በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ

‹‹ገና›› የሚለው ቃል ከግሪክ ቃል የተወረሰ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ቃል ሲተረጎም ‹‹ልደት›› ማለት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ገና›› በትንቢተ ነቢያት የተነገረለት የሰው ልጆችን በጥንተ-ተፈጥሮ የፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ የተወለደበት ቀን ነው ፡፡

በዘመነ ሄሮድስ የንግሥና ዘመን የይሁዳ ክፍል በነበረችው የቤተልሔም ከተማ ኢየሱሰ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ከበስተምሥራቅ የመጡ ጥበበኞች ሕጻኑን ለማየት አለበት ከተባለ ሰፍራ ገሰገሱ። ሳጥናቸውን ከፍተውም የእጃቸውን ስጦታ አበረከቱለት ፡፡

እኒህ የሰባሰገል ሰዎች ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ ይዘው ነበር፡፡ ጥበበኞቹ ከሠረገላ ፈረሳቸው ወርደው ወደ ግርግሙ ባመሩ ግዜ ከእናቱ ዕቅፍ ለነበረው ሕጻን ጎንበስ አሉ፡፡ ተንበርክከውም ሰገደሉት፡፡

በየዓለማቱ ያሉ ሀገራት የገናን በዓል በተለያየ ባሕልና ልማድ ያከብሩታል፡፡ አብዛኞቹ ገና ከመድረሱ በፊት የሚኖሩትን ጥቂት ቀናት በጾምና ጸሎት የሚያሳልፉ ናቸው፡፡ በዩክሬን በዓሉ ከመድረሱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ በየቤቱ እየዞሩ ገናን በዝማሬ የመቀበል ልማድ አላቸው፡፡

ቤሉሩሲያውያንም ዕለቱን ቂጣና ዓሣ በማዘጋጀት በተለየ ደስታ ያሳልፉታል፡፡ በሞንቴግሮ ሳንቲም ያለበት የድፎ ዳቦን ማዘጋጀት የተለመደ ነው፡፡ ዳቦው ሲቆረስ ሳንቲሙን ያገኘ ሰው ዕድሉ የተቃና ይሆንለታል ተብሎ ይታሰባል፡፡

በሩሲያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ደግሞ ከአዲስ ዓመት መባቻ ጀምሮ እስከ ዕለተ ገና ድረሰ ያሉትን አስራ ሁለት ቀናት የተለያዩ ምግቦችን በመመገብ የሚያሳልፉ ናቸው፡፡ የአስራ ሁለቱ ቀናት ተምሳሌትም አስራ ሁለቱን ሐዋርያት በማስታወስ ለመዘከር እንደሆነ ይነገራል ፡፡

በሰርቪያ የገና በዓል የሚከበረው ከጫካ እንጨት ቆርጦ በማምጣት እንጨቱን በማንደድና በዙሪያው ተሰባስቦ ጣፋጭ ራትን በመብላት ነው፡፡ ጆርጂያውያንም ከቤት ወደ ጎዳና በመውጣት የክርሰቶስን ልደት በተለየ ደስታና ዝማሬ ይቀበሉታል፡፡

በዓለማችን አውሮፓና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የክርስትና ዕምነት ተከታይ ሀገራት የገናን በዓል በድምቀት ያከብራሉ፡፡፡ እነዚህ ሀገራት የከርስቶስን የልደት ቀን የሚያከብሩት ከዘመን መለወጫቸው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በታኅሣሥ ወር አጋማሽ ላይ ነው፡፡

ከአፍሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ግብፅ ዕለቱን ታኅሣሥ 29 ላይ አስበው ያከብራሉ፡፡ በነዚህ ሀገራት የገና ዕለት በአንድ የመመሳሰሉ ምክንያት ሁሉም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን በመከተላቸው ነው ፡፡

ከክርስቶስ ልደት በፊት ዓመቱን በሙሉ አረንጓዴ ለሚሆኑት ዛፎች የተለየ ክብር ይሰጥ ነበር፡፡ በወቅቱ እነዚህ ዛፎች ርኩሳት መናፍስትን፣ አስማተኞችንና በሽታን በሙሉ የማጥፋት ኃይል እንዳላቸው ሲታመንበት ቆይቷል፡፡

አብዛኞቹ አረማውያን ዛፎቹን እየቆረጡ በየበራቸውና አጥሮቻቸው ላይ ይሰቅሉ ነበር፡፡ ከሁሉም ደግሞ አይሼሪያውያን የተባሉት የደኖቹን ዛፎች እስከማምለክ መድረሳቸው ይነገራል፡፡

ሰዎቹ ለዛፎቹ ክብራቸውን ለመግለጽ ወደቤታቸው በማምጣት በተለዩ ጌጣጌጦች ያስውቧቸው ነበር፡፡ ይህ ልማድ ዋል አደር ሲል ስያሜው ተቀየረ፡፡ ከገና በዓል መከበር ጋር ተያይዞም ወደ ቤተክርስቲያን የመግባት አጋጣሚውን አገኘ፡፡

ከገና በዓል መከበር ጋር የተለመደው የስጦታ መለዋወጥ ልማድም የራሱ መነሻ ታሪክ አለው፡፡ በ19ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ በቱርክ የተወለደውና ከስሙ በፊት ‹‹ቅዱስ›› የሚል መጠሪያን የተቸረው ሊቀጳጳሱ ኒኮላስ ታላቅ ክብር የተሰጠው ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ከገና አባት ጋር ስሙ ቢነሳም በአብዛኞች ዘንድ የባዕድ አምልኮ መሠረት እንዳለው ይታመንበታል፡፡

ታሪክ እንደሚያረዳው በዘመኑ የነበረች የአሮማውያን አማልዕክት ከስፍራው ተወግዳ ቦታው በኒኮላስ አማልዕክት ከተተካ ወዲህ የእሱ ተከታዮች መብዛታቸው ይነገራል፡፡ ይህ ሰው የአማልክቷን ቦታ ከያዘ በኋላ የስጦታዎች መለዋወጥ ተስፋፋ፡፡ የኒኮላስ ተከታዮችም ወደን የተባለና ነጭ ጢም ያለው በዓመት አንድ ጊዜ  በሰማይ ይጋልባል የሚባልለትን አማልዕክት ያመልኩ ነበር፡፡

በሀገራችን ከዚህ የአምልኮ ታሪክ ጋር የተያያዘ አንዳች ግንኙነት የለም፡፡ ይሁን እንጂ የገና በዓልን አስመልክቶ የስጦታ መለዋወጥ ልማድ በበጎነት የተወረሰ ባሕል ሆኖ አሁንም ድረስ ይተገበራል፡፡

በኢትዮጵያ የልደት በዓል በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ ይህ ቀን ግን ልክ እንደ ዘንድሮ በአራት ዓመት አንዴ ታኅሣሥ 28 ላይ የሚውልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እንዲህ ለመሆኑ ምክንያቱ በዘመነ ዮሐንስ የጳጉሜ ወር ከአምስት ይልቅ ስድስት ቀናትን ስለምታስቆጥር ነው፡፡

በሀገራችን የገና በዓል አከባበር ጥንታዊ መሠረት አለው፡፡ በተለይ በገጠሩ ክፍል ወጣቶች በያዕቆብ በትር ተምሳሌት የሚሆን የተሸለመ ዱላና ሩር በመያዝ የገና ጨዋታን በሜዳ በመስኩ ተጫውተው ያሳልፉታል ፡፡

በዚህ ቀን በገናው ሩር አንዱ ሌላውን ቢመታ፣ ቢፈናከት መቀያየም መኮራረፍ አይኖርም፡፡ ሁሉም እንዳሻው ሊሆን ተፈቅዶለታልና ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ይሉት እውነት ተተግብሮ ይታያል። የገና በዓል በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ ቀናት ዋንኛው ነው፡፡ በዚህ ቀን ቤተሰብ፣ ጓደኛና፣ የሥራ ባልደረቦች ስጦታ የመለዋወጥ ልማድን አዳብረዋል፡፡

ቀደም ሲል ዕለቱን ለማድመቅ በየቤቱ በተፈጥሮ ጽድ የሚዘጋጅ የገና ዛፍ የሚጌጥበትና በተለየ ደስታ ሁሉም የሚያከብርበት ተሞክሮ ነበር፡፡ በፅድ ዛፍ የማክበር ልማድ አሁን እየቀረ ቢሆንም እሱን በሚተካ የሰው ሠራሽ ዛፍ በመብራትና በጌጣጌጦች ተውቦ በየቤቱ፣ በየሆቴሉና በታዋቂ ስፍራዎች ደምቆ የመታየቱ ልማድ ለበዓሉ የልዩ ውበት ማሳያ ነው፡፡

ገና የእየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን በመሆኑ ሕጻናት በተለየ ጉጉት ይጠብቁታል፡፡ ይህን ዕለት ለማክበርም ደማቅና አሸብራቂ የማስዋቢያ ቁሶችን መጠቀም ምርጫቸው ነው፡፡

የገና በዓል በሀገራችን ታላቅ ተብለው ከሚከበሩት ዓውደ ዓመቶች መሐል አንዱ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ አብዛኛው ሕዝበ ክርስቲያን በጾም በፀሎት የሚቆይበት በመሆኑ ዕለቱን በዕርድና በተለየ ዝግጅት የማሳለፍ ልማድ አለው፡፡

ይህ አጋጣሚ ብዙኃንን በማኅበራዊ ሕይወት ያስተሳስራል፡፡ ጉርብትናን አብሮ መኖርን፣ ተጠራርቶ መብላት መጠጣትን በማጉላት ኢትዮጵያዊነትን በጉልህ ያደምቃል፡፡ በዚህ ግዜ ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ይሉት አባባል ትርጉም አለው፡፡ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ መልካም የገና በዓል ይሁን፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You