ልምድና ዕውቀትን በማጣመር የተጀመረ የንግድ ሥራ

ወላጅ አባቷ ረጅሙን የሕይወት ጉዟቸውን በተለያዩ የንግድ ሥራዎች አሳልፈዋል፡፡ ልጆቻቸው ግን ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያደርጉ በማሰብ በከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር አሳድገዋል፡፡ እሳቸው ከተሰማሩባቸው የንግድ ሥራዎች መካከል አንዱ በአነስተኛ መጭመቂያ ማሽን ዘይት አምርቶ መሸጥ ነበር፡፡ ‹‹በወቅቱ አባቴ የዘይት መጭመቂያ ማሽን በመጠቀም የምግብ ዘይት ከቅባት እህሎች አምርቶ ለገበያ ሲያቀርብ አስታውሳለሁ›› የምትለው የዕለቱ እንግዳችን ወይዘሮ መርየም ሳልህ ትባላለች፡፡

ከነጋዴ ቤተሰብ የተገኘችው ወይዘሮ መርየም ከትምህርትና ከቅጥር ሥራ በኋላ በወጪና ገቢ ንግድ ተሰማርታ መድኃኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ታስመጣለች፤ በምትኩ ደግሞ ማሾን ጨምሮ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ መድኃኒት ለማስመጣት የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ታሟላለች፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ሥራ በተለይም ኤክስፖርት ንግድ ብዙ ውጣ ውረድ ያለበትና እጅግ ፈታኝ ቢሆንም መሥራት የግድ ነው›› የምትለው ወይዘሮ መርየም፤ የንግድ ሥራን ከወላጅ አባቷ የወረሰች ስለመሆኑ ትናገራለች፡፡

ገና ልጅ እያለች ጀምሮ በንግድ ሥራ እንደምትሰማራ ታውቅ እንደነበርና ጓደኞቿም ወደፊት ነጋዴ እንደምትሆን ያመላክቷት እንደነበር የምታስታውሰው ወይዘሮ መርየም፤ በእሷ የንግድ ሕይወት ውስጥ የወላጅ አባቷ ድርሻ ትልቅ መሆኑንም ትናገራለች፡፡

እሷ እንዳለችው ፤ወላጅ አባቷ ሳይማሩ የተማሩ ጎበዝ ነጋዴ ነበሩ፡፡ ዘይት ጨምቀው ከመሸጥ ጀምሮ በሸቀጥ ሱቅ፣ በመኪና መለዋወጫና በሌሎችም የንግድ ሥራዎች ተሰማርተው ሰርተዋል፡፡ አነስተኛ በሆነች የዘይት መጭመቂያ ዘይት ጨምቀው በሚነግዱበት ወቅት ከመንግሥት በተጣለባቸው ከፍተኛ የግብር ጫና ምክንያት ማሽኑን ነቅለው ከሥራው ወጥተዋል። ቀጥለውም በሸቀጥ ንግድና በሌሎች የንግድ ሥራዎች የተሰማሩት ወላጅ አባቷ፣ ብርቱና ታታሪ ነጋዴ እንደነበሩ ትገልፃለች፡፡

የንግድ ሥራን ከወላጅ አባቷ እየተመለከተች ያደገችው ወይዘሮ መርየም፤ ‹‹ከንግድ ሥራው በተጨማሪ ብዙ የሕይወት ልምዶችንም ጭምር ከወላጅ አባቴ ተምሬያለሁ። ለዚህም ምክንያቱ ከሌሎች ልጆች በተለየ ሁኔታ አባቴን ስለምቀርበው ነው›› ትላለች፡፡ ከወላጅ አባቷ ያገኘችውን ልምድና ዕውቀት ተጠቅማ ከትምህርት በኋላ በሁለት ተቋማት ተቀጥሮ የመሥራት ዕድል የገጠማት ቢሆንም በተለይም ሁለተኛውን ሥራዋን የለቀቀችው ሳትወድ በግድ እንደነበር አጫውታናለች፡፡

ወይዘሮ መርየም በአዲስ አበባ ከሚገኘው የንግድ ስራ ትምህርት ቤት በሴክሬቴሪያት ሳይንስ እና በቢሮ አስተዳደር ዲፕሎማዋን፣ ሥራ ላይ እያለች ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝታለች፡፡ ትምህርቷን በከፍተኛ ውጤት ታጠናቅቅ እንደነበር ያስታወሰችው ወይዘሮ መርየም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀጥራ የሠራችው ኦሜዳድ በተባለ ድርጅት ውስጥ ነበር፡፡ በዚሁ ድርጅት ውስጥ የነበራት የሥራ ቆይታም ከአስር ወራት በላይ መሻገር አልቻለም፡፡

ሁለተኛውን የሥራ ዕድል ያገኘችው ደግሞ ከአንጋፋውና የአገር ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገዱ በነበራት የስራ ቆይታ ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ ትሄዳለች›› እንደሚባለው ዝቅተኛ ከሚባለው የሥራ መደብ ጀምራ እያደገች በበርካታ የሥራ ኃላፊነቶችም ሰርታለች፡፡

ለአስራ አምስት ዓመታት በቆየችበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ከብዙዎች በመማር ልምድና ዕውቀት በመቅሰም ራሷን አብቅታለች፡፡ ሥራዋን በሙሉ አቅሟና በትጋት ትሰራ እንደነበር ነው ያስታወሰችው፡፡

ይሁንና ባጋጠማት የቤተሰብ ችግር ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ ከሥራ ውጭ ሆና ትቆያለች፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለረጅም ጊዜ ጠብቋት እንደነበር ገልጻ፣ እሷም ሳትፈልግ፣ ተቋሙም ማሰናበት የግድ ሆኖበት ተለያይተዋል፡፡

የአገር ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተተሰናበተች ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከችግሯ ማገገም ሰትችል ተመልሳ ወደ ቅጥር መሄድ እንደሌለባት በማመን የግል ሥራ መጀመር እንዳለባት ትወስናለች፡፡ በንግድ ስሙ ሜርሲ ሜድ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተባለ ድርጅት መስርታ በአስመጪና የላኪነት ንግድ ሥራ ተሰማራች፡፡

በወቅቱ ወደ ግል ሥራዋ ለመምጣት ዙሪያ ገባዋን ስታማትር ቆይታ ወደ አስመጪነት ያቀናችው ወይዘሮ መርየም፤ ለሥራ ያላትን ፍላጎትና ቅልጥፍና እንዲሁም አስተዳደር ላይ በነበራት ብቃት ብዙዎች ያውቋታል፡፡ በመሆኑም ብዙዎች የግል ሥራዋን ስትጀምር አብረዋት ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት እንደነበራቸው አጫውታናለች፡፡

የሜርሲ ሜድ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መርየም፤ የንግድ ሥራዋን ለመጀመር መነሻ ካፒታል ያገኘችው ከባንክ በመበደር ነበር፡፡ በወቅቱ የግል ባንኮች የቤት መግዣ ብድር ያበድሩ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ከአዋሽ ባንክ ባገኘችው ብድር የመድሃኒት አስመጪነት ፈቃድ በማውጣት የንግድ ሥራዋን ‹‹ሀ›› ብላ የጀመረችው የዛሬ አምስት ዓመት ነው፡፡ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎችን በመቅጠር የጀመረችው የመድሃኒት አስመጪነት ሥራ፤ እጅግ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን በወቅቱ የሚፈልግ በመሆኑ ሥራውን ፈታኝ ያደርገዋል ትላለች።

መድሃኒቶቹን ከአገር ውስጥ አምራቾችና ከውጭ በማስመጣት ለገበያ የምታቀርበው ወይዘሮ መርየም፤ አንድ መድሃኒት ሲጠፋ አልያም በቶሎ ወደ ሀገር ውስጥ ሳይገባ ሲቀር ውስጧ እጅጉን እንደሚያዝንም ትናገራለች፡፡ በመዘግየት ሂደት ውስጥ መድሃኒት አጥተው ሕይወታቸው የሚያለፍ ብዙ ሰዎች እንዳሉም ጠቅሳ፣ መድሃኒት ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት እንደሚፈልግ ትገልጻለች፡፡

እሷ እንደምትለው፤ በአገር ውስጥ የሚመረቱ የመድኃኒት አይነቶችን እንዲሁም ከውጭ የሚመጡ የተለያዩ መድሃኒቶችን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥና በክልል ከተሞች ለሚገኙ ለጅምላ አከፋፋዮች ታስረክባለች። ከጅምላ አከፋፋዮች ደግሞ ቸርቻሪዎች ተረክበው በየአካባቢው በሚገኙ ፋርማሲዎች አማካኝነት መድሃኒቱ ማህበረሰቡ ጋር እንዲደርስ ይደረጋል፡፡

ማህበረሰቡ እንዲጠቀምባቸው ወደ ገበያ የሚቀርቡት የመድሃኒት አይነቶች በየጊዜው የሚፈለጉ ናቸው፤ ከምታቀርባቸው መዳህኒቶች መካከል ማህበረሰቡ በየእለቱ የሚገለገልባቸው እንደ ስሪንጅ፣ ግላቭ፣ ማስታገሻ መድሃኒቶች፣ የስኳር እንዲሁም የደም ግፊት መድሃኒቶች ይገኙበታል፡፡

ወይዘሮ መርየም የህክምና ትምህርት ባይኖራትም በልምድ ከባለሙያዎች ጋር ባላት ቀረቤታና ለነገሮች በምትሰጠው ከፍተኛ ትኩረት መድሃኒቶችን ለይታ እንደምታውቅ ትናገራለች፤ ሥራውን ተላምዳ በተነሳሽነትና በጥንቃቄ እየሠራች መሆኗን አጫውታናለች፡፡

መርየም እንዳለችው፤ መድሃኒት የማስመጣት ሥራዋ ተጠናክሮ የቀጠለ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በርካታ የተለያዩ መድሃኒቶችን ከአገር ውስጥ አምራቾችና ከውጭ በማስመጣት ለክልል ከተሞች ጭምር ተደራሽ ታደርጋለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተወሰኑ አካባቢዎች በተፈጠረው የሰላምና ጸጥታ ችግር ምክንያት መንገዶች ተዘጋግተው መድሃኒቶች በአግባቡና በፍጥነት እየደረሱ አይደለም የምትለው ወይዘሮ መርየም፤ ይህም በሥራው ላይ ከሚያሳድረው ጫና ባለፈ እጅጉን የሚያሳስባትና የሚያሳዝናት ጉዳይ መሆኑን ተናግራለች፡፡

መድሃኒት ማለት ሰዎች ለሚገጥማቸው የጤና ችግር መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸለች፤ በዚህ ላይ በመስራቷም እርካታ ይሰማታል፣ በተመሳሳይ ደግሞ መድሃኒቱ እያለ በሰላምና ጸጥታ ችግር ምክንያት ሰዎች መድሃኒት አጥተው ሕይወታቸው ሲያልፍና ሲሰቃዩ ማየትና መስማቷ ደግሞ በእጅጉ እንዲሰማት አድርጓታል። ያም ቢሆን ተፈላጊ መድሃኒቶችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚቻላትን ሁሉ እየደረገች መሆኗን ወይዘሮ መርየም ጠቅሳ፣ በተለይም መድሃኒቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቃለች፡፡ ክትትል፣ ትኩረትና ሰላም ይፈልጋሉ ትላለች፡፡

መድሃኒቶችን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት ባለፈም በኤክስፖርት ሥራ ላይ መሰማራት መቻሏን ያጫወተችን ወይዘሮ መርየም፤ የኤክስፖርት ሥራ በኪሳራ የሚሰራ መሆኑን ጠቅሳ፣ ኪሳራው ግን በውጭ ምንዛሬ እንደሚካካስ ገልጸለች፡፡ መድሃኒቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘትም ማሾን (የእህል ዘር) ጨምሮ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመግዛት ወደ ውጭ ገበያ ትልካለች፡፡

እሷ እንዳለችው፤ በኤክስፖርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ ለሚመጣው ዕቃ ጠቃሚ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኤክስፖርት በኪሳራም ቢሆን ይሰራል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር አንድ በወጪ ንግድ የተሰማራ ነጋዴ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ልኮ ከሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ 30 በመቶ ያህሉን ብቻ በቀጥታ እንዲጠቀም ነበር በመንግስት በኩል የሚፈቀድለት፡፡ 70 በመቶው በመንግሥት አሰራር ውስጥ አልፈው ነበር የሚጠቀሙት፡፡

ይህ አሰራር የኤክስፖርት ንግዱ አትራፊ እንዳይሆን አድርጎት መቆየቱን ነው መርየም ያስታወሰችው። በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥት አሰራሩን አሻሽሎ 50 በመቶውን የውጭ ምንዛሬ ነጋዴው በቀጥራ ራሱ እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጻለች፡፡

ይህ አሰራር መንግሥት ካለባት የዶላር እጥረት የመጣ መሆኑን ጠቅሳ፣ አሰራሩን ነጋዴውም እንደሚቀበለው ገልጻለች፡፡ ነገር ግን መድኃኒት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ቢባልም በሚፈለገው ልክ አይደለም ትላለች፡፡

ለመድኃኒት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ማግኘት እንደማይቻልም ገልጻለች፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መድሃኒቶች በከፍተኛ ወጪ እንደሚገቡ አመላክታ፣ የውጭ ምንዛሬው ተገኝቶ መድሃኒቶቹ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላም መድሃኒቶቹ ታክስ የሚደረጉበት ላይ ችግር እንዳለም ጠቁማለች፡፡ አንድ አስመጪ በሰጠው ዋጋ ሁሉም አስመጪ መቀረጣቸው የዘርፉ ሌላው ችግር መሆኑን አመልክታለች፡፡

እሷ እንዳስገነዘበችው፤ መድኃኒት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውና ጊዜው ካለፈ የሚያደርሰው ጉዳት አደገኛ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ያሻዋል፡፡ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደመምጣቱ መድሃኒት አስመጪዎች ተናብበው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለአብነትም አንድ መድሃኒት በአገር ውስጥ ጠፋ ከተባለ ሁሉም መድሃኒት አስመጪዎች ተረባርበው ያስመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ መድሃኒቱ በአገሪቷ ይጥለቀለቃል፡፡ የተትረፈረፈ ነገር ደግሞ ዋጋው መውረዱ አይቀርምና በዚህ ምክንያት ለመድሃኒቱ ከወጣው ወጪ ባነሰ ዋጋ ለመሸጥ መገደድ ይመጣል፤ ይህም ሌላኛው የዘርፉ ተግዳሮት ነው፡፡

ልጅ እያለች ጀምሮ በንግድ ሥራ መሰማራት እንደምትችል የሚሰማት ወይዘሮ መርየም፣ ‹‹ነጋዴ መሆን ብችልም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ሥራ መሥራት እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ነው›› ትላለች፡፡ ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለነጋዴው የተሰጠው ስም ጤናማ እንዳልሆነም ጠቅሳ፣ ነጋዴው በሄደበት ሁሉ በአግባቡ አይስተናገድም፤ ሁሉም እንደ አጭበርባሪ ይታያል ስትል ትገልጻለች፡፡ ነጋዴው ብዙ ዋጋ ከፍሎና ብዙ ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ እንደሚሰራም አስታውቃ፣ በተለይም ገቢ ሰብሳቢ ተቋም የግሉን ዘርፍ በአግባቡ ሊያገለግል፣ ሊያደምጥ፣ ሊረዳና ሊንከባከብ እንደሚገባ አመላክታለች፡፡

በአገር ውስጥ መድሀኒት የማምረት ሃሳብ ያላት ወይዘሮ መርየም፤ በአሁኑ ወቅት ለ30 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች፤ በቀጣይም ሥራዋን በማስፋት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር ፍላጎት አላት፡፡

አትክልት የመትከልና የመንከባከብ ልምድ እንዳላትም ጠቅሳ፣ በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም ነው የነገረችን፡፡ ግብርና የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ጠቅሳ፤ በዘርፉ ለመሰማራት ያላትን ዝግጁነት ገልጻለች፡፡

ነግዶ ለማትረፍም ሆነ ዘርቶ ለመቃም፤ ወልዶ ለመሳምና ወጥቶ ለመግባት ሰላም መተኪያ የለውም ያለችው ወይዘሮ መርየም፣ እያንዳንዳችን ለሀገር ሰላም የበኩላችንን እናዋጣ የሚል መልዕክቷንም አስተላልፋለች።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You