‹‹የበዓሉ ዋና ዓላማ ልምድ መፈጸም ሳይሆን እግዚአብሔር ያደረገልንን መልካምነት በተግባር ማሳየት ነው››መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል በመምሪያ ኃላፊ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ

የዛሬው የዘመን እንግዳችን መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ ነው፤ ይሁን እንጂ እድገታቸው አዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ እርሳቸው፣ ዘመናዊውንም ሃይማኖታዊውንም ትምህርት ተምረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚሰሩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያሪክ የሊቃውንት ጉባኤ ውስጥ ነው፡፡ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት ያገለግላሉ፡፡ ሆኖም ትምህርታቸውም ሥራቸውም ሃይማኖቱ ላይ ያተኩራል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቲዮሎጂ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ያጠናቀቁት በቋንቋ ሥነ ልሳን በሙዚየም ጥናት ነው። አሁን ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ፊኒሎጂ የሚባለውን የትምህርት ዘርፍ በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡

መምህር ዳንኤል ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በጥናትና በተለያዩ ሥራዎች ላይም ተሳትፎ አላቸው። በምሥራቅ አፍሪካ የማኅበረሰብ ጥናት ቡድን ውስጥ አባል በመሆን ሰርተዋል፡፡ የኢትዮጵያንና ከኢትዮጵያ ጋር ትስስር ያላቸውን የመካከለኛና የሩቅ ምሥራቅ እንዲሁም የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ታሪክ ጋር በተያያዘ፤ በባህልና በሥነ ጥበብ ዙሪያ መጣጥፎችንም በማዘጋጀት ለሕትመት አብቅተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዋና ሙዚየም ቤተመዛግብትን አደራጅተዋል፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍም ሃይማኖታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ በማቋቋምና በመምራት ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ውስጥም እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ መምህሩ፣ በሃይማኖቱ ውስጥ ሰፊ አበርክቶ ያላቸው ናቸው፡፡ እኛም ከዛሬው በመምሪያ ኃላፊ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ ከሆኑት እንግዳችን ከመምህር ዳንኤል ጋር የገና እና የጥምቀት በዓላትን መሠረት አድርገን ቆይታ ያደረግነው ሲሆን፣ ስለ ሰላምና ተያያዥ ጉዳዮችም አንስተን የሚከተለውን አጠናቅረን አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- መምህር በቅድሚያ ገና ምንድነው? ስለ ጥምቀትም አያይዘው ያብራሩልን?

መምህር ዳንኤል፡- የገና እና የጥምቀት በዓላት መሠረታቸው ሃይማኖታዊ ነው፡፡ በዓላቱ በቤተክርስቲያን አበይት ወይንም ዋና በዓላት ከሚባሉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ዋና በዓላት የሚያሰኛቸው በሃይማኖት ውስጥ ከሚሰጡት መንፈሳዊ ትርጉምና ዋጋ እንዲሁም በዓላቱን በማክበር ብቻ የማይተካ ዋጋ ስላላቸው፣ የሃይማኖታዊ ትምህርት መሠረትም ስለያዙ ነው፡፡

የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የገና በዓል፤ የአምላክ ሰው መሆን ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆኖ የሰው ልጅን ያዳነበት ነው፡፡ ጥምቀት ደግሞ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበትን ሥርዓትና ዘላለማዊ የሆነ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርስበት ነው። በዓሉን የምናከብረው የድህነት መንገድ የመሠረተልን ስለሆነ ነው፡፡ የበዓላቱ የመከበሪያ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስና የሃይማኖት መዛግብት መሆናቸውም መዘንጋት የለበትም፡፡ በአጠቃላይ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ማኅበራዊ እሴት ያላቸው ናቸው፡፡

ገና ማለት የግሪክ ቋንቋ ነው፡፡ ትርጉሙም ልደት ማለት ነው፡፡ አዲስ ኪዳን መጽሐፍ ወደ ግዕዝ ቋንቋ የተተረጎመው ከግሪክ ነው፡፡ ከግሪክ ወደ ግዕዝ የተረጎሙት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አንዳንድ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ ያሉ ቃላትን እንዳለ አስቀምጠዋል፡፡ ከነዚህ ቃላት ውስጥ ገና አንዱ ነው፡፡ ገና ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳንና ዘላለማዊ ሕይወት ለመስጠት ሲል ሥጋ ለብሶ ሰው ሆኖ የተወለደበት ቀን ነው፡፡ በምድረ እስራኤል በቤተልሄም በከብቶች በረት ውስጥ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ መላእክት ልደቱን ያመሰገኑበት፣ እረኞችም በተወለደበት የከብት በረት ውስጥ ተገኝተው የጎበኙት፣ ሰባሰገል ጠበብት ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀረቡበት፣ ፍጡራን ሁሉ የተደሰቱበት በመሆኑ ቤተክርስቲያን ትልቅ ክብርና ቦታ የምትሰጠው በዓል ነው፡፡

ባዕለ ጥምቀትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ በእደ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበት ነው፡፡ መጠመቁ እግዚአብሔርን አምነው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስና ዘላለማዊ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚፈልጉ የእግዚአብሔር ልጆች ለመባል የሚያችል ነው፡፡ ከገና በዓል ጀምሮ የሚከበረው ዘመን ደግሞ ዘመነ አስተርዮ ይባላል፡፡ በዓሉ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ይዘልቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዓላቱ ሃይማኖታዊ ይዘት ቢኖራቸውም፤ በተለይ የጥምቀት በዓል ማኅበራዊ ይዘታቸው ያመዝናል ይባላልና ስለዚህ ሁኔታም ቢገልጹልን?

መምህር ዳንኤል፡- በዓላቱ ሃይማኖታዊ ናቸው። መሠረታቸውም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ይሄን እውቅና መስጠት አለብን፡፡ የሚከበረውም በኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በአማኞችዋ ዘንድ ነው፡፡ ሆኖም ግን አማኙ የራሱ የሆነ ማኅበራዊ አገልግሎት አለው። የኅይማኖቱ ማንነት በማኅበራዊ ሕይወቱ ውስጥ ይገለጻል፡፡ ሃይማኖታችንን ስናከበር ብቻችንን ሳይሆን፤ በጉባኤ፣ በማህበር በአንድ ተሰባስበን ነው። በማኅበራዊ ጎዳናችን ውስጥ ያሉ ግን ደግሞ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑትንም ወገኖቻችንን በማሳተፍ አብረውን እንዲያከብሩ እናደርጋለን፡፡

በተለይም የጥምቀት በዓል በአደባባይ ስለሚከበር ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎችና የዓለም ሀገራት የሚመጡ ሁሉ የሚካፈሉበት ለማሰባሰብ እድል የሚሰጥ በዓል ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የምታስተምረው ሃይማኖታዊ ትምህርትና መልእክትም ብዙዎችን በአንድ ጊዜ ለመድረስና የመሰማት እድል አለው፡፡

በዓሉን የምናከብረው እንዲያው ልምድ ለመፈጸም ብቻ አይደለም፡፡ የሰላምን ዋጋ፣ የአንድነትን አስፈላጊነት፣ ከማስመሰል የወጣን መሆናችንን፣ የምንከባበር፣ የምንሰማማ መሆናችንና እነዚህ ሁሉ መልካም የሆኑ እሴቶች እንዳሉን ቤተክርስቲያን በአደባባይ ታስተምራለች፡፡ ተከታዮቹም ይህን የመልካም እሴት የሆነውን ማንነት ተላብሰው የሰሙትን ወይንም የተማሩትን በተግባር እንዲተገብሩት ምክርም ይሰጣቸዋል፡፡ ይተገብሩታልም ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የተጣላ ታርቆ፣ የቀማ መልሶ፣ ያስቀየመ ወይንም የበደለ ክሶ፣ እርስበርስም በመዋደድ በዓሉን ማክበር ግዴታ እንደሆነም ቤተክርስቲያን አጥብቃ መልእክት ታስተላልፋለች፡፡ ትገስጻለችም፡፡

ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኩነቱ የሚያመዝንበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉት። አንዱ ከወቅት ጋር የሚያያይዘው ነው። ገበሬው ሰብሉን ከማሳው ሰብስቦ እህሉን ጎተራ የሚያስገባበት ወቅት በመሆኑ ከእርሻ ሥራ ፋታ ያገኛል፡፡ ወደ ማኅበራዊ ሕይወቱ በመመለስ ለሠርግ፣ ለማህበር ድግስና ለተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ጊዜ ይሰጣል፡፡ በዓላቱም በምግብና በመጠጥ ስለሚታጀቡ ደግሶ በዚህ አጋጣሚ ዘመድ ወዳጅ ጎረቤት ጠርቶ በጋራ ደስታውን ያሳልፋል፡፡

የጥምቀት በዓል በአጠቃላይ ሰው ከሰው የሚገናኝበት ነው፡፡ በሥራና በተለያየ መንገድ ተራርቆ የቆየ ዘመድ ከወዳጁ ይገናኛል፡፡ ወጣቶችም አዲስ ኑሮ ለመመስረት እርስበርስ ለመተዋወቅ እድል ያገኛሉ፡፡ የተለያየ አካባቢ የባህል አለባበስ፣ የባህላዊ አጨፋፈር ስልት፣ ታሪክና ወግ የሚታየው በዚህ በጥምቀት የአደባባይ በዓል ላይ ነው፡፡ ሁሉም በሚያስደስተው ነገር አምሮ፣ ደምቆና ተዘጋጅቶ ስሜቱን የሚገልጽበትና አምልኮቱንም የሚፈጽምበት ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚም አንዱ የሌላውን ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ለማወቅ ያስችለዋል፡፡ አድናቆቱን በመግለጽ አብሮነቱን ያሳያል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ሁሉም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን አብሮ ይፈጽማል፡፡ ተጫውቶና ተደስቶም ይውላል፡፡ በዓሉን ሲጨርስም እንዲሁ አይለያይም ለከርሞ በሰላም አድርሷቸው በድጋሚ ተሰባስበው በዓሉን ለማክበር እንዲያበቃቸው አንዱ ለሌላው ቸር ተመኝቶ ነው የሚለያዩት፡፡

የተጣሉ ሰዎችም እርቅ የሚፈጽሙት በዚህ የበዓል አጋጣሚ ነው፡፡ በማስታረቅ ሽምግልና ውስጥ የሚገቡም ሰዎች ዛሬ ካልታረቃችሁ መቼ ልትታረቁ ነው በማለት ነው እንዲታረቁ ተጽእኖ የሚያሳድሩት። የሰው ንብረትም ወስዶ ያልመለሰ ካለ አሁን ሞልቶልሀል በል መልስ በማለት ገስፀውና መክረው እንዲመልስ ያደርጋሉ፡፡ በዓሉን በፍጹም የልቦና ንጽህና እንዲያከብሩ አበክረው ይሸመግላሉ፡፡

ይህ ወቅት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሆነበትን የምንዘክርበት በመሆኑ፤ ቤተክርስቲያን የምታስተምረው ከፀብና ከጥላቻ ርቀን እርስ በርስ መዋደድ እንዳለብን ነው፡፡ ለዚህም ነው የተለያየ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ሰዎች ለአንድ ዓላማ በአንድ ስፍራ ተገናኝተው በጋራ የሚያከብሩት፡፡ ይሄ በሩቅ ለሚያይ ሰው ያስደንቅ እንደሆን እንጂ አያስተችም፡፡ ብዝሀነት የሚታይበት በዓል ነው፡፡

ጥምቀት በማይዳሰስ ቅርስነት በተባበሩት የዓለም መንግሥታት የሳይንስ፣ ባህልና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ሲመዘገብ በቅድመ መረጃ አሰባሰብ ሂደት፤ በዓሉ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው የእርስበርስ ግንኙነት፣ ሰላማዊና በሰዎች መካከል ልዩነት የማይፈጥር መሆኑ በሌሎች አግራሞትና አድናቆት ያገኘ እንደነበር እንዲመዘገብ በነበረው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ውስጥ በነበረኝ ሚና አስታውሳለሁ፡፡

የገና በዓልም ቢሆን ምን ያህል ሰላማዊ የሆነ በዓል እንደሆነ አንዱ ማሳያ፤ በውሃ ቀጠነ ቁጣ የሚቀናቸው አንዳንድ ሰዎች እንኳን የገና እለት ከቁጣቸው በረድ ይላሉ፡፡ “ለገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለ በባህላዊ ጨዋታ የሚገለጸውም በዓሉ ነፃነት ያለው መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ለማኅበረሰቡ ደግሞ ትልቁ ነገር ሰላም ነው፡፡

የጥምቀት ከተራ ታቦታት ከማደሪያቸው ወጥተው በአንድ ስፍራ በድንኳን ስለሚያድሩ የእምነቱ ተከታዮች ወይም ምእመን አጅበው የወሰዱትን ታቦት ለብቻው ጥለው አይመለሱም፡፡ በታቦታት ማደሪያ ታቦታቱን አጅቦ በድንኳን ውስጥ አብረው ያድራሉ፡፡ ያ በዚያ የተሰባሰበው ምእመን እርስ በርሱ አይተዋወቅም፡፡ ከተለያየ ቦታ የተሰባሰበ ነው፡፡ ነገር ግን አንዱ ለሌላው ፍቅርና አክብሮት ሰጥቶ የያዘውንም ምግብ በጋራ ተቋድሶ የሄደበትን ዓላማ በጋራ ይፈጽማል፡፡ አንዱ ሌላውን የሚያየው እንደስጋት ሳይሆን፤ እንደበረከት ነው፡፡ እንዲህ ሰላምን የሚፈጥር አውድ ወይም መድረክ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡

በሃይማኖቱ በኩል ደግሞ፤ እንዲህ ከተለያየ አቅጣጫ ለተሰበሰበው ማኅበረሰብ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጡ ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ በአደባባይ ከሚሰጡ ትምህርቶች ከብዙ በጥቂቱ ስናነሳ፤ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በአደባባይ ሲያስተምር ወደ እርሱ ሄደው ትምህርቱን የሚከታተሉ ሰዎች ነበሩ፡፡

የሮም የመንግሥት ወታደሮች ወደ እርሱ ሄደው እኛ ምን እናድርግ ይሉታል፡፡ ግፍ አትስሩ፣ የናንተ ያልሆነውን አትንኩ ይላቸዋል፡፡ ቀራጮች (ግብር ሰብሳቢዎች) እንዲሁ ወደርሱ ሄደው እኛ ምን እናድርግ ይሉታል፡፡ ከተፈቀደው ግብር በላይ አትውሰዱ፣ ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች እኛ ምን እናድርግ ይሉታል፡፡

ሁለት ያለው አንዱን ለሌላው ያካፍል፣ ቸር ይሁን፣ መተዛዘን ይኑር፣ ጠማማው ቀጥ ይበል፣ ሻካራው ይለስልስ ብሎ ይላቸዋል፡፡ መልእክቱ ሻካራና ጉርብጥብጥ የሆነ አስተሳሰብ ያለው ግለሰብም ሆነ ማኅበረሰብ ይለስልስ ነው፡፡ ፍትህን፣ ለእያንዳንዱ እንደሚገባው መኖርን ማስተማር ነው፡፡ ይሄ መልእክት ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን፤ ማኅበራዊ ይዘት ያለው ነው። በየዘመኑ ላለው ትውልድ እንዲህ በጎነት ያላቸው ትምህርቶች እየተሰጡ መልካም የሆነ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር በማድረግ ቤተክርስቲያን ኃላፊነቷን ትወጣላች፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዓሉ ከደስታና ፈንጠዚያ ባለፈ ሰዎችን በመልካም ነገር የሚያንጹ ትምህርቶችም የሚሰጡበት እንደሆነ ገልጸውልናል፡፡ በትምህርት የሚሰጡትን በጎ ነገሮች ሆኖ መገኘት ላይ ያለው ነገር ምን ይመስላል? አሁን ላይ ሀገራችንን የገጠማት የውስጥ ችግር በሃይማኖት ከታነፀ ማኅበረሰብ ያፈነገጠ ነገር የለውም? እዚህ ላይ  ምን ይላሉ?

መምህር ዳንኤል፡- በቤተክርስቲያን የሚሰጡት ትምህርቶች የሰው ልጅ የተማረውን በሕይወቱ እንዲተገብረው ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት፤ ሰላምን፣ አንድነትን፣ መከባበርን፣ ፍቅርን፣ መዋደድን፣ ርህራሄን፣ ግፍ ጠል መሆንን ትምህርት ሲሰጥ ትምህርቱን የተከታተለውም ይህን እንዲተገብረውና ሆኖ እንዲገኝ ነው የሚፈለገው፡፡ ሰው ይሄን ቢያደርግ በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ተከብሮ እንደሚኖር፣ ፈጽሞ ባይገኝ ግን ከሰውነት እንደሚጎድል ነው ቤተክርስቲያን አጥብቃ የምታስተምረው፡፡

ሆኖ መገኘት ሌላው ብቻ እንዲያደርገው አይደለም። እኔ አስተማሪ ብሆንም መልእክቱን ሳስተላልፍ ከእኔ ጀምሮ መተግበር ይጠበቅብኛል። የምንማረውንም በሕይወት የማንተገብር ከሆነ ከዓለማዊው ቲአትር ተለይቶ አይታይም፡፡ እውነተኛ የሆነ መንፈሳዊ አከባበር አይደለም ማለት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን የምታስተምረው ስዕላዊ በሆነ አገላለጽ ሰዎች ሊተገብሩት በሚያስገድድ ሁኔታ ነው፡፡ አምላክ ወደዚህ ዓለም የመጣው የሰውን ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት ለማምጣት፣ ሰላምንም ለማስፈን ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልንን ነገር በእኛ ሕይወት ውስጥ ልንተረጉም የምንችለው እኛ ያንን በተግባር ስንተረጉም ነው፡፡ ያንን ካልሆንን ከእግዚአብሔር የምናገኘውን ዋጋም ደስታም እናጣለን፡፡ የደካማነት መገለጫ ተደርጎም ይወሰዳል። እውነተኛውን የሃይማኖት ሥርዓት ፈጸምን ለማለት አይቻልም፡፡ በዓሉን ስናከብርም በምድራዊው ዓለም፣ በዘላለማዊውም ሕይወታችን ለመጠቀም ነው፡፡ የበዓሉ ዋና ዓላማ ልምድ መፈጸም ሳይሆን እግዚአብሔር ያደረገልንን መልካምነት በተግባር ማሳየት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንዲህ ያሉ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች አሁን ላይ የሚስተዋሉ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በጎሳ፣ መከፋፈልን ለማስቀረት ለምን አቅም አልኖራቸውም? ምክንያቱም ችግሩ እየተፈጠረ ያለው በእምነት ውስጥ ባሉ አካላት ጭምር ነው፡፡ በዚህ ላይ ሃሳብ ቢሰጡ?

መምህር ዳንኤል፡- ነገሩ ያስጨንቃል፡፡ ጥናትም ይፈልጋል፡፡ ቤተክርስቲያን ማስተማር የሚገባትን የሃይማኖት እሴት ታስተምራለች፡፡ የምታስተምረውም የእግዚአብሔርን ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እኛ እንድንጠፋፋ፣ እርስበርሳችንም እንድንጠላላ፣ በጥርጣሬና ባለመተማመን ውስጥ እንድንኖር፣ በማያቋርጥ ግጭት ውስጥና መከፋፈል ውስጥ እንድንኖር አይፈቅድም፡፡ እግዚአብሔር በልዩ እንደፈጠረን ነው የምናምነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሰው ልጅ በፍቅር፣ በስምምነትና በደስታ እንዲኖር ነው፡፡

የምናስተምርባቸው መጻሕፍትም የመጥፎ ምሳሌዎች አይደሉም፡፡ የተዛባ ትምህርት አስተምረን የፈጣሪን ስም የምናረክስም አይደለንም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከማይወደው ነገር ውጭ የሆነ ነገር እንዴት መጣ? መጥፎ ነገሮች በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዴት ሳለ? በተለይ ደግሞ አማኝ በሆነው ማኅበረሰብ ውስጥ፣ የሚለውን በጥልቀት ማየትና መወያየት ይፈልጋል፡፡ በመደማመጥና በመሰማማት ነገሩን በጥልቀት መዳሰስ ያለብን ይመስለኛል፡፡

በርግጥ በጉዳዩ ላይ ቤተክርስቲያን ሳትነጋገርበት አልቀረችም፡፡ እንዲያው 90 በመቶ በሚሆነው አማኝ ማኅበረሰብ ውስጥ መጥፎ ነገሮች እንዴት ተፈጠሩ ብለን በውይይት መድረኮች ላይ እናነሳለን፡፡ አንዳንዶቹ የምንሰማቸው ድርጊቶች አማኝ አይደሉም በሚባሉት እንኳን ይፈጸማል ተብለው የማይጠረጠሩ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትና ግጭቶች በመካከላችን መፈጠሩ ከማሳዘን አልፎ ጥያቄ የፈጠረ ጉዳይ ነው፡፡

ችግሮቹ እጅግ የበረቱ ናቸው፡፡ ሁላችንንም አሳስበዋል፡፡ ግን በሽታውን ወደ ማባባስ ወይንስ ወደ ማዳን ነው መሄድ ያለብን? በእኔ እምነት ይሄ ጉዳይ በሃይማኖት ተቋማት ብቻ የሚፈታ አይደለም። ያገባናል የሚሉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች። ለፖለቲከኞችም በጋራ ሆነው የጋራ የሆነ መፍትሔ ለመስጠት መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በመንግሥት የወጡ ሕጎች አሉ፡፡ በሃይማኖትም ጥብቅ የሆነ አስተምሮ አለ፡፡ በእምነቱ ሰው ወገኑን ወይንም ወንድሙን ጠልቶ እግዚአብሔርን እወደዋለሁ ማለት እንደማይችል አስተምህሮ አለ፡፡ ሰውን መጥላት እግዚአብሔርን መበደል ነው፡፡ ስለዚህ ሕጎቹን ወደ ማኅበረሰቡ መተርጎም ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓላት የስጋት ምንጭ እየሆኑ የመምጣታቸው ጉዳይ እየተነሳ ነው፡፡ ከስጋት ነፃ ሆኖ ለማክበር ከማን ምን ይጠበቃል?

መምህር ዳንኤል፡- ቤተክርስቲያን በዓላቷን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ በውጭውም ባሉት አብያተ ክርስቲያናት ጭምር በልዩ ክብር ታከብራለች። ስጋት ውስጥ ሆኖ ማክበር የራሱ የሆነ አሉታዊ ጎን አለው። ግን አሁንም ደጋግመን የምንለው ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመሰማማት መፍታት እንጂ በዓላትን የችግር መነሻ ለማድረግ መሞከር ተገቢ አይደለም፡፡

ሰላምን የምንጋራው ሁላችንም ነው፡፡ ሁላችንም በምንጋራው ውስጥ ደግሞ ሁላችንም አለንበት፡፡ ስለዚህ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ከሚወጡ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ሕግ ከሚያስከብረው ጋር በጋራ ቤተክርስቲያን በዓሉ በሰላም እንዲከበር የምትሰራው ሥራ እንዳለ ሆኖ እያንዳንዱ ሰው በሰላም ግንባታ ለፀጥታ መስፍን፣ ስጋትን በማስወገድ፣ ኃላፊነት ስላለበት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የገና እና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር የተደረጉ ዝግጅቶች በተለይም የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል በመሆኑ የተሰጠውን ትኩረት ደግሞ ቢገልጹልን?

መምህር ዳንኤል፡- ዝግጅቱን በተመለከተ መደበኛ የቤተክርስቲያናችን ዓመታዊ በዓል ስለሆነ፤ ከዋናው መንበረ ፓትሪያሪክ ጀምሮ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት መንፈሳዊውንም፣ ማኅበራዊውንም በተለመደ መንገድ ቀኖናዊ ሥርዓቱን ተከትሎ እንዲከናወን ነው፡፡

ገና በላልይበላ፣ ጥምቀት ደግሞ በጎንደር የተለመደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዓላቱ ወደዚያ እንደሚያመዝኑ ይታወቃል፡፡ ከዓለም አቀፍ ሳይቀር እንግዶች የሚታደሙበት እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ከታሪካዊ የአካባበር ሥርዓትና በአካባቢውም ካለው ተደራራቢ ታሪክ፣ መስህቦች፣ ቅርሶችና የማኅበረሰብ እሴቶች ጋር ተያይዞ አካባቢዎቹ ሰፊ ድምቀትና መስህቦች አላቸው። ይሄ እድል የተለየ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በሌሎችም አካባቢዎች በዓሉ በተመሳሳይ በደስታና በፍቅር ይከበራል፡፡ ሰዎችም ይታደማሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ጎብኚዎች የሥነ ጥበብ ቅርሶች፣ ሥነ ሕንፃና ግብረ ሕንፃዎች፣ ታሪክና ባህል የሚስባቸው ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ከነዚህ ጎብኚዎች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት መንፈሳዊ የሆኑ ወይም የሕዝብ በዓላት ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በዚህ የገና እና የጥምቀት በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚመጡት መካከልም አብዛኞቹ የክርስትና እምነት ተከታይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጉብኝት ብቻ ሳይሆን፤ ጉዞአቸው መንፈሳዊም ነው፡፡ ይህን እኔም በማስጎበኝበት ውስጥ በአንድ ወቅት በነበረኝ ተሳትፎ እውነታውን አረጋግጫለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የገና እና የጥምቀት በዓላት የቱሪዝም መስህብም ሆነው በሀገር ምጣኔ ሀብት ላይ ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑ ይታወቃል። ቤተክርስቲያን በዚህ ረገድ ስላላት አበርክትዎ ቢነግሩን?

መምህር ዳንኤል፡- ቱሪዝም በባህሪው ቅስቀሳና ማስታወቂያ ይፈልጋል፡፡ ቤተክርስቲያን በራሷ ባቋቋመቻቸው የመገናኛ ብዙሃን፣ በሕትመት ውጤቶች፣ በማኅበራዊ ድህረ ገጾችና በተለያየ መንገድ በማስተዋወቅ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ አሁንም እየሰራች ነው፡፡ በቅርቡም በቅርስ መመሪያዋ ሥር የቱሪዝም መምሪያ ከፍታለች፡፡ ይህን ክፍል ያዋቀረችውም ቱሪዝም እንዲያድግና በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ አበርክቶ እንዲኖረው ካላት ፍላጎት የተነሳ ነው፡፡

በዓላት ሲከበሩም እንዲሁ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ትሰራለች፡፡ በጋራ የምትሰራቸው ሥራዎች ደግሞ የበለጠ ውጤት እንደሚያስገኙም ስለምትገነዘብ ከመንግሥት ጋርም በትብብር ትሰራለች፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ውስጥም እንደሚሰሩ ገልጸውልኛልና ይህ ተቋም አሁን ላይ ምን እየሰራ ነው?

መምህር ዳንኤል፡– ይህ ተቋም ረዘም ላለ ጊዜ ሲሰራ የቆየ በመሆኑ የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል። አሁንም እየሠራ ይገኛል፡፡ የዚህ ተቋም ትልቁ እሴት ሃይማኖቶች በመከባበርና እርስ በርስ በመደጋገፍ አብረው እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ በተቋሙ የማስተማሪያ መጻሕፍት ተዘጋጅቶ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ ትምህርቱ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ትምህርቱ ጥሩ ተሞክሮ አስገኝቷል፡፡ አንዱ ሃይማኖት የራሱን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ያለው በዓል ሲያከብር የሌላው እምነት ተከታይ ሳይነቅፍ፣ በጠላትነትም ሳያይ፣ ይልቁንም በመተጋገዝ፣ በመተባበርና በፍቅር አብሮ ለማድመቅ የሚደረግ ጥረት በማስገኘት መልካም የሆነ ተሞክሮ ማጎልበት ተችሏል፡፡ ይህ በፖለቲካ ተጽእኖ ወይንም በሌላ ጣልቃ ገብነት ሳይሆን ትክክለኛ በሆነው የሰው ልጅ ስሜት ነው እየተፈጸመ ያለው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከገና እና ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ እንዲሁም ስለሰላሙም መልእክት እንዲያስተላልፉ እድሉን ልስጥዎ?

መምህር ዳንኤል፡- በዓላቱ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ትስስርን የሚፈጥሩ፤ የሰው ልጅ በጎነት፣ ደግነት፣ ደኅንነት፣ የእርስበርስ መጣመር የሚያጠነክሩ፣ ለተሻለ የጋራ ጥቅም እንዲሆን የሚያደርጉ ትምህርቶችና እሴቶች ያላቸው እንዲሁም በውስጣቸው ፍቅርን፣ መከባበርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን መደማመጥን በጣም አጥብቀው የሚያስተምሩ ናቸው። በመሆኑም እኛ የምንመኘው እነዚህ እሴቶች በልባችን ውስጥ ዘልቀው ገብተው በማኅበረሰብ ውስጥ መጥፎ የጥላቻ አስተሳሰቦችን እንዲያስወግድልን ነው፡፡ ጥላቻ በግለሰብ፣ በሀገር ደረጃ እጅግ ጎጂ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ እነዚህን መጥፎ የሆኑ ነገሮች በማስወገድ፤ ለሀገራችን አንድነትና ሰላም በሚሆን መንገድ እራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- መምህር፣ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡ መልካም በዓል እንዲሆንልዎ እንመኛለን፡፡

መምህር ዳንኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You