በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ያለ ጥናትና ምርምር ጋት እልፍ ማለት አይቻልም። በመሆኑም፣ ጥናትና ምርምር፣ የጥናትና ምርምሩ ግኝትና ምክረ ሀሳብ (ሀሳቦች) የሁሉም ነገር መሽከርክሪት እንዲሆኑ ዘመኑ ፈቅዶላቸዋል።
እንደ መታደል ሆኖ፣ ዓለም እንደ አጠቃላይ ስትታይ የሰው ልጅ አእምሮ (ያው ጥናትና ምርምር ማለት ነው) መሰልጠንና መራቀቅ ምክንያት ከነበረችበት ዳዴ ተስፈንጥራ ጨረቃ ላይ ወጥታለች። “በምድር ተሽከርካሪ፤ በሰማይ በራሪን መጠሪያዋ ከማድረግም አልፋ ባህሩን በማቋረጥ እስከ መሰርጎድ (ሰርጓጅ መርከቡን አስቡት) ድረስ ረቃ፣ ተራቃለች።
እንዳ አለመታደል ሆኖ ደግሞ፣ በዚህ ባቡር ላይ ያልተሳፈሩ፣ ተሳፍረውም ከሆነ እየተንጠባጠቡ የትም የቀሩ የዓለም አካላት ያሉ ሲሆን፤ ቁጥራቸውም የትየለሌ፣ ችግራቸውም በዛው ልክ የምድር አሸዋን ያህል ሆኖ ኑሮን (“ኑሮ ከተባለ ማለት ነው) እየኖሩት ይገኛሉ።
የጥናትና ምርምር ሥራ ከማይፋታቸው፣ ተነጥሎም ከማይታይባቸው ጉዳዮች አንዱ ትምህርት ነው። ከጥናትና ምርምር በፊት ትምህርት መኖር አለበት። ትምህርት በሌለበት ተመራማሪ አይጠበቅም፤ ከተጠበቀም ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደ መሰማራት ነው የሚቆጠረው። በመሆኑም፣ የትምህርት ሥርዓት ላይ ወገብን ጠበቅ አድርጎ መስራት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው።
ይህ በትምህርት ላይ፣ በተለይም በትምህርት ጥራት ላይ ወገብን ጠበቅ አድርጎ መስራትን በተመለከተ በስፋት ከተሰራባቸውና እየተሰራባቸው ካሉ ተግባራት አንዱና ምናልባትም ዋናው ሲሆን፣ ውጤቱንም በመጠባበቅ ላይ ያሉ በብዙዎች ናቸው።
እንደሚታወቀውም ሆነ የዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ መጽሐፉም “ሁሉን መርምሩ፤ የተሻለውን ያዙ እንደሚለው፤ ዩኒቨርሲቲዎችም ሲቋቋሙ በየ“ዓላማዎቻቸው ስር እንዳሰፈሩት የትምህርት ጥራት በተጠበቀበት ምህዳር ጥራቱን የጠበቀና የአካባቢ ማህበረሰብን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማግኘት ብርቅ አይደለም። ማህበረሰብን፣ በተራዛሚውም ሀገርን ከገባበት አረንቋ ጎትተው የሚያወጡ ችግር ፈቺ የጥናትና መርምር ስራዎችን ማግኘት የሚገድ አይሆንም። ይህ ደግሞ የግድ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን፣ ባደጉት ሀገራት እንደሚታየው ከወታደራዊ ማእከላትም ችግር ፈቺ ብቻ ሳይሆን፣ አለማችንን ካለችበት አንድና ሁለት እርምጃዎች ወደ ፊት የሚያስኬዱ የጥናትና ምርምር (በተለይም ቴክኖሎጂ በማመንጨቱ መስክ) ሲፈልቁ እየታየ ነውና ዘርፉ ብዙዎችን ያስተሳሰረና የሚያስተሳስርም ነው። ጉዳዩን እናቅርበውና ወደ ሀገራችን እናምጣው።
የእኛ ሀገር ምሁራን የጥናትና ምርምር ስራዎች በይዘትና አቀራረባቸው “አንቱ የተባሉ (ወይም፣ ሊባሉ የሚችሉ) ሆነው ሳለ እስከ ዛሬ ያተረፉት ግን መደርደሪያ ላይ እየተንቀዋለሉ አቧራ መቃም ብቻ ነው። እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድም በመጥረጊያ ተጠርጎ መጣል (በአሁኑ ዘመን አማርኛ መወገድ) ነው።
እኛ ሀገር ላይ ዋጋ ያጡት የጥናትና ምርምር ስራዎች ብቻ አይደሉም፤ እራሳቸው ተቋማት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ያፈሰሱባቸውና ያስጠኗቸው ጥናቶች እንኳን ዞር ብሎ የሚያያቸው በመጥፋቱ በሁለትና ሶስት አመት ውስጥ እነዛው ጥናቶች እንደ ገና ብዙ ሚሊዮን ብር ተከፍሎ እንዲጠኑ ይደረጋል።
አይደለም የጥናትና ምርምር ስራዎች፣ የፖሊሲ ሰነዶች እንኳን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የማይደረጉበት፣ ደንብና ሥርዓት እንደ ልብ የሚጣስበት፤ ስንትና ስንት ታሪካዊና ፍልስፍናዊ ድርሳናት ተሽቀንጥረው የሚጣሉበት የእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን፤ እንደ አህጉር በድፍን አፍሪካ የጥናትና ምርምር ስራዎች ስፍራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይህ ደግሞ ሀሚታ ወይም አሉባልታ ሳይሆን የአፍሪካ ህብረት ያዘጋጃቸውን የተለያዩ ሰነዶች በመመልከት የተደረሰበት ድምዳሜ ነው።
ሌላው ሀገር የሌሎች ሀገራትን የጥናትና ምርምር ስራዎች እየዘረፈ ወደ ራሱ በማዳቀልና ሥራ ላይ በማዋል ትርፋማ ሲሆን፤ ወደ አፍሪካ ሲመጣ ግን እውነቱ የተገላቢጦሽ ሆኖ ይገኛል። ከዚህም በማለፍ “ነጮቹ እኮ ከአፍሪካ የዘረፉትን ነው ∙ ∙ ∙ በማለት ለመመፃደቅ ይሞከራል። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
አሁን አሁን፣ የዓለም ሁለንተናዊ ግስጋሴ እየፈጠነና እየረቀቀ በመሄዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ አልያም በድሮው መንገድ የሚሄዱ በአዲስ መንገድ በሚሄዱት ሊሰለቀጡ የሚችሉበት እድልና አጋጣሚ እየገሰገሰ በመምጣት ላይ ሊሆን ይችላል አንዳንድ ሀገራት ወደ ቀልባቸው እየተመለሱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም አንዷ ነች።
ዘንድሮ ከሌሎቹና ካለፉት ለየት የሚለው ምንጊዜም “ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ስራቸው በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምር ተግባራትን አጠናክረው ለሀገር እድገት የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ ማጎልበት እንዳለባቸው ሲናገር እንደ ነበረው፤ ሰሞኑንም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ስራዎች ላይ የመከረውና በቦንጋ በተካሄደው የየዩኒቨርሲቲዎች ምክትል ፕሬዚዳንቶች ፎረም ላይም እንደደገመው፤ ትምህርት ሚኒስቴር ዘንድሮ ጉዳዩን በሕግ ማእቀፍ አስደግፎ፤ የሕግ ማእቀፍ እንዲኖረው አድርጎ ወደ ሥራ ለመግባት መንደርደሩ ነው። ወደ ሰነዶች እንሂድና ገዥ የሆነውን በመመልከት “አዋጁ ምን ይላል?የሚለውን እንይ።
ማንኛውም ተግባር በአግባቡ እንዲከናወን፣ የሚመለከታቸውም በራስ መተማመን መንፈስ ወደ ሥራ እንዲገቡ ከተፈለገ ጉዳዩ የሕግ ማእቀፍ ያስፈልገዋል የሚል ነገር አለ። እውነት ነው፤ አንድ ጉዳይ ወይም ተግባር የሕግ ማእቀፍ ካለው፣ የሕግ ማእቀፉ በአሰሪ ፖሊሲዎች ከተደገፈ ውጤታማነቱ የሚያሻማ አይሆንም።
ሰሞኑን ይፋ የሆነው፣ የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ቁጥር 1298/2015 የአዋጁን መውጣት አስፈላጊነት ሲያስቀምጥ:−
• በሀገራችን የተጀመረውን ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ተገቢነት ማረጋገጥ ለምናስበው ሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ በመሆኑ፣
• የትምህርትና ሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የተማሪዎችና ሠልጣኞች የተግባር ሥልጠና (ኢንተርንሽፕ)፣ የመምህራንና አሠልጣኞች የኢንዱስትሪ ተሞክሮና ጉድኝት (ኤክስተርንሽፕ)፣ የኢንዱስትሪ ሙያተኞች በትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የሚያበረክቱት የተግባር ትምህርትና ሥልጠና አስፈላጊ በመሆኑ፣
• ከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና የምርምር ተቋማት ከኢንዱስትሪ ጋር በመተሳሰር ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማማከር አገልግሎት ሥራዎችን ማከናወን ስለሚጠበቅባቸው እና ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ ለመገንባት ለኢንዱስትሪው ብቁ የሰው ኃይል፣ ችግር-ፈቺ ምርምር የማካሄድና ቴክኖሎጂ የማመንጨት ተልዕኮ ስላላቸው፣
• የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ ምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪ ትስስር በጋራ ተጠቃሚነትና የትስስር አካላትን ንቁ ተሳታፊነት ስለሚጠይቅ፤ እንዲሁም፣ በሀገራችን ብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ላይ የተመላከቱ የትስስር ቁልፍ ጉዳዮችን በሕግ መደንገግ በማስፈለጉ፣
• በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55(1) (፶፭(፩)) መሠረት የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ወጥቷል፡፡
በማለት ነው።
ከዚህ አኳያ ከተመለከትነው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ለየአካባቢያቸው ማህበረሰብ ከሚሰጡት አገልግሎት ባለፈ አገራዊ ጥቅማቸው በቀላሉ የሚታይ አይሆንም ማለት ነው።
አዋጁ ትስስር (በፎረሙ ላይ “ጉድኝት በሚል ጥቅም ላይ ውሏል) የሚለውን መሰረተ ሀሳብ ሲያብራራም:−
“ትስስር” ማለት በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፣ በምርምር ተቋማት እና በኢንዱስትሪ መካከል በዚህ አዋጅ በተደነገጉ አቅጣጫዎች፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርሆዎች የሚካሄድ የተማሪዎችና ሠልጣኞች የተግባር ትምህርትና ሥልጠና (ኢንተርንሽፕ)፣ የመምህራንና አሠልጣኞች የኢንዱስትሪ ተሞክሮና ጉድኝት(ኤክስተርንሽፕ)፣ የኢንዱስትሪ ሙያተኞች በትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የሚያበረክቱት የተግባር ትምህርትና ሥልጠና፣ እና በትብብር የሚካሄድ የምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና የማማከር ሥራዎች ጉድኝት ሥራዎች ነው፡፡
በማለት ሲሆን፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምንም:-
“ከፍተኛ ትምህርት ተቋም’’ ማለት በመንግሥት ወይም በግል ባለቤትነት ሥር የሚተደደርና በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ የዲግሪ መርሐ ግብሮች የሚሰጥ፣ የጥናትና ምርምር እና የማህበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን የሚሠራ ተቋም ነው፡፡
በማለት ይገልፀዋል። የትስስሩ አካላትንም:−
“የትስስሩ አካላት” ማለት የትስስሩ ዋና ተዋንያን ሲሆኑ እነርሱም ቅድሚያ ትኩረት የተሰጣቸው የኢኮኖሚ ሴክተር መሪ መሥሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የምርምር ተቋማት፣ የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት፣ የግል አምራችና አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች፣ የፌዴራልና ክልል ንግድ ምክር ቤትና ዘርፍ ማህበራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀገር በቀል ድርጅቶች፣ የሙያና ሲቪክ ማህበራት እና ሌሎች በምክር ቤቱ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ሲል ይዘረዝራል።
“የትስስሩ ዓላማን በተመለከተም− “የትስስር ሥራዎችን ሀገራዊ የልማት አጀንዳን ባገናዘበ መልኩ በቅንጅት፣ በወጥነት፣ በተጠያቂነት እና በብቃት በመተግበር፣ ውጤታማነትን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ ነው። ይላል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተግባር እና ኃላፊነትን በተመለከተም በአዋጁ አንቀፅ 9 ስር “የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚከተሉት ተግባር እና ኃላፊነ[ቶች] ይኖ[ሩታ]ል በሚል ንኡስ ርእስ ስር የሰፈረ (ሰባት ነጥቦች) ሲሆን፣ ሙሉ ቃሉም የሚከተለው ነው።
በተቋማዊ የስትራቴጂ ሰነዶች ውስጥ የትስስር ሥራን የማካተት፤ የትስስር ሥራን ለመስራት የሚያስችል የሰው ኃይልና በጀት የመመደብ፣ የትስስር ገቢን የማስተዳደር እና የአሠራር ሥርዓት የመዘርጋት፤ በትስስሩ ሂደት የማህበረሰቡን ችግር ትኩረት ሰጥቶ መፍታትና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ፤ በምክር ቤቱ የተለዩ እና ቅድሚያ የተሰጣቸውን የትስስር ተግባራት መሠረት በማድረግ የተቋሙን የተልዕኮ ልየታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ እንዲሁም፣ የቁልፍ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በሚያረጋግጥ አግባብ የማቀድና የመተግበር፤ በትስስር የሚከናወን ምርምርና ፈጠራ በትስስሩ ለማሳካት የተለዩትን የባለድርሻ አካላት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የማረጋገጥ እና አስፈላጊውን ፈንድ በጋራ ማፈላለግ፤ በትስስሩ የሚከናወኑ ተግባራት ለትምህርትና ምርምር ጥራት፣ ለማህበረሰብ ጉድኝት፣ ለኢንዱስትሪዎች እና ኢንተርፕራይዞች ውጤታማነት በሚያግዝ አግባብ መተግበሩን ማረጋገጥ፤ በትስስር የሚገኝ የአእምሯዊ ንብረት መብት ጸንተው ሥራ ላይ ባሉ ሕጎች እና የትስስሩን አካላት መብት እና ጥቅም በሚያስጠብቅ አግባብ ለትምህርታዊ አገልግሎቶች የማዋል ተግባርና ኃላፊነት አለበት፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ ተለዋውጠውበታል፤ ቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ተቀምጦበታል፤ አዳዲስ አሰራሮችና ፕሮግራሞች ተዋውቀውበታል፤ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስርአት ተዘርግቶበታል፤ እንዲሁም፣ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል ከሚያደርጉት የጥናትና ምርምር ስራዎች ባለፈ በቅንጅት የሚሰሩበትን እድል ይፈጥራል፣ የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ምርምር ተቋማትና ኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ተደርጎበታል በተባለለት፣ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲው የምክክር ፎረም ላይስ ምን ምን ጉዳዮች ተነሱ፤ ምን ውሳኔስ ተላለፈ?
የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሳተፉበት፣ በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ተግባራት አፈጻጸም ላይ በመከረው፤ ከሩሲያና አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተመራማሪዎች ጭምር በተገኙበት በዚሁ የምክክርና የጉድኝት መድረክ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ እንዳመለከቱት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ስራቸው ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የሆኑ የተለያዩ ጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ለሀገር እድገት የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
ከተቋቋመ ካለፉት 5 ዓመታት ጀምሮ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ መስኮች ያከናወናቸው ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸው፣ አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግም ባለፈ፣ የመኖሪያ ቤትና የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታን በማከናወን ላይ መሆኑ በተነገረለት ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ይህ ፎረም፣ በአይነቱ የመጀመሪያ ባይሆንም “የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ ምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ የተዋወቀበትና የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለአገራዊ ፋይዳና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ለማዋል፤ ቃል የተገባበት መሆኑ “የመጀመሪያው ያደርገዋል።
በመጨረሻም፣ ምንም እንኳን “ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች፣ “ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ∙ ∙ ∙፣ “የአገሪቱን ልማት የሚያፋጥኑ፣ “የዲሞክራሲ ባህልን የሚያሰርፁ ∙ ∙ ∙፤ “ሰላምና ወንድማማችነትን የሚያሰፍኑ ∙ ∙ ∙ ወዘተ የሚሉት የቃላት ድርድሮች እንኳን ለእኛ በሩቅ ለሚያውቁንም የሰለቹ ብቻ ሳይሆኑ የቸኮሉም ጭምር ናቸው። በመሆኑም፣ ሪፎርምን እጅጉን ይፈልጋሉ።
ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲን የመሳሰሉት የጥናትና ምርምር ስራዎችን እታች ድረስ በማውረድና አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ጥሩ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ቢሆንም፤ እንደ ሀገር በዚህ መልኩ እየተሰራ ነው ለማለት ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ የለም። በመሆኑም፣ በዚህ፣ 5ኛ ትውልድ በሆነው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ምክክር አማካኝነት ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውና ወደ ተግባር ለመግባት በአዋጅ የተደገፉት እቅዶች ያለ ምንም መዛነፍ ተጠናክረው ሊቀጥሉና ሙሉ ለሙሉ በተግባር ሊገለጡ፤ በተለይ፣ የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንቶችም ጉዳዩን ዳር ከማድረስ አኳያ በርትተው ሊሰሩ ይገባል እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም