ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዱባይ ማራቶን ለድል ይጠበቃሉ

በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚካሄዱ ታላላቅ የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱና ዋነኛው የዱባይ ማራቶን ነው፡፡ የዱባይ ማራቶን ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት የሚገኝበት ከመሆኑ በዘለለ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ፍፁም የበላይነት የሚንፀባረቅበት መሆኑ ይታወቃል፡፡

የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያው ትልቅ የጎዳና ላይ ውድድር የሆነው የዱባይ ማራቶን የ2024 መርሀ ግብሩን በመጪው ዓርብ ሲያከናውንም የተለመደው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ይጠበቃል። ለዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከወዲሁ መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡

የ2023 የዱባይ ማራቶን በአንድ ለየት ያለ ክስተት ይታወሳል፡፡ ይህም በሁለቱም ፆታ አንድ ቤተሰብ ቻምፒዮን የሆነበት ታሪክ ነው፡፡ የ2022 የዓለም የማራቶን ቻምፒዮኑ ኢትዮጵያዊ አትሌት ታምራት ቶላ ባለቤት የሆነችው አትሌት ዴራ ዲዳ በሴቶች አሸናፊ ስትሆን የታምራት ወንድም አብዲሳ ቶላ ደግሞ በወንዶቹ ፉክክር አሸናፊ ነበር፡፡ ታምራት ቶላም ቢሆን ከዓመታት በፊት ይህንኑ የዱባይ ማራቶን ያሸነፈ አትሌት በመሆኑ በውድድሩ ስኬታማ ቤተሰብ አሰኝቷቸዋል፡፡

የአምናዋ ቻምፒዮን ዴራ ዲዳ 2018 እና 2020 ላይ በዚሁ ውድድር ሰባተኛና አምስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ግን ፉክክሩ ገና ሁለት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት ቀድማ በመውጣት በአስደናቂ ብቃት 2፡21፡11 በሆነ ሰዓት ማሸነፏ ይታወሳል፡፡ ይህች አትሌት ዘንድሮም በውድድሩ አሸናፊነትን ለማስጠበቅ መዘጋጀቷ ታውቋል፡፡ የባለቤቴ ወንድምና የአምናው ቻምፒዮን አብዲሳ ቶላ ግን በጉዳት ምክንያት በዘንድሮው ውድድር እንደማይፎካከር ታውቋል፡፡

ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው የማራቶን ውድድሮች አንዱ በሆነው የዱባይ ማራቶን ዘንድሮ ዴራ ዲዳን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ሀገራቸውን ወክለው በታላቁ መድረክ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ሰዓት ለማስመዝገብ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ አስደናቂ ለውጥና ብቃት እያሳየች የምትገኘው አትሌት ዴራ ዲዳ በ2023 በ10 ሺ ሜትር እንዲሁም በግማሽ ማራቶን ውድድሮች የራሷን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ከዚህ ስኬት ከሰባት ወራት በኋላም ነበር የዱባይ ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ ማሸነፍ የቻለችው። የ27 ዓመቷ አትሌት ከዱባይ ማራቶን ድሏ በኋላም ዘንድሮ በበርሊን ማራቶን 2፡19፡24 የሆነ የራሷን የማራቶን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ የዱባይ ማራቶንም እያሳየች የምትገኘውን ለውጥ ታስቀጥላለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በ10 እና 5ሺ ሜትሮች የሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ድራ ዲዳ ‹‹ባለፈው የዱባይ ማራቶን ውድድሩን መምራት ስትጀምር እንደማሸንፍ አውቅ ነበር፣ ፉክክሩም አስደናቂ ነው፣ ከእኔ ቀጥሎ የወንዶቹን ውድድር አብዲሳ ማሸነፉ ደግሞ የተለየ ስሜት ነበረው›› በማለት ስለ አምናው ውድድር ታስታውሳለች።

የሁለት ጊዜ የዓለም አገር አቀራጭ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ዴራ ዘንድሮም ዱባይ ላይ ሌላ ታሪክ እንደምትሰራ የውድድሩ አዘጋጆች ተስፋ አድርገዋል፡፡

የዱባይ ማራቶን ውድድር ዳይሬክተር ፒተር ኮኔርቶን  ‹‹ ሁሌም ቢሆን የውድድሩ አሸናፊዎች ዳግም ሲወዳደሩ ያስደስተናል፣ ከአንድ ቤተሰብ ሁለት ሰው ሲያሸንፍ ማየት ትልቅ ስኬት ነው፣ ዘንድሮም ዴራ ቻምፒዮንነቷን ለማስጠበቅ ወደ ውድድሩ በመመለሷ ተደስተናል›› በማለት ለመገናኛ ብዙኋን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዘንድሮው ውድድር የዴራ ዲዳ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደምትሆን የምትጠበቀው የሮተርዳምና የኦሳካ ማራቶን አሸናፊዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሄቨን ሀይሉ የአሸናፊነት ፉክክሩን ከተቀላቀሉ ጠንካራ አትሌቶች አንዷ ሆናለች። የ25 ዓመቷ ድንቅ አትሌት በርቀቱ የራሷን ፈጣን ሰዓት በ2፡20፡ 19 ያስመዘገበችው በ2019 አምስተርዳም ማራቶን ላይ ነው። የ2023 የሮም ማራቶንን በ2፡23፡02 ያሸነፈችው ኬንያዊቷ ቤቲ ቼፕክዎኒ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ጠንካራ ፉክክር ታደርጋለች፡፡

በዘንድሮው የዱባይ ማራቶን በወንዶች እስከ ትናንት በይፋ እንደሚሳተፉ ያረጋገጡ ኢትዮጵያውያን ሁለት አትሌቶችን አዘጋጆቹ ይፋ አድርገዋል፡፡ በ2022 ሀምበርግ ማራቶን 2፡ 05፡07 የራሱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው አትሌት ወርቅነህ ታደሰ አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው አትሌት ከበደ ቱሉ ሲሆን 2020 ሙምባይ ማራቶን ላይ ከተወዳደረ በኋላ በዘንድሮው የሴቪሊ ማራቶን የራሱን ምርጥ ሰዓት በ2፡05፡19 ማስመዝገብ የቻለ ነው። በዘንድሮው የዱባይ ማራቶን በሁለቱም ፆታ የሚሳተፉ ሌሎች በርካታ አትሌቶችም በመጪዎቹ ቀናት ይታወቃሉ፡፡

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You