የማዳበሪያ አቅርቦት ማነቆ መፍቻው ያስገኛቸው ውጤቶች

የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የመንግሥት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ለእዚህም በማዳበሪያ አቅርቦት፣ በማሳና በሜካናይዜሽን እንዲሁም ለሜካናይዜሽን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር በታመነበት ኩታ ገጠም ማሳ ማስፋፋት ላይ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

መንግሥት ለምርትና ምርታማነት ማሳደጉ ሥራ ወሳኝ ከሆኑት ግብዓቶች መካከል አንዱ የሆነውን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በድጎማ እያቀረበ ይገኛል፤ ለእዚህ የሚመደበው በጀትም ከዓመት ዓመት እያደገ፣ የሚቀርበው የማዳበሪያ መጠንም እንዲሁ እየጨመረ መጥቷል።

ለአፈር ማዳበሪያ የሚያስፈልገውን በጀት በመመደብ ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት ማደግ መንግሥት ቁርጠኛ ቢሆንም፣ ማዳበሪያውን በመግዛትና ለአርሶ አደሩ በማቅረብ በኩል ያለው ሂደት እስከ አለፈው የመኸር ወቅት ድረስ ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል። በተለይም ፈተናውን ከባድ ሲያደርጉ ከነበሩት ችግሮች መካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የማዳበሪያ የግዥ ሥርዓቱ ችግር ያለበት መሆኑ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር በተለይም ያለፉት ሦስት ዓመታት፤ በተለይ ደግሞ የአምናው የመኸር ወቅት የግብርናው ዘርፍ ፈተና ሆኖ ታይቷል። በዚያን ወቅት የአንዳንድ አካባቢ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ በወቅቱ እየደረሳቸው ስለአለመሆኑ በስፋት ቅሬታ ያቀርቡም ነበር። በአንጻሩ ማዳበሪያ መያዝ የማይገባቸው አካላት ማዳበሪያውን በሕገወጥ መንገድ ያዘዋውሩ የነበረበት፣ በዋጋ በኩልም እንዲሁ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ያልተፈጸመበት ሁኔታ ስለመስተዋሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቆማዎች ይቀርቡ ነበር።

ይህ የማዳበሪያ ችግርና በግብርና ዘርፉ ላይ አሳድሮት የቆየው ተግዳሮት ዘንድሮ መፍትሔ እንዲያገኝ ተደርጓል። ለእዚህ ውጤት የተደረሰው በጣም በብዙ ፈተና እና ተግዳሮቶች ውስጥ ታልፎ መሆኑንም በቅርቡ መግለጫ የሰጡት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አስታውቀዋል። ሚኒስትሩ ግብርና በባሕሪው ሊሻገራቸው የሚገባ ማቆዎች እንዳሉትም ነው ያስታወቁት።

እርሳቸው እንዳሉት፤ የግብርናው ዘርፍ አንዱ ማነቆ የተባለው ጉዳይ ግብርናው የዝናብ ጥገኛ መሆኑ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ አሁን ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ዝናብ በወቅቱ የማይጥልበት ሁኔታ ሲፈጠር ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። አርሶ አደሩም እንደ እስከ አሁኑ ልምዱ ዝናብ ብቻ ጠብቆ የሚያርስ ከሆነ ግብርናውን ለፈተና ተጋላጭ ያደርገዋል። ስለዚህ ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ/ሥራው በዓመት፣ በሁለትና ሦስት ዓመት ውስጥ የሚሠራ ባይሆንም/ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ይኖርበታል።

ሌላው ማነቆ ሆኖ የቆየው የማዳበሪያ አቅርቦት ነው፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የማዳበሪያ አቅርቦት የጨመረበት ወቅት ነው ማለት ብቻ ሳይሆን የማዳበሪያ ዋጋም ከእጥፍ በላይ የናረበት ጊዜ ነበር ማለቱ ሁኔታውን ይበልጥ ገላጭ እንደሚያደርገው ሚኒስትሩ ያስረዳሉ። የማዳበሪያ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጨመሩ እንዳለ ሆኖ የእኛ የግዥ ሂደት የተንዛዛ መሆኑ የበለጠ በውድ እንድንገዛ አድርጎናል ሲሉም ሚኒስትሩ ያብራራሉ። በመንግሥት ቁርጠኝነት በግዥ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፣ በዚህም ለማዳበሪያ ግዥ ይወጣ የነበረውን ወጪም መቆጠብ መቻሉን ተናግረዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት መንግሥት ለማዳበሪያ ግዥ ድጎማ አያደርግም ነበር። በገዛበት ዋጋ ቀጥታ ለአርሶ አደሩ ያስተላልፍ ነበር። አምና 13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ መንግሥት ድጎማ አድርጓል። በአምናው ዋጋ ማዳበሪያ ገዝተን ቢሆን ኖሮ ዘንድሮ 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት ብዙ ቢሊዮን ብር ያስፈልገን ነበር።

አሁን ተግባራዊ በተደረገው የግዥ ሥርዓት ለውጥ ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ በሚፈለግበት ጊዜ ገዝቶ ማድረስ ተችሏል። ይህ ብቻ አይደለም ወጪ መቀነስም ተችሏል። መንግሥት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የድጎማ ጫናም በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይም የራሱ የሆነ ትርጉም ይኖረዋል።

በቀጣዮቹ ዓመታትም ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰድ ከተቻለ የተቀነሰው ድጎማ በኢኮኖሚው ውስጥ ገብቶ ለሌላ ዘርፍ ድጋፍ እንዲውል ማድረግ ያስችላል። በግብርና ዘርፍ ውስጥ ለሚከናወኑ ሥራዎች ድጋፎችን ማድረግ እንደሚያስችል ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የግዥው ሥርዓት ከዋጋ አንጻር ያለውን የድጎማ መጠን ቀንሷል የሚሉት የግብርና ሚኒስትሩ፣ የግዥ ሥርዓቱ የመስተካከሉ ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ፋይዳ የአፈር ማዳበሪያን በብዙ መጠን ለመግዛት መርዳቱ መሆኑንም አመልክተዋል። አምና 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መገዛቱን አስታውሰው፣ የአሠራሩ መስተካከል ዘንድሮ 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በመግዛት ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ የማድረግ አቅም ሰጥቶናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው ማዳበሪያ ብቻ እንዳልሆነም የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ መድኃኒት፣ ነዳጅ እና ሌሎችንም እንደምታስገባ ይገልጻሉ፤ በአፈር ማዳበሪያ ግዥ ላይ የተፈጠረው ብቃት አንደኛ የመንግሥትን የድጎማ ጫና መቀነስ ማስቻሉን ተናግረዋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መጠኑ ሰፊ የሆነ ከአምናው አንጻር ሲተያይ ስድስት ሚሊዮን ተጨማሪ ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ጨምረን እንድንገዛ አቅም ፈጥሮልናል ሲሉ አብራርተዋል። በሦስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና ዋና ተብሎ የሚጠቀሰው የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱና በጊዜው ወደ እርሶ አደሩ ማድረስ መቻሉ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ እንደሚሉት፤ አምና የነበረው ችግር ማዳበሪያ መግዛት ላይ ብቻ የታየ አይደለም። አርሶ አደሩ ለመዝራት ሲዘጋጅ ማዳበሪያ እርሱ ዘንድ አለመድረሱም ላይ ነው። የተገዛው ማዳበሪያ በሰዓቱ እና በሚያስፈልገው ጊዜ ወደአርሶ አደሩ የማይደርስ ከሆነ የቱንም ያህል በብዙ መጠን ቢገዛ ትርፉ ድካም እንጂ ውጤት አይኖረውም።

አሁን እኛ ፈተና እየሆነብን ያለው ማስቀመጫ ቦታ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ማዳበሪያውን እያስገባን ያለነው ቀድመን ስለሆነ ለአርሶ አደሩ ቶሎ ተደራሽ ካላደረግን የማከማቻ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል ብለዋል። ‹‹የምንገዛውን 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ማከማቸት የሚያስችል መጋዘን (ቦታ) የለንም። ›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ማዳበሪያውን የምናመጣው ወቅት እየጠበቅን መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል። ለምሳሌ ለመስኖ የምናመጣውን አርሶ አደሩ ወዲያውኑ ይወስደዋል። ከዚያ መጋዘናችን ክፍት ስለሚሆን ለበልግ ደግሞ እናመጣለን። የበልጉ ቦታ ሲለቅ ለመኸር ይመጣል ሲሉ ያብራሩት ሚኒስትሩ፣ ስለዚህ የምናመጣውን የአፈር ማዳበሪያ በየወቅቱ በመከፋፈል ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።

ለአብነትም ደቡብ ምዕራብ ክልልን ለእነርሱ መኸር የሚባለው ከሌላው አካባቢ በወቅት ደረጃ የተለያየ ነው። በክልሉ በቆሎ የሚዘራበት ጊዜ የካቲት ወይም መጋቢት አካባቢ ነው። ሌላው አካባቢ ደግሞ የሚሆነው ሚያዚያ ላይ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት እየገባ ያለው የአፈር ማዳበሪያ ለእነርሱም ጭምር የሚውል ነው ሲሉ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

‹‹በአሁኑ ወቅት የበልግ ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ተገዝቷል። ስለዚህ ለበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች ማዳበሪያ ቀድሞ መጋዘናቸው ውስጥ ይገኛል። ስለዚህ ማዳበሪያውን መግዛት ብቻ ሳይሆን ሪፎርም ያደረግነው ማዳበሪያ የሚጫንበትንና የሚደርስበትንም ጊዜ ጭምር ነው›› ብለዋል።

ሚኒስትሩ፣ ከዚህ ጋር አያይዘው የጠቀሱት ጉዳይ የአፈር ማዳበሪያን ከሚያጓጉዙ ትራንስፖርተሮች ጋር በቅርቡ የተደረገውን መወያየታቸውን ነው። ‹‹በወቅቱ ከትራንስፖርተሮቹ ጋር በተደረገ ውይይት ከእነርሱ በኩል የተገለጸው ወደ ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር የሚገባው ምርት የሚበዛባት እና የሚያንስበት ጊዜ መኖሩ ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ እኛ ማዳበሪያ የምንጭነው በጥቅምት፣ ኅዳርና ታኅሣሥ ላይ ነው። ትራንስፖርተሮቹ በዚህ ጊዜ ሥራ አልነበራቸውም። እኛ ያደረግነው ይህን አቅም መጠቀም ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።

‹‹አምና ሎጅስቲክስ ሁሉ አቁመን ነው ማዳበሪያ ሰኔና ግንቦት አካባቢ የጫንነው›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስታውሰው፤ ይህ የተደረገው ሁሉም በአንድ ጊዜ ስለመጣ መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹ስለዚህ ዘንድሮ ምንም አይነት የሎጂስቲክስ መንገራገጭ ሳይኖር ቀድመን በማምጣት ያለን የሎጂስቲክስ አቅም ነፃ በሚሆንበት ጊዜ በመጫን ባቡሩን ተጠቅመን ሌሎች የኢኮኖሚ ሥራዎች ላይ ተፅዕኖ በማይኖርበት ሁኔታ መሥራት ችለናል ሲሉ አብራርተዋል።

ግዥያችንን ስላቀድን የትኛውን ማዳበሪያ መቼ እንጫን? የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ አቅማችን የሀገራችን ይታወቃልና በማይንገራገጭበት ሁኔታ እንዴት እንጫን? የሚለውን ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በጣም ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ሥራ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። እውነቱን ለመናገር እንደ እኔ አመለካከት በዚህ ላይ የተሠራው ሥራ ባለፉት አምስት ወራት ሠራን ከምንላቸው ትልቅ ሪፎርሞች ውስጥ እንደ አንዱ ሊቆጠር የሚችል ነው። ምክንያቱም 20 ቢሊዮን ብር መቆጠብ ለኢትዮጵያ በቀላሉ የሚታይ አይደለም›› ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ምርጥ ዘርም ሆነ ማዳበሪያ አርሶ አደሩ እንዲወስድ ሁሌም ይጠይቅ እንደነበር አስታውሰው፣ ያኔ ግብዓትን እምብዛም የሚወስድ እንዳልነበረ ገልጸዋል። በዚህ የተነሳም ምርጥ ዘር መጋዘን ውስጥ የሚበሰብስበት፣ በተመሳሳይም የአፈር ማዳበሪያ የሚወገድበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህ አመለካከት መቀየሩን ጠቅሰው፣ ባለፉት ዓመታት በተሠሩ የኤክስቴንሽን ሥራዎች አርሶ አደሩ “ቴክኖሎጂ አምጡ” የሚልበት ሁኔታ መፈጠሩን መመልከት መቻሉን አስታውቀዋል። አርሶ አደሩ ማዳበሪያውንም ምርጥ ዘሩንም አቅርቡ እያለ ጥያቄ እንደሚያቀርብ ጠቅሰው፣ ማሟላት ያልተቻለው ይህን አርሶ አደሩ ዘንድ የተፈጠረውን ፍላጎት መሆኑን አስታውቀዋል። በቀጣዮቹ ዓመታት ትልቅ ሥራ መሥራት ያለብን በአርሶ እና አርብቶ አደሩ ዘንድ የተፈጠረውን ይህን የቴክኖሎጂ ፍላጎት ለማሟላት መረባረብ ላይ ይሆናል ብለዋል ።

እርሳቸው እንዳሉት፤ ለዚህም ነው ማዳበሪያ ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት የተፈለገው። ማዳበሪያን በተመለከተ አምና የቀረበው 13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ነበር። የዘንድሮው ፍላጎት ሲጠና 23 ሚሊዮን ማቅረብ የሚያስችል ፍላጎት እንዳለ ተለይቷል። ለእዚህም ነው 23 ሚሊዮን ኩንታል ለማቅረብ ታቅዶ የነበረው። ይህ አኃዝ ከአምናው የአስር ሚሊዮን ጭማሪ ያለው ነው።

ይህ ፍላጎት ሁሌም የሚገደበው አቅም መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ቢያንስ ዘንድሮ በተሻለ መንገድ በመግዛታችን ከአምና ያነሰ ሀብት ቢመደብም እንኳ 19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ከአምናው የስድስት ሚሊዮን ጭማሪ ያለው ማዳበሪያ እንገዛለን ብለዋል። ይህም በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የተደረገ ትልቅ ጭማሪ ነው ብለን ወስደናል ብለዋል።

ግብርናን ማዘመንን አስመልክተው ሲገልጹም ‹‹አማራጮችን መጠቀም ከቻልን፣ ግብርናችንን ሜካናይዝ ካደረግን፣ ኩታ ገጠምን ሰፋ አድርገን ከሄድንበትና ግብዓት ማቅረብ ከቻልን ግብርናን ማዘመን ከእነዚህ ውጭ ሌላ ነገር የለውም ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ይህንን መንገድ ጀምራለች፤ ግብርናዋ ተንቀሳቅሷል። ነገር ግን መድረስ የሚገባት ደረጃ ላይ አልደረሰችም። በእዚህ ሁሉ ውጤታማ ለመሆን የጀማመረቻቸውን ሥራዎች እና ውጤት የተገኘባቸውን ሥራዎች እያሰፋች መሔድ ይጠይቃታል ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You