ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለድል የሚጠበቁበት የዱባይ ማራቶን ነገ ይካሄዳል

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደምቀው ከሚታዩባቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ ዱባይ ሲሆን፤ በውድድሩ ሰፊ የአሸናፊነት ታሪክም አላቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ 21 የዱባይ ማራቶኖች 29 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች የበላይነቱን መያዝ ችለዋል፡፡ ነገ በሚካሄደው የዘንድሮው ውድድር ላይም በሁለቱም ጾታዎች የተለመደ አሸናፊነትን ለመቀዳጀት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ሳምንታት ከሚካሄዱ የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከል በስፖርት ቤተሰቡ በስፋት የሚጠበቀው ይህ ውድድር ዝነኛ አትሌቶችን የሚያፎካክር መሆኑም ይታወቃል፡፡ ይህንን ተከትሎም አምና በዚሁ ውድድር በሴቶች አሸናፊ የነበረችውን ኢትዮጵያዊት አትሌት ደራ ዲዳን ጨምሮ ልምድ ያላቸው አትሌቶች በወንዶች በኩል ለድል የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የምን ጊዜም ተፎካካሪ የሆኑት ኬንያዊያን አትሌቶችም እንደተለመደው በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ከመሆን ባለፈ ለአሸናፊነት ብርቱ ትንቅንቅ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡

በሴቶች በኩል ለዳግም አሸናፊነት ትልቅ ግምት የተሰጣት አትሌት ደራ ዲዳ እአአ በ2018 እና 2020 የውድድሩ ተሳታፊ ብትሆንም ውጤት ርቋት መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን የአትሌቷ በተደጋጋሚ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ መሆኗ የተሻለ ልምድ እንድታገኝና ውድድሩ ከሚካሄድበት ስፍራ ጋር ይበልጥ እንድትላመድ ስላደረጋት አምና 2ሰዓት ከ21ደቂቃ ከ11ሰከንድ በመሮጥ አሸናፊ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ አትሌቷ በዓመቱ ከተሳተፈችባቸው ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የበርሊን ማራቶን ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ብታጠናቅቅም የገባችበት 2:19:24 የሆነ ሰዓት የግሏ ፈጣን በመባል ተመዝግቦላታል፡፡ የ27 ዓመቷ አትሌት ለነገው ውድድር አሸናፊ ለመሆንም መዘጋጀቷን ጠቁማለች። ‹‹የአምናው አስደሳች ውድድር ነበር፤ ይበልጥ ግን የቤተሰቤ አባል የሆነው አብዲ ቶላ በወንዶቹ ማሸነፉ ስሜታዊ አድርጎኝ ነበር›› ብላለች፡፡

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት የኦሳካ ማራቶን አሸናፊዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሄቨን ኃይሉም በውድድሩ በብርቱ ተፎካካሪነት ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ አትሌቷ እአአ በ2019 በተካፈለችበት የአምስተርዳም ማራቶን 2:20:19 የሆነ የግሏን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበች ሲሆን፤ ይኸውም ለዳግም አሸናፊነት ከምትወዳደረው የሀገሯ ልጅ ጋር በአንድ ደቂቃ የፈጠነ ሰዓት ባለቤት መሆኗ አሸናፊ የመሆን እድሏ ሰፊ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ በሌላ በኩል ከወራት በፊት የሮም ማራቶን አሸናፊ የነበረችው አትሌት ቤቲ ቼፕክዎን በሩጫው ተሳታፊነቷን ያረጋገጠች ኬንያዊት አትሌት ስትሆን ለኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶችም ፈተና እንደምትሆንባቸው ይጠበቃል፡፡

በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድርም ለመጀመሪያ ጊዜ በዱባይ ማራቶን የሚሮጡት ወርቅነህ ታደሰ እና ከበደ ቱሉ ለአሸናፊነት የተገመቱ አትሌቶች  ሆነዋል፡፡ 2:05:07 የሆነ ሰዓት ያለው አትሌት ወርቅነህ በውድድሩ ከሚሳተፉት ፈጣኑ ሲሆን፤ ከበደ ደግሞ በሰከንዶች ተበልጦ 2:05:19 ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ እአአ የ2019 አሸናፊው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጌታነህ ሞላ ደግሞ በወቅቱ የገባበት 2:03:34 የሆነ ሰዓት የቦታው ክብረወሰን ነው፡፡ በመሆኑም ለክብረወሰኑ የቀረበ ሰዓት ያላቸው ሁለቱ አትሌቶች አዲስ ሰዓት በማስመዝገብ ሌላኛውን ታሪክ እንደሚጋሩም ይጠበቃል፡፡ ይህንን ተከትሎም ከሁለቱ አትሌቶች የበላይነቱን ማን ሊይዝ ይችላል የሚለው አጓጊ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ሜዳማ በሆነ ስፍራ የሚካሄደው የዱባይ ማራቶን ፈጣን ከሆኑ የጎዳና ሩጫዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ይታወቃል፡፡በዚህ ውድድር ላይም እንደተለመደው ፈጣን ሰዓት ሊመዘገብ ይችላል የሚለው ይጠበቃል፡፡ በዱባይ አሸናፊ የሚሆነው አትሌት 80ሺህ ዶላር ሲያገኝ፤ ሁለተኛው 40ሺህ፤ እንዲሁም ሶስተኛ የሚወጣው አትሌት 20ሺህ ዶላር ይሸለማል፡፡ እስከ አስር ባለው ደረጃ የሚገቡ አትሌቶችም እንደየ ቅደም ተከተላቸው እስከ 1ሺህ 500 ዶላር ያገኛሉ፡፡

በዚህ ውድድር ለበርካታ ጊዜያት በመሳተፍና አሸናፊ በመሆን በወንዶች ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ተጠቃሽ ሲሆን፤ እአአ 2008 እስከ 2010 ድረስ በተከታታይ ለሶስት ጊዜያት የበላይነቱን በመያዝ ቀዳሚው ነው፡፡ በሴቶችም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሰለፈች መርጊያ እአአ በ2011፣ 2012 እና 2015 በማሸነፍ ታሪካዊት አትሌት ናት፡፡ ከዚህ ባለፈ ለአሸናፊነት የምትጠበቀው ደራ ዲዳ፣ ባለቤቷ ታምራት ቶላ እና ወንድሙ አብዲሳ ቶላ በመድረኩ አሸናፊነትን የተቀዳጁ የአንድ ቤተሰብ አባል ናቸው፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You