የዓመቱ የመጀመሪያ ዙር ብሄራዊ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዛሬ ይካሄዳል። በመላው የሀገሪቷ ክፍሎች በሚደረገው በዚህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይም ሚሊዮኖች ይሳተፋሉ በሚል እንደሚጠበቅ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አስታውቋል፡፡
በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆን ጤንነቱን እንዲጠብቅ ለማድረግ ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፍ ትኩረቱን ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ሊሆንም ችሏል፡፡ ከዚህ ቀደምም በመላው የሀገሪቷ ክፍሎች ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በስፋት ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ የሆነው መርሀ ግብር ዛሬ የሚከናወን ይሆናል፡፡
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አዘጋጅነት የሚደረገው ንቅናቄው ‹‹የአንድ ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለሚሊዮኖች እና ለአብሮነት›› የሚል መሪ ሃሳብን አንግቧል፡፡
መርሀ ግብሩ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ከጠዋት ጀምሮ ሁሉም በያለበት ስፍራ እንዲሁም በተመረጡ ስፍራዎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በተገኙበት ለአንድ ሰዓት ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴው የሚደረግ ይሆናል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ላይም 12 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ተሳታፊ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፤ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን አንድ ላይ አሰባስቦ በማሳተፍ ህብረተሰቡ ማህበራዊ ትስስሩን እንዲያጠናክርና አብሮነቱን እንዲያዳብር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሀ ግብር ስፖርትን ባህሉ ያደረገ በአካል እና በአእምሮ የጎለበተ ማህበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል፡፡ በስፖርት ተሰጥኦ ያላቸውን እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርገው ሊያስጠሩ የሚችሉ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። በመሆኑም መንግሥት ይህንን በመረዳት የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ ፖሊሲ ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
ለዚህ መርሀ ግብር አስቀድሞ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፤ ስፖርት ለማህበራዊ ልማት ያለውን አስተዋጽኦም እንደሚያሳይ የጠቆሙት ደግሞ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ በቀለ ናቸው፡፡ ስፖርት አብሮነትንና ወንድማማችነት ለማስፋት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ አስቀድሞ በመርሀ ግብሩ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠርም ተችሏል። ከክልሎች ጋርም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆን ከመግባባት ላይ በመድረስ በተለይ በትምህርት ቤቶች ላይ በማተኮር የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ለማሳተፍ ታቅዷል፡፡
ከዚህ ባለፈ በየክልሉ በተመረጡ ስፍራዎች ላይ እንቅስቃሴው ይካሄዳል፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በዋናነት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ አመራሮች በተገኙበት የሚከናወን ይሆናል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ላይ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ፣ ሲዳማ ክልል በሃዋሳ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሆሳዕና(አርብ ዕለት ደግሞ በወልቂጤ ከተማ) በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል፣ ድሬዳዋ እና ሀረሪ ክልሎች ላይም ይኸው ንቅናቄ በስፋት እንደሚከወን ታውቋል፡፡ የማህበረሰብ አቀፍ አካል ብቃት እንቅስቃሴው በዓመቱ በአራት ዙር የሚካሄድ ሲሆን፤ በየካቲት፣ ሚያዝያ እንዲሁም ሰኔ ወሮች ላይ በመላው ሀገሪቷ ለማካሄድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡
በ2015ዓ.ም በተደረገው ብሄራዊ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች አምስት ሚሊዮን ያህል ህብረተሰብን ለማሳተፍ ታቅዶ 5ነጥብ4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ተካፋይ ማድረግ ተችሏል፡፡ በቀጣይም የተሳታፊዎችን ቁጥር በመጨመር በዓመት አራት ጊዜ ለማካሄድ እንደታቀደና ሰፊ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ገልጸዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም