ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ከሚዳሰሱ ቅርሶች መካከል ተፈጥሯዊ የሰሜን ተራሮች ፓርክና የጊዲዮ ባህላዊ መልከዓ ምድር፤ ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ደግሞ የሸዋሊድ በተባበሩት መንግሥታት የባህል፣ የሳይንስና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ማስመዝገቧ ይታወሳል። ከዚህ ቀደም የተመዘገቡትን ጨምሮ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች ወደ 16 ከፍ ብለዋል። ከእነዚህ ውስጥም 11ዱ ቅርሶች የሚዳሰሱ፤ አራቱ ደግሞ የማይዳሰሱ ናቸው።
ቅርሶቹ በዩኔስኮ መመዝገባቸው የበለጠ ደህንነታቸው እንዲጠበቅና በሌላው ዓለም ያላቸውንም እውቅና ከፍ በማድረግ ረገድ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ቅርሶቹን ከማስመዝገብ ባለፈ በሀገር ምጣኔያዊ ሀብት ላይ ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ እየተነገረ ይገኛል።
በዚህ ጭስ አልባ የቱሪዝም ኢንደስትሪ በዓለማችን የምጣኔ ሀብት እድገት ያስመዘገቡ ሀገሮች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ደግሞ እምቅ የቱሪዝም መስህብ የሆኑ ሀብቶች እያሏት፤ ነገር ግን ባላት ሀብት ልክ እንዳልተጠቀመች በተደጋጋሚ ይነሳል።
በተለይ ደግሞ የዓለም ስጋት ሆኖ በነበረው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት፤ የተዳከመው ዘርፍ ሳያገግም፤ በተጨማሪ ባጋጠመ የውስጥ አለመረጋጋትና ጦርነት እንዲሁም ተያይዞ በመጣው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አጣብቂኝ ውስጥ ስለመግባቱ እየተነገረ ይገኛል። በመሆኑም በዚህ ወቅት ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ሰላም እና መረጋጋት ከማስፈን ጎን ለጎን ሀብቶችን በማስተዋወቅ በኩልም የበለጠ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ይጠቀሳል።
በአጠቃላይ ኢንደስትሪውን የማነቃቃት ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በዩኔስኮ የተመዘገቡት ቅርሶች በምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከፍ ያለ ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ምን እየተሰራ እንደሆነና ስለ ቀጣይ ተግባራት ዘርፉን የሚመሩ፣ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ፣ መምህርና ተመራማሪ በሚከተለው መልኩ ሙያዊ ምልከታቸውን ሰጥተዋል።
የቱሪዝም ሚኒትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ብቻ ሶስት ቅርሶችን በአንዴ ማስመዝገብ መቻሏን እድለኛ እንደሚያደርጋት ነው የገለጹት። እርሳቸው እንዳሉት ይህን ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት በመንግሥት በኩል ብዙ ሂደቶች ታልፈዋል። በብዙ መመዘኛዎች ውስጥ አልፈው በዩኔስኮ የተመዘገቡት እነዚህ ቅርሶች፤ በዓለም ላይ የማይገኙ ልዩ የሆኑ፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚታዩ መልከዓ ምድር፣ ባህላዊ እሴት ወይም ክዋኔዎች ናቸው ብለዋል።
ቅርሶቹ በዩኔስኮ መመዝገባቸው ስለቅርሶቹ መረጃዎችን በጽሑፍና በምስል አደራጅቶ ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚወስደውን ጊዜና ድካም በማስቀረት ወጪን እንደሚቆጥብ ያስረዱት አቶ ስለሺ፤ ከዚህ በኋላ ቱሪስቶችን ለመሳብ የዩኔስኮ ቅርስ ነው ማለት ብቻ በቂ እንደሆነ ገልጸዋል። በዘንድሮ ዓመት የተመዘገቡትን ቅርሶች በቀጣይ በማስተዋወቅ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይቻላል ብለዋል። ብዛት ያላቸው ቱሪስቶች ቅርሶቹን ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በዩኔስኮ የተመዘገቡት አክሱም፣ ላልይበላ፣ ሐረርና ሌሎችም ቅርሶች መስህብ ሆነው ጥቅም እየሰጡ እንዳሉት ሁሉ በእነዚህ አዲስ በተመዘገቡት ቦታዎች ላይም ቱሪስቶችን መሳብ እንደሚቻል የሚያጠራጥር አይደለም ያሉት አቶ ስለሺ፤ ቅርሶቹን መጎብኘቱ ከዓለም በሚመጡ ቱሪስቶች ላይ ብቻ ጥገኛ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፤ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችንም በማነሳሳት ዘርፉን በማነቃቃት ኢንደስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ሚናው የጎላ እንዲሆን መሠራት እንዳለበት በመንግሥት በኩል እምነቱ መኖሩንም ገልጸዋል።
ቅርሶቹ ባሉባቸው አካባቢዎች መሟላት አለባቸው ያሏቸውንም አቶ ስለሺ እንዳስረዱት፤ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴል ቤቶች፣ ሎጅ፣ ሪዞርት፣ አስጎብኚዎች መኖር አለባቸው። በተለይም በአስጎብኚነት በዘርፉ ከሰለጠኑት በተጨማሪ የአካባቢው አርሶ አደር በቅሎ በማከራየት ቱሪስቶችን በመሳብ እርሱንም ሀገርንም ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅበታል። እነዚህን ከማሟላት ጎን ለጎንም የመረጃ ማዕከላትን አብሮ ማደራጀቱ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ያሰፋዋል ብለዋል።
በዚህ ረገድም የባለሀብቶች ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ አለው። መንግሥትም በዘርፉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እየሰራ ነው። ኢንቨስተሮች ለሚያከናውኑት የግንባታ ሥራም ሆነ በሆቴል ውስጥ ለሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች የሚውሉ ከቀረጥ ነፃ ከውጭ እንዲያስገቡ የሚያደርገው ድጋፍ ይጠቀሳል ብለዋል፡፡
በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ሊኖራቸው ከሚችለው ፋይዳ በተጨማሪ የአካባቢ ማኅበረሰብን ተጠቃሚነት ማሳደግ ስላለባቸው፤ በዚህ በኩልም ኅብረተሰቡ በማህበር ተደራጅቶ እንዲሰራ የብድር አቅርቦት በመንግሥት በኩል የማመቻቸቱ ጥረትም እንደሚጠናከር ነው የገለጹት።
በቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል የሚጠበቀው ሥራ እንዳለ ሆኖ ክልሎችም በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን መሠረት አድርገው ከሀገር ውስጥም ከውጭም በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮችን የመሳብ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውና ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ያመቻቸው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ አዋጅ እንደሚጠቅማቸው ገልጸዋል።
በዘርፉ ከ200 በላይ አባላትን ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተሮች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ፍፁም ገዛኸኝ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በዩኔስኮ የተመዘገቡት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ የሚሆኑ ሀብቶች ናቸው። ሆኖም ግን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ወደ ኢኮኖሚ መለወጥ ካልተቻለ በዩኔስኮ ማስመዝግቡ ብቻውን ግብ አይሆንም። ከዘርፉ የሚጠበቀውን ምጣኔያዊ የሀብት እድገት ማስመዝገብ የሚቻለው እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን መወጣት ሲችል ነው።
እንደ አቶ ፍፁም ማብራሪያ፤ ሀብቶቹን በዩኔስኮ የሚያስመዘግበው መንግሥት ነው። መንግሥት ሀብቶቹን ሲያስመዘግብ የመጠበቅና የመንከባከብ እንዲሁም የማስተዋወቅ ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ቃል ይገባል። ስለዚህ በገባው ቃል መሠረት ሥራዎችን በመሥራት ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። የአካባቢ ማህበረሰብ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆንም ምቹ መደላድሎችን መፍጠር የመንግሥት ድርሻ ነው። ማኅበረሰብ ከቅርሶቹ ከሚገኘው ገቢ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ለተተኪ ትውልድ የማሸጋገር ድርሻም ስላለው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
የቅርሶቹ ባለቤቶች መንግሥት፣ ወይም አብያተ ቤተክርስቲያናትና የማኅበረሰብ ክፍሎች ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ቅርሶቹ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ወይም የሀገር እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። በመሆኑም ለማስተዋወቅም፣ ለመጎብኘትም የሚመች ማድረግ፣ የሚጠየቀው ዋጋም ጎብኚዎችን የሚስብ መሆን ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ቱሪስቶችን ለመሳብ በሚዘጋጀው የጉዞ ጥቅል ውስጥ ለማካተት አስቸጋሪ ይሆናል ብለዋል።
ሌላው ኃላፊነትና ድርሻ የአስጎብኚ ድርጅቶች ነው። አስጎብኚ ድርጅቶች ቱሪስቶች የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ እምቅ የሆኑ የቱሪስት ሀብቶችን በዓለም ላይ ለሚገኘው ቱሪስት በማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ፍፁም፤ አስጎብኚ ድርጅቶቹ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡ ፡ ስለቅርሶቹ በቂ ግንዛቤ ከመያዝ በተጨማሪ ሙያዊ (ፕሮፌሽናል) በሆነ መልኩ የጉዞ ጥቅሎችን በተደራጀ መልኩ አዘጋጅቶ ለጎብኚዎች የማስተዋወቅና የመሸጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ካሣ፤ ቅርሶቹ በዩኔስኮ ተመዝግበው ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ጥረት እንደተደረገ ሁሉ የእንክብካቤና ጥበቃ ሥራው ላይም በተመሳሳይ መሠራት እንዳለበት ይገልጻሉ።
እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ማብራሪያ፤ የቅርሶቹን ጥቅም ከሀገር አንጻር ብቻ የሚታይ ከሆነ ዘርፉ በምጣኔያዊ እድገት ላይ እንዲያመጣ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም። የማኅበረሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መኖር አለበት። ማኅበረሰብ ሲጠቀም ጠብቆና ተንከባክቦ ይይዛቸዋል። የኔነት ስሜት ይኖረዋል። ይህ ካልሆነ ቅርሶቹ የመኖር ህልውናም ፈተና ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡
ማን ምን ይስራ የሚለውንም ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደገለጹት፤ በመንግሥት ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ከፍተኛውን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል። ተቋሙ በማስተባበር፣ በመምራት፣ ምቹ መደላድል የመፍጠር ሚና አለው። የሚሰራውን ሥራም ተግባርና ተልዕኮውን መወጣት ያለበት በፖሊሲ በማስደገፍ ነው። በሌላ በኩልም ቅርሶቹ በሚገኙበት አካባቢዎች መንገድ፣ መብራት፣ ስልክ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ለእንግዶች ወይንም ለቱሪስቶች ማረፊያና መዝናኛ መሟላቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በተለይ ማረፊያና መዝናኛዎችን ማሟላት የሚቻለው ከግሉ ዘርፍ ጋር በመሥራት በመሆኑ ኢንቨስትመንትን መሳብና ማበረታታት ያስፈልጋል።
እነዚህን ነገሮች ማሟላት ከተቻለ ቀጥሎ የሚመጣው ቅርሶቹ የሚገኙበትን አካባቢ በስፍራውም ስላለው ሁኔታ መልካም ገጽታን በሚገነባ ሁኔታ በተደራጀ መልኩ መረጃ ይዞ በማስታወቂያ እራስን መሸጥ ነው። ይህን ተልዕኮ የመወጣት ሚና መጫወት ያለባቸው በማስታወቂያ ዘርፉ ላይ የሚገኙ ብቻ ሳይሆኑ መገናኛ ብዙኃንም ሀገራዊ ገጽታን በመገንባት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። ሁሉም የየድርሻውን ሲወጣና በቅንጅት ሲሰራ የሚፈለገውን ስኬት ማስመዝገብ ይቻላል።
በባህልና ቅርስ ላይ በጥናትና ምርምር ሥራ ላይ የሚገኙትም ቢሆኑ ቅርሶች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ፋይዳቸው፣ አሉታዊና አዎንታዊ ገጽታቸውን በጥናትና ምርምር ለይቶ መልካም የሆኑት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ አሉታዊ የሆኑትንም ለመከላከል እንደሚያስችል አስረድተዋል። ስለቅርሱም ትክክለኛ የሆነ መረጃ እንዲኖር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ቋንቋ በጽሑፍ የተደገፈ ነገር ማኖር ከዘርፉ ምሁራን የሚጠበቅ ሥራ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በተለያየ ቋንቋ ተሰንዶ ሲቀመጥ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ ይቻላል። እንዲህ በዘርፉ ምሁራን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ሥራዎች በጠረጴዛ መደርደሪያ ላይ መቅረት እንደሌለባቸውም አመልክተዋል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው በተለያየ አጋጣሚ በሚገኙባቸው መድረኮች፤ ቅርሶቹ በሚገኙበት አካባቢዎች የተሟላ መሠረተ ልማት ካለመኖር ጋር ተያይዞ እንደሚነሳ አስታውሰው፤ ለምክክር በሚቀርቡ መድረኮች ላይ የሚነሱ ክፍተቶችን ለይቶ መፍትሔ እየሰጡ መሄድ ካልተቻለና ምክክሩ ውጤት የማያመጣም ከሆነ ውይይት ለይስሙላ ብቻ ሆኖ እንደሚቀር አስረድተዋል።
ቱሪስቶች አንዴ ከመጡ በኋላ በድጋሚ እንዲመጡ የማድረግ ሥራ ካልተሠራ ቱሪስቶቹ መጥፎ ገጽታ ይዘው ሊመለሱ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችልም ገልጸዋል።
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ፤ ቀጣይ ሥራዎች ላይ ርብርብ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ቅርሶቹ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ የተደረገው ጥረት ለውጤት እንዲበቁ ማድረግ ሁሉም ባለድርሻ የየራሱን ኃላፊነት መወጣትና በቅንጅትም መሥራት እንዳለበት ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም