የከተማዋን ቮሊቦል ስፖርት ለማነቃቃትና ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው

የቮሊቦል ስፖርት በኢትዮጵያ ተዘውታሪ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል ይመደባል። በክለቦች፣ በቡድኖች፣ በፕሮጀክት፣ በትምህርት ቤቶችና በመኖሪያ አካባቢዎችም በስፋት ይዘወተራል። ነገር ግን ቀድሞ ስፖርቱ በስፋት ከሚዘወተርባቸው ከተሞች አንዱ በሆነው አዲስ አበባ ከወቅቶች መቀያየር ጋር ተያይዞ ተዳክሞ ቆይቷል። ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም የከተማዋ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ደማቅ ውድድሮች ይዘጋጅበት የነበረው፤ እንዲሁም ጠንካራ ተፎካካሪዎች የነበሩት ከተማው ባለፉት ጊዜያት በዓመት አንድ ጊዜ ከሚዘጋጅ ሀገር አቀፍ ውድድር በስተቀር ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አልነበረውም። ዳግም መነቃቃት የጀመረው ከ2013 ዓ∙ም ወዲህ ሲሆን፤ ለዚህም በከተማ ደረጃ ክለቦች፣ ቡድኖችና የታዳጊ ፕሮጀክቶችን ለማቋቋም በስፋት ጥረት በመደረጉ ነው። የከተማውን የቮሊቦል ስፖርት መነቃቃት ለማስቀጠልና ይበልጥ ለማሳደግም ውድድሮችን ማብዛት፣ የክለቦችን ቁጥር ማሳደግ፣ ታዳጊ ስፖርተኞችን ማሰልጠንና ባለሙያዎችን በብዛት ማፍራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌትሽ አስራት፤ ተወዳጅና ተዘወታሪ ከሆኑ ስፖርቶች አንዱ በሆነው የቮሊቦል ስፖርት ከሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት በፊት የነበሩ ትልልቅና ጠንካራ የከተማዋ ክለቦች በመንግሥት ለውጥ ምክንያት በመፍረሳቸው ስፖርቱ መዳከሙን ያወሳሉ። ከአራት ዓመት በፊት የተመረጠው ሥራ አስፈጻሚም ውድድሮችን በማዘጋጀት፤ እንዲሁም ሌሎች ጥረቶችን በማድረግ የተቀዛቀዘው ስፖርት እንዲያንሰራራ በመደረግ ላይ ነው።

የውድድር ዕድሎችን ከማስፋት አንጻርም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚሳተፉ ክለቦችን ጭምር የሚያካትት ከተማ አቀፍ የዋንጫ ውድድር ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ተካሂዷል። የክለቦች የዙር እና በከተማ ደረጃ የሚካሄዱ የተማሪዎች ውድድሮችም በተጨማሪነት ከሚደረጉ ውድድሮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። የዚህን ዓመት የክለቦችና የተማሪዎችን ውድድሮች ለማካሄድም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ከተማው ካለው የሕዝብ ብዛትና አቅም አኳያ የሚካሄዱት ውድድሮች በቂ ባይሆኑም፣ ስፖርቱ ተዳክሞ ከመቆየቱ አኳያ መሻሻሎች መኖራቸው እሙን ነው። ፌዴሬሽኑ ይህንን አጠናክሮ ለመቀጠልና ውድድሮችንም በክፍለ ከተሞችም ጭምር ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በስፖንሰር ለመሸፈን ጥረቱን እንደ ቀጠለ ነው። ለዚህም እንዲረዳ በየክፍለ ከተማው ፌዴሬሽኖች ተቋቁመው ድጋፍና ክትትል እየተደረገባቸው ሲሆን፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ ውድድሮችን ለማካሄድ በእቅድ መያዙን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል።

ከአራት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በሚደረግ ድጋፍ ከ13 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው አራት የታዳጊ ፕሮጀክቶች ውጤታማነትና የሚገኙበትን ሁኔታ የፌዴሬሽኑ ኮሚቴ ክትትል አድርጎ ያሉበትን ሁኔታ እየገመገመ እንደሆነም ተጠቁሟል። ሥራ አስፈጻሚውም በቦታው የቅርብ ክትትል በማድረግ የቁሳቁስ ድጋፎችን በማድረግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመደረጉ የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በክፍለ ከተማ ደረጃ የተያዙ አምስት ፕሮጀክቶች ሲኖሩ እነዚህን ለማስፋት ይሰራል። ከፕሮጀክቶቹ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ስድስት ታዳጊዎች ተመልምለው በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ስልጠናቸውን በመከታተል ላይም ናቸው።

ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለማነቃቃትም የክለቦችንና ቡድኖችን ቁጥር በማብዛት፤ እንዲሁም ታዳጊ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል ጠንካራ ዕቅድ አውጥቶ እየሠራ ይገኛል። ለዚህም የገንዘብ አቅሙን ለማጠናከርና ድጋፎችን ለማሰባሰብ ዕቅድ ነድፎ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት የማስገባት ሥራዎችን እየሰራ ነው። በከተማው ጠንካራና በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ሲኖሩ፤ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ መቻል፣ ማረሚያ፣ ጌታ ዘሩ እና ብሔራዊ አልኮል ናቸው።

በክፍለ ከተማ ድጋፍ የሚደረግላቸው ቡድኖች ደግሞ ለሚ ኩራና አቃቂ ቃሊቲ የሚገኙ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ የካ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቡድን ለማቋቋምና በውድድር ለመሳተፍ ምላሽ የሰጡ መሆኑንም ተጠቁሟል። ፌዴሬሽኑ ለክለቦቹ የሙያና የቴክኒክ፣ እንዲሁም ለቡድኖቹ የቁሳቁስ እገዛንም ያደርጋል። የክለቦቹንም ቁጥር ለመጨመር በ23 ተቋማት ላይ ቅስቀሳ ቢደረግም በተለያዩ ምክንያቶች ምላሽ ሳይገኝ ቀርቷል።

ለስፖርቱ ዕድገት ወሳኝ የሆነውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የአሰልጣኝነትና የዳኝነት ስልጠናዎች እየተሰጡ ሲሆን፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በተጨማሪም በስፖርቱ የታየውን መነቃቃትና ዕድገት ለማስቀጠል ፌዴሬሽኑ እያከናወነ ያለውን ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አረጋግጠዋል።

 ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2016

Recommended For You