የቀንዲል መስራቹ ጋሽ አያልነህ

ለወጣቱ አያልነህ ሙላት በሩሲያ ኑሮ ተመችቶታል። አካሄዱ በድርሰት ማህበር አማካኝነት ባገኘው የትምህርት እድል ነበር። በሞስኮ ሬዲዮ ጣቢያ የአማርኛ ክፍለ ጊዜ “የገጣሚው ደብተር” የተባለ ዝግጅት ያቀርባል። በትምህርቱም ሁለተኛ ዲግሪውን ከማጠናቀቁም ባሻገር ሦስተኛ ዲግሪውን ሊቀበል ከጫፍ ደርሷል፡፡

በኢትዮጵያ አብዮት ፈንድቷል፤ የለውጥ ጭላንጭል ብቅ ብሏል። በወቅቱ የባህል ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ የነበረው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ለጉዳይ ወደ ሞስኮ ባቀናበት አጋጣሚ “ብቻዬን ነኝ፤ ሰው የለኝምና አግዘኝ” ሲል ወጣት አያልነህን ደጅ ጠና። ያኔ አያልነህ የፒኤችዲ ትምህርቱን ወደማጠናቀቅ ተቃርቦ ነበር። ተማሪው አያልነህ ያኔ ትምህርቱን ትቶ ጓዜን፣ ማቄን ሳይል ጸጋዬን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። “እሳት ሲነድ” የተሰኘ በሀገረ ሩሲያ የተጻፈ ተውኔቱን ጸጋዬ ይዞት መጥቶ እውቁ አዘጋጅ አባተ መኩሪያ ሲያዘጋጀው፤ ሠአሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ መድረኩን አዘጋጅቶ የተዋጣለት ተውኔት በመሆን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትር ቤት መክፈቻ ሆነ።

ሀገርን ማገልገል

በባህል ሚኒስቴር ውስጥ የቲያትር ጥበባት ድርጅትን በማቋቋም ትያትር ቤቶችን በሥሩ በማድረግ ሥራውን “ሀ″ ብሎ ጀመረ። ይህ የሥራ ጅማሮ የወራትን እድሜ እንዳስቆጠረ፤ ጊዜው የአብዮት ነውና ከሩሲያ እናት ሀገሩን ሊያገለግል የተመለሰው አያልነህም ሆነ እንዲመለስ ጠሪው ሎሬት ጸጋዬ ማረፊያቸው እስር ቤት ሆነ። ጋሽ አያልነህ የታሰረው ጽፎ ለሳንሱር ክፍል በቀረበው “ሻጥር በየፈርጁ” በተሰኘው ቲያትር ላይ “በደርግ መቃብር ላይ ሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ትገነባለች፡፡” የሚል አረፍተ ነገር በማግኘታቸው መሆኑን ይናገራል።

ትያትሩ ገና የግምገማ ሂደቱን ያልጨረሰና ሴንሰር ይፍቀደው፣ አይፍቀደው አልታወቀም ነበር። በመሆኑም ቢፈልጉ ኖሮ ቁረጠው ወይም በሌላ ተካው ማለት ይችሉ የነበረ ቢሆንም ምክንያት ይፈልጉ ስለነበር ነው ይላል። ከአንድ ቀን የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ቢፈታም፤ ወደ ቀድሞ ሥራው መመለስ የማይታሰብ ሆነ። ይልቁንስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲያስተምር ይሁንታን አገኘ። በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ጽሁፍ መምህር በመሆንም ሕይወት ቀጠለ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ ትያትር ይሠራበት የነበረው በቀድሞ ኪነ-ጥበባት ወቲያትር ይባል የነበረው ተዘግቶ የቤተመጻሕፍት መጽሐፍ መደርደሪያ ሆኖ አየው። በዚህ ቅር የተሰኘው አያልነህ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት “እባክህ ፍቀድልኝና ልክፈተው” ሲል ተማጸነ። ፕሬዚዳንቱ ከማስተካከያ የተወሰነ ብር ጋር ፍቃዳቸውን ቸሩ። ያኔ መደርደሪያው ወጥቶ፣ አዳራሹ ታድሶ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማእከል ተቋቋመ። በዚህ የተነሳም በኢትዮጵያ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የባህል ማእከል ያቋቋመ የመጀመሪያው ሰው ለመሆን በቃ።

የባህል ማእከሉን ያቋቋመው ማእከሉን ከሚመሩ የቦርድ አባላት ጋር ነው። የሥነ-ጽሁፍ ዘርፉን የሚመራው ዶክተር ኃይሉ አርአያ የተባሉ የሥነ- ጽሁፍ ባለሙያ፣ የቲያትሩን ዘርፍ የሚመራው ደበበ ሰይፉ፣ የጋዜጠኝነትና የውይይት ዘርፉ የሚመራው በእውቁ ጋዜጠኛ ነጋሽ ገብረማርያም፤ የዘመናዊ ሙዚቃው የሚመራው በኢትዮ-ጃዝ ፈጣሪው ሙላቱ አስታጥቄ፤ የባህላዊ ሙዚቃው በተስፋዬ ለማ እንዲመራ በማድረግና እነዚህን ጎምቱ ሰዎች የባህል ማእከሉ የቦርድ አባላት በማድረግ፤ ጋሽ አያልነህ ሙላት የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን የባህል ማእከሉ ወደ እንቅስቃሴ ገባ። በየቀኑ አምስቱም ዘርፎች ፕሮግራም ነበራቸው። በዚህ ሂደት የዩኒቨርሲቲው የባህል ማእከል እስካሁን የሚታወስበትን “እንኳን ደስ አላችሁ”፣ “አባይ አባይ” እና መሰል ሕብረ ዝማሬዎችን አበርክቷል።

በባህል ማእከሉ ትልቅ ሥራ ቢሠራም በሚያስተምርበት የትምህርት ክፍል የሚያስተምሩ መምህራን ዩኒቨርሲቲውን ለቆ አስመራ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ሪሌሽን ኃላፊ ሆኖ እንዲሄድ ተስማምተናል ብለው በመፈራረም በወቅቱ ለነበረው ከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን (ሀየር ኮሚሽን) አቀረቡ። የቀረበለት አካልም በዝውውር ሃሳቡ በመስማማት በአስቸኳይ ወደ አስመራ እንድትሄድ የሚል ደብዳቤ እንዲደርሰው ያደርጋል። “አልሄድም!” የሚል ሙግት ገጥሞ ባለበት ሰዓት እምቢ የማይባል ሌላ ፈላጊ ይገጥመዋል። እሱም “ኢሰፓኮ” በኋላ “ኢሰፓ” የተሰኘው የደርግ ፓርቲ መቋቋሙን ተከትሎ፤ በሦስት ቀን ውስጥ በእጁ የሚገኙ ንብረቶችን አስረክቦ ማእከላዊ ኮሚቴ እንዲመጣ የሚል ደብዳቤ ደረሰው። “አማራጭ አልነበረኝምና ሁሉን ነገር ትቼ ኢሰፓ ውስጥ ገባሁ፡፡” ይላል።

17 ዓመታት ከደርግ ጋር ሠርቷል፤ በዚህ ሒደትም “ሕዝብ ለሕዝብ” ላይ አስተባባሪ ሆኖ የመሳተፍ እድል አግኝቷል። ጋሽ አያልነህ ሕዝብ ለሕዝብ ቡድኑ የተደራጀው ለሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መልስ የሚሰጥ ቡድን እንዲሆን ተደርጎ መሆኑን ያነሳል። በዚህም እነማይክል ጃክሰን እራሱ እስክስታን እየጨፈሩ ከየት አመጣኸው ሲባል “ከፒውፕል ቱ ፒውፕል” ማለት መጀመራቸውና ይህም ትልቅ ስኬት መሆኑን ይናገራል። ሕዝብ ለሕዝብ ምእራባውያን ለረዥም ጊዜ ባህል እያመጡ ሲጭኑ የነበረውን የማስቀረትና የኢትዮጵያን ባህል ለሌሎች ሀገራት የሚያሳይ ቡድን ለመፍጠር መሥራቱን ይናገራል። ያም ቢሆን እስካሁን በስኬት ስሙ የሚነሳው ቡድን ሲመለስ ቡድኑ ከመፍረሱም ባሻገር የቡድኑ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ መሪ የሆነው ጋሽ አያልነህ 17 ክሶች ጠብቀውታል፡፡

በወቅቱ ጋሽ አያልነህ ወደ ሀገርህ ብትገባ እስር ቤት ነው የምትገባው ስለተባለ ከቡድኑ ጋር ወደ ሀገር ቤት አልገባም። በዛው ጥፋ የሚል ምክር ቢለገስም ቡድኑ ሐሙስ ገብቶ እሱ ቅዳሜ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ሀገር ውስጥ እንደገባ እንደተፈራው እስር ቤት ባይገባም ከሥራው ታግዶ የቀረበበትን 17 ክስ የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ትልልቅ ባለሥልጣናት ጉዳዩን ማጣራት ጀመሩ። ያኔ ታዲያ ደሞዙን ባይከለከልም ከሥራው ታግዶ ሲፈለግ ቀርቦ ለጥያቄያቸው መልስ እየሰጠ ባለበት ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ሥልጣን ተቆጣጠረ። ያኔ ክሱን መጣራቱ ቀርቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመለስ የሚል ደብዳቤ ደረሰው። ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ለስምንት ወራት እንደቆየ ከ40 መምህራን ጋር ጊቢውን ለቀህ እንድትወጣ የሚል ሌላ ደብዳቤ ደረሰው። የባህል ማእከሉ ዘማሪ የነበሩ 17 ዘማሪያንም አብረው እንዲወጡ ተደረገ።

ብሶት የወለደው ቀንዲል

ከባህል ማእከሉ የተባረሩት 17 ዘማሪያን ወደ ጋሽ አያልነህ በመምጣት “አንተ ብቻ ሳይሆን እኛም አብረንህ ወጥተናልና መላ ፍጠር” አሉት። ያኔ ታዲያ የኪነ-ጥበብ ጥሙንም ለማርካት እና ለእሱም ሆነ ለዘማሪያኑ ገቢ ለመፍጠር በማሰብ ቀንዲል ቤተ-ተውኔት ተፈጠረ። ትያትርን ጨምሮ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ውጤቶችን በጣልያን ባህል ማእከል ማሳየት ጀመሩ። ሁለት የጣልያን ትያትሮችን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመተርጎምና ሁለት የጋሽ አያልነህ አዲስ ድርሰቶችን ትያትር በማሳየት ገቢ ማግኘት ተጀመረ።

ጋሽ አያልነህ ሁኔታውን መለስ ብሎ ሲያስታውስ “ዳቦ እየበሉ ከመኖር ወደ ምግብ ቤቶች ጎራ ማለት ጀመርን” ይላል። ያኔ ታዲያ የባህል ማእከሉም አይቶት የማያውቀውን ሕዝብ ማስተናገድ ጀመረ። ሆኖም በጣልያን አምባሳደር “ለምን ብለህ እንዳትጠይቀኝ ግን ቤቱን ለቀህ ውጣ!” መባሉን ተከትሎ ከጣልያን የባህል ማእከል ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋረጠ። ያኔ ታዲያ አማራጭ የለምና በአዲስ አበባ፣ ግንፍሌ አካባቢ የእድር ቤት አዳራሽ ለመከራየት ተገደዱ። የቤቱ አካባቢ ቆሻሻ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ትያትር ቤቱ የሚመጣ እንግዳ አፍንጫውን ይዞ ሽታውን ለማምለጥ በጥድፊያ መራመዱ የግድ ነበር።

ቤቱ ዝናብ ሲጥል ጣርያው ያፈስ ነበርና ሥራ የሌላቸው የቡድኑ አባላት ለእንግዶች ጥላ ይይዙ ነበር። ያም ቢሆን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና ሌሎችም የተከበሩ እንግዶች የቤቱ ደምበኞች ነበሩ። ያም ቢሆን የቡድኑ አባላት ወደ ጊቢው ሊገቡ ሲሉ የፓርቲ አባል የነበሩ ሰው ከ200 በላይ የሚሆኑ የእድሩ አባላትን በመሰብሰብ ቤታችሁን ሊወርሱ ነው በማለታቸው ከእድር ቤቱም ተባረሩ፡፡

ያኔ ታዲያ ጋሽ አያልነህ የሩሲያ የባህል ማእከል በመሄድ በተደጋጋሚ ከመንግሥት ጋር የሚያጋጨው ትያትር ነበርና፤ ትያትር እንደማያሳይ ቃል በመግባትና የባህል ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር በመሆን ለማገልገል በመስማማት ሥራ ጀመረ። በፑሽኪን የቀንዲል ቤተ-ተውኔት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በርካታ በጥበቡ ዓለም የሚገኙ ሰዎች ሥራቸውን ለታዳሚ ለማቅረብ እድል የከፈተ መድረክ መሆኑን ይመሰክራሉ። መድረኩ በሀገራችን አሁን ለተስፋፋው የሥነ-ጽሁፍ ምሽት መነሻ መሆኑን በርካታ የሥነ-ጽሁፍ ምሽት አዘጋጆች ይመሰክራሉ። የቀንዲል መድረክ በርካታ ገጣሚያንና የጥበብ ሰዎችን ማፍራት አስችሏል። ቀንዲል በእውቀቱ ስዩም፣ ኤፍሬም ስዩም፣ አበባው መላኩ፣ ምስራቅ ተረፈን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ በኪነ-ጥበብ ከፍተኛ ቦታ ለደረሱ ሰዎች ልምድ ማግኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው።

ቀንዲል ከጋሽ አያልነህ ጋር አብረው የነበሩ የያኔ ታዳጊዎችና ወጣቶች የአሁን አንጋፋዎች፤ ጋሽ አያልነህ ያኔ እምቅ አቅማቸውን ከእነሱ ቀድሞ እያየ አምኖ መድረክ ስለሰጣቸውና ትልቅ ኃላፊነት በመስጠት ያለ ጣልቃ ገብነት፣ በነጻነት ሥራዎች እንዲሠሩ በማድረጉ ያመሰግኑታል። ለጋሽ አያልነህ ማንበብ አያደክምም፤ ለመጻፍም ሃሳብ አያልቅበትም። በዛው ልክ በርካታ ተውኔቶችን ለተመልካች እንካችሁ ይላል። ግን መድረክ ከመነፈግ አንስቶ ከአንድ መድረክ ያልዘለሉ በርካታ ሥራዎች አሉት።

ለጥቁር አፍሪካ ፌስቲቫል በናይጄሪያ የቀረበው “ትግላችን” የተጻፈው በጋሽ አያልነህ ነው። ሙዚቃዊ ተውኔቱ በፌስቲቫሉ ላይ ሦስቴ የመታየት እድል አግኝቷል። ከዛም ባሻገር በናይጄሪያ ዩኒቨርሲቲዎች እየዞረ እንዲታይ የናይጄሪያ መንግሥት በመጠየቁ በዩኒቨርሲቲዎች ለእይታ በቅቷል። ከዛ መልስም በኩባ በነበረው የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ እንዲቀርብ ጥያቄ በመምጣቱ ትግላችን በኩባ መድረክም ተመድርኳል። በሁለት አህጉራት የታየው ይህ ትያትር በኢትዮጵያ ግን በአንድም መድረክ አልታየም፡፡

በተመሳሳይ በርካታ የዓለም ሀገሮች የታየው “ሕዝብ ለህዝብ” እራሱ በኢትዮጵያ መድረክ አልታየም። በብሔራዊ ትያትር አንድ መድረክ የተተወነው “የመንታ እናት” ትያትር በወቅቱ የሀገሪቱ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም የተመረቀና የታየ ከመሆኑ ባሻገር የሀገር መሪውንም ያስለቀሰ ትያትር ነበር። ትያትሩን የታደመ አንድ የደርግ አባል የሶማሌ ገጸ-ባህሪ ወክሎ የሚጫወተውን ተዋናይ በሽጉጥ ካልገደልኩ ብሎ በገላጋይ ቢታገስም፣ ድጋሚ የመሠራት እድል አላገኘም። በተመሳሳይ “መስከረም” የተሰኘውን የባህላዊ ሙዚቃ ድራማ የወቅቱ ምክትል መሪ የነበሩት ፍቅረሥላሴ ወግደረስ መርቀው ቢመለከቱትም ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን ተደርጓል።

የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘና አያልነህ ሙላትም ከዩኒቨርሲቲ ከተባረረ በኋላ አልጀርስ በሚካሄድ የፓን አፍሪካ ስብሰባ ላይ የሚቀርብ ተውኔት እንዲያዘጋጅ በደብዳቤ መጠየቁን አስመልክቶ “ሉሲ”ን አዘጋጀ። “ሉሲ” የተሰኘው ሙዚቃዊ ተውኔት በአልጀርስ የተሳካ ቆይታ አድርጎ ቢመለስም የሀገር ውስጥ መድረክ ከመከልከል አላመለጠም። እነዚህ የተከለከሉ ተውኔቶች አሁን ድረስ ለምንና ማን ከለከላቸው የሚለው ጥያቄ ሳይመለስ እስካሁን እንቆቅልሽ እንደሆነ አለ።

ባለቅኔ፣ ገጣሚ፣ ጸሀፌ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሰዎች እያፈራረቁም ሆነ በጋራ ከስሙ በፊት የሚጠቀሟቸው ማእረጎች ናቸው። እሱ ግን ከሁሉም በላይ “ጋሽ አያልነህ” ደስ ይለኛል ይላል። በትምህርት፣ ብሎም በሥራ የቆየበትን የሩሲያ ቋንቋ ተክኖታልና በርካታ የሩሲያ ሥራዎችን ወደ አማርኛ ተርጉሟል። በተመሳሳይ የእንግሊዝኛ ተውኔቶችን ወደ አማርኛ መልሷል። የእሱም ሥራዎች ተተርጉመው ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የመድረስ እድል አግኝተዋል። “ደሃ አደግ” የተሠኘ ድርሰቱ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ለሁለት ዓመት በእንግሊዝ ተዋናዮች ለንደን ላይ ተተውኗል። “የመንታ እናት” በሩሲያኛ ተተርጉሞ ለእይታ በቅቷል።

ፋውንዴሽን

አያልነህ ሙላት ፋውንዴሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ለመግባት መንገዶችን እየጠረገ ነው። ጋሽ አያልነህ ፋውንዴሽኑ “አለ ለማለት ሳይሆን ሀገር በቀል እውቀት ላይ የተመሠረተ ጥበብን ለመገንባት ያሰበ ነው፡፡” ይላል። ፋውንዴሽኑ በሀገር በቀል እውቀት ላይ የተመሠረተ ትያትር፣ ሙዚቃና ሥነ-ሥዕል ለመፍጠር ያሰበ ነው። እንደ ጋሽ አያልነህ ማብራሪያ አዲሱን ትውልድ አስኳላ አበላሽቶታል፤ ኢትዮጵያውያን ወይ የራሳችንን ይዘን አልተጓዝን፤ ወይ ምእራባዊያኑን አልሆንን። አጉል ሥልጣኔ የራሳችንን ልብስ እንኳን ከማሳደግ ይልቅ አስጥሎናል፡፡

ፋውንዴሽኑ ሀገር በቀል እውቀት ላይ የተመሠረተ ጥበብ የሚዳብርበትን መንገድ መፍጠር ዓላማው ነው። ለዚህም የሀገር በቀል እውቀትን ይዞ የሚያሳድግ ትምህርት የሚሰጥበት መድረክ ማመቻቸት፤ እንዲሁም፣ በሀገር በቀል እውቀት ዙሪያ የተሻለ የሠሩ ሰዎች የሚሸለሙበትና የሚበረታቱበት መድረክ ለመፍጠር ይሠራል። በቁጭት “አውሮፓ ስለእኛ ትያትር አያውቅም፡፡” የሚለው ጋሽ አያልነህ፣ ለዚህም የእነሼክስፒርን ሥራ ለመሥራት ምእራባዊያኑ ከእኛ የተሻለ መድረክ፣ ተዋናይ እንዲሁም አዘጋጅ ስላላቸው የኛ እነሱን ለመድገም መሞከር ከንቱ ልፋት ነው።

በፋውንዴሽኑ የጥበብ መስኩን ወደ ኢትዮጵያዊነት የሚመልስ ዘርፍ ለማደራጀት እቅድ ተይዟል። ሌላው ዓለም በራሱ የሚያውቀውንና የሰለቸውን የኪነ-ጥበብ ውጤት ከማቅረብ በራሳችን ማንነት ብንቀርብ “ሆ” ብለው ይቀበሉታል የሚለው የፋውንዴሽኑ ሃሳብ ነው። ሀገር በቀል የነበሩት የጥበብ ሙያዎች፣ ሽመና፣ ቀጥቃጭ፣ የሸክላ ሥራ ∙ ∙ ∙ እየተባለ ባለሙያዎቹ እየተናቁና ሌላ ሥም እየተሰጣቸው እንዲተዉት ሲደረግ ቆይቷል የሚለው ጋሽ አያልነህ፤ መድኃኒት፣ ድግምትና መሰል ሀገራዊ እውቀቶች “የጠንቋይ ነው” እየተባለ እንዲጠፉ ተደርጓል። ስለዚህም መሰል ሀገር በቀል እውቀቶችን ለመመለስ ይሠራል፡፡

በምእራባዊያን ዘንድ “አድቬንቸር ፊልም” እየተባሉ በምናብ የሚሠሩት በሀገራችን የነበሩና በማውገዝ የተተውና የተመናመኑ መሆናቸውን ያነሳል። ምእራባውያን እኛን እያስተው እነሱ የኛን በጎን የሚወስዱበትን አሠራር የሚያስቀርና ሀገር በቀል እውቀቶች ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ መፍጠር ዓላማው አድርጎ፤ ሃሳቡ የገባቸው ሰዎችን ከጎኑ አሰልፎ ለመንቀሳቀስ ፋውንዴሽኑ በሩ ክፍት መሆኑን ይናገራል። የፋውንዴሽኑን ዓላማ ለማሳካት ከመንቀሳቀስ በተጨማሪ፤ ሲገባና ሲወጣ ከከረመበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሁን ለሦስተኛ ዙር ተመልሶ እያስተማረ ይገኛል። አዕምሮውን ወጣት እንደሆነ ለማቆየት ማንበብና መጻፍ ምርጫው ነው። አካሉን ለማደስ በሳምንት ሦስት ቀን ይዋኛል፡፡

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You