ግጭት መፍቻዎችን ለሀገራዊ ሠላም

በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ከዘመናዊው የዳኝነት ሥርዓት ጋር ባልተናነሰ መልኩ ማኅበረሰቡ ለዘመናት ሲጠቀምባቸው ቆይቷል፤ አሁንም እየተጠቀመባቸው ይገኛል:: በእነዚህ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች አማካኝነት ማኅበረሰቡ ፍትሕ አግኝቷል፤ እያገኘም ነው:: አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በሀገሪቱ ለተከሰቱ ግጭቶች ማኅበረሰቡ በሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች የመዳኘት ፍላጎት እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ:: በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውና እነርሱን አጎልብቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተነግሯል::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪና መምህር ደሳለኝ አምሳሉ(ዶ/ር) እንደሚናገሩት የሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ውጤታቸው ከፍ የሚልበት ዓውድ አለ:: በተለይ ግጭቶቹ አካባቢያዊ፣ ሀብትን መሠረት ያደረጉና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የሌለባቸው ከሆኑ መፍትሔ ሊያመጡ ይችላሉ:: ከዚህ ባለፈ ግን ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች አሁን ባሉበት ሁኔታ በአሠራር፣ በሕግና በሌሎች መንገዶች ሳይጠናከሩ ሀገራዊ የሆኑ ችግሮችን ለብቻቸው ሊፈቱ አይችሉም:: የራሳቸውን አስተዋፅዖ ግን ሊያበረክቱ ይችላሉ::

ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች አሁን ባለው ሁኔታ ለብቻቸው ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ ሊያመጡ የማይችሉባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ:: ከእነዚህም ውስጥ በበርካታ አካላት የበርካታ ፍላጎቶች መኖር፣ የተለያዩ የታሪክና የፖለቲካ ትርክቶች መንሰራፋት፣ የጉዳዮች ባለቤትና ተዋንያን መብዛት፣ በሀብት ክፍፍል ላይ የተለያየ አቋም መያዝ፣ በውስብስብና ታላላቅ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም አለመኖርና ሌሎችም ናቸው::

በሀገሪቱ በርካታ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ቢኖሩም የግጭት መፍቻ መንገዶቹ እንደ የአካባቢዎቹ ሁኔታና እንደ ሕዝቡ ፍላጎት የሚለያዩ እንደ መሆናቸው፤ እንዲሁም አንዱ የግጭት መፍቻ መንገድ በሌላው አካባቢ ሊሠራ የማይችልበት ሁኔታ በመኖሩ ሁሉም የግጭት መፍቻ መንገዶች ለሀገራዊ ችግር መፍትሔነት ሊውሉ አይችሉም:: ግን ደግሞ ለመፍትሔው የየራሳቸው አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል::

ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታትና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ለማድረግ ሀገር በቀል ግጭቶችን መጠቀም ይቻላል:: ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን የግጭት መፍቻ ዘዴዎቹን ለአካባቢያዊ ችግር መፍቻ መጠቀም ሲቻል ነው:: አካባቢያዊ ችግሮች ሲፈቱ ሀገራዊ ችግሮችን በሌላ መንገድ ለመፍታት ያስችላል::

በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ሀገር በቀል ግጭት መፍቻ መንገዶችን ማሳደግ ይቻላል:: በሀገሪቱ ካሉ ከመቶ በላይ የሚጠጉ የግጭት መፍቻ መንገዶችን በማሳደግ ሀገራዊ ግጭቶችን መፍታትና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ይቻላል:: እነዚህ የግጭት መፍቻ መንገዶች ምንም እንኳን አተገባበራቸውና አካባቢያዊ ዓውዳቸው የሚለያይ ቢሆንም የጋራ የሚያደርጋቸው እሳቤና ግብ አለ:: ይኸውም ሰላም፣ መከባበር፣ አብሮ መኖር ….. እና የመሳሰሉት ናቸው::

ስለዚህ ሀገር በቀል ግጭት መፍቻ መንገዶች የአተገባበራቸው ልዩነት እንዳለ ሆኖ የጋራ የሚያደርጋቸውን ነገር በማሳደግና ወደ ላይ በማምጣት ሀገራዊ የሆኑ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያን የባሕል እሴት የጠበቁ ግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን መገንባት ይቻላል:: በእነዚሁ የግጭት መፍቻ መንገዶችም ሀገራዊ ችገሮችን መፍታት ይቻላል:: ሚናቸውም ከፍ ይላል:: ይሁንና ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች በሚፈለገው ደረጃ አላደጉም::

ደሳለኝ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ሁሉንም ሀገራዊ ጉዳዮች ይፈታሉ ማለት አይደለም:: ነገር ግን፣ መፍታት የሚችሏቸውን ችግሮች እንዲፈቱ እድል መስጠት ያስፈልጋል:: ማሳደግ ያስፈልጋል:: በዚህ ላይም ሰፊ ሥራ መሥራት ይገባል:: ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር እንድትወጣና ሰላም እንዲረጋገጥ ሀገር በቀል የግጭት ሥርዓቶችን አሳድጎ ጥቅም ላይ ከማዋል በዘለለ ከዝቅተኛ አስከ ከፍተኛ ድረስ ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል::

ሀገራዊ ችግሮቹ የታሪክ፣ የድህነት፣ የሥልጣን ክፍፍል፣ ያልታወቀና የማንነት፣ የክልልነት፣ የፖለቲካና ሌሎችም ሊሆኑ ይችላሉ:: እነዚህ ችግሮች በሕግ ውስጥም፤ በአተገባበር ላይም ያሉ ናቸው:: ለአብነትም የማንነትና ያልታወቀ ጥያቄን በተመለከተ በተቀመጠ መስፈርት መሠረት ሕገ መንግሥቱ ይፈቅዳል:: በተመሳሳይ ክልል ለመጠየቅ ወይም ደግሞ ከቀበሌ ወደ ወረዳ ከፍ ለማለት፣ ወረዳ ያለው ዞን ለመጠየቅ፣ ዞን ያለው ክልል ለመጠየቅ፣ ክልል ያለው ሀገር ለመሆን ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ ሆነው በሕጉ መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ ቀላል ነው::

ስለዚህ አሁን ያለውን ሀገራዊ ችግር ለመፍታትና በዋናነት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ለማድረግ በሕጉ በኩል ያሉ አሠራሮችን ማስተካከል ያስፈልጋል:: በአተገባበር በኩልም ቢሆን ‹‹እኔ ልብላ፣ እኔ ልኑር፣ እኔ ልሰማ፣ እኔ ልደመጥ›› የሚለውን ሀሳብ በመተው አብረን እንኑር፣ አብረን እንሥራ፣ አብረን እንለወጥ፣ አብረን እንብላ፣ አብረን እንደመጥ›› የሚሉትን እሳቤዎች ማስቀጠል ያስፈልጋል:: ይህም ማለት ሙስና፣ ብልሹ አሠራር፣ የአንድ ብሔር የበላይነትና ሌሎችንም ማስወገድ ይገባል:: ከሁሉም በላይ፣ ለሀገራዊ ችግር መፍትሔ ለማምጣት ግን ቁርጠኝነት ያስፈልጋል:: ለዚህም የጋራ መተማመን ሊኖር ይገባል::

በአፈሙዝ ጊዜያዊ ሠላም ሊመጣ ይችላል:: ነገር ግን ዘላቂነት ያለው ሠላም በአፈሙዝ ሊመጣ አይችልም:: ይህም በብዙ ሀገራት ውስጥ ተሞክሮ ውጤቱ ምን እንደሆነ በሚገባ ታይቷል:: ከአፈሙዝ ይልቅ ጠረጴዛ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ይዞ መምጣት ይችላል:: ስለዚህ ከዚህ የጠረጴዛ መፍትሔ በዘለለ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን በማሳደግና ለሀገራዊ መፍትሔ በመጠቀም የሚፈለገውን ሠላም ማረጋገጥ ይቻላል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You