የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እአአ ከ2014 አንስቶ የትኛውንም አህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በሜዳው እንዳያስተናግድ መታገዱ ይታወቃል።ቡድኑ ጨዋታዎችን ከሚያደርግባቸው ስታዲየሞች መካከል አንዱ የሆነው የባሕርዳር ስታዲየምም ይኸው ዕጣ ደርሶት ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ርቆ ቆይቷል።በቅርቡ ግን የአማራ ክልል መንግሥት ስታዲየሙ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ በተቻለ ፍጥነት ይጠናቀቅ ዘንድ ተጨማሪ በጀት በማፅደቅ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ጀምሯል። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በባለሙያዎቹ አማካይነት በተለያዩ ጊዜያት ምልከታዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ ሂደቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ይፋ አድርጓል።
ከፕሮጀክቱ ባለቤት የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ፤ እንዲሁም፣ ከተቋራጮች ጋር በመሆን በስፍራው ተገኝተው ምልከታውን ያደረጉት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መምሪያ ኃላፊ አቶ አምሐ ተስፋዬ ሲሆኑ፤ ስታዲየሙ የካፍ መመዘኛን በጠበቀ መልኩ ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን፣ በተለያዩ ምዕራፎች ተከፍሎ እየተከናወነ እንደሚገኝ፤ የማሻሻያ ሥራውም በመጫወቻ ሜዳ፣ በልምምድ ሜዳ፣ በስታዲየም ዙሪያ፣ በተለያዩ ክፍሎች እና የመስመር ዝርጋታዎች ላይ ያተኮረ እንደ ሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በሜዳዋ እንዳታደርግ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ክልከላው እንዲደረግባት ካደረጉ ጉዳዮች መካከል ዋንኛው የመጫወቻ ሜዳን የሚመለከት መሆኑ ይታወቃል።በዚህም በሃገር ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ መገንባት የሚችል ድርጅት ባለመኖሩ በውጪ ሃገራት ባለሙያዎች እንድታሠራም ግብረ መልስ ተሰጥቶ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።በመሆኑም የባሕርዳር ስታዲየም ሜዳ የፊፋ እና ካፍ ፍቃድ ባለው የፈረንሳይ ድርጅት ግሪጎሪ ኢንተርናሽናል እየተከናወነ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ግንባታው ከዚህ በፊት የነበረውን ሜዳ ሙሉ ለሙሉ ያነሳ ሲሆን፤ በዚህ ወቅትም የፍሳሽ መስመሮች ዝርጋታ እየተሠራ ይገኛል። በተጓዳኝም የአፈር እና አሸዋ ምርመራ ተጠናቆ ዝግጁ በመሆኑ የመስመር ዝርጋታው እንደተጠናቀቀ የሚሞላ ይሆናል። ቀጣዩ ሥራ ሜዳውን በሣር መሸፈን ሲሆን፣ የሣር ዘር ከውጪ ለማስገባት በሂደት ላይ ነው። ዘሩ የኢትዮጵያን መመዘኛዎች ሟሟላቱ በግብርና ሚኒስቴር ካረጋገጠ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል።እንደተረጋገጠም፣ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ሙቀት እና ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያለውን የአየር ሁኔታ መቋቋም የሚችል የሣር ዝርያ በሦስት ወራት ውስጥ ዝግጁ ይሆናል። የሜዳውን ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኘው ተቋም የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ አይቮሪኮስትን ጨምሮ በካሜሩን፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋልን በመሳሰሉ ሀገራት መሰል ፕሮጀክቶችን እየሠራ ይገኛል።በመሆኑም በውሉ መሠረት ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ ሠርቶ እንደሚያስረክብ አረጋግጧል።
ከዋናው የመጫወቻ ሜዳው በተጨማሪም ግንባታው ሁለት የልምምድ ሜዳዎችን ሲያካትት፤ በግሪጎሪ አማካኝነት ከመጫወቻ ሜዳው ጋር በተመሳሳይ የጥራት ደረጃ የሚከናወን ይሆናል። የሁለቱም የልምምድ ሜዳዎች የመታጠቢያ እና የልብስ መቀየሪያ ክፍሎች ተሠርተው የተጠናቀቁ ሲሆን፤ የፓውዛ ተከላ ተጀምሯል። አጥሮች እና መጠነኛ ተመልካች የሚይዝ የብረት የተመልካች መቀመጫም እየተሠራለት ይገኛል። ከሜዳዎቹ ሥራ ባለፈ ወደ ስታዲየሙ የሚያስገቡ በሮች ከሁለት ወደ አምስት እንዲያድጉ ተደርጓል። ተመልካቾችና ሌሎች ባለሙያዎች ከውጪ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ወደ ቪአይፒ፣ ቪቪአይፒ፣ ሚዲያ እና የእግር ኳስ ቡድኖች መኪና ማቆሚያ መግቢያዎች እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ የደጋፊዎች መኪና ማቆሚያ እና እግረኛ መግቢያም ተለይቶ ሥራዎች ተጀምረዋል።
በስታዲየሙ ከዚህ ቀደም በካፍ አስተያየት የተሰጠባቸው አስፈላጊ ክፍሎች ግንባታቸው እየተከናወነ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የነበሩትንም ደረጃቸውን የማሳደግ ሥራ በመከናወን ላይ ነው። ስታዲየሙ በአንድ ጊዜ አራት ቡድኖችን ለማስተናገድ በሚያስችል መልኩ አራት መልበሻ ክፍሎች እና የዳኞች መልበሻ ክፍል ግንባታ እየተደረገለት ይገኛል። በቀጣይም የሊፍትና የተመልካች ወንበር ገጠማ፣ የስክሪን ገጠማ፤ እንዲሁም በምሽት ጨዋታ ለማድረግ የሚረዳ ፓውዛ ለመግጠም ዝግጅት ተጀምሯል።
ስታዲየሙ የማሻሻያ ግንባታውን ሙሉ ለሙሉ ሲያጠናቅቅም በካፍ መመዘኛ አራተኛ ላይ (የካፍ የመጨረሻ የጥራት ደረጃ መመዘኛን የሚያሟላ) ሆኖ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ማለት የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን (የአፍሪካ ዋንጫን ጨምሮ) እስከ ፍጻሜ ድረስ፤ እንዲሁም፣ የአፍሪካ የክለብ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በየጊዜው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና የመስክ ጉብኝት በማድረግ ክትትል እና ሙያዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የውጪ ሀገራት ተሞክሮ እንዲወሰድ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ይገኛል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም