ክፋት ያልበረዘው፣ ተንኮል ያልወረሰው ማንነት፡፡ በዕንባና ሳቅ የተዋዛ ለንፁህ አንደበት የተገዛ ሰውነት። የሕይወትን ጣፋጭ/መራር ጣዕም የማይለይ፣ እሳት ውሃውን የማይመርጥ ደግ ጊዜ – ልጅነት፡፡
ዛሬ እንግዳ ሆኜ የተገኘሁት ይህን እውነታ ቀርቤ በማይበት ዕንቦቀቅላ ሕፃናት መሀል ነው፡፡ አብዛኞቹ ለማየት የሚያሳሱ ናቸው፡፡ በአግባቡ የተያዙ፣ በቆንጆ ልብሶች የተዋቡ ንጹህ ሕፃናት፡፡ ልብሳቸው ብቻ ሳይሆን ውስጣቸው ጭምር እንደ ነጭ ወረቀት ጎልቶ የሚታይ ንፁሃን መሆናቸውን ነጋሪ አላሻኝም፡፡
በእናቶቻቸው ዕቅፍ ያሉትን ጨምሮ ከወዲያ ወዲህ የሚሯሯጡ ልጆች ቤቱን አድምቀውታል። በቻልኩት አቅም የሁሉንም ገጽታ ለማስተዋል ሞከርኩ፡፡ አብዛኞቹ ጸጉራቸው ትኩስ መላጣ በሚባል መልኩ ሙልጭ ብሎ ተላጭቷል፡፡ በሁሉም ገጽታ ፍጹም በቃል የማይገለጽ የዋህነት ይነበባል፡፡
ውስጤ አንዳች ነገር ያቀብለኝ ይዟል፡፡ እነዚህ ልጆች ስለነገ ብዙ ናቸው፡፡ ሀገር በእነሱ ላይ ብሩህ ተስፋን ትጥላለች፡፡ የራሳቸው፣ የቤተሰቦቻቸው ድካም ወደፊት የማንነታቸው መሠረት ይሆናል። ከእነሱ መሀል ስለነገ መድረሻው አስቀድሞ የሚያልም አለ፡፡
ዶክተር፣ ፓይለት፣ ኢንጂነር፣ መምህር፣ ሀገር ጠባቂ ወታደር መሆን የሚሻ ብዙ ነው፡፡ አሁንም እያንዳንዱን ሕፃን በአትኩሮት ማስተዋል ይዣለሁ። በገጽታቸው ላይ የተለያየ መልክ እያየሁ ነው፡፡ የሳቀ፣ ያኮረፈ፣ የተከዘ፣ ዝም ያለ ፊት ከፊቴ ይመላለሳል፡፡
ዛሬ የገና ዋዜማ ነው፡፡ በዚህ ቀን በርካቶች ስለበዓሉ ስጦታ ይለዋወጣሉ፡፡ ማግስቱን ለሚከበረው ዓመት በዓል ቤታቸውን ያስጌጣሉ፣ የገናውን ዛፍ በድምቀት ያስውባሉ፡፡ እነዚህ ሕፃናትና ወላጆቻቸው ግን ዛሬ በቤታቸው አልተገኙም፡፡ ልጆቹ እንደ እኩዮቻቸው፣ እናቶቻቸውም እንደ ጎረቤቶቻቸው አውደ ዓመትን ለማክበር ጉድ ጉድ የሚሉ አልሆኑም፡፡
እነሱ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው፣ በዚህ ስፍራ የተገኙት በምክንያት ነው፡፡ አሁን ወላጆቻቸው ስለ ልጆቻቸው መኖር ግድ ይላቸዋል፡፡ ልጆቹ በጤና ዘልቀው ተስፋቸው ይሰምር ዘንድ ዛሬን ከቤትና ቀያቸው ሊርቁ ተገደዋል፡፡ እነዚህ ሕፃናትና ወላጆቻቸው በትናንትናው የሕይወት መንገድ ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጠዋል፡፡ ስለነገ ግን ከቶውንም ተስፋ አይቆርጡም፡፡
እነሆ በ“ማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ” ቅጥር ግቢ ተገኝቻለሁ፡፡ የገና በዓል ዋዜማን ከካንሰር ሕሙማን ሕፃናት ጋር እያከበርኩ ነው። በዝግጅቱ ሕፃናቱንና ወላጆቻቸውን ጨምሮ የግቢው ማኅበረሰብ፣ የሶሳይቲው ወዳጆችና ሌሎችም እንግዶች በአካል ተገኝተዋል፡፡
ዕለቱን አስመልክቶ ዋዜማውን ከልጆቹ ጋር ለማሳለፍ በስፍራው የተገኙት የማርዮት ሆቴልና አፓርትመንት ሠራተኞች ለልጆቹ የገና ስጦታን ይዘዋል፡፡ በዓሉን የሚመጥኑ ጣፋጮችንም አዘጋጅተዋል፡፡ በዝግጅቱ የታደሙት ወላጆች የዕለቱ ልዩ እንግዶች ናቸው፡፡ እንደ ወጉ ዓውደ ዓመቱን በቤታቸው ባያከብሩም እነሱን አክብሮ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!!!›› የሚል ወገን ማግኘታቸው አስደስቷቸዋል፡፡
ዝግጅቱ በድምቀት ተጀምሯል፡፡ በመሰብሰቢያ አዳራሹ ግድግዳ ላይ የተሰቀሉት ቀይና ነጭ ፊኛዎች፣ መብራቶችና ደማቅ ጌጣጌጦች ለበዓሉ ልዩ ውበትን አላብሰዋል፡፡ ጣፋጮቹ፣ ከረሜላዎቹና ስጦታዎቹ በዓይነት ተደርድረዋል፡፡
ልጆቹ ይህ ሁሉ የሆነው ለእነሱ መሆኑን እያወቁት ነው፡፡ አንዳንዶቹ በተኮላተፈ ጣፋጭ አንደበታቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ሀፒ በርዝደይ ∙ ∙ ∙” (መልካም ልደት) እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ሁሉም ፍጹም ጨዋነት በተሞላው ሁኔታ ከእንግዶቹ ጋር እያሳለፉ ነው፡፡
የማርዮት ሆቴልና አፓርትመንት ሠራተኞች ላለፉት ስድስት ዓመታት ከሶሳይቲው ጋር በተለያዩ ተሳትፎዎች አሳልፈዋል፡፡ የአንድ ቀን ደመወዛቸውን ከማበርከት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ በማድረግም እስካሁን ከካንስር ከሕሙማኑ ጎን አልተነጠሉም፡፡
የማርዮት ሠራተኞች ሁሌም እንደ ቅርብ ቤተሰብ ናቸው፡፡ ከጓዳ፣ ከማጀቱ የጎደለውን አይተው ይሞላሉ፡፡ የገበታው በረከት ለመሆንም እጃቸው ሰስቶ አያውቅም፡፡ ለተቋሙ አስፈላጊ የሆኑ የሥልጠና ድጋፎችን ማበርከት ልማዳቸው ነው፡፡ እንደ ዛሬው ዓውደ ዓመት በሆነ ጊዜም ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!!!›› ለማለት ቀዳሚዎች ናቸው፡፡
የማርዮት ሆቴልና አፓርታማ መርህ ሁሌም ማኅበረሰቡን መሠረት ያደርጋል፡፡ በተለይ ደግሞ በሕመም ለተጎዱና ልዩ ድጋፍ ለሚያሻቸው ወገኖች ያለው እይታ ለየት ይላል፡፡ ሠራተኞቹ ሁሌም በዚህ ስፍራ በተገኙ ጊዜ ፍቅራቸው ከፊታቸው ይነበባል፡፡ ትህትናን በማሳየት ‹‹ከጎናችሁ ነን›› ማለትን ያውቁበታል፡፡ ከጊዜያቸው ጊዜ ቀንሰው፣ ከኪሳቸው ማካፈል የዘወትር መለያቸው ነው፡፡
የማርዮት ሠራተኞች ለበዓል ያመጡትን ስጦታ ለማበርከት በሶሳይቲው አዳራሽ በተገኙ ጊዜ ወይዘሮ ሳምራዊት ስለ እሷና ስለ ሥራ ባልደረቦቿ መልዕክት አስተላለፈች፡፡ ሳምራዊት የማርዮት ሠራተኛ እንደ መሆኗ በንግግሯ ብዙኃኑን ወክላለች፡፡
ሳምራዊት እንዳለችው እሷና ሌሎች ሠራተኞች ወደ ማቲዎስ ሶሳይቲ በመጡ ጊዜ በተሰሩት ተግባራት በእጅጉ ተደስተው ነበር፡፡ በወቅቱ ይህን የመረዳዳት ዕድል በማግኘታቸውም ዛሬን አብረው ተጉዘዋል፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ለድርጅቱ ያላቸው አክብሮትና ምስጋና በእጅጉ የላቀ ነው፡፡
ሳምራዊት እንደምትለው በመስጠትና መቀበል መካከል ባለው ሂደት መመስገን ያለበት ሰጪው ሳይሆን ተቀባዩ ነው፡፡ “ለምን?” ከተባለ ደግሞ የእርካታና ደስታው ውጤት ሲለካ ሚዛኑ የሚደፋው በሰጪው አእምሮ ላይ ስለሆነ ነው፡፡
ከማቲዎስ ወንዱ ጋር የነበረው የዓመታት ጉዞ መሠረቱም ይኸው ነው፡፡ ሁሉም ሠራተኛ በሚባል መልኩ ለድርጅቱ አቅምና ጉልበት ለመሆን ወደኋላ ብሎ አያውቅም፡፡ የዛሬው የገና በዓል ስጦታና ቆይታ በዚህ ብቻ አይቋጭም፡፡ ወደፊት በሚኖሩ መሰል አውደ ዓመቶችና አስፈላጊ ቀናት ሁሉ የማርዮት አጋርነት አይጓደልም፡፡
በስፍራው ተገኝተው እንግዶቹን የተቀበሉት የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መስራችና ባለቤት አቶ ወንዱ በቀለ ስለተደረገው ስጦታ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ከንግግራቸው ለማወቅ እንደተቻለው ማርዮት ማለት ሸራተንን ጨምሮ የሚያስተዳድርና በዓለም ላይ ወደ ስምንት ሺህ ሆቴሎች ያሉት ታዋቂ ድርጅት ነው፡፡
በአዲስ አበባው ማርዮትና ሸራተን ሆቴል ለካንሰር ሕሙማን ገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆን የርዳታ ሳጥን እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ ለዚህ ሳጥን መቀመጥ ፈቃድ የተሰጠው ብቸኛ ድርጅት ደግሞ የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ብቻ ነው፡፡
የማርዮት ሠራተኞች ከደመወዛቸው በማሰባሰብ ለድርጅቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ይገዛሉ፡፡ በሆቴሉ መጠቀም ባስፈለገ ጊዜም ክፍያውን በግማሽ በመቀነስ ትብብራቸውን ያሳያሉ፡፡ ዛሬ ደግሞ ከግቢው የካንሰር ታማሚ ሕፃናት ጋር የገና በዓል ዋዜማን ለማሳለፍ ተገኝተዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት በዓለማችን ወደ 200 የሚጠጉ የካንሰር አይነቶች አሉ፡፡ ካንሰር አስቀድሞ ከተደረሰበት መፍትሔው ይገኛል፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን የሕፃናትን ካንሰር አስቀድሞ መከላከል አለመቻሉ ነው፡፡ በተለይ እኛን በመሰሉ ሀገራት ሕመሙ ባጋጠመ ጊዜ ሕይወት ፈተና ይሆናል፡፡ እንደ አቶ ወንዱ ገለጻ ካንሰር በሕፃናት ላይ መገኘቱ አስቀድሞ ከታወቀ ግን አክሞ ለማዳን ያለው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ ሆኖ የቀረበው ወጣቱ አለኸኝ ነበር፡፡
አለኸኝ ዕለቱን በሶሳይቲው ተገኝቶ በበዓል ዋዜማው ተሳትፏል፡፡ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በዕጢ ካንሰር መያዙ ሲታውቅ ገና የአስር ዓመት ልጅ ነበር፡፡ ኑሮው በገጠር የሆነው ሕፃን በወቅቱ ቤተሰቦቹ ስለሕመሙ ምንነትና ክብደት አንዳች የሚያውቁት መረጃ እንዳልነበረ ያስታውሳል፡፡
ዛሬ የሃያ አንድ ዓመት ወጣት የሆነው አለኸኝ በሕይወት ውጣ ውረድ ብዙ አሳልፏል፡፡ ለሕክምና ከጎጃም አዲስ አበባ ሲመላለስ መንገዶች አልጋ በአልጋ አልነበሩም፡፡ በየጊዜው የሚወስደው ‹‹ኬሞቴራፒ›› ከባድ ቢሆንም ከትምህርት አላገደውም፡፡ በጥንካሬ ተጉዞ ዘጠነኛ ክፍል ደርሷል፡፡
አለኸኝ አንድ እግሩ ላይ የተገኘውን የእጢ ካንሰር ለመታከም ከሚኖርበት ወረዳ ወደ ደብረማርቆስ፤ ከዛም ባህር ዳርና አዲስ አበባ ተመላልሷል፡፡ ሕክምናው በቋሚነት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሆነ ጊዜም በዘመድ ቤት እያረፈ፣ ጤናውን ሲከታተል ቆይቷል፡፡
የማቲዎስ ወንዱ ሶሳይቲ ቤተሰብ እስኪሆን ድረስ እንግልቱ ቀላል አልነበረም፡፡ አንዳንዴ ቤተሰቦቹ ታክሞ ይድን አይመስላቸውም፡፡ ሁሌም ለትራንስፖርት ሊሰጡት አይፈልጉም፡፡ ለእነሱ የእሱ ከገጠር አዲስ አበባ መመላስ ዋጋ ቢስ ነው፡ ፡ ሁሌም በንግግራቸው ከቤቱ አርፎ እንዲቀመጥ ይመክሩታል።
የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ አለኸኝን የመሰሉ ታካሚዎች መኖራቸውን ባወቀ ጊዜ ሙሉ የትራንስፖርት ፍጆታቸውን ይሸፍናል፡፡ አስፈላጊ የሚባሉ መድኃኒቶችን በመግዛትም ሸክማቸውን ያቀላል፡፡ የላብራቶሪና፣ የሲቲስካን ወጪዎችን በተጠየቁ ጊዜ ሁሌም ከጎናቸው ነው፡፡
ድርጅቱ ሆስፒታል ተኝተው መታከም ላለባቸው ሕሙማን አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ወደኋላ አይልም፡፡ ከአጋር ድርጅቶች በሚያገኘው እገዛም በትምህርት ዓለም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ተማሪዎች ያስተምራል፡፡ አቶ ወንዱ እንደሚሉት ወደፊት ይህ ሶሳይቲ ብዙ ዕቅዶችን ነድፏል፤ ራዕይም ሰንቋል፡፡
‹‹ጤናማ አፍሪካ›› በሚል ስያሜ በሚቋቋመው ደሀ ተኮር ፕሮጀክት በሽታን አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበትና ጤናማ ኑሮን መምራት የሚታሰብበትን ጉዳይ ዕውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
ዕለቱን ከሕፃናቱ ጋር ዋዜማውን ለማሳለፍ ከተገኙት እንግዶች መካከል ወጣት አልሻዳይ አንዷ ነች፡፡ አልሻዳይ ኑሮዋ በሀገረ አሜሪካ፣ ሺካጎ ከተማ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለእረፍት በመጣች ጊዜ በአንዲት ባልንጀራዋ ምሪት ድርጅቱን በአካል ተገኝታ የማየት አጋጣሚውን አግኝታለች፡፡
የኤልሻዳይ ፍላጎት ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ሁሌም በሰዎች መሀል ተገኝታ ስሜታቸውን መጋራት፣ ችግራቸውን መካፈል ትወዳለች፡፡ በዚህ ሰፍራ ባየችው ነገር ሁሉ ደስተኛ ነች፡፡ ወደፊት በሶሳይቲው ስላገኘቻቸው ልጆች የያዘችውን ህልም በተግባር የመፍታት ዕቅድ አላት፡፡
በስፍራው ተገኝተው ለሕፃናቱ ፍቅር ከለገሱት እንግዶች መካከል ርብቃና ጓደኞቿ ይገኙበታል። እነ ርብቃ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው። በማቲዎስ ወንዱ የካንሰር ሶሳይቲ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች በመሆን ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡
በእነ ርብቃ እሳቤ ሰዎች ከመቀበል ይልቅ በመስጠት የሚያገኙት እርካታ ይበልጣል፡፡ ብዙዎች ይህን ባደረጉ ጊዜ ስለሕይወት ያላቸው ዕይታ ይቀየራል፡፡ እነ ርብቃ በዚህ መንገድ መጓዝ ከጀመሩ ወዲህ ውስጣቸው ያደረው ሰላምና እፎይታ ከሁሉም የላቀ ነው፡፡
እንደ በጎ ፈቃድ አገልጋይነታቸው ሁሌም በስፍራው በደረሱ ጊዜ ውስጣቸው ሰላምና ፍቅር ያገኛል፡፡ ዘወትርም በመስጠት ይጠቀማሉ፣ በመስጠት ይደሰታሉ፡፡ ይህ እውነት ወደ እነሱ ይመላለስ ዘንድም በየጊዜው ከበጎነት አይርቁም፡፡
እንደ አቶ ወንዱ በቀለ ተሞክሮም ሰዎች ከእጃቸው ያለውን በሰጡ፣ ባበረከቱ ቁጥር ጥቅሙን የሚወሰዱት ራሳቸው ይሆናሉ፡፡ ለዚህ እውነታም ምስጋናውን ማድረሰ የሚኖርባቸው ተቀባዮች ሳይሆኑ ሰጪዎች ሊሆኑ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በመስጠት የሚገኘውን ደስታና ርካታ በመውሰድ ቀዳሚዎች ናቸው፡፡
የገና በዓል ዋዜማን ከሕፃናቱ ጋር ለማሳለፍ የተገኙትን እንግዶች ጨምሮ የማቲዎስ ወንዱ ሠራተኞች ዕለቱን አስመልክቶ ለልጆቻቸው ስጦታዎችን አበርክተዋል፡፡ በስጦታው ወቅት ተቀባዮቹ ስማቸው በተጠራ ጊዜ የነበረው አቀባበል ይለያል፡፡ ልጆቹ ከነበረቡት ተነስተው ስጦታቸውን በሚቀበሉበት ወቅት ሲባል የነበረውን የእርካታ ትርጓሜ በእውን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ልጆቹ ስጦታቸውን ሲወስዱ የታየባቸው ፈገግታ ከተለመደው የልጅነት ስሜት የዘለለ አልነበረም። በስፍራው የነበረው ታዳሚ ግን በርግጠኝነት ደስታ የሚሸመተው ከተቀባዩ ሳይሆን ከሰጪው ልቦና መመንጨቱን በተግባር አይቶ አረጋግጧል፡፡
ይህን እውነት ደግሞ ከልጆቹ ወላጆች ጥልቅ ምርቃትና ደማቅ ፈገግ ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡ አዎ! ይህ ሀቅ በመስጠት ለራስ የሚተርፍ እውነተኛ የደስታን ስሜትን መሸመት እንደሚቻልም ያረጋግጣል፡፡ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ምዕመናን በሙሉ መልካም የገና በዓል ይሁን!!!
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም