በክልሉ የየብስ ትራንስፖርትን ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- ከተለያየ አቅጣጫ ወደ ክልሉ የሚገቡ የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከየብስ ትራንስፖርት አንጻር የገጠመውን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ እየተሠራ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በተለይ በመጪው የገናና የጥምቀት በዓላት መዳረሻ ድረስ የፀጥታ ኃይሉ ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር ጥምረት በመፍጠር ሠላም እንዲሰፍን፣ ትራንስፖርት እንዳይቆራረጥ፣ እንግዶች እንዳይንገላቱ፣ ከተለያየ አቅጣጫ ወደ ክልሉ የሚገቡ የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር ሰፊ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።

በተጀመረው ሠላም የየብስ ትራንስፖርት ከተለያየ አቅጣጫ መምጣት ጀምሯል ያሉት ኃላፊው፤ በቀጣይ ተጠናክሮ ተግባራዊ በሚደረገው የሠላም ሁኔታ የሕዝብ ትራንስፖርት ሙሉ ለሙሉ እንዲጀመር እየተሠራ እንዳለ ተናግረዋል። በተለይ የገና በዓል መዳረሻ ቀናት ውስጥ ብዙ ነገሮች እንደሚስተካከሉ ጠቁመው፣ እንግዶች በየብስም ሆነ በአየር የትራንስፖርት አማራጮች ወደ ክልሉ መምጣት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በአሁን ወቅት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከአዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ጎንደር ላሊባላ እየተሰጠ እንዳለ በመጥቀስ፤ አሁን ደግሞ ከባሕርዳር ላሊበላና ጎንደር አገልግሎት እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በመንገድ ትራንስፖርት በተለያየ መንገድ ተጀምረው የቆሙት ዳግም መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጎዱ መንገዶች ጥገና እንዲደረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ኃላፊው አክለው እንደተናገሩት፤ የፀጥታ ኃይሉ የአካባቢውን ሠላም ለማስጠበቅ እየሠራ ይገኛል። በአሁን ወቅት አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙ ችግሮች ውጪ በአንጻራዊነት በብዙ ቦታዎች ላይ ሠላም ሰፍኗል። የሚገጥሙ ችግሮችንም የፀጥታ ኃይሉ እየተከታተለ ከምንጫቸው ለማድረቅ እየሠራ ይገኛል።

በተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች የሚሰማውና መሬት ላይ ያለው እውነታ ይለያያል ያሉት ዶክተር መንገሻ፤ ኅብረተሰቡ ለራሱ የፀጥታው ባለቤት ሆኖ መረጃዎችን እየሰጠ፣ ችግር ያለባቸውን አካላት እያጋለጠ እንደሚገኝ፤ በዚህም በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉና ሠላም እየሰፈነ እንዳለ ተናግረዋል።

ሆኖም በውጪ ያሉ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ በቱሪዝም ከዓለም ድርሻዋን እንዳትወስድ የሀገርንና የክልሉን ገጽታ የማበላሸት ተልዕኮ አንግበው እየሠሩ እንዳለ ጠቅሰዋል። የራሳቸው የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አካላትም ቱሪስት እንዳይመጣ፣ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዳይሆን የራሳቸውን ቅስቀሳ እያደረጉ እንዳለ ጠቁመዋል። ይህ ሁኔታ ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዳ በመሆኑ በዚህ እኩይ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ ወገኖች የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማሰብ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ጎብኚዎች ኢንቨስት አድርገው ኢኮኖሚው ላይ የራሳቸውን አስተዋፅዖ አበርክተው በተወሰነ መልኩ መንገራገጭ የሚታይበትን የቱሪዝም ዘርፍ ማበረታታት እንዲችሉ የአካባቢው አመራር፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ከወጣቶችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ማድረግ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፤ “ሕዝቡ እየተጎሳቆለ ነው ያለው። የሕዝቡን ጥቅም የሚጎዳ ነገር ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም። ይህ መታረም አለበት። ይህን ለማስተካከል ሥራዎች ተሠርተዋል። በክልሉ የሠላም ጥሪ ተላልፏል። ብዙዎቹ ወደ ሠላማዊ መንገድ መጥተዋል። አንዳንድ የራሳቸውን ፍላጎት በተለያየ መንገድ ጥቅም ማስከበሪያ አድርገው የወሰዱ ኃይሎችና ወደ ሠላማዊ መንገድ ባልመጡት ላይ የሕግ ማስከበር ሥራው እየተሠራ ነው”።

ከኢንተርኔት አኳያ ቱሪስት በሚያስተናግዱ ሆቴሎች የኢንተርኔት መስመር የተለቀቀላቸው እንዳሉ ጠቁመው፤ ሁኔታዎች እየተገመገሙ አገልግሎቱ በአጠቃላይ እንዲኖር እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You