መንግሥት ከዘጠኝ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ድጎማ አድርጓል

. አምስት ሺህ 786 ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ተጠቃሚነት ታግደዋል

አዲስ አበባ፡- መንግሥት በ2016 በጀት ዓመት አምስት ወራት ለሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ከዘጠኝ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ድጎማ ማድረጉን ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ። በአምስት ወራት አምስት ሺህ 786 ተሸከርካሪዎች ከድጎማ ተጠቃሚነት መታገዳቸው ተመላክቷል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ብሔራዊ የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሰልማን መሐመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫና ለማቃለል የታለመ ዓላማ ያለው የነዳጅ ድጎማ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። በዚህም በ2016 በጀት ዓመት አምስት ወራት ለሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ከዘጠኝ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ድጓማ ተደርጓል፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን በመለየት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ያሉት ፕሮጀክት አስተባባሪው፤ በ2016 በጀት ዓመት አምስት ወራት ብቻ ለታለመለት የነዳጅ ድጎማ ከዘጠኝ ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሰልማን ገለጻ፣ በድጎማ ማስተግበሪያ ሥርዓቱ ውስጥ የድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተመዘገቡ 241 ሺህ 035 ጠቅላላ ተሽከርካሪዎች ውስጥ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 198 ሺህ 771 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ድጎማ እያገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በድጎማ ሥርዓቱ ከተመዘገቡት ተሽከርካሪዎች 82 በመቶ የሚሆኑት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት የድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ 21 ሺህ 677 ተሽከርካሪዎች መኖራቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በክልል እና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት መዋቅሮች ተለይተው በማስተግበሪያ ሥርዓቱ የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች 241 ሺህ 35 መድረሳቸውን አመልክተው፤ በአምስት ወሩ 10 ሺህ 17 ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የተሰጣቸውን የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉና በሕገወጥ መንገድ ሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ብቻ አምስት ሺህ 786 ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ተጠቃሚነት እንዲታገዱ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

አራት ሺህ 500 ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሳይሰጡ የተጠቀሙትን ከዘጠኝ ነጥብ 76 ሚሊዮን ብር በላይ የድጎማ ገንዘብ በዕዳ መልኩ መልሰው እንዲከፍሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በጠቅላላው 38 ሺህ 415 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ተጠቃሚነት እንዲታገዱ መደረጉን አስታውሰው፤ በታለመ ነዳጅ ድጎማ አሠራር መሠረት በሚመለከታቸው የትራንስፖርት መዋቅሮች ወደ ድጎማ ተጠቃሚነት እንዲመለሱ የሚቀርቡ ሪፖርቶችን መሠረት በማድረግ ወደ ድጎማ ተጠቃሚነት እንዲመለሱ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ድጎማቸውን በአግባቡ ያልተጠቀሙ ተሽከርካሪዎች የድጎማ ተመላሽ ገቢ ማድረጊያ የቴሌ ብር አጭር ኮድ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስም እንዲዘጋጅ ተደርጎ የድጎማ ተመላሽ በቴሌ ብር አጭር ኮድ ከኅዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንዲጀመር ተደርጎ እየተሠራበት እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት የታለመ ነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው በማስተግበሪያ ሥርዓቱ የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ከ46 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር በላይ በቴሌብር የነዳጅ ግብይት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You