ለገና ላሊበላ -ለጥምቀት ጎንደር እንገናኝ

ኢትዮጵያ የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ቅርሶች ባለቤት ነች። የተፈጥሮ ሀብቶቹ ከኤርታኢሌ እስከ ዳሎል፤ ከራስ ዳሽን እስከ ታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ሥፍራዎች ተካተውበታል።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ከሚያበቋት ነገሮች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት 16 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ነች። በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በመከናወን ላይ ናቸው።

ሀገራዊ ለውጡ ዕውን ከሆነበት 2010 ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማወቅ፤ በመለየት፤ በማልማትና በመጠቀም ረገድ እምርታዊ ለውጦች ታይተዋል። በአጠቃላይ ወቅቱ ለቱሪዝም ዘርፉ ትንሳኤ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ሃሳብ አፍላቂነት እና መሪነት ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት የሚያበረታታ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሸገር፤ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በሚል ማዕቀፍ በሀገራችን የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መልክ እንዲለሙ እና ለቀረው ዓለም እንዲተዋወቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ሥራ ተገብቷል። መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም ማዕዘናት ሀብቶችን በመለየትና በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እጅግ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በገበታ ለሸገር የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ የአንድነት፤ የወንድማማችት እና የእንጦጦ ፓርኮች ለአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋታል። ለወትሮው በቱሪስት መተላለፊያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ የቱሪስቶች መቆያ የመሆን ዕድልም አግኝታለች። በገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም የጎርጎራ፤ የኮይሻ እና የወንጪ የቱሪስት መዳረሻዎች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥረዋል።

ከእነዚሁ የቱሪዝም ሀብቶች በተጨማሪ ኃይማኖታዊ በዓላት የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው። በተለይም ደግሞ በላሊበላ የሚከበረው የገና በዓልና በጎንደር የሚከበረው የጥምቀት በዓላት ልዩ ድባብ ያላቸውና በቱሪስቶችም ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቁ ናቸው። ገና በላሊበላ ልዩ ድምቀት አለው። ላሊበላም በገና ልዩ ግርማ ሞገስ ታገኛለች። ይህንኑ በዓል ለማድመቅም እስከ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች በላሊበላ ይታደማሉ።

ገና የሚለው ቃል ከግሪክ ቋንቋ የተገኘ ሆኖ ትርጉሙም ልደት ማለት ነው። የክርስቶስ የልደት በዓል በመላው ዓለም በተለያዩ ሀገራት የሚከበር ሲሆን፣ የጎርጎሮስያኑን የዘመን አቆጣጠር በሚከተሉ ሀገራት ታኅሣሥ 16 (December 25) ይከበራል።ሌሎች ጥቂት ሀገራት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ታኅሣሥ 29 ያከብሩታል። በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ እንደ ዘንድሮው ታኅሣሥ 28 ይውላል።

በዚህም ሕንድ፣ እስክንድርያ፣ ግብጽ፣ ሶሪያ እና አርመንያ የመሳሰሉት ከኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይ ቀን የገና በዓልን የሚያከብሩ ሀገሮች ናቸው።

በኢትዮጵያ የገና በዓል በየአካባቢው እና በየቤቱ የተለየ ድባብ ባለው መልኩ ቢከበርም የላሊበላን ያህል ግዝፈት ያለው አይደለም። ከላይ እንደገለጽነው በዓል አከባበር ሲነሳ ደግሞ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን አለማሰብ የሚቻል አይደለም።

ውቅር አብያተ-ክርስቲያናቱን በ13ኛው ክፍለ ዘመን የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት ንጉሠ ነገሥት የነበረው ላሊበላ ከአንድ ወጥ ቋጥኝ ጠርቦ የሠራቸው እንደሆነ ይታመናል። የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት ቅዱስ ላሊበላ ከአስራ አንዱ የዛግዌ ሥርወ-መንግሥት ነገሥታት አንዱ ነው፣ ለአርባ ዓመት ከነገሡት ሰባቱ ውስጥም አንዱ ናቸው።

ንጉሥ ላሊበላ ለኃይማኖታዊ ጉዞ በተደጋጋሚ ወደ እየሩሳሌም ያቀኑ እንደነበር እና እየሩሳሌምን ንጉሥ ላሊበላ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢትዮጵያውያንም መሳለም ይፈልጉ ስለነበር፣ በግብጽ በረሃ ይደርስባቸው የነበረውን ችግር ለማስቀረት የእየሩሳሌምን አምሳያ በኢትዮጵያ እንደተከሉ ይነገራል። በዚህም ንጉሥ ላሊበላ 11 ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ያሳነጹ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ቤተ-መድኃኔዓለም ከኹሉም ትልቁ እና 72 አዕማዳት ያሉት ነው።

ቤተ-ማርያም ደግሞ ንጉሡ አብዝተው ይወዱት የነበረና በቀን ለብዙ ጊዜ የሚመላለሱበት፣ ቤዛ ኩሉ ያሬዳዊ ዜማም የሚቀርብበት ነው ሲሉ ይገልጻሉ መምህሩ። ቀሪዎችም ቤተ-ደናግል፣ ቤተ-መስቀል፣ ቤተ-ደብረ ሲና፣ ቤተ-ጎለጎታ፣ ቤተ-አማኑኤል፣ ቤተ-አባ ሊባኖስ፣ ቤተ-መርቆሪዎስ፣ ቤተ-ገብርኤል ወሩፋኤል እና ቤተ-ጊዮርጊስ (ባለ መስቀል ቅርጹ) ናቸው።

በላሊበላ የገና በዓል ታኅሣሥ 29 (በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ታኅሣሥ 28) በልዩ ድምቀት ይከበራል። ዕለቱ ንጉሥ ላሊበላ የተወለዱበት ቀንም ነው። ቤዛ ኩሉ ተብሎ የሚጠራው ያሬዳዊ ዝማሬ ደግሞ በዚሁ በዓል የሚቀርብ ልዩ እና ታላቅ መንፈሳዊ ትዕይንት ነው። ዝማሬው የሚደረገውም ከቅዳሴ በኋላ በቤተ-ማርያም ነው።

ከታች ባለ ነጭ ካባ ካህናት፣ ከላይ ደግሞ ባለ ጥቁር ካባ ካህናት፣ እንዲሁም ዲያቆናትና ምዕመናን ተደርድረው በቅዱስ ያሬድ ዜማ ቤዛ ኩሉ እያሉ ይዘምራሉ። ይህም ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ በሰማይ መላዕክት፣ በምድር ደግሞ እረኞች (ሰብዕ) በአንድነት ሆነው መዘመራቸውን ለማሳየት መሆኑ ይነገራል።

ከዚህ የተነሳም በገና ሰሞን ላሊበላ መገኘት እንደ ዕድል የሚቆጠርና የሕይወት ዘመን ትዝታና ደስታ ሆኖ የሚዘልቅ መሆኑን በዓሉን የታደሙት ሰርክ የሚናገሩት ነው። ይህም ለገና ቀጠሯችን ላሊበላ ላይ እንድናደርግ ለማስቻል ከምክንያቶች በላይ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ፤ ለዚህም ነው ቀጠሯችን ላሊበላ ላይ እንድናደርግ ማለቴ።

ሌላኛው ውብ ትዕይንትና ኢትዮጵያን በቱሪስቶች ዘንድ ተናፋቂ የሚያደርጋት በጎንደር የሚከበረው የጥምቀት በዓል ነው። ጥምቀት በጎንደር ልዩ ድባብ አለው። ኢትዮጵያ ዜና ጥምቀተ ክርስቶስን ከሰማችበት ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አንሥቶ በተለይም ከአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት (6ኛው መ/ክ/ዘ) ወዲህ የጥምቀትን በዓል ዛሬ በሚታየው አኳኋን ስታከበር እንደ ቆየች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

በክብረ በዓሉ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት የሚወርዱት ታቦታት በካህናቱ ሃሌታ፣ በምእመናኑ እልልታ እና በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ በተቋቋሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዝሙሮች ታጅበው በተመሳሳይ አኳኋን እንደሚመለሱ ይታወቃል።

በጥምቀት ዕለት የጎንደር አባቶችና እናቶች፤ ወጣቶችና ታዳጊዎች ባማረ የባህል ልብሶቻቸው ተውበው ደምቀው ጎንደርና ጥምቀትን ያደምቋታል አባቶች ጥንግ ድርብ እና አልፎ አልፎም ቀደምቱን ያማራ በርኖስ የባህል ልብሳቸውን ለብሰው ጥምቀትን ደምቀው ሲያደምቁት ፣ የቀረው ነዋሪም “ለጥምቀት ያልሆነ ልብስ ይበጣጠስ” ሆነና አቅሙ የፈቀደ አዲስ ልብስ አስርቶ ይለብሳል።

ወጣቶች አምረውና ደምቀው የሚታዩት በጥምቀት ነው። በጥምቀት የጎንደር ስመ ጥሩ የአርባ አራቱ ታቦት ፣ ሊቃውንት፤ ስመጥር የደብር አለቆችና ካህናት በሚያምረው ልብሰ ተክህኖ አምረውና ደምቀው ይታያሉ . . . በነጭ የባህል ልብሳቸው ላይ ጣል ከሚያደርጉት ጥቁር ካባቸውንና በራሳቸው ጥምጣም የሚታወቁት በጎንደር የቅኔ ፤ የመወድስና የአቋቋም ዝማሬ ሊቃውንት ባማረው አንደበታቸው የውዳሴ መዝሙር ጣዕመ ዜማ፣ ወርብና ሽብሸባውን በአደባባይ የሚያሰሙበት ልዩ አጋጣሚ ቢኖር ይህ የጥምቀት በዓል ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ስንሄድ ያልተነኩ እምቅ ሀብቶች በስፋት የሚገኙባት ሀገር ነች። እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ከታወቁ፤ ከለሙ እና ተገቢው ጥበቃ ከተደረገላቸው የኢትዮጵያ የብልጽግና እና የሕዝቦቿ የኑሮ መሠረቶች እንደሚሆኑ ይታመናል። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጅማና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶችን ሲጎበኙ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ሀገሩን ያላወቀና ሀብቱን በአግባቡ ያልተጠቀመ ትውልድ የባከነ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፤ ታሪክና በዓል ያላት ሀገር በመሆኗ በየጊዜው በዩኒስኮ የሚመዘገቡ ቅርሶቿ እየጨመሩ መጥተዋል። ዘንድሮ 16 ደርሰዋል። ሆኖም ከእነዚህ ቅርሶች እንደ ሀገር ምን ያህል ተጠቅመናል የሚለው ዛሬም ምላሽ የሚያሻው ጥያቄ ነው። ከኢትዮጵያ አነስተኛ ቅርስና የተፈጥሮ መስህብ ያላቸው ሀገራት የሚያገኙት ዓመታዊ ገቢ በእጅጉ ከፍተኛ ነው።

እንደ አብነት ብንወስድ ግብጽ በዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ስታገኝ ሞሮቾ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ አምስት ቢሊዮን ዶላር ያፈሳሉ። ኢትዮጵያ 1ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት በአፍሪካ በሰባተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዩኒስኮ በርካታ ቅርሶች በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ለሆነችው ሀገራችን ይህ ደረጃ የሚመጥናት አይደለም።

ሆኖም ኢትዮጵያ እንደ ገናና ጥምቀት እንዲሁም ላሊበላ፤ አክሱም፤ ጎንደርና መሰል ቅርሶች በጎብኚዎች የሚወደዱ ቢሆኑም የመሠረተ ልማት አለመሟላትና ግጭትና ጦርነት ቱሪስቶችን የሚያርቁ ያልተፈቱ ማነቆዎች ናቸው። በተለይም በርካታ የቱሪስት ምስህቦች የሚገኙበት ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተደጋጋሚ በጦርነት አዙሪት ውስጥ መነቆጡ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም የምታገኘው ሀብት እንዳያድግ እንቅፋት ሆኗል።

በኢትዮጵያ በቱሪዝም መስዕብነት የሚያገለግሉ ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሮ ናቸው። በተለይም ከታሪክ ጎብኚዎች አንጻር ትልቁ የቱሪስቶች መስዕብ በሰሜን የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ያነጣጥራል። ይሁንና አካባቢው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጦርነት መጎዳቱ እና አሁንም ሙሉ ለሙሉ ሰላማዊ ሆኖ አለመዝለቁ ቱሪስቶች ወደ አካባቢው እንዳይመጡ አድርጓል።

በርግጥ እየተሰሩ ባሉ ሰላም የማስከበር ሥራዎች በላሊበላ የሚከበረው የገና በዓልና በጎንደር የሚከበረው የጥምቀት በዓል ሰላማዊ እንደሚሆንና በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች እንደሚታደሙበት የአማራ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሰሞኑን ይፋ ማድረጉ መልካም ዜና ሊባል የሚችል ነው።

ሌላው ችግር ከመሠረተ ልማት ጋር የተያያዘ ነው። ቱሪዝም ሰፊ ሀብት የሚጠይቅና በሰጡት ልክ ምላሽ የሚሰጥ ዘርፍ ነው። በርካታ ሀብት ያፈሰሱ ሀገሮች በምትኩ ከቱሪዝም ዘርፉ በርካታ ሀብት ያፍሳሉ። ስለዚህም ከዘርፉ ለመጠቀም የመሠረተ ልማት ደረጃ ማሻሻል፣ ፓርኮችንና ሎጆችን ከዋና መንገድ ጋር የሚያገናኙ መጋቢ መንገዶችን መገንባትና መጠገን፣ እንዲሁም በፓርክና በእንስሳት መጠበቂያ የሚገኙ የዱር እንስሳትን አደን መከላከል፣ ቅርሶች የሚገኙበትን አካባቢ መጠበቅ ያስፈልጋል።

የሰላም እጦትና መሠረተ ልማት ችግሮች ዘወትር የሚነሳ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ ችግር ቢሆንም ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጋር በተያያዘ አሁን አሁን እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው። በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የቱሪዝም ሀብቶችን ከመለየት፤ ከማልማትና ከመጠቀም ጋር እየተሰሩ ያሉት ሥራዎች መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እንቅስቃሴ የትንሳኤ ዘመን ነው ብሎ መወስድ ይቻላል። እስከዚያው ግን አይረሴ ጊዜያትን ለማሰላፍ ገናን በላሊበላ ጥምቀትን በጎንደር እንዲደርጉ በመጋበዝ የዛሬውን ነፅ ሃሳቤን በዚሁ ልቋጭ።

አሊ ሴሮ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2016

Recommended For You