የቀጣናውን ሀገራት ለአዲስ የትብብር መንፈስ የሚያነቃቃ ስምምነት

የኢትዮጵያን ቀጣይ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ አቅጣጫ ይወስናሉ ተብለው በግንባር ቀደምትነት ከተቀመጡ ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የባህር በር ነው፡፡ ሀገሪቱ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ባለቤት ነች። በአፍሪካ የተነቃቃ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗም ተደምሮበት የባህር በር ይህንን እድገት ሳይንገራገጭ ለማስቀጠል ወሳኝ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ ከወራት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር በር ኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት በመግለፅ ጥያቄው ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

ለአንድ ሀገር ሕዝብና ትውልድ የእድገትና የስልጣኔ መንገድ ጠራጊ ተደርገው ከሚወሰዱት ውስጥ አንዱ የባህር በር ነው፡፡ 22 ከመቶ ገደማ ያክሉ የኢኮኖሚ መነቃቃት በዚህ የወደብ የገበያ ልውውጥ በኩል የሚመጣ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆም እንዲያስችል ኢትዮጵያ የባህር በር አጀንዳን ወደፊት ያመጣችው። ላለፉት ጥቁት አስርት ዓመታትም ማኅበረሰባችን ቀደምት ታሪኮችን በመጥቀስ የባህር በር ፍላጎቱን ሲያንፀባርቅ ቆይቷል።

ከሰሞኑ አጀንዳውን ወደፊት አምጥቶ ከመወያየት የዘለለ የተግባር ርምጃም ተወስዷል። ይህንን ተከትሎም በኢትዮጵያና በሱማሌ ላንድ መንግሥት በኩል ታሪካዊ የሁለትዮሽ ስምምነት በወደብ ጉዳይ ተፈርሟል። ይሄንኑ እውነታ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በተሰማ መግለጫ አረጋግጠናል። ስምምነቱ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን መንገድ ከመጥረጉም ባለፈው ጥያቄው ሕጋዊና ትክክል እንደሆነ ማረጋገጫ የሚሰጥም ጭምር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ታሪካዊ ነው በተባለው የመግባቢያ ሰነድ ላይ በመዲናችን አዲስ አበባ ፊርሚያቸውን አኑረዋል፡፡ የሰነዱ አስፈላጊነት የትብብርና የአጋርነት መንፈስን ከማስረጽ ጎን ለጎን በተለያዩ ዘርፎች ማለትም፤ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ ኢትዮጵያ ካነሳችው የባህር በር ጥያቄ አንጻር ፋይዳው ላቅ ያለ ስለመሆኑም በስፋት እየተነገረም ነው። የሀገሪቱን የባህር በር የማግኘት መሻት ተጨባጭ የሚያደርግ፣ የወደብ አማራጮችን የሚያሰፋ፣ የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ፣ የጸጥታ የሚያጠናክር ነው፡፡ ለምሥራቅ አፍሪካ ሆነ ለአፍሪካ ሀገራት አዲስ የትብብር መነቃቃትን የሚፈጥርም እንደሚሆን በስፋት እየተነገረ ነው፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ፣ የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ‹ኢትዮጵያ ከስምምነቱ በኋላ ለሶማሌ ላንድ ነፃ የሀገርነት እውቅናን የምትሰጥ የመጀመሪያዋ ሀገር እንደምትሆንና በምላሹ ሱማሌላንድ ደግሞ ኢትዮጵያ የባህር በር እና የባህር ኃይል ቤዝ እንዲኖራት በቀይ ባህር በኩል 20 ኪሎ ሜትር ርቀትን የሚሸፍን መሬት በሊዝ እንደምትሰጥ የተናገሩበት ሁኔታ ነበር፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶር) እንኳን ለኢትዮጵያ ስብራት ጥገና ቀን በጋራ አደረሰን፤ አደረሳችሁ፤ በተደጋጋሚ ለሕዝባችን በገባነው ቃል መሠረት ኢትዮጵያ ካሏት ዋና ዋና ስብራቶች መካከል አንዱ ቀይ ባህርን የመጠቀም በዛውም የማልማት ፍላጎት ከሱማሌላንድ ወንድሞቻችን ጋር በተደረገ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመናል›› ሲሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ስምምነት ተከትሎ የሶማሌላንድ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ አሊ ሀሰን ሞሀመድ ‹‹ታሪክ እየተሰራ ነው። ይህ ጨዋታ ቀያሪ ትልቅ ትርጉም ያለው ስምምነት ነው፡፡ ትልቅ እና ወኔ የሚጠይቅ ርምጃ ነው። ወደፊት ለሁለቱ ሀገራት የብሩህ አድማስ በሮችን የሚከፍት ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ይህ በሁለቱ ሀገራት መካከል አዲስ ምዕራፍ ከፋች ስምምነት በኢትዮጵያ በኩል ራሱን እንደቻለ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ሊታይ የሚገባው ነው። በባህር በር የይገባኛል ጥያቄ በኩል ቀጣይ ተጨባጭ አቅጣጫዎችን እንድናማትር እድል ሊሰጥ የሚችል ጭምር ነው፡፡ በሰጥቶ በመቀበል፣ ተካፍሎ በመብላት፣ በመጋራትና በማጋራት መርህ ላይ የተመሠረተው የሀገራችን አስተማማኝና ቀልጣፋ የወደብ አማራጭ የማግኘት ጥያቄ፤ አሁን ላይ ይዞት የመጣው ተስፋ ሰጭ ውጤት፤ በቀጣይም በተመሳሳይ መልኩ ተጨማሪ ወደቦችን ማግኘት የሚያስችል ክስተት ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ለዚህም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳነሳንው እኛ ያሉንን ሀብቶች የመጋራት፣ የመካፈልና በጋራ የመልማት ፍላጎት እንጂ ማንንም በኃይል የማስገደድ ፍላጎት የለንም ስንል የነበረው ሃሳብ ወደተግባር ተቀይሮ ዛሬ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለሶማሌ ሕዝብ የምናበስረው የምስራች ሆኗል›› ሲሉ በሁለትዮሽ ስምምነቱ ወቅት የተናገሩትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ዛሬም ካለን ላይ እየሰጠን፣ የሚገባንን እየጠየቅን በትላንቱ የአባቶቻችን ዳና ላይ መቆየት ይገባናል። እንደ ሕዝብ ነውር እና ይሉኝታ የምናውቅ ሕዝቦች ነን። ዘመናዊነትን ከባህልና ከሥርዓት ጋር አቻችለን መኖር የሚያስችሉን እሴቶች ባለቤት ነን፡፡ ትላንት ዛሬም የምንታወቅበት በዚሁ ነው፡፡ ከሰሞኑ የተደረገው የሰጥቶ መቀበል መርህም ከዚሁ እሴታችን ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። እዚህ ጋር የሚከተለውን ምሳሌ ታሪክን አጣቅሰን ማንሳት ይገባናል።

የእስልምና ሃይማኖት መስራቹ ነብዩ መሀመድ በአረብና በሌሎች ሀገራት የሚሳደዱ ተከታዮቻቸውን ‹‹ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ። እዛ ሰው የማይበድል ራሱም የማይበደል መንግሥትና ሕዝብ አለ›› ብለው እንደላኳቸው እናስታውሳለን፡፡ በሽሽት ወደ ሀገሪቱ ከገቡ በኋላም የወቅቱ ንጉስ በኢትዮጵያዊ ሥነ ሥርዓት በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንደተቀበላቸው የታሪክ ሰነድ አገላብጠን ማግኘት እንችላለን፡፡ ከዚህ ታሪክ ቀደም ባሉት ግዚያት ጭምር በትብብር፣ በጋራና በአብሮነት ስሜት ከሰው ልጆች ጋር መኖር እንደምንችል እንማራለን። ዛሬ እኛ ለኢኮኖሚ እድገታችን፣ ለዓላዊነት ዘብ የሚሆን የባህር በር ትንፋሽ ስንፈልግ ደግሞ በዚሁ የመተባበር መንፈስ በዲፕሎማሲና ውይይት ልናሳካው ችለናል።

ሌላው በትብብርና በሰጥቶ መቀበል መርህ እንደምንሰራ ምሳሌ የሚሆነን ጉዳይና የባህር በር ጥያቄ ጋር የሚመሳሰለው አጀንዳ የዓባይ ግድብ ነው። ይህንን ታላቅ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ያለ አንዳች የውጭ ኃይል ድጋፍ በሕዝባችን ሕብረት ስንገነባ እራሳችንን ብቻ አስበን አይደለም። ይልቁኑ ቀጣናውን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳርና በጋራ ለማደግ ነበር።

ጎረቤት ሀገራት ሰፋፊ የባህር በር ባለቤት ቢሆኑም ጥያቄያችንን በይፋ እስክናቀርብ ድረስ ማናቸውም በገፀ በረከትነት አላቀረቡልንም። እኛ ግን የዓባይን ግድብ ፕሮጀክት ‹‹የጋራችን ነው›› እናም በጋራ አስበን፣ በጋራ መክረን በጋራ እንልማ›› በሚል ሚዛናዊነትን ያስቀደመ አስተሳሰብን አንስተናል። ከነዚህ ሁለት እውነታዎች ተነስተን ለፍትህ፣ ለእውነትና ለሚዛናዊነት ያለንን ቦታ መረዳት ይቻላል። ዛሬም ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረግነው ስምምነት ይህንን መነሻ ያደረገ መርህ ላይ የቆመ ነው።

ጥያቄያችን እንደ መንግሥት ወቅቱን የጠበቀ፣ እንደ ሕዝብ ደግሞ ይገባናልን ያስቀደመ እንቅስቃሴ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ታሪክና ተፈጥሮ ካቋደሱን (ዓባይና ቀይ ባህር) ጸጋዎቻችን ሳንጠቀም በረከቶቻችንን ለሌሎች አሳልፈን የሰጠን መሆናችን ነው። እኛ ‹‹ወቅታዊ የባህር በር ጥያቄያችንን መልሱ ወይም ደግሞ እናንተ እስካሁን ተጠቅማችኋል፤ አሁን የኛ ተራ ነው። ስንበላ ቆማችሁ እዩን›› ሳይሆን የጋራ ‹‹የተፈጥሮ ፀጋዎችን በጋራ እንጠቀም›› የሚል ነው፡፡

በሕዳሴ ግድብ በኩል ታሪክ የሚዘክረውን የጀብደኝነት ተግባር ፈጽመን ዓባይን ገድበናል፡፡ ብዙ ርቀትን ተጉዘን እውነት በማይመስል ታሪክ በኩል ለትንሳኤ መቃረባችን ይታወቃል፡፡ በቀይ ባህር በኩል ደግሞ የይገባኛል ጥያቄ ሰንዝረን ከተጋሪ ሀገራት ጋር ለውይይትና ለተግባቦት በርና ልባችንን ከፍተን እየጠበቅን ነው፡፡ የሰሞኑ የሶማሌ ላንድ የሁለትዮሽ ስምምነትም የዚሁ አካል ነው፡፡

በሂደት በሁለቱም ተፈጥሯዊ ጸጋዎቻችን በኩል ከተጋሪነት ባለፈ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ዳብረን ሀገርን ከድህነት፣ ሕዝብን ከተረጂነት አላቀን በሁለት እግራችን ቆመን የጥንቱን ታሪካችንን የምናድስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ዓባይን ከይገባኛል ጥያቄ ተነስተን እንደገደብነው ይታወቃል። በታሪክም በሕግም ፍትሀዊ የሆነው የባህር በር ጥያቄም ሙሉ ለሙሉ ምላሽ አግኝቶ የከፍታዎቻችን አብሳሪ አቅም እንደሚሆኑ እናምናለን፡፡

አንድም በሕዳሴ ግድብ አንድም በባህር በር የይገባኛል ጥያቄ በኩል የትንሳኤ ጮራ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እየፈነጠቀ ነው፡፡ በፖለቲካም ሆነ በቅኝ ገዢዎች ሴራ፣ በአቅም ማጣትም ሆነ በግዛት መጥበብ መነሻነት የከፍታዎቻችንን ማማዎች አጥተናቸው ብዙ ዘመናት በድህነት ማቅ ውስጥ ከርመናል፡፡ አሁን ጊዜው የቀደመ ሥልጣኔያችንን እና ኃያልነታችንን የምናስመልስበት፣ ኢትዮጵያዊነትን ከብዝሀነት ጋር ቀይጠው ገናናነትን ያሰጡንን ተፈጥሯዊ ጸጋዎቻችንን በነፃነት የምንጠቀምበት፣ በውይይትና በድርድር ወደሁነኛ የአብሮ ማደግ መርህ ውስጥ የምንገባበት ነው፡፡

የባህር በር ይገባኛል ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አግኝቶ ወደሥራ ሲገባ ቀጣዩ የኢኮኖሚ አቀጣጣይ ሆኖ የልማት አርበኝነቱን ይወስዳል፡፡ ይሄ ማለት በየጊዜው ለሚጨምር የሕዝብ ቁጥርና የፍላጎት መናር እንደሁነኛ መፍትሔ የሚወሰድ ይሆናል፡፡ ከመነሻው የይገባኛል ጥያቄውንም የፈጠሩት ከሕዝብ ቁጥርና ከፍላጎት መናር ጋር የማደግ ምኞትን ያነገቡ እኚህ ወቅታዊ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

ከሶማሌ ላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሬት እንዲወርድና ተግባር ላይ እንዲውል ሁላችንም መሥራት ይጠበቅብናል። ይህንን የኢትዮጵያን የማደግ ፍላጎት የሚያረጋግጥ አጀንዳ የሚያሰናክሉ የሴራ ትንታኔዎችን፣ አደናቃፊ ኃይሎችን ችላ ብለን ሙሉ ትኩረታችን ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ማስፈፀም ላይ ማድረግ ይጠበቅብናል።

በጀመርናቸው በትላልቆቹ ማርሽ ቀያሪ የዓባይ ግድብ የመነቃቃት መንፈስ፤ በጀመርነው የባህር በር የማግኘት ተግባራዊ ርምጃ በኩል ድህነትና ኋላቀርነትን ተሰናብተን ከአዲስ የእድገትና የለውጥ መሻታችን ጋር እንደምንወዳጅ የብዙዎቻችን እምነት ነው፡፡ ለውጥ የብዙኃነት ነጸብራቅ ነውና ለጀመርናቸውም ሆኑ ልንጀምራቸው ላሰብናቸው ሀገራዊ እቅዶች ጠጠር ማዋጣት ከሁላችን የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ሰላም!!

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You