አንዳንዴ በሰዎች ያለመፈለግ ስሜት ሊሰማህ ይችላል። ልትገፋ ትችላለህ። መገፋትህን ግን መጥላት የለብህም። ምክንያቱም አንዳንዴ ከባድ ሁኔታዎች ናቸው አንተን አንጥረው የሚያወጡህ። ከህይወታቸው ያወጡህ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ‹‹አትረባም፣ የትም አትደርስም›› ልትባል ትችላለህ። ከስራም ልትባበር ትችላለህ። ከፍቅር ግንኙነትህ ተክደህ ልትለያይ ትችላለህ።
ነገር ግን እነዚህ አንተን የገፉህ ሰዎች ተመልሰው ወደ ህይወትህ ዳግም ሊመጡ ይችላሉ። ሲመጡ ግን ትልቁን ቦታ አይደለም የምትሰጣቸው። መድረኩንም አይደለም የምትሰጣቸው። ይልቁንም አንተ መድረኩ ላይ ቆመህ የምተሰራውን ተአምር ቁጭ ብላችሁ ተመልከቱ ነው የምትላቸው። ስለዚህ በህይወት ወሳኝ ነገሮችና ተፈላጊ ሰው እንድትሆን የሚያደርጉህ እነዚህ ናቸው።
ርግጥ በህይወት ውስጥ ወሳኝ የሚባል ነገር የለም። ሰዎች “በህይወትህ ውስጥ ወሳኝ ነገር ምንድን ነው? ብለው ቢጠይቁህ የመጀመሪያው መልስህ ያንተ መኖርና ጤና ነው። የአእምሮ ዝግጅቱ፣ ስነልቦናው፣ የጊዜና የገንዘብ አጠቃቀሙና ሌሎች ኑሮን ለመምራት የምትጠቀምባቸው ዘዴዎች ቀጥሎ የሚመጡ ናቸው። ያንተ መኖር ግን ከምንም በላይ ወሳኝ ነው። ስለዚህ ያንተ መኖር ከምንም ነገር በፊት ወሳኝ ከሆነ ተፈላጊ ሰው ለመሆን ሚስጥሩ፡-
1ኛ. አመለካከት
አመለካከት ነገሮችንና ሁኔታዎችን የምትረዳበት መንገድ ነው። ያንተ እይታ ነው። ለምሳሌ አይንህ ላይ አረንጓዴ መነፅር ብታደርግ ነገሮች ሁሉ አረንጓዴ ሆነው ይታዩሃል። የቆሸሸ መነፅር ብታደርግ የቆሸሸ ነገር ይታይሃል። ችግሩ ግን ከአንተ አይደለም፤ ከመነፅሩ ነው። ሰዎች ብዙ ግዜ ወደው ክፉ አይሆኑም። ‹‹እኔ መቀየር አልችልም፤ መለወጥ አልችልም፤ የምፈልገውን ማሳካት አልችልም›› አይሉም። ሆን በልው አይደለም ይሄ ነገር የሚመጣባቸው። በህይወታቸው በገጠሟቸውና ባሳለፏቸው ምክንያቶች አመለካከታቸው ተንሸዋሯል። በህይወት አስፍቶ የሚያይ ሰውና ፊት ለፊት ብቻ የሚመጣበትን የሚያይ ሰው ህይወትን እኩል አይኖሯትም።
አስፍቶ የሚያይ ሰው ነው ነገን ያስባል። ህልምና ዓላማ አለው። ምን ቢያደርግ የቱ ጋር እንደሚደርስ ያውቃል። ነገሮችን በቅርብ ብቻ የሚያይ ሰው ግን ህይወቱን ለማቆየት ብቻ ነው የሚኖረው። ኑሮ ባይወደድ ደስ ይለዋል። አይሯሯጥም። የማይመስሉ ነገሮችን ነው የሚያስበው። ለምን? አመለካከቱ በውጫዊ ነገሮች ተከቧል። ሁኔታዎች፣ ነገሮችና ሰዎች የእርሱን ህይወት እንደሚቀይሩለት ያምናል።
ስለዚህ ለፍለጋ ውጪ ከወጣህ አታገኝም። ፊኛ ከፍ ብሎ የሚወጣው ለምንድን ነው? ቀለሙ፣ አልያም ንፋስ አይደለም ወደ ላይ ፊኛውን ከፍ የሚያደርገው። በውስጡ የተሞላው አየር ነው ወደ ሰማይ ከፍ እንዲል ያደረገው። አንተንም ከፍ የሚያደርግህ፣ ከሰው በላይ የሚያደርግህ፣ ትልቅ ቦታ የሚያደርስህ ነገሮችን የምታይበት መንገድና አመለካከትህ ነው። ውስጥህ ከተቀየረ ውጪውን መቀየር በጣም ቀላል ነው። ብዙ ሰዎች ግን ውጪው እስኪቀየር ይጠብቃሉ።
2ኛ. ዓላማ
ዓላማ በህይወትህ ውስጥ ፈጣሪ አንተ እዚህ ምድር ላይ ስትመጣ እንድትጨምረው፣ የሆነ ነገር እንድታበረክት የተላክበት ሰነድ ነው። ለምሳሌ የሰው ልጅ ዓላማውን እንዴት ያውቃል ከተባለ በጣም በብዙ ልፋት ነው ሊያውቅ የሚችለው። የሰው ልጅ ማሽን አይደለም። ማሽን ቢሆን ኖሮ ፈጣሪ ድርሰቱን ይፅፈዋል፤ አንተ ትኖር ነበር። አላማ ከባድነቱ ድርሰቱን የምትፅፈው አንተ ነህ። የምትመራውና የምትቀምረው አንተ ነህ። ተዋኙም አንተ ነህ። አላማ ሲኖርህ ደግሞ ጥሩ ዳይሬክተር ነህ። ምን መሆንና በምን በኩል መሄድ እንዳለበህ ታውቀዋለህ። አላማ ሳይኖርህ ሲቀር ሰዎች ይጠቀሙበሃል። በነፈሰው ትነፍሳለህ። አላማ ከሌለህ መጠቀሚያ ትሆናለህ።
ህልም ከሌለህ ህልም የሌለው አገልጋይ ነው የምትሆነው። ህልምን መከተል አዲስ ቋንቋ እንደመልመድ ከባድ ነው። ብዙ ጊዜ ትሳሳታለህ፤ ትኮላተፋለህ፤ ቀስ ብለህ ግን መልመድህ አይቀርም። ስለዚህ አላማህን ማወቅ፤ ህልምህን ማወቅ በጣም ከባድ ነገር ሊሆን ይችላል። እንዴት ነው ታዲያ የምታገኘው? ትሞክራለህ የምትወደው ከሆነ ትቀጥላለህ። ከቻልክ ቁጭ ብለህ የማሰብ ልማድ ይኑርህ።
ስለዚህ ዓላማውን ማወቅና ህልሙን መረዳት የሚፈልግ ሰው በተቻለው አቅም ቁጭ ብሎ የማሰብ፣ ከሰዎች የመስማት ልምድ ማዳበር አለበት። ስታነብ ስለሰዎች እያወክ ነው፤ ስታስብ ደግሞ ራስህን ጠፍጥፈህ ለመስራት እድል እያገኘህ ነው። አላማህን ለማወቅ የምትፈለግ ከሆነ ጊዜ ውሰድ።
3ኛ. መክሊት
ስትሰራው ጉልበት እንዳወጣህ የማይሰማህ ነገር አለ። ለምሳሌ ስትበላ ‹‹እኔ እኮ ስበላ ይደክመኛል፤ አልበላም›› አትልም። መብላት ትወዳለህ። በተለይ ርቦህ ስትበላ በእጅህ ምግቡን ጠቅልለህ ወደ አፍህ እስክታደርሰው ድረስ ያለውን ሂደት የሆነ የጉልበት ስራ አድርገህ አትቆጥረውም። ደስ ብሎህ ነው የምታስገባው። በተመሳሳይ የሆነ ነገር መስራት ረሀብ /ፓሽን/ ይኖርሃል። ፓሽን ያንን ነገር ስትሰራ ምንም ጉልበት እንዳወጣህ አለመሰማት ነው። እንደውም ያንን በማድረግህ ደስታ ነው የሚሰማህ።
ብዙ አይነት መክሊቶች አሉ። አንዳንድ ሰዎች ቁጭ ብለው ሲያወሩ ደስ ይላቸዋል። ሌላው ደግሞ አምብቦና አድምጦ መፃፍ ደስታ የሚሰጠው ሰው አለ። አንዳንድ ሰው ከመድረክ ጀርባ ሆኖ የሚቀርፅ፤ ሰዎችን አሳምሮ ወደ መድረክ የሚያቀርብ “ፓሽን” ያለው ሰው አለ። ስለዚህ ፓሽን አንተ ሳይከብድህ በቀላሉ የምታደርገው ተግባር ነው።
የሰዎች ህይወት ላይ የሚጨምር ነገር ከሆነ ፓሽን ነው። ነገር ግን ደግሞ መተኛት የኔ ፓሽን ነው ብለህ በሰዎች ህይወት ላይ ምንም የሚጨምረው ነገር ከሌለ ፓሽን ሊባል አይችልም። ስለዚህ የሚያስደስትህ ነገር ሁሉ ፓሽን ነው ማለት አይደለም። የሚያስደስትህ ነገር የሆነ ዋጋ የሚጨምር መሆን አለበት ፓሽን። አድጎ ነገ የሆነ ትልቅ ቦታ ላይ ሊያደርስህ የሚችል መሆን አለበት።
4ኛ. ሰዎት አናሊሲስ /swot analysis/
አንድ ሰው ቢዝነስ ለመስራት ካሰበና ራሱን በደምብ ጠንቅቆ ማወቅ የሚፈልግ ከሆነ ሰዎት አናሊሲስ መስራት አለበት። ጥንካሬውን፣ ድክመቱን፣ እጁ ላይ ያለውን እድልና የእርሱን ተፎካካሪ ወይም ስጋቱን መለየት አለበት። ድክመትና ጥንካሬ ውስጣዊ ናቸው። እድልና ስጋት ደግሞ ውጫዊ ናቸው። እነዚህን ነገሮች ስታጠና ጠላትህን ይበልጥ ታውቀዋለህ። ጠላትህ ያው ማሸነፍ የምትፈልገው ህይወትህ ነው። ጠላቶች ሰዎች አይደሉም። ስለዚህ ህይወትን ማሸነፍ ነው ዓላማህ። ለዛ ነው እነዚህ ነገሮች ጠንቅቀህ ማወቅ ያለብህ።
5ኛ. ጥልቅ ፍላጎት
አሁን ዓለም የደረሰችበትን ቴክኖሎጂና ፈጠራዎች በሙሉ የወሰነው የሰው ልጅ ጥልቅ ፍላጎት ነው። የሰው ልጅ ፍላጎት ባይኖረው በፈረስ እስከዛሬ ድረስ ይጓዝ ነበር። የሰው ልጅ የምኞች ፍላጎቱ ነው ህይወትን የሚቀይርለት። በነፃነት እንዲህ ቢሆን ብለህ ህፃን ልጅ እንደሚመኘው ስትመኝ ያንን ፍላጎት ደግሞ ለማሳካት ስትሮጥ የራስህን ህይወት ብቻ ሳይሆን ዓለምን ልትቀይር ትችላለህ።
6ኛ. ውሎ
‹‹ስላንተ እንድነግርህ ከፈለክ የጓደኛህን ፀባይ ንገረኝ›› ይባላል። ጓደኛዬ እዚህ እዚህ ቦታ ይውላል ካልክ በርግጠኝነት አንተም ከዛ የተለየ ነገር አይኖርህም። ስለዚህ አብዛኛው ሰው ውሎ ሲባል በአካል አብሮ የሚያገኛቸውን ሰዎች፣ አብሯቸው የሚውላቸውን ሰዎች ብቻ ናቸው ብሎ ያስባል። አይደለም! ውሎ ማለት የአእምሮ ውሎ ነው። በስልክህ የምትውላቸው ውሎዎች አሉ። በርግጠኝነት አማካዩ ህዝብ በቀን ውስጥ ከአራትና ከአምስት ሰአታት በላይ ስልኩ ላይ ጊዜውን ያጠፋል። ይህ ማለት ወደድክም ጠላህም በስልክህ ላይ ከምታያቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ ሆነሃ ል ማለት ነው።
ለምሳሌ አንድ ጂምሮን የሚባል አነቃቂ ንግግር ተናጋሪን ደጋግመህ የምታየው ከሆነ ብታውቀውም ባታወቀውም ጂምሮን ጓደኛህ ሆኗል ማለት ነው። አንድ በጣም የምትወደውን ቲክቶከር ወይም አስቂኝ ሰው ስለእርሱ ቁጭ ብለህ የምታይ ከሆነ ብትወደውም ባትወደውም ከዛ ሰው ጋር ጓደኛ ሆነሃል። ስለዚህ ከአስቂኝ ሰው ጋር የምትውል ከሆነ ሙያህ ወደ ኮሜዲያንነት እስካልተለወጠ ድረስ ህይወት ትስቅብሃለች። ከቁምነገረኛ ሰው ጋር በስልክህ የምትውል ከሆነ አንተም ቁምነገረኛ ነው የምትሆነው። ውሎህን ትመስላለህ። ሳታውቀው ማንነትህ መቀየር ይጀምራል።
እየደጋገምክ የምታደርጋቸው ነገሮች ህይወትህ ላይ ሳታውቀው መገለጥ ይጀምራሉ። አሁን የደረስከበት ደረጃ ላይ የወሰኑት ከአመታት በፊት ያደረካቸው ነገሮች ናቸው። በጣም ደጋግመህ የምታደርገው ነገር፣ የምታነባቸው መፅሃፍቶች፣ የምታያቸው ፊልሞች በሙሉ ህይወትህን ወስነውታል። ነገ የምትደርስበትን ደግሞ አሁን የምታደርጋቸው ይወስኑታል። መጠንቀቅ ያለብህ ለዛ ነው።
7ኛ. እምነት
ዓለም ላይ የማይመስሉና አይሆኑም የተባሉ ነገሮች ሆነዋል። ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ጆንኦፍ ኬኔዲ የተባለው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ‹‹በቅርቡ ጨረቃ ላይ ሰው እናስቀምጣለን›› አለ። መሳቂያ ነበር የሆነው። መላው የአሜሪካን ህዝብ ተሳለቀበት። ግን ብዙ ጊዜ አልፈጀም። አሜሪካ ጨረቃ ላይ ሰው አስቀመጠች። ራሺያና ሌሎችም ሀገራት ተከተሉ። የማይመስሉ ነገሮች የሚሆኑት በእምነት ነው። ትንሿ ጥረትህ ትልቁን እንደምታክል አምነህ ካልጀመርክ ምን ታደርጋለህ? አንዳንድ ጊዜ ጭፍን እምነትህ ነው ህይወትህን የሚቀይረው። የማይመስሉ ነገሮችን አምነህ መጀመር አለብህ።
ነገር ግን የሚመስለውን ጥረት እያደረክ መሆን አለበት። አሁን በዚህ ሰአት ሚሊየነር፣ ቢሊየነር መሆን እፈልጋለሁ ካልክ መጀመሪያ አሁን እጅህ ላይ ምን ያህል ብር አለ? አሁን ላይ ተቀጥረህ በምትሰራበት ቦታ ምን ያህል እየጣርክ ነው? በትንሹ ከታመንክ ነው በትልቁ የምትሾመው። እምነት ማለት የማይታየውን፤ የማይጨብጠውን ነገር ማመን ነው። የምታየውንማ ማመን ማን ያቅተዋል፤ የሚል ያየውን ማመን ማለት ማረጋገጥ ነው። አለ ነው። ያላየኸውን ገና ይሆናል ብለህ የምታምነውን እርግጠኛ ስትሆን ነው የምታምነው።
ምድርን ያንቀጠቀጡና አለምን የለወጡ ሰዎች የተነሱት በእምነታቸው ነው። በሀይላቸው፤ በጉልበታቸው አይደለም። መጀመሪያ እምነታቸው ነው ጉልበትና ብርታት የሰጣቸው። አንዳንዴ የማይመስሉ ነገሮች በህይወትህ ይፈጠራሉ። እኔ እኮ ብዙ ግዜ ሞክሬያለሁ፣ ያላደረኩት ነገር የለም፤ ይህን ፍቅርና ትዳር ለማዳን፣ ይህን ቢዝነስ ቀጥ አድርጎ ለማቆም፣ ለመለወጥ ብዙ ሞክሬያለሁ ልትል ትችላለህ። ጥያቄው “ግን አምነሃል ወይ?” ነው። አንዳንድ ሰው እንደሚቀየር ሳያምን ዝም ብሎ ይሞክራል። እርግጠኛ አይደለም።
እምነት ከሌለው የምታደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ ስጋ ለብሰው የእውነት አለም ላይ አይፈጠሩም። አንተም በአእምሮህ ያላየኸው ነገር እውነት ሆኖ አለም ላይ አታገኘውም፤ አትጨብጠውም። አንተ በአይምሮህ ከጨረስከው ነው በእውነታው ለመግለጥ ጉልበት የሚኖርህ። አይምሮህ አንድን ነገር እውነት ይሁን ውሸት መለየት አይችልም። አንተ ደጋግመህ ውሸትም ብትነግረው እውነት ነው ብሎ ነው የሚቀበለው። ግን ያንን ውሸት ለመግለጥ ደግሞ የማያደርገው ጥረት የለም። ሰላም ነው የሚነሳህ።
ለምን? አንተ ተኝተህ ስራውን የሚሰራ አእምሮ ነው ያለህ። ተኝተህ አየር ወጣ አየር ገባ አትልም። ተኝተህ ደምህ ሲዘዋወርና ምግብ ሲፈጭ አንተ አይታወቅህም፤ ተዘርረሃል። ይህንን የሚቆጣጠርልህ የአእምሮ ክፍል አለ። ለዚህ የአእምሮ ክፍልህ እየደጋገምክ መሆን የምትፈልገውን፣ ማሳካት የምትፈልገውን ብታሰርፅበት ጥረትህ ሁሉ ወደዛ ይመራሃል። አእምሮህ አንተ አውቀኸውም ሳታወቀውም ቢሆን፣ ከጀርባ በማታውቀው መንገድ እዛ ቦታ ላይ ራስህን እንድታገኝ ያደርግሃል። አንተ በአእምሮህ ማሳካት የምትፈልገውን ጨርሰው፣ በተግባር ጀምረው መጨረሻ ላይ ሆኖ ታገኘዋለህ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም