በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ሀገራት ዜጎች እንግሊዝኛ ቋንቋን ይናገራሉ፡፡ እኛም በቋንቋው መግባባት ብንችል ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ባለችበት በዚህ ዘመን ብዙ ጥቅም ልናገኝ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እኛ በቋንቋው መሰልጠን አልሆን ብሎን ቋንቋው እየሠለጠነብን ትግል ላይ ያለን እንመስላለን፡፡ ጉራማይሌ ቋንቋ መጠቀምን ባህል አድርገነዋል፡፡
ምትክ ያላቸውን የእንግሊዝኛ ቃላት በየመሃሉ ጣል ማድረግ ከዲፕሎማ እና ዲግሪ በላይ የትምህርት ማስረጃ እየሆነ ነው፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና በእንግድነት የሚቀርቡ ታዋቂ ሰዎች የሚደነቅሯቸውን የእንግሊዝኛ ቃላት መፍታት የጋዜጠኞች መደበኛ ስራ ሆኗል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የእንግሊዝኛ ቃላት ተናግረው ትርጉሙን ያስከትላሉ፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ ‹‹ኦኬ›› ብሎ እሺ የሚል ‹‹አትሊስት›› ብሎ ቢያንስ የሚል እንግሊዝኛ አዋቂ ጥቂት አይደለም፡፡
በሀገር ቤት የሚነገሩ ቋንቋዎችን ቃላት ጣል የሚያደርግ ሰው ቢገኝ የሆነ ክትባት ያመለጠው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አሊያም ምን ማለት ነው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ እንግሊዝኛ ከሆነ ግን ትናንት የተፈጠረ አዲስ ቃል ቢሆን እንኳን ደፍሮ የሚጠይቅ አይኖርም፡፡ እርግጠኛ ነኝ አሁን ‹‹ልሳነ እንግልጣር›› ምን ማለት ነው ብላችሁ እየጠየቃችሁ ነው፡፡ ከግዕዝ ነው የተዋስኩት ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ ማለት ነው፡፡
በብዙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሳምንቱ ቀናት አንደኛው የእንግሊዝኛ ቀን ተብሎ እንዲሰየም ይደረጋል፡፡ ዓላማው የግቢው ማህበረሰብ በዕለቱ በቋንቋው እንዲግባባ ማድረግ ነው፡፡ ሆኖም በዕለቱ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት ጉድ ሞርኒንግ ፣ ጉድ አፍተር ኑን እና ጉድ ባይ የሚሉት ቃላት ናቸው፡፡ በክፍል ውስጥ ቆይታቸው የሚናገሩትን ቃል ሁሉ የሚተረጉሙ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራንም አሉ፡፡ ታዲያ ተማሪዎቻቸው በእንግሊዝኛ የተተነፈሰች እያንዳንዷ ቃል ተመልሳ በአማርኛ እንደምትመጣ ስለሚያውቁ ጨርሶ አይሰሟቸውም፡፡
እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመናገር የሚቸገሩት ተማሪዎች ብቻ አይደሉም፤ መምህራንም በዚህ ስማቸው ይነሳል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ፍርሃት ይመስለኛል፡፡ ብሳሳት አላዋቂ ተደርጌ እቆጠራለሁ ወይም ይሳቅብኛል በሚል ስጋት ራሳቸውን ያቅባሉ፡፡ ብዙዎችን ለቋንቋ ባዕድ የሚያደርጋቸው ይህ ይመስለኛል፡፡ ሰው ሲሳሳት መሳቅ የሚሉት አጉል ፈሊጥ፡፡
እውቁ የወግ ጸሐፊ መስፍን ሀብተማሪያም የትምህርት ቤት ትዝታውን በሚያወጋበት አንድ ጽሑፉ አንዲት ተማሪ ጃንሆይን እርሳቸው ለማለት ፈልጋ they ስትል በክፍሉ ውስጥ ያለው ተማሪ ሁሉ እስኪበቃው መሳቁን ይተርካል፡፡ እንዲህ የተሳቀባት ተማሪ በቋንቋው ላይ ለመሰልጠን ምን አይነት ሞራል ይኖራት ይሆን? የሚማር ሰው ከተሳሳተ ከስህተቱ እንዲማር ነው ጥረት መደረግ ያለበት ብዙዎቻችን ግን መዘባበቻ የማድረግ አባዜ ተጠናውቶናል፡፡ ደግሞ እኮ ‹‹አመድ በዱቄት ይስቃል›› እንደሚባለው እናርማለን ባዮችም ታርመው ያላበቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ አንዲት ቀልድ ትዝ አለችኝ፡፡
አንዲት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርት knife የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ሰሌዳ ላይ ጽፋ ተማሪዎቿ እሷን ተከትለው እንዲያነቡ መመሪያ ሰጠች፡፡ ከዛም ድምጽዋን ከፍ አድርጋ “ናይፍ” አለች፡፡ ከአንድ ተማሪ በቀር ሁለም ናይፍ እያሉ አነበቡ፡፡ ብቸኛው ተማሪ ግን “ክ” ን መግደፍ አልቻለም፡፡ ክናይፍ እያለ አነበበ፡፡ መምህርቷ ደጋግማ ናይፍ እያለ እንዲያነብ ጥረት አደረገች፡፡ ተማሪው ግን ክናይፍ ማለቱን አልተው አለ፡፡ መምህርቷ በንዴት ከነፈች፡፡ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ጋር ወስዳ “ሂ ዳዝንት ክኖው ሀው ቱ ፕሮናውንስ ናይፍ ” ብላ ከሰሰችው፡፡ እሷም “ክ” ን መግደፍ ተስኗት know የሚለውን ቃል ክኖው ብላ አናግራ ተመሳሳይ ስህተት ሰራች፡፡ ርዕሰ መምህሩም ሲያዳምጥ ቆይቶ ‹‹ቦዝ ኦፍ ዩ አር ውሮንግ›› አለ፡፡ እርሱም ሮንግ ማለት ሲገባው ውሮንግ በማለቱ ከስህተት አላመለጠም፡፡
በቋንቋ ትምህርት ምንባቦች በራሳቸው ግቦች አይደሉም፡፡ የማስተማሪያ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ይህን ያነሳሁት ወደ አንድ ገጠመኝ ለመንደርደር ነው፡፡ የተቀየረው የ8ኛ ክፍል እንግሊዝኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሐፍ ላይ የሁለት ታዋቂ ሯጮች እና የሞዴል ሊያ ከበደ ታሪክ ምንባብ ሆኖ ቀርቦ ነበር፡፡ ይህን መጽሐፍ ሲማሩ የቆዩ የማታ ተማሪዎች ለፈተና ተቀመጡ፡፡ የፈተና ወረቀቱ ‹‹ኔልሰን ማንዴላ›› የሚል ምንባብ ይዟል፡፡ ፈተናው ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለት ተማሪዎች “እኛ የተማርነው ስለነ ሊያ ከበደ ነው፡፡ ስለ ኔልሰን ማንዴላ መጠየቅ የለብንም፡፡ ያልተማርነው ነው የመጣው›› ብለው ቅሬታ አቀረቡ፡፡
ከቴክኖሎጂ ጋር የሚመጡ ቃላት አቻ ትርጉም በመስጠት ረገድ ብዙ ስራ የሚጠብቃቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምሁራን ቢቦዝኑም ህዝብ ግን ይቀላል ያለውን ምትክ ቃል ከመስጠት ወደኋላ አይልም፡፡ የአዲስ አበባ ኗሪ አንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ያስተዋወቀውን ሽንጠ ረጅም ተጣጣፊ አውቶብስ እንቅስቃሴው ከሀድያ ባህላዊ ጭፈራ የተቀዳ ነው ብሎ ‹‹ሰለሜ›› እያለ ይጠራዋል፡፡
የኢትዮጵያ አርሶ አደር እናውቅልሃለን ባዮች ካልተጫኑት በቀር በዕለት ተዕለት ህይወቱ ለሚተዋወቃቸው አዳዲስ ቁሶች ቅርጻቸውን ፣ አሰራራቸውን እና ጠቀሜታቸውን ተመልክቶ ምትክ ስያሜ በመስጠት የሚወዳደረው የለም፡፡ አንድ መምህራችን ያጫወቱንን ገጠመኝ ላካፍላችሁ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተነሳ በአንድ ዶክተር የሚመራ ቡድን ጥናት ለማድረግ በአንድ የገጠር መንደር ተገኝቶ ነበር፡፡ መረጃ አቀባዮችን ለመለየት የመንደሩ ኗሪ ሁሉ እሁድ ከቤተ ክርስቲያን መልስ እንዲሰበሰቡ ተደረገ፡፡ የቡድኑ አባላት የተገኙትን ሰዎች ስም ከመዘገቡ በኋላ ገሚሱን መርጠው የተቀሩትን ወደቤታቸው እንዲሄዱ ነገሯቸው፡፡ አንድ አርሶ አደር ‹‹ነገር አዋቂ የሆኑት እነ መምህሬ ሳይመረጡ እኔ መሃይሙ የተመረጥኩበት ምክንያት አልገባኝም›› አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከቡድኑ አባለት አንዱ ‹‹እኛ የመረጥነው በራንደም ሳምፕሊንግ ነው›› ብሎ መለሰ፡፡ ጠያቂው መልሰው ጠየቁ፡፡ ‹‹ምን ማለት ነው ?›› ቡድኑን የሚመሩት ዶክተር ‹‹ የሁላችሁም ስም በተራ ቁጥር ከተጻፈ በኋላ አንዱን እየጠራን አንዱን እየዘለልን ነው የመረጥናችሁ›› አሉ፡፡ ጠያቂው አርሶ አደር ‹‹ታዲያ በብድግ ብድግ ነው የመረጥናችሁ አትሉም እንዴ›› አሉ፡፡ ዶክተሩ ከዚህ ገጠመኛቸው በኋላ ‹‹ራንደም ሳምፕሊንግ›› በማለት ፈንታ ብድግ ብድግን መረጡ፡፡
ጀርመን ሀገር ከውጭ ለሚገቡ አዲስ የቴክኖሎጂ ቃላት ምትክ ቃላት የሚሰጥ ተቋም ስለመኖሩ የሚያትት ጽሑፍ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ተመልክቻለሁ፡፡ እኛም ሀገር እንዲህ አይነት ተቋም ቢኖር መልካም ነው፡፡ ውሰት አንድ የቋንቋ ባህሪ ነው ብለን እጃችንን አጣጥፈን ከተቀመጥን በአጭር ጊዜ ውስጥ በባዕድ ቋንቋ ቃላት የመወረር ዕጣ ይገጥመናል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2011
የትናየት ፈሩ