ዘመኑ ዘመናዊ የግንባታ አሰራሮች ተግባራዊ እየሆኑ ያለቡት ነው። የግንባታውም ዘርፍ ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች እየተካሄደ ሲሆን፣ የአለማችን ትላልቅ ከተሞች ሰማይ ጠቀስ ግንባታዎች የዚሁ ውጤት መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ቴክኖሎጂዎች የግንባታውን ስራ እያቀለጠፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ማድረግ እያስቻሉም ናቸው።
ግንባታዎችም ውስብስብ እና ሰማይ ጠቀስ እየሆኑ መምጣቸውን ተከትሎ ይህን ግንባታ በተቀላጠፈ መንገድ ማካሄድ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ናቸው ስራ ላይ እየዋሉ የሚገኙት። ቴክኖሎጂዎቹ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ፣ ጥራት እና በጀት በወቅቱ ለማጠናቀቅም የሚያስችሉ ሆነው ተገኝተዋል።
በሀገራችንም በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ይህ ቴክኖሎጂ መተግበር ጀምሯል። በተለይ ‹‹ቢም›› የሚባለው ቴክኖሎጂ በግንባታ መጓተት ለምትቸገረው ኢትዮጵያ ጥሩ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል እየተጠቆመ ነው።
በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የኮንስትራክሸን ማኔጀመንት ቴከኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ኢንጂነር ፈለቀ አሰፋ የቢም ቴክኖሎጂን ምንነት አስመልክተው እንዳብራሩት፤ ቢም የተሰኘው ቴክኖሎጂ /የህንጻ መረጃ ሞዴል ወይም ቡይልዲንግ ኢንፎርሜሽን ሞዴል) በዲዛይን፣ በግንባታና በኦፕሬሽን በተናጠል ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩትን አሰራሮች በሙሉ ወደ አንድ ዲጂታል ፕላትፎርም አቀናጅቶ በማምጣት መስራት የሚያስችል ነው።
ዲዛይነሩ ወይም አማካሪው የፕሮጀክቱን መረጃ ግልጽ /ሼር/ በማድረግ መጠቀም የሚያስችሉ እድሎች እንዳሉት ጠቅሰው፣ ቴክኖሎጂው ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ተናግረዋል። የምንፈልጋቸውን መረጃዎች ዲጂታል በሆነ መንገድ ለመፍጠር እንዲሁም ኮምፒውተሩ ላይ የምንፈለገውን በሙሉ በራሳችን ገንብተን ለመጨረስ የሚያስችለን ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በቅድሚያ ኮምፒውተሩ ላይ የተገነቡትን መሬት ላይ የማገናዘብ ስራው ይሰራል። በመሆኑም ፕሮጀክቱ ሁለት ጊዜ ይገነባል፤ የመጀመሪያው በሀሳብ ደረጃ ዲዛይኑንና የሚያስፈልጉ ነገሮች በሙሉ ተገንብተው ይጠናቀቃሉ። ይህ ሲጠናቀቅ ደግሞ ስራ ተቋራጩ በቀላሉ ወደ መሬት ያወርደዋል።
በተለመደው አካሄድ ዲዛይኑ ተዘጋጅቶ ወደ ግንባታ ሲገባ ተጨማሪ ተለዋጭ ስራዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያሉት ኢንጂነር ፈለቀ፣ በዚህ ጊዜም የዲዛይን አለመጣጣም እንደሚፈጠር ይናገራሉ። ይህም ፕሮጀክቶች እንዲዘገዩ፣ ተሻሽሎም ሲመጣ ተጨማሪ ወጪና የግንባታ ጊዜ ይዞ እንዲመጣ እንዲሁም የመረጃ ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያብራራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የቢም ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሲደረግ ከመነሻው የጠራ ዲዛይን፣ የአንዱ ባለሙያ ከሌላው ባለሙያ፤ የአንዱ እውቀት ከሌላው እውቀት ጋር የተናበበ ዲዛይን ተይዞ የሚወጣበት ነው። በዚህ የተነሳም ወደ መሬት ሲወርድም በቀላሉ ፕሮጀክቱን መገንባት የሚያስችሉ እድሎች ይኖሩታል።
ቴክኖሎጂው በተበጣጠሰ መልኩ ያሉትን የአንድ ፕሮጀክት ታሪኮች ወደ አንድ ማምጣትና የጋራ ስራ መፍጠር የሚቻልበት ነው። በጋራ እና በቅንጅት ተመሳሳይ መረጃ በመያዝ ፕሮጀክት በቀላሉ መሰራት የሚችልባቸውን እድሎች ያሰፋል። የዲዛይን ቲምን፣ የኮንስትራክሽን ቲምን እንዲሁም አጠቃላይ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ፕሮጀክቶች በጊዜያቸው ማለቅ እንዲችሉ እና የደንበኞች እርካታንም ለማሳደግ፣ የፕሮጀክቶችን ወጪም ለመቀነስ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ በጀት እንዳይጠየቅባቸው በማድረግ በተጨማሪ በጀትነት ሊጠየቅ የሚችለውን ሀብት ለሌላ ልማት መጠቀም የሚቻልባቸው እድሎች ይኖሩታል። የተያዙትን ፕሮጀክቶች በወቅቱ በማጠናቀቅ እና ሌላ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመጀመር ኢንቨስተመንትን ማሳደግም ያስችላል።
እስከ አሁን ባለው አካሄድ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ ችግር ሲፈጠር ይታያል። ፕሮጀክቶች ይጀመራሉ፣ ይቆማሉ፤ ተጨማሪ ወጪ ይደረግባቸዋል ያሉት ኢንጂነሩ፣ ከዚያ በኋላም ለማጠናቀቅ ሊከብድና ውል ከተገባበት ዋጋ ሁለት እጥፍ ድረስ ወጪ ሊጠየቅ የሚችልበት ሁኔታም ሊያገጥም እንደሚችል ተናግረዋል።
የቢም ቴክኖሎጂ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚያስችል ነው ያስታወቁት። ግንባታዎችን በወቅቱ ማጠናቀቅ እና ጥራትን ማስጠበቅ እንደሚቻል ገልጸዋል። በዚህም ዋጋን መቆጠብ እና የተናበበ ዲዛይን እንዲኖር ማድረግ ከተቻለ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ይችላሉ ። መንገድ፣ ውሃ እና መሰል መሰረተ ልማቶችን አስቀድሞ ለማሟላት ያስችላል። በዚህም የመጨረሻው ተጠቃሚ የሆነው ማህበረሰብ በቀላሉ በተገነባው ፕሮጀክት አገልግሎት ያገኛል።
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከዚህ አኳያ የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል ለተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎች በተከታታይ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። ስልጠናውን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ዩኒቨርስቲዎች ራሳቸውን ችለው ስልጠናውን እንዲሰጡ ለማድረግ የቢም ቴክኖሎጂን በስርአተ ትምህርቱ በማስገባት ተመራቂዎች እውቀቱንና ልምዱን እንዲቀስሙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንጂነሩ እንዳብራሩት፤ ዩኒቨርስቲዎች በቀላሉ ቴክኖሎጂውን መተግበርና የስራ እድል ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግም የወለጋ ዩኒቨርስቲ፣ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ፣ ሰመራ፣ ጅግጂጋ እንዲሁም አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኑቨርስቲዎችን ጨምሮ ከሰባት ዩኒቨርስቲዎች ሰባት አሰልጣኞችን በማፍራት እነዚህ ደግሞ ተመራቂዎችን እንዲያሰለጥኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
እስከ አሁንም 300 ያህል ተመራቂዎችን በሰባት ዩኒቨርስቲዎች ማሰልጠንና ሰርቲፋይ ማድረግ ተችሏል። በቀጣይም በዩኒቨርስቲዎች ቴክኖሎጂው በትምህርት አይነት ተካቶ በሶስት ዓመት፣ በአራት ዓመት፣ በአምስት ዓመት የቢም ቴክኖሎጂው ተካቶ አንዲማሩ እየተደረገ ነው። በዚህ አይነት ከተሰራ ቴክኖሎጂው ነገ አስገዳጅ ይደረግ ቢባል የሰለጠነ የሰው ኃይል ይኖረናል ማለት ነው።
በግንባታውም ዘርፍ እንዲሁ የሰለጠነ የሰው ኃይል የማሟላት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ኢንጂነሩ ፣አማካሪ ዲዛይን ቲም እንዲፈጠርለት፣ ስራ ተቋራጭ የኮነስትራክሸን ቲም እንዲፈጠርለት፣ ዲዛይንና ቡይልዲንግ ቲሞች እንዲሟሉ እየተሰራ ነው ሲሉም አብራርተዋል። በተለይ ፕሮጀክት ያላቸው የመንግስት ተቋማት የዲዛይን ቲም ፣ የግንባታ ቲም እንዲፈጠርላቸው እየተሰራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
የፕሮጀክቶች መጓተት አንዱ ምክንያት የዲዛይን ክፍተት መሆኑን ጠቅሰው፣ ቴክኖሎጂው ተግባራዊ በሚደረግበትም ወቅት ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ችግሩን ለመፍታት የተናበበ ዲዛይን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።
መንግስት እስካሁን ቴክኖሎጂውን አስገዳጅ አላደረገም ያሉት ኢንጂነሩ አንዳንድ ተቋማት በራሳቸው ሙከራ እያደረጉ መሆናቸውን ግን አመልክተዋል። የተወሰኑ ፐሮጀክቶቸም በቴከኖሎጂው እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢንጂነር ፈለቀ እንዳሉት፤ የፌደራል ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ባለሙያዎቹን አሰልጥኖ፣ ሶፍትዌር ገዝቶ፣ ኮምፒውተርም አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ይገኛል። የብሔራዊ ትያትር፣ የሰነዶች ማረጋገጫ ፕሮጀክት ላይ፣ እንዲሁም የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካዛንቺስ አከባቢ በሚያስገነባው ፕሮጀክት ላይ ቢያንስ ዲዛይን ደረጃ ላይ ያሉትን ነገሮች በቢም ቴክኖሎጂ ማኔጅ ለማድረግ እየተሞከረ ነው። በቀጣይም ግንባታ ላይ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ ይኖራል።
ቲኤች ኢንጂነሪንግ በጫካ ፕሮጀክት የሚሰሩ ወደ 29 ህንጻዎችን በቢም ቴክኖሎጂ ተገባራዊ እያደረገ መሆኑን ኢንጂነሩ ጠቅሰው፣ ኦቪድ ግሩፕን የመሳሰሉት ተቋራጮች ፕሮጀከቶቻቸውን ወደ ቢም ቴክኖሎጂ እያስገቡ ናቸው ብለዋል።
መንግስት ቀድሞ ይሄንን መሸከም የሚችሉ ተቋራጭ ተቋማትን መፍጠር ላይ እየሰራ ነው ያሉት ኢንጂነሩ፣ በተለይ በስራ ተቋራጮች ማህበር፣ በአማካሪ መሀንዲሶች ማህበር የሚመጡትን ተቋማት እያበቃ ወደ ስራ እንዲገቡ አሰፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የግንባታ ፕሮጀከቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እና ግንባታዎችን ለማስተዳደር የቢም ቴክኖሎጂ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ስለመሆኑ የኢንፎርሜሽን ቴከኖሎጂ ፓርክ ኮርፖሬሽን/ አይሲቲ ፓርክ በመባል የሚታወቀው ተቋም/ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አፈወርቅ ንጉሴም ይገልጻሉ። እሳቸውም በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት ውስብስብ ህንጻዎች የሚገነቡት በቢም ቴክኖሎጂ በመታገዝ መሆኑን ጠቅሰው ፣ቴክኖሎጂው በዲዛይንም ዘመናዊ አሰራርን በመከተልም ይታወቃል ብለዋል።
በቴክኖሎጂው በመጠቀም ግንባታን በማከናወን ረገድ የኮንስትራከሸን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በሀገር ደረጃ ግንባር ቀደም መሆን መቻሉን አስታውቀው፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሸን ስራዎች ኮርፓሬሽን (ኢኮስኮ)ም እንዲሁ በቅርቡ ቴክኖሎጂውን የሚያስፋፋበትን ማዕከል ማስመረቁንም ተናግረዋል።
ይሄንን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ በኩል ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ በዚህ ላይ ከፍተኛ ልምድ እንዳላትም ተናግረዋል። ኢኮስኮም ከደቡብ አፍሪካ ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ እሳቸውም የዚህ ቦርድ አባል መሆናቸውን ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ እስከ አሁን አብዛኛዎቹ የህንጻ ዲዛይኖች በሁለት ዳይሜንሸን (ኤክስ እና ዋይ) ብቻ በሚያሳይ መልኩ ተሰርተው የሚታዩ ናቸው፤ ቢም ቴከኖሎጂ ተግባራዊ አድርገው የሚሰሩ ህንጻዎች ግን እስከ አምስት ዳይመንሽን (5D) ደርሰዋል። ይህም የህንጻው ግንባታ ካለቀ በኋላ የሚታዩ የህንጻውን አካላት በሙሉ ገና ግንባታው ሳይጀመር መመልከት የሚያስችል ነው።
የቢም ቴክኖሎጂ ሶፍትዌር የግንባታ ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት የግንባታው የተለያዩ ክፍሎችን እና አካላትን አስቀድሞ ለማወቅ ያስችላል፤ ህንጻዎች ከተገነቡ በኋላም ደህንነታቸውን ለመጠበቅ፤ ጥራቱን ባለበት ለማስቀጠል፣ የአቅርቦት ቁጥጥር ለማድረግ ያስችላል።
የህንጻው ግንባታ ከመጀመሩና ከመጠናቀቁ ቀደም ብሎ አጠቃላይ ወለሉን፣ ግድግዳውን፣ የውሃ መስመሩን፣ የኤሌክትሪክ መስመሩን፣ የእሳት መቆጣጠሪያ ሲስተሙን፣ አሳንሰሩን፣ በርና መስኮቱን፣ ጣሪያውን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያውን፣ ሶኬት፣ ወዘተ ሁሉ በቴክኖሎጂው ይመላከታሉ። የህንጻ ግንባታ ጥራት እንዲሁም የመንገድና የተለያዩ ዘርፎች ኤክስቴንሽኖች አጠቃላይ ሁኔታን በተመለከተም ቴክኖሎጂው መረጃ ይሰጣል።
የቢም ቴክኖሎጂ አይነት እና መሰል ቴክኖሎጂዎች በሀገራችን ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸው በግንባታ ዘርፉ ለዘመናት ወደኋላ የቀረንበትን ሁኔታ ለመቀየር ያስችላል ያሉት ኢንጂነር አፈወርቅ፣ ፕሮጀክቶችን ለማፋጠንና ዘርፉን ለማዘመን እንደሚያስችል አስቸውም ገልጸዋል። ሰማይ ጠቀስ እና ውስብስብ ህንጻዎች እንደ ቢም ባሉ ሶፍትዌሮች ሲገነቡ የህንጻውን ውስብስብ ገጽታ በቀላሉ ለማወቅ እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
አርክቴክቱ፣ ሜካኒካል ኢንጂነሩ፣ ኤሌክትሪሺያኑ ወዘተ፣ በተመሳሳይ ጊዜ እየተናበቡ አብረው መስራት የሚችሉበትንም እድል ይፈጥራል ሲሉ አመልክተው፣ አንዱ አንዱን ሳይጠበቅ እየተናበቡ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ፣ ፕሮጀክት በወቅቱ እንዲጠናቀቅ፣ ዋጋ እንዳይጨምር ማድረግም ያስችላል ። ፕሮጀክቱ በበጀት፣ በገንዘብ፣ በጥራትና በጊዜ በታቀደው ልክ እንዲጠናቀቅም ያግዛል ሲሉም አብራርተዋል።
ቴክኖሎጂው ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን እና ስጋቶችንም አስቀድሞ ለመረዳት እድል እንደሚፈጠር ኢንጂነር አፈወርቅ ተናግረዋል። ለግንባታው ግብዓት የሚሆኑትን ነገሮች አስቀድሞ ለማሰብና ለማዘጋጀት እንደሚረዳ ጠቅሰው፣ አስፈላጊ ግብኣቶች አስቀድሞ በማሟላት ከሥር ከሥር በፍጥነት በእቅዱ መሰረት ለመስራት በር እንደሚከፍት ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በቢም ቴክኖሎጂ ከተገነቡ ህንጻዎች መካከል ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ ህንጻ አንዱ መሆኑንም አመልክተው፣ በአዲስ አበባ የተገነቡና እየተገነቡ የሚገኙ ትላልቅ የባንክ ህንጻ ፕሮጀክቶች ቢም ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የዋለባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ዘጠነኛውን የከተሞች ፎረም አስመልክቶ በቅርቡ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቴክኖሎጂው የህንጻ የግንባታ ስራ ተሰርቶ ፊዚካል መሰረተ ልማቱ ከቆመ በኋላ ሳይሆን ገና ከመገንባቱ በፊት ማን ምን ይስራ፣ የቱ ጋ ምን ይሁን፣ ምን እንቀንስ የሚለውን የሚመልስ መሆኑን አስታውቀዋል። ከ30 እና 40 በመቶ በላይ ዋጋ መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑንም ያመለከቱት።
የተቋራጩ እና የደንበኛው/ባለቤቱ/ አለመናበብ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዲዛይን በአግባቡ ሳይበለጽግ የሚወጣበት እና በቅንጅት ምክንያት ግንባታዎች ፈርሰው እንደገና የሚገነቡበትን ሁኔታ እንደሚያስቀር ጠቅሰው፣ ይሄንን ችግር አስቀድሞ የሚቀርፈውና የግንባታ ስራዎችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችለው የቢም ቴክኖሎጂ በሀገሪቱ እየተዋወቀ መሆኑን አመላከተዋል። ቴክኖሎጂው በግሉ ዘርፍ እንዲሁም ፐብሊከ ኢንቨስትመንቱ ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በግንባታው ዘርፍ ላይም ለውጥ እየመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም