የአዲስ አበባ ክለቦችና ታዳጊዎች የብስክሌት ውድድር እየተካሄደ ነው

ከተጀመረ አንድ ሳምንት ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ክለቦችና ታዳጊዎች የአቋም መለኪያና የታዳጊዎች ምዘና ሁለተኛ ዙር ውድድር ነገ መነሻውን ፅዮን ሆቴልና መድረሻውን ጉለሌ እፅዋት ማዕከል በማድረግ ይካሄዳል:: በውድድሩ አራት ክለቦችና ከ80 በላይ የሚሆኑ ታዳጊ ብስክለተኞች የምዘና ፉክክር እንደሚያደርጉ ታውቋል:: ታህሳስ 14 የተጀመረው ይህ ውድድር በአጠቃላይ በአራት ዙሮች ይካሄዳል::

የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች አንዱ የሆነው የክለቦች አቋም መለኪያና የታዳጊዎች የምዘና ውድድር ታህሳስ 14 በርካታ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ የተጀመረ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዙር ውድድርም ነገ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታውቋል:: ውድድሩ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጀና ክለቦች፣ ታዳጊዎችና የግል ተወዳዳሪዎች አቋማቸውን ለመለካትና ለሌሎች ውድድሮች ለመዘጋጀት እንዲረዳቸው ታስቦ ነው የሚካሄደው::

በክለቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ጋራድና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል:: በታዳጊዎች መካከል በሚደረገው ፉክክር ከ40 በላይ ወንድና 18 የሚደርሱ ሴት ብስክሌተኞች ይሳተፋሉ:: በዚህም 5 ዙር የሚፈጅና 17 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የብስክሌት ግልቢያ እንደሚደረግ ተጠቅሷል:: በክለቦች መካከል በሚደረገው የአቋም መለኪያ ውድድር 17 ዙሮችን የሚፈጅና 61 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ፉክክር ይካሄዳል::

የነገው ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ የሶስተኛው ሳምንት ውድድር የቦታ ለውጥ ተደርጎበት ከፒያሳ ቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ለገሀር ባለው መንገድ ላይ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል:: የአራተኛው ሳምንትና የመዝጊያ ውድድርም በተመሳሳይ ቦታ ይካሄዳል::

የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነ፣ ፌዴሬሽኑ የ2016 ዓ.ም የውድድር ዘመንን በአቋም መፈተሻ ውድድር መጀመሩን ተናግረዋል:: ውድድሩ የታዳጊ ወጣቶች ምዘናና የክለቦች አቋም መለኪያ እንደሆነና ለቀጣይ ሶስት ሳምንታት እንደሚቀጥልም አስረድተዋል:: ፌዴሬሽኑ አብዛኛውን ጊዜ የዓመቱን ውድድር በአቋም መለኪያ እንደሚጀምር ጠቅሰው፤ በመቀጠል የክለቦች ቻምፒዮና እና ሌሎች የታሰቡ ውድድሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል:: እነዚህም በስፖንሰር የሚመጡና የቀድሞ የኦሊምፒክ ተሳተፊ ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ የመታሰቢያ ውድድርንም ለማዘጋጀት ፌዴሬሽኑ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል::

የዘንድሮ የአቋም መለኪያና ምዘና ውድድር ለሁሉም ክፍት ሆኖ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ:: እነዚህ ተወዳዳሪዎች በአቋም መለኪያና በክለቦች ቻምፒዮና ውድድሩ ነጥብ እየተያዘላቸውም ይሳተፋሉ::

ፌዴሬሽኑ በቅርቡ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡት አዲስና ነባር ሥራ አስፈጻሚዎች ተቀናጅተው ገንዘብ በማፈላለግ ዓመቱን ለየት ባለና ብዙ ውድድሮችን በማድረግ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ተገልጿል:: በተጨማሪም ክለቦች ቁጥርን ለመጨመር ከተቋማት ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩበት ዓመት እንደሚሆን ጠቁመዋል::

ውድድሩ ብርቱ ፍክክርና የተመልካችን ቀልብ በመሳብ እስከ አራተኛ ሳምንት እንደሚቀጥል የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ብስክሌተኞቹ ለክለቦች ቻምፒዮና በቂ የሆነ ዝግጅትን እንዲያደርጉ እንደሚረዳቸውም ተናግረዋል:: ይህም የመታየት እድል በማግኘት የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አክለዋል:: ብስክሌተኞቹ ዓለም አቀፍ ሰዓታቸውን እንዲያሻሽሉና ዓለም ላይ የመሸጥ እድል እንዲኖራቸው ለመድግም መሰል ውድድሮች ትልቅ ጥቅም እንደሚኖራቸው ይጠበቃል::

ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት በሚመደብ የድጎማ በጀት እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ሲሆን በውድድሮች ከስፖንሰር በሚገኝ ገቢ ታዳጊዎችን ለማበረታታት የቁሳቁስ ድጋፎችን የሚያደርግ ቢሆንም ድጋፍ በቂ የሚባል አለመሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል:: ዘላቂነት ያለው ድጋፍ የሚደረግ ከሆነ ብቁ የሆኑ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንደሚቻልም ጠቁመዋል::

ስፖርተኞቹ ትልቅ ሽልማት ሳይሆን የሚዲያ ሽፋን የማግኘት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ሚዲያዎች ለስፖርቱ ትኩረት በመስጠት ሊያነቃቁ ይገባል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል:: ከዚህ ቀደም ረጃጅም የሆኑ የብስክሌት ውድድሮች የነበሩ ቢሆንም አሁን ባሉት ሀገራዊ ተደራራቢ ችግሮች እየተካሄዱ አይገኙም:: ከአዲስ አበባ አስመራና ወደ ተለያዩ ቦታዎች የተደረጉ ውድድሮች ተጠቃሽ ሲሆኑ የጸጥታና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት መካሄድ እንዳልቻሉም ጠቁመዋል::

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You