሰብዓዊነት ሥራ በኮሚሽኑም ደግመውት እየሰሩ ቢሆንም አሁንም ግን የሌሎች ሙያዎች ባለቤት በመሆን ይበልጥ ወገናቸውን የማገልገል ፍላጎታቸው ጨመረ::
«……የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት መሆን እፈልግ ነበር ያንንም ለማሳካት ኮሚሽኑ ጠቅሞኛል፤ አሁን ላይ ኮሚሽን ኦፕሬተርነት ጀምሮ በኮሚሽኑ የሚሰሩ የአደጋ መከላከል ሥራዎችን አብዛኞቹን እሰራቸዋለሁ::» ይላሉ::
‹‹የማሽን ኦፕሬተር ለመሆን የፈለኩት እኔ እሳት ማጥፋትን እሰራለሁ:: ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሥራዎች አስቸኳይ ይሆኑና ባለሙያው ተዘጋጅቶ ማሽኑን ኦፕሬት የሚያደርጉ ሰዎች ግን ላይኖሩ ይችላሉ:: በዚህ በቀላሉ መከላከል ስንችል ብዙ ንብረት አንዳንዴም ሕይወት የሚጠፋበት አደጋ ስለሚኖር እሱን ከመከላከል አንጻር ለምን ማሽኑንም ኦፕሬት አላደርገውም?›› በማለት ሥልጠናውን ወስደው ባለሙያ ለመሆን ስለመቻላቸው ያብራራሉ::
አቶ ሙሉጌታ ይህንን ሥራም እየሰሩ ‹‹በቀለም ትምህርቱ መስክም አንድ ርምጃ መራመድ አለብኝ›› ብለው በማሰብ በያርድስቲክ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ « በዲዛስተር ሪስክ ማኔጅመንት» የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ስለማግኘታቸውም ያብራራሉ::
«……የሰብዓዊ አገልግሎት በጣም ከሚያስደስቱኝ ተግባራቶች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው ብል ማጋነን አይሆንም:: ፖሊስ ሆኜም ድንገተኛ ነገሮች (አደጋዎች) በሚከሰትበት ጊዜ በማውቀውና በገባኝ ልክ ለሰዎች የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ርዳታ እንዲያገኙ የተቻለኝን ድጋፍ አደርግ ነበር:: ነገር ግን ወደ እዚህ ተቋም መምጣቴ በሙያው በቂ እውቀትን ይዞ አገልግሎት መስጠት ስለሆነ ከፍ ያለ በገንዘብ ሊተመን የማይችል የህሊና እርካታ እያገኘሁበት ነው::» ይላሉ::
አቶ ሙሉጌታ ኮሚሽኑ ከሚሰጣቸው የነፍስ ማዳን ሥራዎች ውስጥ አብዛኞቹ ላይ ተሳታፊ ናቸው:: ይህ የሆነው ሙያውን አውቀውትና ወደውት ስለሚሠሩት ነው:: በሙያና በትምህርት ራሳቸውን ማብቃት ከመቻላቸውም በላይ እንደእርሳቸው እምነት አንድ ሙያተኛ በሄደበት ሁሉ ችግሩን ለመፍታት ሙሉ የመፍትሔ አካል እንጂ ቆይ ለእዚህኛው ችግር እከሌ ይምጣ ብሎ የሚጠቁም (የሚጠራ ) ሊሆን አይገባውም የሚል እምነት አላቸው::
‹‹ከሕክምና ሙያ በስተቀር እኔ ያልተሳተፍኩበት ወይንም ደግሞ ማደረግ የማልችለው ሙያ የለም››
የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ‹‹በዚህም ዘርፈ ብዙ ሙያዎች ባለቤት ነኝ ብል ማጋነን አይሆንም›› በማለት ስለራሳቸው ይገልጻሉ::
«……የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሠራተኛ ለመሆን ከምንም በላይ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፤ ምክንያቱ ደግሞ የምናገኛቸው ሰዎች ጉዳት ላይ ያሉ ሀዘንተኞች ከመሆናቸውም በላይ ለእኛ ለባለሙያዎቹም በቦታው ላይ ያለው እያንዳንዱ ነገሮች አደጋ ያላቸውና ሕይወትን አደጋ ላይ ከመጣል ጋር የሚያወራርዱ ይሆናሉ፤ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፎ ሥራን ከግብ ማድረስ መቻል ትልቅ የአእምሮ እርካታን የሚያስገኝ ነው:: አሳዛኝ ፈታኝ የሆኑ ነገሮች የሥራው መገለጫዎች ቢሆኑም ነገር ግን ችግሮቹን ተቋቁሜ ሥራዬን በአግባቡ እየሠራሁ ነው » በማለት ያስረዳሉ::
በፍላጎታቸው ወደ ሥራው ከመጡ በኋላ መጀመሪያ የገጠማቸው ስልጠና ነበር:: አቶ ሙሉጌታ ስልጠና ሲባል ከቤታቸው እየመጡ የሚሰለጥኑ መስሏቸው ነበር:: ነገር ግን ለሶስት ወር በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ቤተሰብ እየተጠየቀ የሚሰለጠንበት መሆኑን ሲያውቁ ትንሽ ድንጋጤ ቢጤ ቢሰማቸውም ወታደር ቤት ከሰለጠኑት ጋር ሲነጻጻር የማይደራረስ በመሆኑ ራሳቸውን አረጋግተው የሚወዱትን ሙያ ባለቤት ለመሆን ጥረታቸውን ቀጠሉ::
«…….እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስገባ በቀጥታ ሥራው ላይ የሚሰማራ መስሎኝ ነበር:: ነገር ግን አስቀድሞ ከቤተሰብ ተለይተን ለሶስት ወር ያህል መሠረታዊ የሆኑ በጣም ጠቃሚ ሥልጠናዎችን ወስደናል:: እኛም የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን እየሠራን ራሳችንን ብቁ እያደረግን ሄድን::» ይላሉ::
ሥልጠናው ላይ የንድፈ ሃሳብ እውቀትን ከጨበጡ በኋላ የተግባር ልምምድ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ ጥሩ የሚባል ግንባታ ብሎም ሥራውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመሥራት የሚያስችል ብቃትን አግኝተው ስለመውጣታቸው ይገልፃሉ::
የሥራ ላይ ቆይታ
አቶ ሙሉጌታ አስፈላጊውን ሥልጠና ካጠናቀቁ በኋላ፤ በቀጥታ የገቡት ወደ ሥራ ነበር:: በዚህን የመጀመሪያ የሥራ ውሏቸው የማይረሳ አጋጣሚን አስተናገዱ:: “……..ሥልጠናውን እንዳጠናቀቅሁ ሥራ የተመደብኩት ቦሌ አካባቢ ነበር፤ ሠፈሩ ስድስተኛ ጣቢያ ይባላል፤ የእኛን ሥራ በጣም የሚገርም የሚያደርገው ከሰዓታት በፊት ሙሉ የነበረ ነገር ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ አደጋ ደርሶበት ይወድማል:: እኛ በቶሎ ከደረስን ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ሊወድም የነበረ ንብረት ይተርፋል፤ ከዚህ አንጻር ሥራውን ገና እንደገባሁ ስመዝነው እውነትም ኅብረተሰቡን ከችግር የማላቀቅ ሥራ በመሆኑ ከልቤ ተደስቼና ከፍተኛ የሆነ የሥራ ተነሳሽነት ኖሮኝ ጀመርኩት» በማለት ይናገራሉ::
አንዳንድ ጊዜ ይላሉ አቶ ሙሉጌታ፤ የሰው ሕይወትም ሆነ ንብረት ማዳን እየተቻለ በኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ፣አድራሻን በአግባቡ ባለመያዝ፣ በቶሎ ወደ ማዕከል ጥሪ ባለማድረግ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቤቶች በተቀጣጣይ ነገሮች መገንባታቸው ችግሮች እንደሚያባብሱ እና እነርሱም ብዙም መፍትሔ መስጠት ሳይችሉ ሲቀር በጣም እንደሚያሳዝናቸው ነው የሚያብራሩት::
በእሳት ማጥፋት ሥራው ላይ ከማይረሱት ገጠመኝ መካከል አቶ ሙሉጌታ « … ቦታው ቦሌ አካባቢ ነው:: የቤቶቹ አሠራርም የተጠጋጋና 16 ያህል አባወራዎች የሚኖሩባቸው ቤቶች ናቸው:: ቤቶቹ አካባቢ እሳት ተነሳባቸው:: የነገሩ ክፉነት ደግሞ አብዛኞቹ ቤቶች በእንጨት የተሰሩና በላያቸው ላይ ላስቲክ የለበሱ ደሳሳ የሚባሉ ጎጆዎች በመሆናቸው፤ ለእሳት አደጋው መባባስ ምክንያት የሚሆኑ ነዳጅና ዘይት ደግሞ በአብዛኞቹ ቤቶች ውስጥ ነበሩ:: ከሁሉም አስከፊው ደግሞ ለእሳት አደጋ ጥሪው የደረሰው በጣም ዘግይቶ ነው:: ቦታው ለንፋስ የተጋለጠ በመሆኑ ቃጠሎው ተስፋፍቶ ከቁጥጥር
ውጭ በመሆኑ ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ መውደማቸው በጣም አሳዛኝ ነበር » ይላሉ::
ሥራው በተራም ቢሆን ሳምንቱን ሙሉ የሚሰራ፤ በዓልና የእረፍት ቀናቶችን የማይመርጥ፤ የቤተሰብ እንዲሁም የማኅበራዊ ሕይወት ጊዜ የሚባለውን የሚያሳጣ ቢሆንም፤ አቶ ሙሉጌታ ግን ለሙያው ተገዢ ሆነው በቁርጠኝነትና ከልብ በመነጨ የአገልጋይነት ስሜት ስለሚሠሩ ምንም ቅሬታ እንደሌላቸው ያብራራሉ::
«……የእረፍት ቀኔ ነው፤ ወይም በዓል ነው፤ ብዬ ከሥራ ወደኋላ ብል የሰው ሕይወትና ንብረት ይወድማል:: እኔ ግን ያ ነገር ይቅርብኝ ብዬ ራሴን መስዋዕት ባደርግ ለብዙዎች መትረፍ ምክንያት እሆናለሁ:: የእኔ መኖር ለሌሎች ዋጋ የሚያስገኝ ከሆነ ኑሮዬን ከሥራዬ በታች አድርጌ እየሠራሁ ስቆይ ከፍ ያለ የህሊና እርካታ ይሰማኛል» ይላሉ::
ወደ ባህር ጠለቅ ዋናተኛ
አቶ ሙሉጌታ በእሳት ማጥፋቱ ላይ ከሰሩ በኋላ አብዛኛው ሠራተኛ ወደማይፈልገው ግን ደግሞ እጅግ በጣም አስፈላጊ ወደሆነው የባህር ጠለቅ ዋና ሙያ ለመሄድ ራሳቸውን ማሳመን ፈለጉ:: ወትሮም ቢሆን ከፍ ያለ ሰብዓዊነት የነበራቸው አቶ ሙሉጌታ ከእሳት ማጥፋቱ በበለጠ፤ በዚህ ሙያ ቢሰማሩ የብዙዎችን ሕይወት አትርፈው እንዲሁም የተጨነቁ ቤተሰቦችን አግዛለሁ ብለው በማሰብ ወደ ሥራ ገቡ::
«…….አብዛኛው ሠራተኛ ይህንን የሙያ ዘርፍ አይፈልገውም:: ምክንያቱም የእኛ ሀገር ውሃዎች አስተማማኝነታቸው ዝቅተኛ ነው:: የተበከሉ ናቸው:: የመጸዳጃ ቤትና የፋብሪካ ፍሳሾች ጋር የተገናኙ ናቸው:: ሰው የሚሳበው ደግሞ የተሻለ ክፍያና የሥራ ላይ ደኅንነትና የሥራ ቦታን መርጦ ነው:: እኔ ግን ውስጤን የሚያረካኝ ሰው በተቸገረበት ወቅት ያንን አገልግሎት ሰጥቼ እረፍት መስጠት አለብኝ የሚለው በመሆኑ የተቸገረን ለመርዳት የበኩሌን መወጣት አለብኝ በማለት እንዲሁም ለአደጋ ሥራ ሄጄ ይህንን አልችልም ላለማለት ሁለቱንም አገልግሎቶች ለመስጠት ነው::» በማለት ያብራራሉ::
ጎርፍ ሲከሰት ሐይቅ ውስጥ ሰው ሲገባ አደጋ ደረሰ ተብሎ በረው ከደረሱ በኋላ ሙያተኛ ይምጣ ብሎ ጊዜ መውሰዱ በጣም እንደሚያሳቅቃቸው የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ ይህንን ባለመፈለግም ራሳቸውን ሙሉ ለማድረግ የባህር ጠለቅ ሙያተኛን ስልጠና ወስደው የሥራ ዘርፉን ተቀላቀሉ::
በሀገር ደረጃ በዚህ ሙያ ላይ ያሉ ሰዎች ውስን ናቸው:: አቶ ሙሉጌታ ከላይ በጠቀሷቸው ምክንያቶችና ሙያው የሚያስፈልገውን ትኩረት ባለማግኘቱ አሁንም ቢሆን የባህር ጠለቅ ዋናተኛ ባለሙያ የለም ቢባል ይቀላል:: አቶ ሙሉጌታ «……..በዚህ ሙያ ላይ ያለፉ አንድ የእኛ የሥራ ባልደረባና መከላከያ ውስጥ ደግሞ አንድ ሰው ነበሩ:: እነሱም በጋራ በመሆን እኔና ሰባት ጓደኞቼን አሰልጥነውናል:: የመጀመሪያው ራስን የማብቃት ብሎም የመንሳፈፍ ስልጠና የወሰድነው በጊዮን ሆቴል ሲሆን በመቀጠል ባቡጋያ ሐይቅ በመሄድ ሰልጥነናል:: ዛሬ ላይ ግን ሥልጠናው በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ቆሟል፤ አይሰጥም::» ይላሉ::
አሁን ላይ በዘርፉ አቶ ሙሉጌታን ጨምሮ አራት ሰዎች ብቻ ያሉ ሲሆን፤ እርሳቸውም የእሳት አደጋ መኪና አሽከርካሪነት ስልጠና ወስደው እሱን ሲሰሩ እርሳቸውን የሚተካ ባህር ጠለቅ ዋናተኛ ጠፋ:: መሥሪያ ቤቱም ሁለቱንም ሥራ ጎን ለጎን እንዲሰሩ አደረገ:: አሁንም ቡድን መሪ ቢሆኑም ባህር ጠለቅ ባለሙያው ቁጥር በጣም አናሳ ስለሆነ ችግሮች በሚከሰቱና ጥሪ በሚደርስበት ጊዜ ከቢሮ ወጥተው ይሰራሉ::
አቶ ሙሉጌታ ለሙያ ከፍ ያለ ፍቅር ያላቸው ከመሆኑም በላይ በሀገር ደረጃ ባህር ጠለቅ ዋናተኞች ቁጥር በዚህን ያህል አናሳ መሆኑ ያሳስባቸዋል:: እናም እንደ መፍትሔ እርሳቸውና በሥራ ላይ ያሉ ባልደረቦቻቸው የአሰልጣኝነት ሥልጠና ተሰጥቷቸው ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ መሥራት እንደሚፈልጉ ይናገራሉ::
ባህር ጠለቅ ዋናተኝነት ሰዎች በጎርፍ ሲወሰዱ ብቻ የሚያገለግል ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ተፈላጊ ሙያ ነው ካሉ በኋላ፤ ‹‹እኛም እንደ ሀገር በአደጋ ብቻ ሳይሆን ትልልቅ ሀይድሮሊክ ፓወሮች በደለል ሲደፈኑና ሌሎችም ችግሮች ሲኖሩ ገብተን የምናጸዳና ችግሩን የምንፈታ ነን›› በማለት ይናገራሉ::
የሙያው ተግዳሮት
አንዳንድ ሥራዎች በራሳቸው በአደጋ የተሞሉና ከባድ ናቸው:: አቶ ሙሉጌታ የተሰማሩበት የድንገተኛ አደጋ ዘርፍ ደግሞ ከሁሉም የባሰ ከባድ አስቸጋሪ ራስን አደጋ ላይ ጥሎ ሌሎችን ለማትረፍ የሚደረግ ግብግብ ነውና አስቸጋሪነቱ በቃላት የሚገለጽ አይደለም::
«…….ሰው ሰራሽ የወንዞች ብክለት የሙያ ከፍተኛው አስቸጋሪ ጎን ነው:: ይህ ሲባል የተጠራቀሙ ውሃዎች ላይ የተለያዩ ኬሚካሎችን ይደፋሉ:: የመጸዳጃ ቤት ፍሳሾች ከወንዞች ጋር ይገናኛሉ:: እንደዚህ ባሉ ወንዞች ላይ ደግሞ አደጋ ደርሶ ለማውጣት በምንሄድበት ጊዜ የተበከለ ውሃ ውስጥ ለመግባት እንገደዳለን::» በማለት ይናገራሉ::
ይህም ቢሆን ግን አቶ ሙሉጌታ እስከ አሁን ድረስ በተበከሉ ወንዞቻችን ምክንያት የደረሰባቸው የጤና ችግር ባይኖርም በቀጣይ ግን ለሙያው ትኩረት በመስጠት ግብዓት በማሟላት በኩል ሁሉም ድርሻውን ቢወጣ የሚል ሃሳብ አላቸው::
ገጠመኞች
«…..ብዙ ጊዜ ያልጠበቅነው ነገር ይገጥመናል፤ ልክ ሰልጥኜ መጥቼ የመጀመሪያ ሥራዬን ለመሥራት ወጣሁ፤ አሰልጣኛችን አብሮን ነበርና ልግባ ስለው ግባ አለኝ፤ እሺ ብዬ ገባሁና ሁለት ጊዜ እንደዋኘሁ የጠለቀውን ሕፃን ልጅ አገኘሁት:: ሰው መሆኑን አረጋግጬ እዛው ትቼው ስወጣ አሰልጣኜ በመደናገጥ ምን ሆንክ ሲለኝ አገኘሁት አልኩት የት አለ ሲለኝ ውስጥ ነው ላውጣው አልኩት አሰልጣኙም እና ምን ልታደረግ ገባህ ብሎ በመሳቅ ልጁን አወጣሁት:: ይህም የመጀመሪያ ሥራዬ ነበር::» በማለት ከማይረሱት አንዱን አጋጣሚዎቻቸው ይናገራሉ::
ሌላው ደግሞ ይላሉ አቶ ሙሉጌታ «……አዲስ አበባ ውስጥ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ነው:: አንዲት ሴት ቤቷ ግማሽ አካሉ ከወንዙ ወዲህ ግማሹ ከወንዙ ወዲያ ሆኖ በእንጨት ረብራብ ላይ የቆመ ነው፤ የእኛ ተቋምም በጥናት በተደገፈ ሁኔታ ለአደጋ ተጋላጭ ነሽና መነሳት አለብሽ ብሎ በተደጋጋሚ አሳስቧታል:: ነገር ግን መሥሪያ ቤቱ ተለዋጭ ቤት የሚሰጣት መስሏት እዛው እየኖረች አንድ ቀን ቤቱ ውስጥ ከልጆቿ ጋር እንዳለች ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ ቤቱን ይዞት ሄደ፤ ለእኛም ጥሪ ደረሰን:: በሥፍራው ስንገኝ ቤቱ የለም ፍለጋ ጀመርን:: ወንዙ መዳረሻ ድረስ ሄደን ፈለግን፤ ነገር ግን ምንም ማግኘት አልቻልንም ነበር:: በማግሥቱ የአንዱን ልጇን አስከሬን አገኘን ነገር ግን ሕፃኗንና እናቷ ሳይገኙ ቀሩ ይህ በጣም ልቤን የሰበረው የሥራ አጋጣሚዬ ነው::» በማለት ያስረዳሉ::
የቤተሰብ ሁኔታ
አቶ ሙሉጌታ ራሳቸውን ለሰብዓዊነት የሰጡ ቢሆንም ቤተሰብ መመሥረት ላይም ጥሩ ሥራ ሰርተዋል:: በዚህም ትዳር መስርተው የሁለት ልጆች አባት ሆነዋል:: ባለቤታቸው ሥራቸውን የሚረዱ ከመሆናቸውም በላይ ልጆቻቸውም ሥራውን አውቀው እንደሚደግፏቸው ይናገራሉ::
መልዕክት
በሙያው ላይ በቂ ግንዛቤና ችሎታ ያስፈልጋል:: ሙያው በጣም ተፈላጊ ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት ያን ያህል ባለመሆኑ በቂ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል ለማለት ይከብዳል:: በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ሰው ዋና ቢለምድ ቢችል ቢያንስ አነስ ካሉ አደጋዎች እንኳን ራሱን ማውጣት ይችላልና እንደ ቀላል ባይታይ ደስ እንደሚላቸው ተናግረዋል::
በሌላ በኩልም ለሙያው ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ማሰልጠን የሚያስችሉ ቦታዎች ቢኖሩ፤ አሰልጣኝ ባለሙያዎችም ቁጥራቸው ቢበራከት፤ ግብዓቶች በተገቢው ሁኔታ ቢሟሉ ሥራው ከዚህ በላይ ያድጋል በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም