‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የሚለው የእረኞች ጨዋታ ሲወርድ ሲወራረድ መጥቶ አሁን በምሑራን እና ትልልቅ ታዋቂ ሰዎች ጭምር የሚታወቅ የሥነ ቃል ግጥም ሆኗል፡፡ እንዲህ የገና በዓል በመጣ ቁጥር ደግሞ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የማስታወቂያ ማድመቂያ ሆኗል፡፡ ግን ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የተባለው ለምን ይሆን?
የራሱ የሆነ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ወይም ሌላ ትውፊታዊ ትርጓሜ ይኖረው ይሆናል፡፡ በገጠሩ አካባቢ በእረኞች ዘንድ ግን ለምን እንዲህ እንደሚባል የማውቀውን ላስታውስ፡፡
በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች የታኅሣሥ ወር የበጋ ወቅት መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ የበጋ ወቅት ደግሞ የመኸር ሰብል ተሰብስቦ የሚገባበት ነው፡፡ የመኸር ሰብል መሰብሰቡ ለእረኞች ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ ምክንያቱም የመኸር ሰብል ማሳ ላይ ባለበት ወቅት ከብት እንዳያበላሸው እረኞች ከብቶችን ይጠብቃሉ፡፡ በዚህን ወቅት ከብት ወይም ፍየል አምልጦት እህል ያስበላ እረኛ በቤተሰቦቹ ወይም በእህሉ ባለቤት ሊገረፍ ይችላል፤ መገረፉ ቢቀር እንኳን ኃይለኛ ቁጣ ያጋጥመዋል፡፡
እነዚህ እረኞች የበልግ ወቅት ከሆነ ከሚያዚያ እና ግንቦት ጀምሮ፣ ያ ቢቀር ግን ከሰኔ ወር ጀምሮ ለግማሽ ዓመት ያህል የእረኝነት ሥራ ላይ ይጠመዳሉ። በክረምትም ሆነ በመኸር ወቅት ከብቶች ቡቃያ እና ሰብል እንዳይበሉ ይጠብቃሉ፡፡ እረፍት የሚያገኙት ከታኅሣሥ እስከ ሰኔና ግንቦት ድረስ ባሉት ወራት ነው፡
በዚህ ምክንያት የገና በዓል ለገጠር እረኞች ልክ እንደ አውሮፓና አሜሪካ ሀገራት በሉት፡፡ የፌሽታና የደስታ ወቅት ነው፡፡ አውሮፓውያን አዲስ ዓመት ስለሚመጣላቸው፣ የኢትዮጵያ ገጠራማ እረኞች ደግሞ እረፍት ስለሚያገኙ እና ከአቻዎቻቸው ጋር ለረጅም ጊዜ የገና ጨዋታ ስለሚወጫወቱ፡፡
የገና በዓል በበዓልነቱ የዝናውን ሚና ወሰደ እንጂ ለገጠር እረኞች የገና ትልቁ ደስታ የገና ጨዋታው ነው፡፡ ይህ ጨዋታ የገና ዕለት (ታኅሣሥ 29) ብቻ የሚከናወን አይደለም፤ እንዲያውም የዚያን ቀን በዓል ስለሆነ ላይጫወቱ ይችላሉ፡፡ የገና ጨዋታ የሚባለው ከታኅሣሥ ወር አጋማሽ ጀምሮ ያሉትን የበጋ ወራት በሙሉ ነው፡፡ ምንም እንኳን የገና ሰሞን የሚባለው ከታኅሣሥ ወር አጋማሽ በኋላ እስከ ጥር ወር መጀመሪያ ያለው ቢሆንም የገና ጨዋታው ግን እስከ የካቲት ወር ድረስ ይቀጥላል፡፡
‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም›› ጌታ የተባለው ከሌላው ወቅት በተለየ በዚህ ወቅት በነፃነት ስለሚጫወቱ ነው። በሌሎች ወራት (ለምሳሌ በክረምት እና በመኸር) በነፃነት ሊጫወቱ አይችሉም፡፡ ከብቶች (ፍየሎች) ወደ እህል ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ቀልባቸው ተንጠልጥሎ አጫጭር ጨዋታዎችን ብቻ ነው የሚጫወቱት፡፡ ቤተሰቦቻቸው ወይም የእህሉ ባለቤት ይቆጧቸዋል፡፡ በገና ወቅት ግን ከብቶች ወዴትም ቢሄዱ የሚያጠፉት ነገር ስለሌለ የሚቆጣ ጌታ አይኖርም፡፡ ከገና በፊት ባሉት ወራት ግን በነፃነት አይጫወቱም፡፡ ለዚህም እንዲህ የሚል ጨዋታ አላቸው፡፡
ከዱሩ ውስጥ ሆኜ መሰንቆ ስመታ
ፍየሎቼ ከሰው እህል ገብተው እኔሳ ብመታ!
ጨዋታ ጨዋታዬን ሳይ ፍየሎቼ አምልጠውኝ ከሰው እህል ቢገቡ፣ የእህሉ ባለቤት ይገርፈኛል ማለቱ ነው፡፡
‹‹በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ›› ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ ጨዋታው እየተለመደ እና ባሕል እየሆነ ስለሄደ ትልቅ ቦታ የተሰጠው መሆኑን ያሳያል፡፡ ጌታ እና ሎሌ ሳይኖር ሁሉም እኩል ይጫወታል ማለት ነው፡፡ ወይም ይህን ጨዋታ በመጫወቱ ቤተሰቦቹ የሚቆጡት ልጅ አይኖርም ማለት ነው፡፡ በጨዋታው ላይ ብዙ ባሕላዊ ድርጊቶች አሉ፡፡ ጉዳት የሚያደርስ ነገር እንኳን ቢከሰት በገና ጨዋታ ምክንያት ፀብ እንደማይፈጠር በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ይህን ለባሕል ይዘት እንተወው፡፡
እንዲህ አይነት የገና ጨዋታ ባሕላዊ ይዘቶች እያሉን ነው እንግዲህ ስለፈረንጆቹ ‹‹ሳንታ ክላውስ›› ብዙ ትንታኔ እና ማብራሪያ የሚሰጠው፡፡ የገና ጨዋታን በተመለከተ ወደ በይነ መረቡ ዓለም ብትገቡ በጣም ተደጋጋሚ የሆኑ አንድ አይነት ማብራሪያዎችን ነው የምታገኙት፡፡ ሥነ ቃሎቹም አንድ አይነት ናቸው። እንደምንም ብሎ አንድ ሰው ኢንተርኔት ላይ ከጫነው ሬዲዮውም፣ ቴሌቪዥኑም ያንኑ ነው የሚያብራሩት። እርግጥ ነው በሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተሻለ ነገር አለ፡፡ ቢያንስ በበዓሉ ዕለት የባሕል ባለሙያ ወይም የሃይማኖት አባት ተጋብዞ ማብራሪያ ሊሰጥ ይችላል፡፡
በዚህ ላይ የተሠሩ ጥናቶችን እንፈልግ ቢባል ግን እዚህ ግባ የሚባል አይኖርም፡፡ የተሠራ ካለም ምናልባትም ለመመረቂያ እንጂ ባሕሉን ለማስተዋወቅ ሲባል በምርምር ተቋም የተሠራ ማግኘት አይቻልም። ይህን የምለው ለገና ጨዋታ ብቻ አይደለም፡፡ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ባሕልና ትውፊት፣ የማኅበረሰብ ፍልስፍና የሆኑ ነገሮች ላይ በሀገርኛ ቋንቋ እና በሀገርኛ አቀራረብ ማግኘት አይቻልም፡፡ ብዙ ጥናቶች በውጭ ቋንቋ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት በጣም ግልጽ ነው፡፡ በቀላሉ ከኢንተርኔት መገልበጥ ስለሚቻል ነው፡፡ ከዚህኛው ጉዳይ ጋር ባይገናኝም ሰሞኑን ያጋጠመኝ አንድ ጥናት ልጥቀስ፡፡
ስለጥላሁን ግዛው የተሠሩ ጥናቶች ካሉ በሚል የበይነ መረቡን ዓለም ማሰስ ጀመርኩ፡፡ አንድ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈ ‹‹ፒ ዲ ኤፍ›› ጽሑፍ አገኘሁ። ጽሑፉ በወቅቱ በነበሩ በአማርኛ ቋንቋ የተነገሩ የተማሪዎች መፈክሮች እና ግጥሞች የታጨቀ ነው፡፡ ቃላቱ የአማርኛ ናቸው፡፡ እነዚያን ሁሉ የመፈክር ቃላት እና ግጥሞች ግን በእንግሊዘኛ ፊደል ነው የጻፋቸው፤ ምክንያቱም ጽሑፉ በእንግሊዘኛ ስለሆነ፡፡
ጥናቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከሆነ፣ የሚቀርበው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሆነ፣ የቃል ግጥሞቹ ወደ እንግሊዘኛ ካልተተረጎሙ በእንግሊዘኛ መጻፉ ለምን አስፈለገ? እንዲያውም አንባቢን ጭምር ግራ ማጋባት ነው፡፡ የአማርኛ ግጥም በእንግሊዘኛ ፊደል ተጽፎ ምንም ስሜት አይሰጥም፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የምናየውም ይሄው ነው፡፡ ‹‹የባሕል ጥናት ጉባኤ›› ተብሎ ጥናቶች የሚቀርቡት በፈረንጅ ቋንቋ ነው፡፡ አዳራሹ ውስጥ ግን አንድም ነጭ የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ሥነ ቃሎችን በትክክል አያስቀምጧቸውም፡፡ ከኢንተርኔት ማግኘት የሚቻለውን ብቻ ሰብስበው ያቀርባሉ፡፡ ያ ጥናት በየመገናኛ ብዙኃኑ ይሰራጫል ማለት ነው፡፡ ይህን የምለው ለአጠቃላይ ባሕሎቻችን እንጂ የገና ጨዋታን በተመለከተ ብቻ አይደለም፡፡
ወደ ገና ጨዋታ ስንመለስ፤ የገና ጨዋታ በተለይም ለእረኞች በጉጉት የሚጠበቅ በዓል ነው፡፡ ሰፊ ነፃነት ስላለው በዓልነቱም የተሻለ ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጭ ባሉት በዓላት ሰፋ ያለ ጊዜ አይኖራቸውም፡፡ ገናን በጉጉት ከመጠበቃቸው የተነሳ በክረምት ወራት እንዲህ እያሉ ይጫወታሉ፡፡
ፍየሌን ነብር በላት
ለገና ብየ ሳደላድላት!
እንዲህ አይነት ሀገራዊ ትውፊቶች ስላሉን ከፈረንጆቹ ገና ይልቅ የራሳችንን የገና ባሕሎች እንወቅ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም