ደቡብ ኢትዮጵያ- የማዕድን ምርት ቅኝት

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገ ክልል ነው። በክልሉ ከፍተኛ ክምችት ያለው የማዕድናት ሀብቶች ይገኙበታል። ከእነዚህም ውስጥ የድንጋይ ከሰል፣ የከበሩ ማዕድናት፣ የኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን እና የመሳሳሉ በርካታ ማዕድናት የሚገኙበት ክልል ነው። ክልሉ በተለይ በድንጋይ ከሰልና በከበሩት ማዕድናት ልማት ተጠቃሽ ነው።

በክልሉ የማዕድን ዘርፉ የማዕድን ሀብት በጥናት ተለይተው እየተሠራባቸው እንዳሉ ሁሉ በጥናት ያልተለዩም በርካታ ማዕድናት ያሉበት ነው። እነዚህን በማዕድናት በማልማት ረገድም በርካታ አምራቾች ፍቃድ ወስደው ወደ ልማት ሥራ መግባታቸው የክልሉ መረጃ ያመላክታል።

የደቡብ ኢትዮጵያ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ በክልሉ በርካታ የማዕድን ሀብቶች ያሉ መሆኑን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ በጥናት የተለዩና ያልተለዩ ማዕድናት አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ የኮንስትራክሽን፣ የከበሩ ማዕድናት እና ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ተጠቃሾች ናቸው። የድንጋይ ከሰል፣ የቪንቶናይት ፣ የዲያቶማይት እና የመሳሰሉ የከበሩ ማዕድናት ክምችት መኖሩ በጥናት ተለይቷል።

‹‹ክልሉ በዋናነት በድንጋይ ከሰል እና የከበሩ ማዕድናት ላይ እየሰራ ነው›› ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በተለይ የድንጋይ ከሰል፣ ቪንቶናይት እና ዲያቶማይት በጥናት የተለዩና በቡርጂና በጌዲዮ ዞን መኖራቸው የተረጋገጠ ነው ይላሉ። ሌሎች የማዕድን ዓይነቶች ደግሞ ልማቱ ላይ የሚሳተፈው ባለሀብት በራሱ አጥንቶ ወደ ሥራ የሚገባባቸው መሆናቸው ጠቅሰው፤ በዚያ መሠረት ለማልማት ለሚፈልጉ አካላት ክልሉ ፈቃድ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለፃ፤ የድንጋይ ከሰልና የከበሩ ማዕድናት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ጎሞ፣ ወላይታ፣ ጎራዱላ፣ ቡርጂ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዶዮ ፣ ኮንሶ እና ጎፋ ይገኛሉ። እነዚህን ማዕድናት ለማምረት በአነስተኛ ደረጃ የተደራጁ ማህበራትና ኩባንያ ደረጃ ፍቃድ የወሰዱ 123 አምራቾች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አሁን ላይ ወደ ማምረት ገብተው እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት 22 ያህሉ መሆናቸው ጠቁመዋል።

በተያዘው (በ2016) በጀት ዓመት ከማዕድን ዘርፉ 56 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊ፤ በሩብ ዓመቱ ብቻ 14 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ፤ 13 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል። ይህም አፈጻጸሙን የእቅዱን 95 በመቶ እንዲሆን አድርጓታል ይላሉ። ከማዕድን ዘርፉ ከሮያሊቲ ክፍያም እንዲሁ በተያዘው በጀት ዓመት 43 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ በሩብ ዓመቱ 12 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘት መቻሉን አመላክተዋል።

‹‹የማዕድን ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል ነው›› የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊ፤ በተያዘው በበጀት ዓመት ለ8ሺ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፤ በሩብ ዓመቱ ለ878 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ ማዕድን ልማት ዙሪያ ላይ በርከት ያሉ ተግዳሮቶች እንዳሉ የሚገልጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከእነዚህም መካከል የአካባቢ ወጣቶች ሰፊ ኢንቨስትመንት በሚጠይቀው የማዕድን ሥራ ፈቃድ ተሰጥቶአቸው ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ በአልሚዎች ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ መሆኑ ያነሳሉ። ይህንን ተግዳሮት ለመፍታትም ወጣቶችን ከአልሚዎች ከሚገኘው የወጣቶች ፈንድ በሚል ልዩ መመሪያ እንዲወጣ በማድረግ ፈንዱን ወጣቶቹ በሚፈልጉት የሥራ ዘርፍ እንዲንቀሳቀሱበት በሚመለከታቸው አካላት አስተባባሪነት ተግባራዊ ለማድረግ የመመሪያውን የማጽደቅ ሥራ መሥራቱ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኮንስትራክሽን ማዕድን አምራቾች የገበያ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህም በነፃ ተጠቃሚነት ሽፋን ምርቱን እያወጡ የሚሸጡ በፌዴራል ደረጃ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በሚሰሩ አንዳንድ ኮንትራክተሮች የሚስተዋል በመሆኑ አመላክተዋል። ለዚህም ስለተወሰደው የመፍትሔ ርምጃ መኖሩን ጠቅሰው፤ በነፃ ተጠቃሚነት ስም የኮንስትራክሽን ማዕድንን ለግል ጥቅም የሚያውሉ አካላትን በተመለከተ ለወረዳ አመራሮች ተገቢውን ግንዛቤ የመፍጠርና የማዕድን ዘርፍ መዋቅሩ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ አቅጣጫ በማስቀመጥ እግሩን ለመፍታት እየተሞከረ እንደሆነ ነው ምክትል ኃላፊው ያስረዱት፡

ለውጭ ምንዛሪ ጠቃሚ የሆኑ የጌጣጌጥ የከበሩ ማዕድናት በክልሉ የሚገኙ ቢሆንም ከመሠረተ-ልማት እና ከማምረቻ ቴክኖሎጂ ውስንነት የተነሳ በሙሉ አቅም አምርቶ ለመጠቀም ያለመቻሉም አንስተው፤ ይህን ተግዳሮት ለመቅረፍ አቅም ያላቸው ባለሀብቶችን ከጌጣጌጥ ማዕድን አምራቾች ጋር እንዲቀናጁ በማድረግ ምርቱ እንዲወጣ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ምክትል ቢሮ ኃላፊው በተግዳሮትነት የሚነሳው ለሀገር ውስጥ አልሚዎች የኢንዱስትሪ ማዕድን ፈቃድ የመስጠት ሥልጣኑ የክልሎች ሆኖ ሳለ በፌዴራል ማመልከቻዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ክልሎች አልሚዎቹን ተቀብለው ለማስተናገድ አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል። ለዚህም ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በክልል ሊስተናገዱ የሚገባቸውን ክልሉ እንዲያስተናግድ ማድረግ እንዳለባቸው በደብዳቤ የማሳወቅ ሥራ እንደተሰራ ይገልጻሉ።

የድንጋይ ከሰል አምራቾች በቀጥታ ለፋብሪካዎች የማቅረብ እድል ባለማግኘታቸው በመሃል ያሉ በአቅራቢነት ስም የሚታወቁ ከፋብሪካዎች ጋር ውል እየገቡ ምርቱ የሚሄድ በመሆኑ ከማዕድን ምርት ሽያጭ ክልሉ የሚያገኘው ገቢው ዝቅትኛ እንዲሆን አድርጎታል ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ የድንጋይ ከሰል የሚመረትበት ወረዳ ከሮያሊቲ የሚያገኘውን ገቢ ለጊዜው በፋብሪካ ሽያጭ ዋጋ እንዲሰበስብ በክልሉ በኩል አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

‹‹በክልሉ ሰላም የሰፈነበት መሆኑ እንዲሁም ያለው ሰፊ የሰው ኃይል ለማዕድን ልማቱ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥሩ ናቸው›› የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በክልሉ ማዕድናት በማምረት ረገድ ኩባንያዎችና አነስተኛ አምራች ማህበራት ተደራጀተው የሚሰሩ እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይ በከበሩት ማዕድናት ላይ በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩ አምራቾች መኖራቸው ጠቅሰው፤ በከበሩ ማዕድናት አምራቾች ትስስር ስላልተፈጠረላቸው በቂ ገበያ ስለማያገኙ በችግር እንደሚፈተኑ ይገልጻሉ።

የከበሩ ማዕድናት ላይ የሚነሳው የገበያ ትስስር ችግር እንዳለ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ በሕገ ወጥነትም እንደሚጠቁሙ አመላክተዋል። የከበሩ ማዕድናት በቀላሉ ማዘዋወር ስለሚቻል የከበሩት ማዕድናት በሕገ ወጥ መንገድ ስለሚወጡ ያለው የገበያ ትስስር የላለ እንዲሆን እንዳደረገውም አስረድተዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደሚሉት፤ የከበሩ ማዕድናት የሚያመርቱና የሚያዘዋወሩ ሕጋዊ ፍቃድ ያገኙ አምራቾች አሉ። አሁን ላይ ችግሩ ጎልቶ የሚታየው ታችኛ መዋቅር በወረዳ ላይ የሚገኝ ነው። በክልሉ እስከታች ያሉ መዋቅር ድረስ ወርዶ ግንዛቤን የማስፋት ሥራ እየተሰራ ነው። በሕገወጦች ላይም ርምጃ ለመውስድ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሥራዎች እየሰሩ መሆኑን ያስረዳሉ።

‹‹በከበሩ ማዕድናት ልማት ላይ አንዳንዶቹ ፍቃድ ያላቸው አካላት ቢሆን የሚሰሩት ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓትን ተከትለው አይደለም›› የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ እነዚህም ቢሆን ሕጉ በሚፈቅድላቸው አሠራር መሠረት መሠራት እንዲችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰራ እንደሆነ ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከወረዳዎች በሚላከው ሪፖርት መሠረት በሕገ ወጥነት መንገድ ማዕድናት ሲያዘዋወሩ የተገኙት ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንደተወሰደ እንደሆነም አስታውቀዋል።

በድንጋይ ከሰል አምራቾች ላይ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር ስለፈጠሩ እምብዛም የገበያ ትስስር ችግር አይስተዋልም። ነገር ግን በድንጋይ ከሰል ላይ የሚነሱ የጥራት ችግሮች እንዳሉ የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከጥራት አንጻር የሚነሱ ሁለት ዓይነት ችግሮች መሆናቸው ይገልጻሉ። አንደኛው ከአመራረት ዘዴ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የጥራት ጉድለት ችግር ነው። በዘልማድና በባሕላዊ መንገድ የሚያመርት መሆኑና ማዕድናቱ ሲያወጡ ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ከሌሎች ባዕድ ነገሮች ጋር የሚቀላቀልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰው፤ ይህንን ችግር ለመፍታትም የአመራራት ዘዴን በመቀየር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲመረቱ እየተደረገ እንደሆነም አመላክተዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰልን የሚጠቀሙት ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ የተመረተውን የድንጋይ ከሰል ምርት የጥራት ጉድለት አለው በማለት ከውጭ ለማስገባት የመሞከር ነገር ይስተዋላል ይላሉ። መንግሥትም በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከውጭ የሚመጣው የድንጋይ ከሰል ምርት በሀገር ውስጥ ምርት እንዲተካ የማድረግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ቢሆንም እነዚህ ፋብሪካዎች ግን የመቀበል ፍላጎታቸው በጣም አነስተኛ ነው ሲሉም ያነሳሉ። ለዚህም ፋብሪካዎቹ እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት ጥራት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ጥራት ላይ በደንብ ከተሰራ የውጭ ምንዛሬ ማዳን የሚቻልበት እድል መኖሩን ይገልፃሉ።

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ሃሳብ፤ በተለይ የድንጋይ ከሰል በክልሉ ያለው ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ ያለው የድንጋይ ከሰል ላይ በጂኦሎጂካል ሰርቬይ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው የኢነርጂ ይዘቱ ከውጭ ከሚገባው በብዙ የሚተናነስ አይደለም። ጥሩ ይዘት ያላቸው የድንጋይ ከሰል ዓይነቶች አሉ። ይህ ሆኖ ሳለ በፋብሪካዎቹ ጥራት ላይ የሚቀርበው ቅሬታ የሀገር ውስጥ የሚመረተው ጥራት ችግር ኖሮት ሳይሆን የፋብሪካዎች ፍላጎት ውጭ የማስገባቱ ላይ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መገደዳቸውን ነው ያስረዱት።

‹‹በክልሉ የድንጋይ ከሰል ለማልማት 43 የሚሆኑ አምራቶች ፍቃድ ወስደው ልማቱ ላይ ተሰማርተዋል›› ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከእነዚህ ውስጥ ግን አሁን ላይ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ በማድረግ የማምረት ሂደት ላይ ያሉ 12 ያህሉ እንደሆነ ይናገራሉ። የተቀሩት ግን እስካሁን ወደ ማምረት ያልገቡ ሲሆን ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በዘርፍ ላይ ተሰማርተው ማዕድናት ለማምረት ፍቃድ የወሰዱት ሆነ በምርመራ ሂደት ላይ ያሉት በርካታ አምራቾች መኖራቸው ጠቅሰው፤ ቁጥራቸው ብዙ ከመሆኑ በላይ ተበታትነው በየራሳቸው የሚንቀሳቀሱ መሆኑ ሂደቱ ከባድ አድርጎታል ይላሉ። እነዚህ ውስጥ የተወሰኑቱ በአንድ ላይ በጋራ ሆነው ቢሰሩ የተሻለ ማምረት የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ አንስተው፤ በቀጣይም አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው ትልቅ አቅም ፈጥረው ወደ ልማቱ ቢገቡ የተሻለ እንደሚሆን ለማስገንዘብ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከባለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል። የማዕድን ዘርፉ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጠባቸው አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። ይሄ ርምጃ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የሚቆጠር ነው። ሌላው ሰፊ የሰው ኃይል እና በተለይ ወጣቱ ኃይል መኖሩ ሌላኛው ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው። በመሆኑም ባለሀብቱን ከሰው ኃይሉ ጋር በማስተሳሰር በዘርፉ እንዲሰማሩ ማድረግ ይቻላል።

‹‹ክልሉ በአንጸራዊነት ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት ክልል ነው›› ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ሕዝቡም ልማትን የተጠማ ስለሆነ በማዕድን ዘርፉ ልማት ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ አልሚ ባለሀብቶችም ሆነ ግለሰቦች ወደ ክልሉ መጥተው መሥራት እንደሚችሉ ይገልጻሉ። ለዚህም ደግሞ ክልሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ የማዕድን ዘርፉ ላይ ኢንቪስት ማድረግ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2016

Recommended For You