በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ላይ ለሃምሳ አምስት ዓመታት የሠሩት አቶ ኃይሉ ገብረማርያም፤ ሲቪል ኢቪዬሽንን ድሮ እና ዘንድሮን የምናይባቸው ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ሕይወታቸው መማሪያ፣ ማወቂያ እና ነገን መመልከቻም ይሆናል፡፡ አቶ ኃይሉ ገ/ማርያም ትውልዳቸው በቀድሞ አጠራሩ በትግራይ ክፍለ ሀገር ዓድዋ አውራጃ ማይምሻም ተብላ በምትጠራ ቦታ ነው፡፡ ይህችን ምድር በወረሃ ሚያዝያ አስራ ዘጠኝ መቶ ሃያ አምስት ዓመተ ምሕረት ላይ ተቀላቅለዋል፡፡
ከእናታቸው ወይዘሮ ለምለም እንግዳ እና ከአባታቸው መምህር ገ/ማርያም ንጉሴ የተወለዱት አቶ ኃይሉ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት ተምረዋል። በርካታ ተማሪዎች ጥቂት መምህራን የነበሩበት ትምህርት ቤት የተማሩት የወቅቱ ታዳጊው ኃይሉ እንደ እናት ያሳደጓቸው ታላቅ እህታቸው ወይዘሮ አወጣሽ ገ/ማርያም ነበሩ፡፡ አሳዳጊ እህታቸው ነገን በማሳብ የተሻለ ትምህርት ይገኝበታል ወደሚባለው አዲስ አበባ ለመላክ ቢያስቡም ወዳጅ ዘመድ ሁሉ እንዴት ካንቺ ተለይቶ ይሔዳል? ቢላቸውም የወንድማቸው ታላቅ የመሆን የወደፊት ሕይወትን በማሰብ ኃይሉ አዲስ አበባ እንዲሄድ ወሰኑ፡፡
ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ሆነ፤ ታላቅ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ብላታ ገብሩ ተ/ሃይማኖት ጋር ከረዥም ጉዞ በኋላ ደረሱ፡፡ ትምህርታቸውንም ጥሩ ከሚባለው የተፈሪ መኮንን አዳሪ ትምህርት ቤት ለመከታተል ቢያስቡም ጉዞ ላይ በመዘግየታቸው ሳይሳካ ቀረ፡፡ በመሆኑም ትምህርታቸውን በዓድዋ ቀጠሉ። ከዓድዋ ተጉዘው ዕውቀትን ፍለጋ አዲስ አበባን የረገጡት አቶ ኃይሉ፤ የስውዲሽ የሚሽን ትምህርት ቤትን በአስራ ዘጠኝ መቶ አርባ አራተኛ ክፍልን ተቀላቀሉ፡፡ ያላቸውን የትምህርት መቀበል ፍጥነት የተመለከቱት መምህራን ወደ አምስተኛ ክፍል አሸጋገሯቸው፡፡ በወቅቱ የስድስተኛ ክፍል ጓደኞቻቸው ደግሞ ፈተና በሚፈተኑበት ጊዜ ይዘዋቸው በመሄድ ተቀላቅለው አብረው ፈተናውን ወሰዱ፡፡ ቀድሞውኑ የዕውቀት ቀንዲል ነበሩ እና ከሌሎቹ በመብለጥ ካልደረሱበት ክፍል ፈተናውን በቀዳሚነት አለፉ፡፡
ይህንን ፈተና ላለፉ የሁለተኛ ደረጃ መግቢያ ፈተና መዘጋጃ ጊዜ ሆነ፡፡ ፈተናው የተሰጠው የአሁኑ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን የቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ፈተናው ከወሰዱ በኋላ ግን በክረምቱ መሄጃ ስላልነበራቸው ኮተቤ ሰባተኛ ክፍልን ዘለው ስምንተኛ ክፍልን መማር ጀመሩ፡፡ በዚህ የቀጠሉት አቶ ኃይሉ የትምህርት ደረጃቸውን አሳደጉ፡፡
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤትም ፈተናው ቢከብድም አልፈው የዕውቀት ፈለጋቸውን ቀጠሉ፡፡ አስራ አንደኛ ክፍልን እንዳለፉ የቴክኒካል አቪዬሽን ኮሌጅ በዩናይትድ ኔሽን ተቋቁሟል ተብሎ በፊዚክስ፣ በሂሳብ ጥሩ ያስመዘገቡ አስራ ሁለት ተማሪዎች ተመርጠው ሲወሰዱ እርሳቸው አንዱ ነበሩ፡፡
የአቶ ኃይሉ ገብረማርያም የአቪዬሽን ጉዞ በ1945 ተጀመረ፡፡ ለአቶ ኃይሉ ቴክኖሎጂ ትልቅ ፍላጎት ብርቱ ዝንባሌያቸው የሚታይበት መሆን የጀመረው ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ነበር፡፡ በጊዜው በመማሪያ ክፍላቸው ውስጥ በነበረው ትልቅ ሳጥን ላይ በመመራመር ተጀመረ። የዘመኑ ሬዲዮ ላይ የዕውቀት መስመራቸውን ለመክፈት በመሞከር፤ ምርምራቸው ባገኙት ኤሌክትሮ ማግኔቲክ የሚል አዲስ ቃል ላይ በማብሰልሰል ለቴክኖሎጂ ፍላጎት አድሮባቸው ኖሮ የሲቪል አቪዬሽን መቀላቀል የእርሳቸው ወርቃማው ጊዜ ሆነ፡፡ በወቅቱ ሰላሳ የኪስ ብርም ይሰጣቸው ነበር፡፡
አስራ ሁለተኛ ክፍልን እንደጨረሱ ረዳት መምህር በመሆን በአንድ መቶ ሃምሳ ብር በርካታ ዕውቀትን መቅሰም ጀመሩ፡፡ ጊዜው ለአቪዬሽን ትልቁን መንገዳቸው በሰፊው ያመላከተም ነበር። በዚህ ወቅት የሲቪል አቪዬሽን ትምህርትንም ተከታትለው ጨረሱ፡፡ ጉዞው ግን በዚህ አላበቃም ወደ እንግሊዝ ለተሻለ ትምህርት አመሩ። በ1946 በእንግሊዝ በተመቻላቸው የነፃ የትምህርት ዕድል ለመከታተል በዛው ቢደርሱም፤ የመጣው ለአንድ ዓመት ነው የሚል ሃሳብ ተነሳ፡፡ ይሄ ግራ ቢሆንም በኋላ ግን የተሰጣቸውን ፈተና በማለፍ ከኤምባሲውም ጋር ግንኙነት በማድረግ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ጨምሮ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፈቃድም ጭምሮ ሁለት ነፃ የትምህርት እድል አገኙ።
በእንግሊዝ ቆይታቸው ታላቅ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ኩራት እና ክብርም ይሰማቸው ነበር። የሚያገኙዋቸውም በኢትዮጵያዊነታቸው ያከብሯቸው ነበር፡፡ በ1950ም በዛው የተማሪዎች ህብረት ተመሠረተ፡፡ በዚህም ወቅት ከእንግሊዝ የተማሪዎች ህብረት መስራቾች ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡ የኮሚቴውም ፀሐፊ ሆነው አገልግለዋል። ጥሩ ግንኙነት፣ የታቀዱ ሥርዓታዊ ውይይቶች የተካሄዱበት እና ትምህርትም የቀሰሙበት ነበር፡፡ በወቅቱ ሀገርን በሚያበለፅጉ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ አስተሳሰብ ላይም ሰርተዋል፡፡
የምህንድስና ትምህርታቸውን ለአራት ዓመታት ተከታትለው ተመልሰዋል፡፡ በ1954 በሀገራችን የሲቪል የአቪዬሽን ልማታዊ ሥራ ውጤታማ ለማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረበት ወቅት ነበር። እርሳቸው የተመለሱበት ይህ ወቅት የበረራ አየር ማረፊያ የግንባታ ሥራ ተጠናቆ የርክክብ ሂደት ላይ ነበር፡፡ የድሬዳዋ፣ አስመራ እና የጅማ አየር ማረፊያዎች የግንባታ ሥራቸውም እየተጠናቀቀ ነበር፡፡ አቶ ኃይሉ በሲቪል አቪዬሽን አስተዳደር በቴክኒካል ክፍል የራዳር እና ናቪጌሽን ግንኙነት ኢንጂነር ሆነው ባገለገሉበት ዘመን፤ በእንግሊዝ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ ቀን ከሌት እንቅልፍ አልነበራቸውም፡፡
በመሥሪያ ቤቱ የመገናኛ እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራው ቀድሞ የተሠራ ቢሆንም ጥቅም ላይ ብዙም ሳይውል የቆየ ነበር፡፡ ይህም በአቶ ኃይሉ እና ጓደኞቻቸው አማካይነት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ለአየር መንገድ ሥራ ዋናው የሜዳው ሁኔታ ነው የሚሉት አቶ ኃይሉ፤ የቦሌ አየር ማረፊያ ደግሞ በወቅቱ የነበረው ሁለት አውሮፕላን ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለት ብቻ ቢሆኑም በአሜሪካኖች የተሰራው ሜዳ ችግር መፈጠር ጀመረ እና ማሻሻያ ያስፈልገዋል ተባለ። ይህን እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው ዕውቀትን ከብልሃት የታደሉት አቶ ኃይሉ ነበሩ፡፡
በ1960 አውሮፕላን ለማብረር አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ፈቃድ የሚሰጠው በወቅቱ ደግሞ ፈቃዱ የሚገኘው የግድ ኤደን ወይም የመን ከነበረው የእንግሊዝ ቀኝ ገዢ ፈቃድ በማግኘት ነበር፡፡ አቶ ኃይሉም በዚሁ ጉዳይ ኢትዮጵያ በራሷ የአየር ክልል ለምንድነው እራሷን የማታስተዳድረው የሚለውን ለማጥናት ወደ እስራኤል ተላኩ፡፡
ጉዳዩን ሲያጠኑ የመኖች ከእንግሊዝ ነፃ ሊወጡ መሆኑን፤ ይህም ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ፈቃዱን ለማግኘት ቁጥጥሩ በግብፅ ስር እንደሚሆን አወቁ። አቶ ኃይሉ እንዴት ይሻላል ሲሉም ባገኙት ምላሽ ፈቃዱ በራሷ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ኢትዮጵያ በራሷ የአየር ክልል እራሷን ማስተዳደር እንድትችል በሚያደርገው ሥራ ላይ ለአንድ ሳምንት ባደረጉት ተምረው ሪፖርት አድርገውም የድርሻቸውን ተወጡ። ይህ ሥራቸው የእርሳቸው ታታሪነት እንዲሁ አርቆ አሳቢነት ማሳያ አንዱ ነው።
በ1966ም የባህር ዳር እና አክሱም ኤርፖርትን ጨምሮ በርካቶችን ዲዛይን ሲደረጉ ቦታውን የመረጡትም እርሳቸው ነበሩ፡፡ አቶ ኃይሉ የሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት የፕላኒንግ ኮሚሽን በነበሩበት ወቅት አንድ አዋጅ ወጣ፡፡ አዋጁ አስደንጋጭ ነበር፤ ከፕሬዚዳንቱ በሱዳን የአየር ክልል በኩል የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች እንዳያልፉ፤ አየር መንገዱን እንዳይጠቀሙ የሚል አዋጅ ተሰማ። በርካታ በረራዎች በሱዳን በኩል ይደረጉ ስለነበር ሁሉም ተደናገጠ፡፡ በጊዜው የፕላኒንግ ኃላፊ የነበሩት አቶ ኃይሉ ከችግሩ ይልቅ መፍትሔን መሻት ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ፡፡
በወቅቱ ያለው አማራጭ የኢትዮጵያ አንድ አካል በነበረችው አስመራ አድርጎ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በኤር ስፔስ ተጠቅሞ ሰሜን አፍሪካዊት ወደሆነችው ግብፅ መዳረሻ ማድረግ ነበር፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሳዑዲ አረቢያ ፈቃደኝነት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎችን መተዋወቅ እና መግባባት የሚቻላቸው አቶ ኃይሉ፤ በአንድ ስብሰባ ላይ በሳዑዲ አረቢያ የሲቪል አቪዬሽን ከሚሰራ አቻቸው ጋር ተዋውቀው ስለነበር፤ በወቅት ከእርሱ ጋር ያለውን ነገር ተወያይተው ወዲያው ጊዜያዊ ፈቃድ አገኙ፡፡ አቶ ኃይሉ ለማሳመን ማን ብሏቸው የሚባልላቸው ዓይነት ሰው ስለነበሩ ተሳካ፡፡
ጥያቄው ግን ለምን ሱዳን ይህንን አዋጅ ማወጅ ፈለገች የሚለው ነው፡፡ ከመንግሥት የመጣው ሃሳብ እናንተም በተመሳሳይ የሱዳንን የአየር ክልል በኢትዮጵያ ዝጉ የሚል ነበር፡፡ ይህ የሚሆነው አንዳች የሚያተርፈው ጥቅም ሲኖር ነው፤ ታዲያ ሱዳኖች ምን ለማትረፍ ነው? እኛስ ብንዘጋ ምን እንጠቀማለን? ብለው ቀድመው ማሰላሰልን ያዙ። በተጨማሪም ይህ በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የፈረሟቸውን ሁሉ ስምምነቶችም ገደል የሚከት ነበርና ዕውቀታቸውን ከሕጉ ጋር ማጠመር ያዙ፡፡
ሰላማዊ ውይይት፣ መደራደርና መስማማት ያስፈልጋል የሚል እምነት ስላደረባቸው፤ ሱዳን የአየር ክልሏን እንድትፈቅድ የሚያስማማ ጽሑፍን ማሰናዳት ጀመሩ፡፡ ይህም በተጀመረበት ወቅት የአየር መንገድ ኃላፊዎችን ጨምሮ አምስት ሰዎችን ጓድ መንግሥቱ ሀ/ማርያም በተገኙበት በደርግ ጽ/ቤት ሀገራዊ ታላቅ ውይይት ተካሔደ፡፡
በስብሰባው ላይ ለሰላማዊ ድርደሩ የተዘጋጀው ጽሑፍ ተነበበ፡፡ ይህንን ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ፡፡ ሱዳን የአየር ክልሏን መዝጋት ሉዓላዊ መብቷ ነው የሚሉ እና የመሳሰሉ ዓይነት ሃሳቦች ተስተጋቡ፤ ሆኖም በጊዜው ከአቪዬሽን ተወክለው የሄዱት የሕግ አማካሪ አቶ አበራ መኮንን የአቪዬሽንን ሕግ ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር ተገቢውን ምላሽ ሰጡ፡፡
አቶ ኃይሉም ቢሆን በደርግ ጽ/ቤት በተሰበሰቡበት ወቅት በዕውቀት የታገዘ ምላሻቸውን አጋሩ፡፡ ዕውነታውን ከተጨባጭ ዕውቀት ጋር እያስተሳሰሩ ተናገሩ፡፡ አቶ ኃይሉ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ምላሽ ምን እንደነበር ሲናገሩ ‹‹የያዛችሁት በዕውቀት የታገዘ ትክክለኛ ውሳኔ ነው፤ ቀጥሉበት፡፡›› ተብለው እንደተደነቁባቸው ገለፁ። መታገስ መልካም ነውና ሱዳኖችም ከአንድ ወር ድርድር በኋላ ታላቅ ይቅርታን አቅርበው ስጦታም ሰጥተው ግንኙነቱን እንደገና ማደስ ተችሏል።
አቶ ኃይሉ ገ/ማርያም የአቪዬሽንን ሙያ ዘልቀው እንደ ማጥናት እና መመራመራቸው በሁለት ሀገራት መካከል የአየር በረራ ግንኙነት መኖርን ከበፊት ጀምሮ ያምኑበት ነበር፡፡ ሥራን በጀመሩበት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን በአንዳንድ ሀገራት በረራ ይደረግ ነበር፤ ሆኖም በ1966 መንግሥት ሲቀየር በረራ የሚደረግባቸውን ሀገራትም የግድ ማስተካከል ያስፈልግ ነበር፡፡
ለሀገር ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ የሆነው አቶ ኃይሉ ሥራ ላይም በታታሪነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ከ1966 በኋላም ለሀገራችን የተለያዩ ሀገራት የአየር ክልላቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ጥረት አድርገዋል። በተለያዩ ሀገራትም የአየር በረራ እንዲጀመርም አድርገዋል፤ ከእነዚህም መካከል ጋና፣ ኬንያ፣ የመን፣ አቡዳቢ፣ ባህሬን እና ጣሊያን ይነሳሉ፡፡ የአቶ ኃይሉ ህልማቸው በዕውን የተሳካ በመሆኑ ጥረታቸውም ከግብ በመድረሱ ስማቸው በጉልህ ሰፈረ፡፡
በሲቪል አቪዬሽን የፕላኒንግ እና የፖሊሲ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ደግሞ አንድ ያሳኩት ሌላ ቁምነገር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አቢጃን ለመብረር ብዙ ጊዜ ሞክሮ አልተሳካለትም ነበር። በተጨማሪም አየር መንገዱ ትርፋማ ባለመሆኑ የመዘጋት እጣ ፋንታ ከፊቱ ተደቅኖበትም ነበር፤ የነበሩት አውሮፕላኖችም ከማርጀታቸው የተነሳ መላ ዘይዱላቸው የተባለበትም ጊዜ ነበር፡፡ አየር መንገዱ በዚህ ውስጥ ቢሆንም ወደ አቢጃን መብረር አለበት የሚል ቁርጥ አቋም ነበረ፡፡ ነገሩ ደግሞ እንዲህ በቀላሉ የማይቻል ነበር፡፡ ይህ የማይቻለው እንዲቻል ታምኖባቸው ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት የተሰጣቸው ደግሞ አቶ ኃይሉ ነበር።
በዚህ ድርድር ሀገራችንን ወክለው ተጨማሪ ሰዎች ለድርድሩ መምጣት ቢኖርባቸውም በአውሮፕላን እጦት ሳይገኙ ቀሩ፡፡ ስለዚህ ሙሉ ኃላፊነቱ በእርሳቸው ላይ ወደቀ፡፡ አፍሪካዊያን ለአፍሪካዊያን ብቻ መወያየታቸው መፍትሔን እንደሚያመጣ ማሳያ የሆነው ድርድር ቀናት ቢወስድም ተሳካ፡፡ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የአየር በረራ ፈቃድን አሰጡ፡፡ ይህ በሁሉም ውስጥ መደነቅን የጫረ ነበር፡፡
ይህ የአቶ ኃይሉ ጥረት ከሀገራችን አልፎ በዓለም አቀፍ ሰዎች በጉልህ እንዲጠራም አድርጎታል፡፡ ሁ ኢዝ ሁ ኢን አቪዬሽን የተሰኘ የመረጃ መጽሐፍ እ.ኤ.አ በ1973 ባወጣው እትሙ የእርሳቸውን ስም በደማቅ ብዕሩ አስፍሮታል፡፡ በሶስት መንግሥታት ሥር ሀገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት ያገለገሉት የሀገር ባለውለታ አቶ ኃይሉ ገብረማርያም ከወይዘሮ አሰፋሽ ጋር ትዳር መስርተው ሶስት ልጆችን ማፍራት ችለዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም