በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ በስፔን ማድሪድ በተካሄደው ዓመታዊው የሳን ስልቬስትሪ ቫሌካና 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸንፈዋል። በወንዶች አትሌት በሪሁ አረጋዊ ተፎካካሪዎቹን አስከትሎ ሲገባ፤ በሴቶች ደግሞ አባብል የሻነህ የበላይነቱን ልትቀዳጅ ችላለች።
በየዓመቱ በፈረንጆች አዲስ ዓመት ዋዜማ በሚካሄደው በዚህ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስቀድሞ ተገምቶ ነበር። ከፍተኛና አጓጊ ፉክክርን ባስተናገደው የወንዶች ውድድርም ወጣቱ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ከስፔናዊው አትሌት ሞሃመድ ካጢር ጋር እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ በማድረግ የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት በድል መጀመር ችሏል። ሁለቱ አትሌቶች የቦታውን ክብረወሰን ለማሻሻል ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ለጥቂት ሳይሳካላቸው ቀርተዋል። በሪሁ 27ደቂቃ ከ15 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመሮጥ አሸናፊ ሲሆን፤ ሞሃመድ ካጢር ደግሞ በ27ደቂቃ ከ30ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
በሪሁ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ጨምሮ በበርካታ ውድድሮች ላይ ሀገሩን በመወከል እንዲሁም በግሉ ሲወዳደር እንደቆየ ይታወቃል። በዚህ የጎዳና ውድድር ላይም ከድሉ በተጨማሪ በ5ሺ ሜትር 12ደቂቃ ከ40ሰከንድ በመሮጥ የግሉን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገም ስኬታማ ጅማሮ ማድረግ ችሏል። በቤት ውስጥና በመም ውድድሮች የግል ምርጥ ሰዓት ባለቤት መሆን የቻለው አትሌቱ የስፖርት ቤተሰቡ ተስፋ ከጣለባቸው ኢትዮጵያዊያን ወጣት አትሌቶች መካከል አንዱ መሆኑም ይታወቃል። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመትም ሀገሩን በወከለባቸው ውድድሮች ላይ በሚጠበቀው ደረጃ በድል ባይታጀብም በግሉ ግን ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል።
በሴቶች መካከል በተደረገው ፉክክር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ውድድሩን በበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል። አትሌት አባብል የሻነህ ደግሞ በፉክክሩ ብልጫ በማሳየት አሸናፊ ሆናለች። አትሌቷ 27 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ውድድሩን ያሸነፈችበት ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አስማረች አንለይ ሁለተኛ በመሆን ስታጠናቅቅ ርቀቱን ለመሸፈንም 30 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ፈጅቶባታል። አትሌት ልቅና አምባው ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ለማጠናቀቅ 30 ደቂቃ ከ32 ሰከንዶች ወስዶባታል።
ይህ ውድድር እአአ ከ1964 ጀመሮ እየተካሄደ ሲሆን በርካታ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከተሳትፎ ባለፈ ማሸነፍ ችለዋል። በመድረኩ ኢትዮጵያዊያኑ ለ10 ጊዜ መንገስ ሲችሉ፣ በሴቶች 7 ድሎች እንዲሁም በወንዶች 3 ድሎች ተመዝግበዋል። በወንዶች የመጀመርያውን ድል ያስመዘገበው አትሌት ታደሰ ቶላ እአአ በ2008 ነበር። ሌሎች በመድረኩ ማሸነፍ የቻሉት ውጤታማ ወንድ አትሌቶችም ሀጎስ ገብረህይወት እና ታሪኩ በቀለ ናቸው።
በሴቶች በ1999 ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ማሸነፍ ችለዋል። አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በመድረኩ ካሸነፉ አትሌቶች አንዷ ስትሆን፤ አትሌት ገለቴ ቡርቃ ሁለት ጊዜ አሸንፋለች። ያለምዘርፍ የኋላው፣ ደጊቱ አዝመራው እና ሔለን በቀለ ድሉን ከተጎናጸፉት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተርታ ተመዝግበዋል። በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ የሚካሄደው በዚህ ውድድር አትሌቶችና አትሌት ያልሆኑ ሰዎችን ይሳተፉበታል። በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ ተሳተፊ የተመዘገበው እአአ በ2012 ሲሆን፤ 40 ሺ የሚደርሱ ሯጮች የተካፈሉበት ወቅት ነበር።
ሌላው ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የተሳተፉባት የባርሴሎና 5 ኪሎ ሜትር ጎዳና ውድድር በኬንያዊቷ አትሌት ቢትረስ ቺቤት አሸናፊነት ተጠናቋል። አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ስታጠናቅቅ አትሌት መዲና ኢሳ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች። ኬንያዊቷ አትሌት ቢትረስ የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል ማሸነፍ ችላለች። 14 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ውድድሩን ለማጠናቀቅ ፈጀባት ሰዓት ነው። የቀድሞው ክብረወሰን በ2021 በአትሌት እጅጋየሁ ታዬ የመዘገበው 14፡19 የሆነ ሰዓት እንደነበር ይታወሳል።
አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ከኬንያዊቷ አትሌት በመቀጠል 14፡21 የሆነ ሰዓትን በማስመዝገብ የጎዳና ውድድሯን በሁለተኝነት አጠናቃለች።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም