ብዙ ጭንቀቶች እያለፉም ቢሆን ሕይወት ይቀጥላል። ተሰማ መንግሥቴ፣ ገብረየስ ገብረማሪያም እና ዘውዴ መታፈሪያ አንዳንዴ በየተራ ብዙ ጊዜ ደግሞ በአንድ ላይ ብዙ የጭንቀት ጊዜዎችን አልፈዋል። አንድ ሰሞን ተሰማ ስለ ቤተሰቡ ስለ ዘመዶቹ በአጠቃላይ ስለ ሀገሪቷ ሁኔታ አብዝቶ ሲጨነቅ ነበር። በሌላ በኩል አንድ ሰሞን ገብረየስም ስለ ዘመዶቹ በተለይም ትግራይ አካባቢ ስላሉ ወገኖቹ አብዝቶ ሲያዝን እና ሲያለቅስ ነበር። የዘውዴ ደግሞ ተደጋጋሚ ነው። ዘውዴ ጭንቀቱ ቀለል የሚልለት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። በአብዛኛው ስለራሱ እና ስለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ስለአጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታ አብዝቶ በተደጋጋሚ ይጨነቃል።
ሰሞኑን ምንም እንኳ በበዓል ሰሞን መደሰት ቢኖርባቸውም ሶስቱም ጭንቀት ውስጥ ናቸው። እንደልማዳቸው በማምሻ ግሮሰሪ ተገናኝተዋል። የበዓል ሰሞን በመሆኑ ግሮሰሪው ሞቅ ብሏል። እነርሱ ግን ተጨንቀዋል። ገብረየስ ‹‹ወገኖቼ በርሃብ ሊያልቁ ነው›› ብሎ ይብከነከናል። ተሰማም ‹‹ዘመዶቼ በዘራፊዎች እየተሰቃዩ ከነገ ዛሬ ታፍነው ገንዘብ እጠየቃለሁ›› ብሎ ስጋት ውስጥ ገብቷል። ዘውዴም በየቀኑ ቀያቸው አካባቢ ባለው ችግር ሳቢያ እከሌ ሞተ እየተባለ የሚሰማው ዜና ከዕለት ወደ ዕለት እርሱን የተለየ ዕብደት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
ሶስቱም ማምሻ ግሮሰሪ ተገናኝተው ጭንቀታቸውን አንዱ በሌላው ላይ ይተነፍሳል። አሁን ግን አንዱ ታግሶ የሌላውን እያዳመጠ አይደለም። አንዱ ሲናገር ሁሉ ይሰማል፤ ሁሉ ሲናገር ማን ይሰማል? ይባላል። ይህ መደማመጥ እና መግባባት እንዲኖር ተራ ጠብቆ ማውራት ይገባል ለማለት ያህል ቢሆንም፤ እነተሰማ ግን በየራሳቸው ጭንቀት ውስጥ ተወጥረው ከመናገር ይልቅ ዝምታን መርጠው መቆዘሙን ተያያዙት።
ነገር ግን ዝምታቸውም ብዙ አዋጭ አልሆነላቸውም። ሶስቱም የውስጥ ጭንቀታቸው ከሚጠጡት ቢራ ጋር ተቀላቅሎ ሶስቱም ራሱን እንዳመመው ሰው ፊታቸው አብጦ ዓይናቸው ተንጠልጥሎ የተከፋው ፊታቸው የተደሰተ ሰውን ከማስጨነቅ አልፎ ያስኮርፋል። ለተሰማ ቢራ የከፈተው አስተናጋጁ ይርጋ ‹‹ በዓል እኮ ነው፤ ምነው ተከዛችሁ?›› ብሎ ጠየቀ። ዘውዴ ‹‹የምን በዓል ነው? እኛ በእውነት እግዚአብሔርን መውደድ የማንችል ሰዎች የፈጣሪን የኢየሱስ ክርስቶስን የመወለድ በዓል ለምን እናከብራለን? ›› ሲል ጥያቄውን በጥያቄ መለሰ። ይርጋ ለመመለስ አቅሙም ጊዜውም ስላልነበረው መሰስ ብሎ ወደ ሥራው ተመለሰ።
ገብረየስ የዘውዴን ሃሳብ በሚያጠናክር መልኩ መናገር ጀመረ። ‹‹ በርግጥም ኢትዮጵያውያን ስለ እግዚአብሔር ደጋግመን እንናገራለን። ነገር ግን ድርጊታችን እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው የሚፈፅመው አይደለም። እንደውም ብዙዎቻችን በአፍ እንጂ ከልብ በመነጨ ስሜት እግዚአብሔርን የምንወደው አይመስለኝም። የማንወደው ከሆነ ደግሞ ጓደኞቻችንን እና በአጠቃላይ የሰው ልጆችን ሙሉ በሙሉ መውደድ አንችልም። ከሰማይ ወርዶ በጠባብ ማሕፀን የተወሰነው ፈጣሪ ግን፤ የተወለደበት ትልቁ ምክንያት ሀጢያተኛውን የሰውን ልጅ ለማዳን ነው። የርህራሄና የፍቅር አምላክ የሆነው ጌታ የመወለዱን ልደት ለማክበር ቀድመን እግዚአብሔርን መውደድ እና ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ራሳችንን መግዛት ይኖርብናል። ሰው ሆኖ የሰውን ልጅ ከዘላለም ሞት የታደገውን አምላክ ልደቱን ለማክበር እኔም ብቁ ነኝ ብዬ አላምንም።›› ሲል ሃሳቡን ገለጸ።
ዓይኑን ቡዝዝ አድርጎ ፈዞ የገብረየስን ንግግር ሲያዳምጥ የነበረው ዘውዴ፤ ‹‹ አይ ገብረየስ እኛን ክፉዎቹን ክርስቶስን ለመስቀል የተፎካከርን ግብዞች የእኛን ፍቅር ከክርስቶስ ፍቅር ጋር ታነፃፅረናለህ? ›› ሲል ጠየቀና ሃሳቡን ቀጠለ። ‹‹ ክርስቶስ ለእኛ ሲል ፍፁም ሰው ሆኖ የእኛን መከራ ሊቀበል ከመወለድ በተጨማሪ በሽተኛዎችን ሲፈውስ፣ የተጨቆኑትን ከፍ ሲያደርግ፣ በበጎነት ሲመላለስ፣ ትዕግስትን ሲያስተምር፣ ራስ ወዳድ አለመሆንን ሲያሳይ እና ሲሰብክ፣ በመጨረሻም ይቅር ባይነቱን በመስቀል ላይ ሆኖ የሰቀሉትን ወንበዴዎች ጨርስልኝ እንደማለት ‹የሚያደርጉትን አያውቁትምና፤ ይቅር በላቸው› ያለ የፍቅርን ጥግ ያሳየ አምላክ ነው። እኛ ግን እርስ በእርስ በምናደርገው የቀን ተቀን ግንኙነቶች ውስጥ ሳይቀር ከፍቅራችን ይልቅ ጎልቶ የሚታየው ብዙ ሰዓት የሚይዘው ጠባችን ነው። የእኛ መገለጫ ባህሪያቶች ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
በሁሉም ግንኙነቶቻችን ውስጥ በተለይም ከግለሰባዊ ባሻገር በቡድናዊ ግንኙነት ውስጥ የምናሳያቸው ባህሪዎች በልባችን ውስጥ ፍቅር እንዳለ የሚያሳዩ አይደሉም። ሰው ሆነን ደግ ሆኖ ሰዎችን ከመርዳት በተቃራኒው ባልሰሩት ጥፋት ሰዎች ሲቀጡ ቅንጣት ፀፀት የማይሰማን ጨካኞች፤ ትንሽ ደግነት እንኳ የሌለን ክፉዎች ነን። በርግጥም እግዚአብሔርን እና የሰው ልጆችን መውደድ ካልቻልን በዓሉን ማክበር አይገባንም።›› ብሎ አቀረቀረ።
ተሰማ በበኩሉ ‹‹እኔ ግን እናንተ እንደምትሉት አይመስለኝም። ለሰው ልጅ ፍቅር የሚሰጡ እና በጎ ነገር የሚያደርጉ ሞልተዋል።›› ሲል ዘውዴ ግን ከተሰማ ፍፁም በተቃረነ መልኩ፤ ‹‹ ተው እንጂ ተሴ ከሚሊየን አንዱ የሚያደርገውን በመጥቀስ መገለጫችን ነው ማለት አይቻልም። ብዙሃኑን አስበህ መናገር ይሻላል። እኛ እኮ እግዚአብሔርን እንወዳለን እያልን የአምላክን ልደት ለማክበር የምንሞከር ደፋሮች ብንሆንም፤ እውነታው ግን ደካሞች ላይ የምንበረታ ጨካኞች፤ የሞተን ሰው እንኳ ይቅር ለማለት የምንቸገር ግብዞች፤ አልፈን ተርፈን የሞተን የምንሰቅል አረመኔዎች ነን። ›› እያለ እየተንገሸገሸ እየተንቀጠቀጠ ሲናገር፤ ገብረየስ ፊቱን ቅጭም አድርጎ ‹‹ ብዙሃኑን መኮነን እንኳ ትክክል አይደለም። ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ደካማን የማገዝ ባህል ያለው ለሴት እና ለሕፃን የሚሳሳ፤ ዕድሜው የገፋ ሰውን አብዝቶ የሚያከብር መሆኑን መካድ አትችልም።›› አለው።
ተሰማ ገብረየስን በመደገፍ፤ ‹‹ማየት የምንችለው ማየት የምንፈልገውን ነው። ዘውዱ ሁልጊዜም የሚታዩት አጥፊ የሆኑ ክፉ ሰዎች ብቻ ናቸው። ደግ ሰዎች ሲኖሩ አውቆ ሳይሆን ሳያውቅ ሳያይ ያልፋቸዋል። የሚሠሩትን አያስተውልም። ክፉ ሰዎችን ደግሞ ተከታትሎ ያያቸዋል። ስለዚህ የሰው ልጅ ሁሉ ክፉ ይመስለዋል። ሰው ክፉ ብቻ ሳይሆን፤ ደግም ነው። ለሰው ልጅ በብዙ መልኩ ክብር ያለው ሰው እንዳለ ሁሉ በብዙ መልኩ ሰዎችን በማዋረድ ሥነልቦና ውስጥ ያደገ ያንንም እየተገበረ የሚኖር እንዳለ አይካድም።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ለሰዎች ክብር የመስጠት ይቅር የማለት ባህል አለ። እንደውም ከእነ አባባሉ በሽማግሌ የታረቀ በፀሐይ የደረቀ ይባላል። ይህ የሚባልበት ምክንያት ሽማግሌ ያስማማው ዕርቅ የሠመረ ይሆናል በሚል እምነት ነው። ሰው ይህንን የሚለው ለታላላቅ ሽማግሌዎች አክብሮት እና ፍቅር ስላለው ነው። ደግሞም ጠብ ቢኖርም በይቅርታ በፍቅር ይተካል። ስለዚህ ሙሉ ለሙሉ ፍቅር የለም። የገና የአምላክ ፍቅር የተገለጠበት በዓልም መከበር የለበትም ማለት አይገባም።›› ሲል ተናገረ።
ዘውዱ ግን ሃሳቡ ፍፁም ከተሰማ የተቃረነ ነው። ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ አሁን የክርስቶስ መወለድን ለማክበር የሚያበቃ ፍቅር የለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ፍቅር ሳይኖር በዓል አከብራለሁ ማለት ራስን መሸንገል ነው። በዓል የሚያስደስተው ከተግባር ጋር ሲጣመር ነው። የኢትዮጵያ በዓል ግን በተለይ አሁን አሁን ከተግባር ጋር የተጣመረ ሳይሆን የተቃረነ ነው። ግፍ እየፈፀሙ በዓል መከበር የለበትም።›› ሲል ያመነበትን ተናገረ። አንድ ወንድም ቢታሠር አንድ ቀን ለመጎብኘት ወደ እስር ቤት ለመሔድ አንሞክርም። የተወሰነ ሰው ግን ይህንን ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ይሆናል ካለ በኋላ፤ ስሜቱን በማረጋጋት አንድ ታሪክ ሊነግራቸው ወደደ።
ከብዙ ዓመታት በፊት ስለተከሰተና አንድ የጎረቤት አርሶ አደርን ስለሚመለከት ጉዳይ መግለፅ ጀመረ። ጎረቤታሞች ብቻ ሳይሆኑ ጥብቅ ጓደኛሞች የነበሩት ወንዶች ሚስቶቻቸው በአብዛኛው ስምምነት ስላልነበራቸው በእነርሱ መጣላት ይጨነቁ ነበር። ‹ኧረ እባካችሁ ለምን ፍቅር አይኖራችሁም ? › እያሉ ይወቅሷቸው ነበር። አንድ ቀን አንዱ አርሶ አደር በጤፍ ማሳ የጎመራው የጓደኛው ይዞታ ላይ ከብት ሲገባ አይቶ ዝም ይላል። የጓደኛው ሚስት ይህንን አይታ ትታዘባለች። በባሏ ይዞታ ውስጥ ያለውን ከብት የባሏ ጓደኛ እንዲሁም ጎረቤት የሆነው ሰው ለማውጣት አለመፈለጉ የደረሰው ጤፍ መርገፉ እና በዚህም ምክንያት ለረሃብ የሚጋለጡበትን ሁኔታ መከላከል እየቻለ የባሏ ወዳጅ ይህን አለመሞከሩ እጅግ አበሳጫት። ለራሷ ‹እነርሱ ፍቅር ሳይኖራቸው ፍቅር ይኑራችሁ ይሉናል።› ብላ ታዝባ ዝም አለች።
ያየችውን ለባሏ ለመንገር አሰበችና ተወችው። ባሏ በበኩሉ በዛው ሰሞን ከአካባቢው ርቆ ሔዱ ሲመለስ ለጓደኛው ስጦታ ይዞ መጣ። ለመስጠት ሲነሳ ግን ሚስቱ አልፈቀደችለትም። ባል የሚስትን ምክንያት ባያውቅም ነገር ግን ገፍቷት መሔድ አልወደደምና ስጦታ መስጠቱን ተወው። በጓደኛው ማሳ ላይ ከብት ሲገባ ተመልክቶ ያልተከላከለው አጥፊው አርሶ አደር፤ ውሎ አድሮ በድርጊቱ ተፀፀተ። ብዙም ሳይቆይ ይቅርታ ለመጠየቅ ወሰነና ወደ ጎረቤቱ ቤት አመራ። እንደደረሰ ጓደኛው እግር ላይ ወድቆ ‹ ተጸጽቻለሁ፤ አጥፍቻለሁ ይቅር በለኝ› ብሎ ተማፀነ። ጓደኛው ግን ጥፋቱን አላወቀምና ይቅር ብዬሃለሁ ተነስ ብሎ አስነሳው። ካስነሳው በኋላ ምን እንደፈፀመ ሲጠይቀው የፈፀመውን ስህተት ነገረው።
እኔ በርሃብ እንድሰቃይ የፈረደብኝ ሰው በፍፁም ይቅርታ አይገባውም ሲል አሰበ። ‹ፍፁም ይቅር አልልህም› አለ። ያንን ያደረገው ሰው አሁን ሞቷል። ይቅርታ አላደርግም ያለው ሰው አሁንም በሕይወት አለ። አሁንም ለሞተው ጓደኛው ይቅርታ እንዳላደረገለት በዚህም እንደማይፀፀት ይናገራል። እኛ ጥሩ ብንመስልም ክፋታችን ይሔን ያህል ነው። ተራውን ነገር ይቅር ለማለት የሚያዳግተን ነን። ይሔ አርሶ አደር ቀድሞም ቢሆን ሲያስመስል እንጂ ለጓደኛው በቂ ፍቅር አልነበረውም። ይህ ተራ ጉዳይ ነው። ተለቅ አድርገን ስናየው ደግሞ ራሳችን የሰው ሕይወት ማጥፋት፤ ወይም የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት እንሆናለን። አንፀፀትም። ብንፀፀትም ይቅርታ ብንጠይቅም ይቅር የሚለን የለም። በሌላ በኩል የበደሉንን ይቅር ለማለት ዝግጁ አይደለንም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆነን የፍቅር በዓልን፤ ዓለምን ለማዳን ሲል የተወለደውን አምላክ ልደቱን እናክብር ማለታችን እኔ እንደሚመስለኝ ማሾፍ ነው።›› በማለት በዓሉን ለማክበር ብቁ ነን ብሎ እንደማያምን ተናገረ።
ተሰማ፤ ‹‹እኔ ግን ሙሉ ለሙሉ እንዲህ ክፉ እና ጨካኝ ነን ለማለት እቸገራለሁ። በርግጥ እኛ አምላክ ካሳየው ፍቅር ጋር ሊወዳደር ቀርቶ ሊታሰብ የሚችል ፍቅር አለን የሚል እምነት የለኝም። ነገር ግን ከረጅም ጉዞ እና ድካም በኋላ ሀብት ያፈሩ ሰዎች ሰዎችን ሲረዱ አይተናል። ፋብሪካ አቋቁመው ሠራተኞች ቀጥረው ለሰዎች የሥራ ዕድልን ሲፈጥሩ አስተውለናል። ተስፋ ቆርጠው መታከሚያ አጥተው ሞታቸውን ሲጠባበቁ የነበሩ በሽተኞችን አክመው እና አሳክመው እንዲድኑ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች መኖራቸውንም አስተውለናል። በየመንገዱ በፀጥታ ተስፋ ቆርጠው የሚያለቅሱትንም ከበው የሚያናግሩ፤ ያላቸውን ሰጥተው የሚያፅናኑ መኖራቸውንም አንክድም። ይህንን የሚያደርጉ ደግሞ ጥቂት ሳይሆኑ ብዙ ናቸው። ነገር ግን ይህንን ለማየት ክፉ ክፉውን ብቻ ሳይሆን ደግ ደጉንም ለማየት እና ለማዳመጥ መሞከር አለብን። ደግ ደጉ ከታየን ይህንን የፍቅር በዓል ለማክበር ብዙ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ።›› ሲል በተቃራኒው ያለውን እምነት ተናገረ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም