በቴሌ ብር አማካኝነት አንድ ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተደርጓል

– በቀን የአምስት ቢሊዮን ብር ዝውውር ይደረጋል

አዲስ አበባ፡- የቴሌ ብር አገልግሎት ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ አንስቶ አንድ ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ብር ዝውውር መደረጉን ኢትዮ ቴሌኮም ገለጸ። በቀን የአምስት ቢሊዮን ብር ዝውውር እንደሚደረግም አስታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት፤ የቴሌ ብር በዲጂታል አማራጭነት ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ገንዘብ ዝውውር ተደርጓል።

25 ባንኮች ከቴሌ ብር ጋራ ገንዘብ ዝውውር በማድረግ በትስስር እየሰሩ ይገኛል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ በዚህም የየዕለት የገንዘብ ዝውውሩ ሲታይ በቀን አምስት ቢሊዮን ብር ዝውውር ይደረጋል ብለዋል።

በቀን ዝውውር ከሚደረገው የገንዘብ መጠን 19 በመቶ የሚሆነው ከሌሎች ባንኮች ወደ ቴሌ ብር የሚገባ ሲሆን፤ 21 በመቶ የሚሆነው ከቴሌ ብር ወደ ሌሎች ባንኮችና የዲጂታል ፋይናንሲንግ አማራጮች የሚዘዋወር መሆኑን አስረድተዋል።

ከአጠቃላዩ የገንዘብ ልውውጥ 42 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ በኢ-ብር ግብይት ላይ ይውላል ሲሉ ተናግረው፤ ይህም ኢኮኖሚን ከገንዘብ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ለመገንባት ያለው ሚና የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።

አሠራሩ ጥሬ ገንዘብ ማሳተም ሳያስፈልግ በዲጅታል ፋናንሲንግ ብቻ ለመጠቀም እድል እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

 ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደተናገሩት፤ ከቁጠባ ሂሳብ አንጻርም በአንድ ዓመት ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ደንበኞች 7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የቁጠባ ሂሳብ ተንቀሳቃሽ አድርገዋል።

በተጨማሪም በአንድ ዓመት ውስጥ ከንግድ ባንክና ከዳሽን ባንክ ጋር በጋራ በተቀረጸ የዲጅታል ፋይናንሲንግ አቅርቦት ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ደንበኞች ስምንት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የብድር አገልግሎት መሰጠቱን አስታውሰዋል።

የብድር አቅርቦቱ ለተለያዩ የሥራ ዕድል ፈጠራዎችና ለኢኮኖሚ ግንባታ እየዋለ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አመላክተዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፤ አሁን ላይ የቴሌ ብር ደንበኞች ቁጥር 40 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት 44 ሚሊዮን ለማድረስ እቅድ ተይዟል።

ኢትዮ ቴሌኮም 73 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት አመላክተው፤ ደንበኞቹ ስልክ ከመደወል እና መልዕክት ከመላክ ያለፈ በስልካቸው አማካኝነት በርካታ ተግባራትን እንዲከውኑ ለማስቻል አዳዲስ ሥራዎች በቀጣይ እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You